ወልቃይት ውስጥ የአማራ ክለቦችን ማሊያ መልበስም ወንጀል ሆኗል – የአዲረመጥ ነዋሪዎች በማንነታቸው ምክንያት ወከባ እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተገለፀ
የአዲረመጥ ነዋሪዎች በማንነታቸው ምክንያት ወከባ እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተገለፀ
የአዲረመጥ ከተማ ነዋሪዎች በማንነታቸው ምክንያት ወከባ እየተፈፀመባቸው መሆኑ ተግልፆአል። ወልቃይት አዲረመጥ ከተማ የሚገኙ ወጣቶችን፣ ባለሀብቶችንና ሌሎችንም ነዋሪዎች ወደ አዲረመጥ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዱ እያዋከቡ እንደሆነ የወልቃይት አማራ ማንነት ጠያቂ ነህ ተብሎ ከአሁን ቀደም ክስ የቀረበበት ወጣት ከአዲረመጥ ከተማ በስልክ ገልፆልኛል።
በተለይ የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄን ታነሳላችሁ፣ ትደግፋላችሁ በሚል ወጣቶችንና ባለሀብቶችን “ታግለን ያማጣነው ነው። አንድ ኢንች መሬት አንስጥም” በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።
“የወልቃይት ጥያቄን ትደግፋላችሁ፣ ታበረታታላችሁ” እያሉ በሕዝብ ላይ ወከባ የሚፈፅሙት የትግራይ ክልል ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና መከላከያ አዛዦች መሆናቸውም ተገልፆአል።
ዛሬ ግንቦት 22/2010 ዓም ከቀኑ 8:30 ጀምሮ ፖሊስ ወጣቶችን እየያዘ ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ እየወሰደ እያስፈራራ እንደሚለቃቸው ወጣቱ ገልፆአል። እስካሁን ከ30 በላይ ወጣቶች ተይዘው ማስፈራሪያና ዛቻ የተፈፀመባቸው ሲሆን ፖሊስ ወጣቶቹን እየያዘ ወደፖሊስ ጣቢያው መውሰዱን እንደቀጠለ ተገልፆአል።
ወልቃይት ውስጥ የአማራ ክለቦችን ማሊያ መልበስም ወንጀል ሆኗል።
ፍቃዱ አስፋ ይባላል። ዛሬ ከቀኑ 8:30 ጀምሮ የአድረመጥ ነዋሪዎች ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ እየተወሰዱ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል። የመከላከያ አመራሮች፣ የትግራይ ፖሊስና ሚሊሻ ወጣቶችን እያስፈራራ ለቅቋቸዋል።
የማንነት ጥያቄ እንዳያነሱ ለማስፈራራት ከተያዙት ወጣቶች መካከል ፍቃዱ አስፋ አንዱ ነው። ፍቃዱ የፋሲል ከነማ ደጋፊ ነው። በወቅቱም የፋሲል ከነማን ማሊየ ለብሶ ነበር። በህዝብ ላይ ሲዝቱ የዋሉት የትግራይ መከላከያ፣ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት ፍቃዱ የፋሲል ከነማን ለብሰሃል ብለው አስረውታል።
“የፋሲል ከነማ ማሊያ የለበስከው አማራ ነኝ ስለምትል ነው” ብለው ማሊያውን አስወልቀው ራቁቱን እንዳሰሩት ታውቋል። ወልቃይት ውስጥ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ቱርክ፣ ሳውዲ፣ የሚገኙ ክለቦች ማሊያ መልበስ ወንጀል አይደለም። መሆንም የለበትም። የትግራይን ክለቦች ማሊያ ቢለብሱም ገዥዎቹ ደስታቸው ነው። የአማራ ክለቦችን ማሊያ መልበስ ግን ወንጀል ሆኗል። እያሳሰረ ነው። አማርኛ መናገር፣ በአማርኛ መስበክ፣ በአማርኛ ማንጎራጎርና መዝፈንም ወንጀል ሆኗል።