ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ምኒስትርነት የመጡት የለማ ቡድን የሚባለው የለውጥ ኃይል በሰራው ሰፊ ድርጅታዊ ስራ እና አቅም ግንባታ ወያኔን ታግሎ በልጦና አሸንፎ ለመሆኑ ከዋዜማው ጀምሮ በወያኔ ሰፈር የሚታየው የሚሰማውና የሚሰራው ግልጽ ማሳያ ነው፡፡

በቀላሉ ግንቦት ሀያን ምክንያት አድርገው በመቀሌ የተሰባሰቡት ሰዎች ከሚናገሩዋቸው ቃላቶች በላይ አነጋገራቸውና ፊታቸው ላይ የሚነበበው ተበለጥን ተሸነፍን የሚል የቁጭት ስሜት ነው፡፡ ስሜት ብቻ አይደለም በቀላሉ እጅ መስጠት የለብንም የሚሉ በሚታወቁበት ሴራቸው ከመታገል የማይሰንፉ መሆናቸውን በግልጽ አሳይተውናል፡፡

እሳትን ጭድ እንዴት አንድ ላይ ይሆናል ይህ አለመስራታችንን ነው ያለው ጌታቸው ረዳ በመቀሌው አዳራሽ ደግሞ ስለ ኢቲቪ ተነስቶ ባዕድ አስተሳሰቦች የተሸነፉ አስተሳሰቦች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡ብሎናል፡፡አቶ ስዩም መስፍንም ገንዘብ ብቻ አይደለም አስተሳሰባችንንም እየተሰረቅን ነው ሲል ተደምጧል፣፡ሌላም ሌላም፡፡

በዶ/ር አብይ የሚቀነቀነው ጋዜጠኞችም ተቀብለው እያስተጋቡት ያለው ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና አንድነት ነው ባእድ የተሸነፈ ስተሳሰብ የተባለው፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባችን ወደ ጎን ተገፋ የደደቢት ህልማችን ተሸረሸረ ነው የስም መስፍን ስጋቱ፡፡

ይህም በአንድ ጽሁፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት ጠቅላይ ምኒስትሩ እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እሳት ውስጥ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል፡፡ተጨማሪ እሳት ሆኖ አብን መለብለብ ኢትዮጵያዊነት ባይሸነፍም ዳግም ሸብረክ እንዲልና ህውኃቶች እየተብሰከሰኩበት ያለው እሳትና ጭድ የማድረግ ሴራቸው እንዲያንሰራራ ማገዝ ነው የሚሆነው፡፤

ሰዎቹን ያለሀፍረት እንዲህ በአደባባይ የሚያናግራቸው በእኛ ላይ ጀንበር አትጠልቅም ሲሉ ኖረው ዛሬ እያዘቀዘችባቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ከውስጣቸው በወጡ ሰዎች መሆኑ ደግሞ ብስጭታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡ እናም በምንም ሁኔታ የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ዴክራሲያዊት ሀገር እንድትሆን እንሻለን የምንል ንግግራችን የድብቅ ፍላታችን ሽፋን ሳይሆን ከልብ የምናምንበት ዓላማችን  በጽናት የምንታገልለት ግባችን ከሆነ አብይን መደገፍ ቢያንስ ሁለት ወሳኝና መሰረታዊ ጥቅም አለው፡፡ ግላዊ ሳይሆን ሀገራዊ፡፡

የመጀመሪያው ህውኃቶች በምንም ሴራ የእነ ለማ/አብይን የለውጥ ጉዞ ማደናቀፍ እንደማይችሉ ከሞከሩት ግበአተ መሬታቸውን ማፋጠን እንደሆነ ተረድተው አድበው እንዲቀመጡና በአብይ ከለላ ሹልክ ብለው ከመድረኩ እንዲወጡ ያስችላል፡፤

በዚህ ሂደት ቃል ብቻ ሆነ የምንለውን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉባቸው መሆኑን በመገንዘብ ለሀገር ዴሞክራሲያዊነት ለህዝብ ፍቅርና አንድነት ይበጃል ብለን የተቀበልነው ተፈጻሚ እንዲሆን በሚቻለው ሁሉ ማገዝ፣መሰናክሉን ማንሳት ቆሻሻውን ማጽዳት፡፡

ሁለተኛው  እኔ ዶ/ር አብይ ንግግር ውስጥ ዲፕሎማሲ የሚል የቁልምቻ ስም የተሰጠውን ሽንገላም ሆነ የምናውቀውንና የለመድነው የፖለቲካ አነጋገር አላየሁምና የሚናሩት የሚያምኑበትን ብሎም የህዝብን ድጋፍ ካገኙ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተውና ቆርጠው የተነሱበትን ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡አንዳንድ ወገኖች ወያኔ ያስቀመጠው በቃላት ሸንግሎ ትግሉን ሊያቀዘቅዝ የመጣ ከማለት አልፈው የሚሰሩት ሁሉ በወያኔ እቅድና ምሪት እንደሆነ ሲጽፉ ይታያል ሲናገሩ ይሰማል፡፡ሌላው ሁሉ ቢቀር የመቀሌው ግንቦት ሀያ የተከበረበት አዳራሽ ላይ የሆነውን አይቶ አብይን ወያኔ ነው ያስቀመጠው ብሎ ለመናገር አንዴት እንደሚደፈር አይገባኝም፡፤

የሚሉት ሊሆን ይችላል ቢባል መፍትሄው ንግግራቸውን መንቀፍ ስራቸውን  ለማደናቀፍ መታተር አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ወያኔዎቹ የሚሰሩት ይበቃል፡፡እየደገፉ እያበረታቱ በጀመሩት መንገድ በፍጥነት መጓዝ እንዲችሉ አቀጣጣይ ነዳጅ መሆን ነው የሚሻለው፡፡ከዚሁ ጋር በተዛማጅ ዶ/ር አብይ የሚናገሩትን አይፈጽሙም የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖችም በመራቅና በማራቅ ሳይሆን በመቅረብና በማቅረብ በመገናኛ ብዙኃን ዲስኩር ሳይሆን መሬት በረገጠ ተግባር እያገዙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ከያዙት መንገድ ውጪ ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ከዚህ መንገድ ቢወጡ በአንድ በኩል በህዝቡ በሌላ በኩል በወያኔ ጥቃት የሚደርስባቸው ከፍተኛው ተጎጂ እንደሚሆኑ ማሳየት ነው፡፡

ይህ ደግሞ ርሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን የሚጎዳ በመሆኑ ከህውኃት በተቃራኒ የቆመ ዜጋ ሁሉ በለውጥ ጎዳና ላይ ያሉት ሰዎች እንዲጠናከሩ መደገፍ ይኖርበታል፡፤ ይህ ሀሳብ በግል አብይን ከመውደድ ወይንም በንግግራቸው ከመማረክ የመጣ አይደለም፡፡

አንደኛ ትክክለኛና ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ በመሆኑ፣ሁለተኛ አይደል የተሸለ የሚገዳደር ምርቻምአማራችም በዚህ ሰአት የሌለ መሆኑ ነው፡፤

በርግጥ ከጸብ የሚያተርፉ ፍቅርን ከመለያየት የሚጠቀሙ አንድነትን እንደማይሹ እሙን ነው፤የኢትዮጵያዊነት ማንሰራራት የቆሙበትን የጎሳ መሰረት ያናጋብናል ብለው የሚሰጉ መኖራቸውም እየታየ ነው፡፡በመሆኑም ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ በሌሎች የምንገፋ ሳይሆን ፈጣሪ ማመዛዘኛ ህሊና ሰጥቶናልና በራሳችን እየወሰንን ቢሆን መልካም ነው፡፤

የእነ አብይ በዚህ ወቅት መከሰት ከፈጣሪ የታዘዘ ከሆነ ማንም አያቆመውም፡፡ስለሆነም ይህን መልካም የታሪክ አጋጣሚ ወደ መልካም ፍጻሜ እንዲደርስ ከፊት ሆነመጎተት ከኋላ ሆኖ መግፋት ከጎን ሆኖ መደገፍ እንጂ ሀዲዱን እንዲስት መሰናክል ማስቀመጥ፣ ጎዞው እንዳይፈጥን ለመግታት መጣጣር ነገ የህሊና ጸጸት ያተርፋል በታሪክና በትውልድ ያጠይቃል ያጠያይቃል፡፡

የምንሻውን ለውጥ ለማግኘት አብይን ከሴረኞቹና መሰሪዎቹ ወያኔዎች እንጠብቃቸው፣በየቦታው የተሌዩ ጥፋችን በማድረስ ሰውየው ወሬ ብቻ ነው አንዲባልና የህዝብ ድጋፋቸው እንዲሸረሸርና ያኔ እነርሱ የሚሹትን  ለማድረግ ወያኔዎቹ ብዙ ወንጀሎችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በመረዳት አካባን በንት መጠበቅ አደጋ ሲደርስ ጉዳቱ አንዳይሰፋና አንዳይከፋ መረባረብ ከዛም እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል ማለት፡፡ ( እንደ አይጧ)

በመጨረሻም ለወያኔዎች፤ሀያ ሰባት አመት ሙሉ አይናችሁ አላይ ጆሮአችሁ አልሰማ ብሎ የአገዛዝ ዘመናችሁን ማሳመር አልቻላችሁም፡፤የእናንተ እብሪትና ማን አህሎኝነት ከህዝቡ ትዕግስት በላይ ሆነ፡፡ሳታውቁ የናቃችሁት ህዝብ ሲነሳ አጋአዚ ሊያቆመው እንዳልቻለ አይታችኋል፡፡ ወዳችሁና ፈቅዳችሁ ሳይሆን ከመሞት መሰንበት ብላችሁ ጠቅላይ ምኒስትር ያደረጋችኋቸው ሰው ኢትዮጵያንና ህዝቧን ብቻ ሳይሆን እናንተንም የሚታደግ ጉዞ ጀምረዋልና አእንዴት አንበለጣለን በሚል እልህና ቁጭት ይህን አወራረዳችሁን የማሳመሪያ መልካ አጋጣሚ አንዳታበላሹት፡፡ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ለመላላጥ ነው የሚለው አባባል በትግረኛ ይኑር አይኑር ባላውቅም ማስታወሱ ግን ይጠቅማችኋል፡፤

የኢትዮጵያ ህዝብ እናንተ አንደምትሉትና ሀያ ሰባት አመት እንደሰበካችሁት አይደለም፡፡ ሰውን በግል ድርጅትን በጥቅል አይደለም የሚጠላው፡፡ የጠላው ክፉ ተግባራችሁን ነው፡፤ከኢትጵያዊነት ጋር ያጣላችሁን ርኩስ መንፈስ ነው፡፡ለፍቅር ሳይሆን ለጥላቻ ለአንድነት ሳሆን ለመለያየት ታጥቃችሁ መስራታችሁን ነው፡፡

አያችሁት አይደል ሀገሩን የሚያሞግስለት ፍቅር የሚሰብከው ስለ አንድነት የሚዘምርለት ለዜጎች ክብር የሚሰጥ ሰው ሲያገኝ ለመቀበልና ለመደገፍ ማነው ምን ነበር ወዘተ አላለም፡፡ እናንተ ደግሞ በሰው መወደድን ህዝበኝነት በሚል አሉታዊ ገጽታ ሰጥትችሁ አንደምትኮንኑ ይታወቃልና መራሄ መንግስትነቱን ከማጣችሁ በላይ የአብይ ህዝባዊ ተቀባይነት አብደ እግር እሳት እያቃጠላችሁ ስለመሆኑ የትናነቱ የመቀሌ አዳራሽ ብቻ በቂ ማሳያ ነው፡፤

በአብይ ከመቅናትና ለማሰናከል በመሞከር ፋጻሜአችሁን የከፋ ለማድረግ ከመጣር ይልቅ ራሳችሁን ውቀሱ፡አብይ ያደረገውን ለምን መለስ ማድረግ አልቻለም፣ ብላችሁ ጠይቁ፡፡እናም ማድረግ ስትችሉ በተጠናወታችሁ የደደቢት ልክፍት ምክንያት የተሰጣችሁን ሀያ ሰባት አመታት መጠቀም ባለመቻላችሁና የህዝቡን ትእግስትና ዝምታ በፈሪነትን በዝም ብሎ ተገዢነት ተርጎማችሁ እብሪታችሁ በማየሉ የመጣ ክስተት ነውና አሜን ብላችሁ ተቀበሉ፡፡ከክፉ ስራም ከተካናችሁበት ሴራም ራሳችሁን አቅቡ፡፡ይህ የህዝብ ማእበል ዳግመኛ ከተነሳ ወደ ሱናሜ ይቀየርና አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡