
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በሱዳን፣ኬንያ እንዲሁም በሳውዲ አረብያ በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዲለቀቁ አድርገዋል።
የእርሳቸውን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በአገር ውስጥም በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከእስር ተፈተዋል። የተለያዩ ተግባሮችንም ፈፅመዋል። ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተለያዩ ለውጦችን እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት እንዲሁም ግጭት በማነሳሳት ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት እንደ ኢሳትና ኦ ኤም ኤን ያሉ ሚዲያዎች ክሳቸው መቋረጥ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ ከፍ ያደረገው ይመስላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ወራት ውስጥ ያመጧቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት በናይሮቢ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልሳ ቀናት
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበረው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ “እስካሁን ድረስ በርካታ ቃል ኪዳኖች ተገብተዋል፤ ነገርግን በተግባር የተፈጸመው እስረኞችን መፍታት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ አይደለም” ይላል፡፡
ግለሰቦቹ የታሰሩት የተለያዩ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን ስላነሱ እንደሆነ የጠቀሰው ጦማሪው እስካሁን ግን ለጥያቄዎቻቸው መልስ አላገኙም፤ መልስ መስጠትም አልተጀመረም ሲል ይገልጻል፡፡
እነዚያ ቃልኪዳኖች በህግ አግባብ ወይም በተቋማዊ ተሃድሶ ተግባራዊ መደረግ ካልጀመሩ ሊቀለበሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለውም ጨምሮ ተናግሯል፡፡
በአምነስቲ የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት አጥኚ የሆኑት ፍሥሀ ተክሌ በበኩላቸው “ቢያንስ ለአስርና ለአስራ አምስት ዓመት ወደ ኋላ የሄደ የሰብዓዊ መብት ጉዞ ላላት አገር ሁሉን ነገር ለማስተካከል ሁለት ወር በጣም ትንሽ ነው፤ ነገር ግን ከተገባው ቃልና ህዝቡ ካለው ተነሳሽነት አንፃር ጅምሩ ጥሩ ነው” ሲሉ የጦማሪውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
“ሁለት ወሯ የስራው ማስተዋወቂያ እንደመሆኑ ብዙ ባንጠብቅም መሰረት የምንጥልበት ጊዜ ነው” ይላሉ
ቃልኪዳኑ የግል ወይስ የፓርቲ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚገቡት ቃል ኪዳን አወንታዊና አሉታዊ በሆነ መልኩ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ጦማሪ በፍቃዱ ‘አሁን ለጠቅላይ ሚንስተሩ የሚከብዳቸው የኢትዮጵያን ህዝብ መምራት ሳይሆን ፓርቲያቸውን ራሱ መምራት ነው’ ሲሉ ዶክተር መራራ ጉዲና በአንድ ወቅት ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ የእርሳቸው ስጋት የእርሱም ስጋት እንደሆነ ይናገራል፡፡
ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ፈተና የመወጣት ሃላፊነት አለባቸው፤ ይህ ደግሞ የሞራል ግዴታም ጭምር ነው ሲል ይገልጻል፡፡
የፓርቲያቸው ድጋፍ በሌለበትና ፓርቲያቸው ባላለው ነገር ላይ ይናገራሉ ብለው እንደማያስቡ የተናገሩት የሰብዓዊ መብት አጥኝው ፍሰሃ “ወክለው አይደለም የሚናገሩት የሚል ማስረጃ እስከሌለ ድረስ በመርህ ደረጃ ፓርቲያቸውን ወክለው ነው የሚናገሩት ብለን እናስባለን” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የኢህአዴግ አዲሱ አረማመድ
ኢህአዴግ ራሱ እንደ ፓርቲ ማሻሻል ላይ ነው ማለት ይከብዳል የሚለው ጦማሪ በፍቃዱ “ኢህአዴግ አራት ቡድኖች ናቸው ያሉት፤ አንዳንዶቹ ቡድኖች በተለይ ደግሞ ኦህዴድ ቀድሞ የነበረው አካሄድ ትክክል አይደለም የሚል አቋም አለው፤ እርሳቸውም የመጡት ከዚሁ ፓርቲ ነው:: ቢሆንም ግን ፓርቲዎች አንድ ዓይነት አቋም ይዘው ቢወጡም ግለሰቦች የተለየ ሃሳብ ሊኖራቸው ይችላል” የሚል እምነት እንዳለው ይናገራል፡፡
አሁን ባለው ርዕዬተ ዓለማዊ አካሄድ መሰረት አልተለወጠም፤ ነገር ግን ቃል የሚገባቸው ማሻሻያዎች በራሱ የርዕዬተ ዓለም ለውጥ ያመጣሉ ብሎ እንደሚገምት በፍቃዱ ይገምታል፡፡
የፖለቲካ እርቅ ስራዎች መሰራት አለበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት አለበት ፣ አዋጆች መሻሻል አለባቸው፣ አንዳንድ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዳይሰፋ የሚያደርጉ ህገ መንግስታዊ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ወደተግባር የሚገበቡበት ጊዜም ነው ሲልም ይጠቅሳል፡፡
“አሁንም ህዝባዊ ተቃውሞዎች የተቀዛቀዙት ጥያቄዎቻችን ይመለሳሉ በሚል ተስፋ እንጂ ጥያቄዎቻቸውን ረስተው አይደለም፤ ይህ ካልሆነ ህዝባዊ ተቃውሞዎች መልሰው ማገርሸታቸው አይቀርም” ሲልም ስጋቱን ገልጸል።
በየጊዜው አንደዚህ ብለው ነበር የት አደረሱት እያለ የሚጠይቅ የተነቃቃ ፓርላ ቢኖር ስራቸውን ያግዛቸው ነበር የሚሉት ፍሰሃ ተክሌም ወደኋላ መመለስ እንዳይኖር የሚገቡ ቃል ኪዳኖችን ህጋዊና ተቋማዊ መልክ ማስያዙ ትልቁ መንገድ ነው፤ ይህም በቅርቡ ይጀመራል ብየ አስባለሁ ይላሉ፡፡
አክለውም የፓርላማ አባላት በሙሉ የኔ ናቸውና አንድ ድምጽ ይስጡ የሚለው አስተሳሰብ ከመሰረቱ መቀየር አለበት፤ አገሪቷን ለችግር ከዳረጋት አንዱ ምክንያት የሆነው ተቋማትን ጥቅም የለሽ ማድረግ ነው ይላሉ።
SOURCE – BBC/AMHARIC