በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይፈፅማል ያለውን የልዩ ኃይል ፖሊስን መንግሥት እንዲበትን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጠው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

አምነስቲ እንዳመለከተው በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመግባት ግድያን ይፈፅማሉ ያለቸውን የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይልን የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስወጣና እንዲበትን ጠይቋል።

በሶማሌ ክልል የፀረ-ሽብር ልዩ ኃይል ሆኖ የተቋቋመው የዚህ ቡድን አባላት በዚህ ሳምንት በሶማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን 48 ቤቶች በማቃጠል ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲሸሹ ማድረጉን ጠቅሷል።

መግለጫው ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የልዩ ፖሊስ ክፍልን በአስቸኳይ በመበተን ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎች ተገዢ በሆነ የፖሊስ ኃይል እንዲተካም ጠይቋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የታላላቅ ሃይቆች ዳይሬክተር የሆኑት ጆዋን ኒያኑኪ እንዳሉት “የልዩ ኃይሉ አባላት እንደፈለጉ በህዝብ ላይ ግፍ እንዲፈፅሙ መፈቀድ የለበትም” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ልዩ ኃይሉ በምሥራቃዊ ኦሮሚያ ጭናቅሰን ወረዳ ውስጥ በሚገኙ አራት መንደሮች ላይ በፈፀመው ጥቃት 5 አርሶ አደሮች ሲገደሉ 50 የሚጠጉ ቤቶች በእሳት ተቃጥለዋል።

በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ መኖሪያቸውን ጥለው መሄዳቸውን የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል።

“የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህ ጥቃት እንዲያበቃ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ያሉት ጆዋን ኒያኑኪ “ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ፖሊስ የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር ማድረግና በጥቃቱ ተሳታፊ የሆኑትን በነፃና ገለልተኛ ምርመራ በመለየት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ልዩ የፖሊስ ኃይሉ ባለፈው ዓመት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቁ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በማጠቃለያው በአካባቢው ላለው ውጥረት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት፤ የኦሮሚያንና የሶማሌ ክልሎችን ድንበር ለይቶ ለማስቀመጥ በ1996 በተካሄደውን ህዝበ-ውሳኔ የተገኘውን ውጤት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ይህንን ሪፖርት ተከትሎ የኢትዮጵያን መንግሥት ባለሥልጣናትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

SOURCE    –   BBC/AMHARIC