ግንቦት 24/2010
አዎ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኃላ ቀር በሚል ልዩ ስም የአፋር ክልል እንዲጠራ ተደርጓል።
ያደረገው ደግሞ ህወሀት ነው።
የአፋር ክልል እራሱን ችሎ በሁለት እግር እንዳይቆም፣ የራሱን ውሳኔ በራሱ እንዳይወስን፣ ሆነ ተብሎ ስማቸውን እንኳን መጻፍ የማይችሉ መሃይሞች እንደ አደራ ጠባቂ ቁጭ አድርጎ የተማሩ የክልሉ ልጆች ለህዝባቸው እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆነዋል።
ህወሀት ይህን ሲያደርግ ብዙ ምክንያቶች አሉት።
አንደኛ በአፋር ክልል የሚገኘውን የተፈጥሮ ሃብትን ለመዝረፍ እንዲያመቸው ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ የአፋር ክልል በመልከዓ ምድር አቀማመጥ ያለው የጂዮፖለቲካል ፋይዳ ላይ በኢትዮጲያ ደረጃ የበላይ ሆኖ ለመወሰን ነው።
ይህ ደግም የአፋር ህዝብን ላለፉት ሃያ ሳባት አመታት ክፉኛ ጎድቶታል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝብ ያለበት ክልል እንዴት ነው በመሃይሞች የሚመራው ?
እውነት ክልሉን በብቃት አስተዳድሮ የዕድገት አቅጣጫ የሚቀይስ አንድም ምሁር በክልሉ ጠፍቶ ነውን ?
እቅድ ነድፎ፣ አጥንቶና መርምሮ፣ የህዝብን ቅሬታ በማዳመጥ ፍትህ የሚሰጥ፣ በህዝብ ተመርጦ ለህዝብ የሚሰራ፣ የመከላኪያ ጀነራሎችን ሳይሆን የህዝብን ፈላጎት የሚያዳምጥ መሪ ማግኘት ያልቻለው ለምንድነው የአፋር ህዝብ ?
የአፋር ክልልን ከሃያ አመታት በላይ ከመቀሌ በሚመጣላቸው ቀጭን ትዕዛዝ ሲመሩ የነበሩት አቶ እስማኢል ተንስተው ሌላኛው የቀድመው የህወሃት ተጋይ አቶ ስዩም አወል ተኩዋቸው።
በግዜው አቶ እስማኢል ከስልጣን ሲነሱ ወጣቶቹ ዛሬማ አንድ የተማረ መሪ መምረጥ አለብን ብለው ባደረጉት ሽኩቻ፣ በክልሉ መሪው ፓርቲ ውስጥ ትልቅ ውጥረት ተፈጥሮ ነበረ።
የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አብዴፓ ) የራሱ ህግ-ደምብ በሚለው እንኳን የወጣቶቹ ቡድን አብላጫ ድምጽ ነበራቸው።
ቢሆንም ግን ከብዙ ክርክርና ሰብሰባዎች በኃላ ህጉን እርግፍ አድርጋችሁ የአቶ ስዩም ቡድን መንግስት ይመስርት የሚል ትዕዛዝ ተወልደ ዕዉር የሚባል አንድ የህወሀት ሰው ጣልቃ በመግባት ወሰኑ።
አቶ ስዩም አወልም ህገ ወጥ ወምበራቸው ደርበው የፓርቲው ሊቀመንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ቁጭ አሉ።
ምን ይሄ ብቻ፣ በፓርቲያቸው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዉን በቅርብ ዘመዶቻቸው ሞሉ።
በዚህ ብቻም አላበቁም፣ ከቀበሌ እስከ ክልል የተቀናቃኞቻቸውን ደጋፊዎች ባሉዋቸው ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ወሰዱ።
አቶ ስዩም አወል ከእስማኢል አሊ ሲሮ በፊት ገና ክልሉ ሲመሰረት ጀምሮ የዞን ሁለት የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ የነበሩ፣ ከዛ በኃላም በአቶ እስማኢል ግዜም ወደ ክልል ደረጃ ከፍ በማለት የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ በመሆን ከሃያ አመታት በላይ የሰሩ ሰው ናቸው።
አቶ ስዩም አወል ይህንን ስልጣንን በመጠቀም በአቶ መለስ የተመሰረተውን የልዩ ፖሊስ አዛዦች ከላይ እስከ ታች የገዛ ቤተሰቦቻቸውን በመሾማቸው ሰማቸው ይነሳል።
በሌላ በኩል በክልሉ የጨው ሃብት ውስጥም ስማቸው በሙስና በስፋት ይነሳል።
የአፍዴራ ጨው ማህበር ሃላፊ የወንድማቸው ልጅ ሲሆን እሳቸውን ጭምሮ አንዳንድ የፓርቲው ሃላፊዎች ከአፍዴራና ዶቢ የጨው ምርት የተለየ ጥቅም እንዳላቸው ፀሃይ የሞቀው ሀገር ያወቀው ጉዳይ ነው።
በክልሉ ከህግም ከህዝብም በላይ የሆኑ የአንባገነኖች ቁንጮ የሆኑት አቶ ስዩም እሳቸውን የተቃወመ ሁሉ ያለ ፍርድ መቀመቅ በማውረድ ያሰቃያሉ።
በዚህ ሁኔታ የአፋር ክልል ታዲያ ኃላ ቀር ተብሎ ቢጠራ ምን ይደንቃል¸ ?
አሁን ግን በኢትዮጲያ እየታየ ካለው የለውጥ ተስፋ ምስኪኑ የአፋር ህዝብ ብዙ ነገር ይጠብቃል።
ለውጥ ፈላጊ የሆኑ ወጣቶች በክልሉ በተለያዩ መንገድ እያደረጉ የሚገኙት ትግል በክልል ደረጃ እየተቀጣጠለ ይገኛል።
በክልሉ ርዕሰ መዲና ሰመራ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የሰመራ ጤና ሳይነስ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ የሰመራ-ሎግያና አጎራባች ከተሞች ነዋሪዎች በነቂስ የወጡበት ሰላማዊ ሰልፍ ከቀናት በፊት ተደርጓል።
በፈስ ቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች መንግስትን ተችታችኃል ተብለው የታሰሩ ወጣቶች እስካሁን አልተፈቱም።
ዶ/ር አብይ በጡረታ የሸኙዋቸው የህወሀት መሪዎች ፊታቸው ወደ አፋር ክልል ያዞሩ ይመስላል።
የህወሀት መሪዎች የአፋር ክልል መሪ ፓርቲ አብዴፓን እና የሶማሌ ክልል መሪው ፓርቲ ሶዴፓን በመያዝ ለመንቀሳቀስ ሙከራ በማድረግ ላይ ናቸው።
በግንቦት 24/ 2010 በጎበዛይ ወ/አረጋይ የሚመራ የህወሃት ቡድን ወደ ሰመራ በመምጣት ከአብዴፓ ካድሬዎች ጋር መምከራቸው ተስምቷል።
የመከሩበት ነጥብም አሁን በክልሉ የአፋር ወጣቶች እንቢትኝነት ( ዱኮ ሂና ) በምል ስም የተራጀ የለውጥ ፈላጊ ወጣቶች እንቅስቃሴ የአዲሱ መንግስትን ድጋፍ ሳያገኝ ማክሸፍ አለብን በማለት እየዶለቱ ይገኛሉ።
ማንኛውም ነገር ቢመጣ አብዴፓና ህወሃት አንድ መሆን አለብን፣ አሁን የመጣው አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በትግላችን ያረጋግጥነውን የብሔር ብህረ ሰቦች መብትን የሚያዳክም ሰለሆነ ልንታገለው ይገባል በማለት፣ የመጀመሪያ ስራቸው ተሃድሶ እንዲደረግ የሚጠይቁ የዩንቨረሲቲ ተማሪዎችንና ምሁራን ወጣቶችን የጀመሩትን ተቃውሞ ማክሸፍ አለብን በማለት መክሯል።
በዚህ መሰረት በሰመራ ከተማ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባብራችኃል የተባሉት የጤና ሳይነስ ኮሌጅ ተማሪዎች ከትምህርት ትባረራላችሁ እስከ ማለት ማስፋራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ይገኛል።
በክልሉ የጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አማክይኘት ተማሪዎቹ ተቃውሞውን የሚቀጥሉ ከሆነ ከትምህርት እንደሚባረሩ ተነግሯቸዋል።
ይህን ሁሉ ለማድረግ በህወሃት እየተላኩ ያሉ የክልሉ አመራሮች በተለይ በጤና፣ በትምህርትና የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ዘርፎች ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት በአዲስ አበባ ሳይቀር ቤቶች ሲገዙ የ አፋር ህዝብ በኮሌራና በ አተት ተላላፊ በሺታዎች እያለቀ ይገኛል።
አቶ ያሲን ሃቢብ የጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሲሆን ከሃጂ ስዩም አዲሱ ካቢኔ ውስጥ አንዱ እሱ ነው።
በሶስት አመት ስልጣኑ በአዲስ አበባ ሁለ ቪላ ቤቶች ለመግዛት የበቃ ሙሰኛ ነው።
ዛሬ ወጣቶቹ መብታቸውን ለማስከበር ሲታገሉ የእናቱ ቤት ይመስል አባርራችኃለሁ ማለቱ በክልሉ ያለው የመብት ረገጣ የደረሰበትን ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሰየን አንዱ ማሳያ ነው።
በአጣቃላይ በክልሉ ያለው ጫፍ የረገጠ ሙስናን በተመለከተ በስፊው በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ።
ለዛሬ ግን ለማጣቃለያ ያህል በየተኛውም ቦታ የምትገኙ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጲያዊያን በሙሉ አፋርን ከህወሀት መጠቀሚያነት እንድናድን ትኩረት እንድታድርጉ መልክቴን አስታላልፋለሁ።
ደህና ሰንብቱ
አካደር ኢብራሂም አኩ