ስንወስን ፣ ውሣኔዎቻችን ሊያስከትሉ የሚችሉትን ሁለንተናዊ ጥቅምና ጉዳዮች እየመዘን ይሆን!!

ዐኅኢአድ ልሣን-መቅደላ ልዩ ዕትም ፪፩ ግንቦት ፪፱ ቀን ፪ሽ፲

የሰው ልጅ አጠቃላይ የሕይዎት ጉዞ በውሣኔዎች የተሞላ ነው። ለመንቀሳቀስ፣ ለመመገብ፣ ለመሥራት፣ ለመተኛት፣ ለመነሳት፣ ለመዝናናት፣ ወዘተ ወዘተ እየወሰን ነው። ውሣኔአችንም ለመወሰን መነሻ የሆነውን ጉዳይ ለይተን፣ ውሣኔው ሊያስከትል የሚችላቸውን ሁኔታዎች በግራ በቀኝ መዝነን፣ ጥቅምና ጉዳቱን አወዳድረን እንደሆነ ይታመናል። የአንድ ውሣኔ ትክክለኛነትም ማረጋገጫውም ለውሳኔው ታማኒነትና ተቀባይነት የቀረቡት የውሳኔ አማራጮች በተገቢው ሁኔታ ሁሉም የቀረቡት ተገቢው ምዘና የተደረገባቸው መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። ውሳኔው ሁሉንም አማራጮች ግምት ውስጥ ያስገባና ያወዳደረ ሲሆን ነው። የሚንሰጠው ውሣኔም ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዘነ መሆኑ በወቅቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ፣ መጭውንም በአግባቡ ግምት ውስጥ ያስገባ የሆነ እንደሆነ ነው። ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ነገር በምንም ተዓምር የውሣኔ ተመራጭ አይሆንም።

ስለ ውሳኔ በመግቢያነት ይህን ያህል ለማለት ያስገደደን፣ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ከሕዝቡ ጋር ለማገናኘት ጋብዟል የሚለው ዜና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት በመሰራጨቱ እና ይህን ተከትሎ የተለያዩ ሀሳቦች ሲለዋወጡ በማየታችን ነው።

ማንም እንደሚያውቀው፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌደሬሽን፣ ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ከገነባቸው የሕዝብ ለሕዝብ መገናኛ ተቋሞች አንዱና አንጋፋው ነው። ይህ ተቋም ሸህ አላሙዲንና ወያኔን ያህል ዋና ጠላት ተቋቁሞ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ በድል የተጓዘ ነው። የኢትዮጵያውያን መገናኛ፣ መወያያ፣ የናፍቆት መወጫ፣ መዝናኛ፣ መደሰቻ፣ የአገር ትዝታ፣ ችግርና ደስታ መነጋገሪያ፣ የኢትዮጵያዊነት አብሮነትና ምንነት መገለጫ፣ ወዘተ በመሆን በማገልገሉ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ብቸኛው የኢትዮጵያዊነት ዕሴቶቻችን ቋሚ ቅርስ ነው። ፌዴሬሽኑን ለዚህ ደረጃ ላበቁት እህት ወንድሞቻችን ያለን አክብሮት እጅግ ከፍ ያለ ነው። በዚህ መልኩ እደግ ተመንደግ ለማለት እንወዳለን።

ሆኖም ግን፣ ሰሞኑን ፌዴሬሽኑ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን፣ የኢሕአዴግን ሊቀመንበር በእንግድነት ጋብዟል የሚለው ዜና መናፈሱን ስንሰማ፣ ዐቢይ እንዲመጣ ሲጋብዙ፣ ምን ምን ሁኔታዎችን አይተው ነው? ከዚህ ውሳኔስ የደረሱት በሰውየው መጋበዝ ምን ጥቅም ይገኛል? ጥቅሙስ ኢትዮጵያውያን ከሚመኙት የአብሮነትና የአንድነት ስሜት ጋር የተጣጣመ ውጤት ያስገኛል የሚለው አመዝኖ ነወይ? ወይስ ዐቢይን ለመደገፍ አገር ቤት ጓዛቸውን ጠቅለው የገቡ “የታማኝ ተቃዋሚዎችን” እንኳን በሩን ከፈታችሁልን እኛም ወደ እናንተው ነን በማለት እጅ ለመሻነት ነው? የዐቢይ መጋበዝ በወደፊቱ የፌዴሬሽኑ ጉዞ ላይ ምን መልካምና መጥፎ ነገሮች ሊያስከትል ይችላል? ጥቅሙ የዐቢይ መጋበዝነው ከተባለ በምን መልኩ? የሚሉት ጥያቄዎች ሊፈተሹና ከኅሊና ዕዳና ወቀሳ ነፃ ሊያወጣን የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ ለተቋሙ የወደፊት ጉዞና ዕድገቱ ሳይጠቅም አይቀርም ብለን እናስባለን። ……. (Read more)