እስር ቤት
INTI OCON

በርካታ እስረኞች ከእስር የተለቀቁ ቢሆንም አሁንም ያልተነገረላቸውና ታዋቂ ያልሆኑ በርካቶች ከሽብርና ሁከት ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው በእስር እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸውና ጠበቃዎቻቸው ይናገራሉ።

ከግንቦት ሰባት ወይም ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላችሁ፤ እነሱን ልትቀላቀሉ ነው በሚል ክስ ተመስርቶባቸው በእስር የሚገኙ ብዙዎች መሆናቸውም ይነገራል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራር የነበረው ነኢ ገመዳ ወንድም የሆነው አማን ኡስማን “ነኢ ብቻ አይደለም፤ በ1984 ዓ.ም ከቤት የተወሰደው ወንድማችንም የት እንደደረሰ አናውቅም፤ በጊዜው የ26 ዓመት ወጣት ነበር፤ እሱ እንደዚያኛው ስለማይታወቅ ከእኛ ውጭ ማንም አንስቶት አያውቅም፤ እኛ ግን እንደ ቤተሰብ እየታመምን ነው ያለነው” ሲል ይናገራል፡፡

የእስረኞች ጠበቃ የሆኑት አቶ ሔኖክ አክሊሉ ሰው የማያውቃቸው፣ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማያታወቁ እስረኞች በርካታ ናቸው ይላሉ፡፡

በተለይ ደግሞ ከ2006 ዓ.ም በፊት የታሰሩ በጣም በርካታ እስረኞች እንዳሉና እነርሱን በተመለከተ ያሰባሰቡትን መረጃ ለሚመለከተው አካል እንዳስተላለፉ ይገልጻሉ፡፡

መረጃውን እንዴት ሊያሰባስቡት ቻሉ?

በተለያዩ ሚዲያዎች፣ ህዝብ ሊያገኛቸው በሚችልበት መንገድ ሁሉ መረጃውን ለማግኘት ጥረት እንዳደረጉ የሚገልጹት ጠበቃው፤ “ያገኘኋቸው ምላሾች በጣም የሚያሳዝኑ ናቸው” ይላሉ፡፡

‘ባለቤቴ እንደወጣ ቀረ፤ ልጄ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ታስሮ ቀረ፤ ከዚያ በኋላ የት እንዳለ አላውቅም’ የሚሉ ብዙዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚናገሩት የታዋቂ ሰዎች፣ ውጭ አገር ያሉ ሰዎች ባላቤቶች፣ ልጆቻቸው የታሰሩባቸው በጣም በርካታ ሰዎችም መረጃ ልከውላቸዋል፡፡

ክሳቸው በአዲስ አበባ የሚታይላቸው ብቻ ሳይሆኑ በተዘዋዋሪ ችሎት የሚታይላቸው አሉ እየተባሉ ብዙ ዝርዝሮችም እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡

በደረቅ ወንጀል የተከሰሱ ሊኖሩ ስለሚችሉ በሽብር ወንጀል ነው የታሰሩት ለማለት ማጣራት ይጠይቃል የሚሉት ጠበቃው ይህንንም ለማጣራት እየሞከሩ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ማን በምን ጉዳይ ታሰረ? የት ነው ያለው? ምን ያህል ዓመት ታሰረ?፣ ምን ያህል ዓመት ይቀረዋል? የሚል ዝርዝር መረጃም የለም፤ የት እንዳሉም አይታወቅም፤ በማለት ይህ ጉዳዩን ውስብስብ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ፡፡

በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በርካታ እስረኞች እንዳሉ የሚናገሩት ጠበቃው “ሞቱ የሚባሉ ሰዎች በህይወት የሚገኙበት፣ አሉ የሚባሉት ይሙቱ ይዳኑ የማይታወቅበት ነው” ይላሉ፡፡

“ቢሆንም ግን በእጃችን ላይ ያሉትን መረጃዎች ለሚመለከተው አቅርበናል፤ እያጣራን ያለውንም አቅርበን እንዲፈቱ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የማይታወቁ እስረኞች ጉዳይ…

ተመሳሳይ ክስ የተፈረደባቸው ሰዎች አንዱ ተፈትቶ ሌላው የማይፈታበት ከህገ መንግስቱም ሆነ ከዓለም አቀፍ መርሆች አንፃር አግባብ አይደለም ይላሉ አቶ ሔኖክ።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ህዝብ ግንኙነት የሆኑት አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው “ጥያቄው ሁሉንም መረጃ በዝርዝር ካለማወቅ ሊመጣ ይችላል” ሲሉ ይጀምራሉ፤ መንግስት በገባው ቃልና በህዝቡ ጥያቄ መሰረት በቅርቡ 137 የሽብር መዝገብ ክስ ተቋርጧል፤ በልዩ ልዩ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ከተባሉ 576 ታራሚዎችም መፈታታቸውን ገልጸዋል።

“እስረኞቹ የአገሪቱን ህግ ተላልፈው ጥፋተኛ የተባሉና በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በጥፋታቸው ተፀፅተው፣ ታርመው ወደ ህብረተሰቡ ቢቀላቀሉ አምራች ዜጋ ይሆናሉ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው” ያሉት ባለሙያው ከእነዚህም መካከል ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው በእስር ላይ የነበሩት 18 ሴቶች በልዩ ሁኔታ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

ምንም እንኳን ሴቶቹ ጥፋተኛ ቢሆኑም በዚህ ሁኔታ መቆየታቸው በልጆቹ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ታስቦ በልዩ ሁኔታ ምህረት እንደተደረገላቸው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

አቃቤ ህግም በተሰጠው ስልጣንና የይቅርታ አፈጻጸም ስርዓት መሰረት በህዝብ ጥያቄና በመንግስት ፍላጎትና ውሳኔ ታራሚዎቹ ይቅር ተብለዋል ሲሉ ያክላሉ፡፡

“ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር፣ ከሁከት ጋር በተገናኘ የታሰሩና ቤተሰብ ሊከታተልላቸው የማይችል በርካታ እስረኞች መኖራቸው አሳስቦኛል” ያሉት አቶ ሔኖክም “ወደፊት ራሱን የቻለ አንድ ኮሚሽን አቋቁሞ እንዲጣራ ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር በግለሰብ ደረጃና በተበታተነ ሁኔታ መስራት አዳጋች ነው” ብለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬም በቀጣይ መፈታት ያለባቸው አሉ ከተባለ እየታየ፣ እየተጣራ ክሳቸው እንደሚቋረጥላቸው ወይም ይቅርታ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

SOURCE     –    BBC/AMHARIC