ሰው ማለት ሰው የሚሆነው ሰው የጠፋ እለት ይባላል፡፡ወያኔ ለምኒልክ ቤተ መንግሥት በቅቶ ነገረ ሥራው ሁሉ ጥፋት በሆነበት እሱ ቤተ መንግሥት ገባ አንጂ መንግስተ ኢትዮጵዊነት እሱ ውስጥ አልገባ ብሎ ስሙ እንጂ ግብሩ የኢትዮጵያ  መንግስት  አለመሆን ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም የማይሆን ስለመሆኑ ምልክቶች በግልጽ በሚታዩበት ያን ወቅት አሸጋግረው የሚያዩ ቀድመው የሚተነብዩ ሰዎች ያስፈልጉ ነበር፡፡ ታዲያ ብዙም ባይሆኑ ተገኝተዋል ሰሚ አጥተው፣ የሚያደንቅ አንጂ የሚደግፍ፣ የሚያጨብጭብ እንጂ ትንበያቸውን ተረድቶ ስጋታቸውን ተጋርቶ የፈሩት እንዳይደርስ ለመከላከል መሆን አለበት ያሉት አንዲሆን የሚታገል ቁጥሩ አንሶ በአጥፊዎቹ ኃይል ከመድረክ  ተገፍተው ተጣሉ እንጂ፡፡ሰው በጠፋ እለት ሰው የሆኑት ሰዎች ንግግራቸውን የሚሰማ ስጋታቸውን የሚጋራ ጥረታቸውን የሚደግፍ ብዙ ሰው ኖሮ ቢሆን ወያኔ ሀያ ሰባት አመት ባልገዛ አሁን ለማጽዳት ያስቸገረ የቆሻሻ ክምርም ባልተጫነን ነበር፡፡

በአንጻሩ ደደቢት የፈጠሩትን ታሪክ እያወሩ ብዙዎችን ያሳተውንና ያሳሰተውን የራስን እድል በራስ መወሰን መርዝ እየሰበኩ ኢትዮጵያዊነትን እያኮሰሱ ጎሰኝነትን ሲያወድሱ ብዙዎች አንዳንዶች ፈጽሞ እዚህ ደረጃ ይደርሳሉ ያልተባሉት ሳይቀር በአንድ ጀንበር የጎሳ ድርጅት እየፈጠሩ ለወያኔ የዘረኝነት ዘር ውኃ አጠጪ ኮትኳችና ተንከባካቢ ሆነው ተሰለፉ፡፡የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ጎድቷል ስንል እነዚህ ባለድርሻዎችም አብረው መታሰብ አለባቸው፡፡

ደራሲ ተውኔት አያልነህ ሙላትን ያያችሁ ብዬ ጀምሬ  ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖብኝ ሌላ ቦታ ገባሁ መሰል ፡፡ስለ አያልነህ ሙላት ብዙ ማለት የሚችሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ከእኔ ጋር በአካል ብንተዋወቅም ስለ እርሱ ብዙ እውቀት የለኝም፡፤ በጋሜ መቅረት የምትለው ቲያትሩ ግን ልቤ ውስጥ አንድ ብቸኛ ስፍራ ይዛ ትኖራለች፡፡

አያልነህ ገና በማላዳው የወያኔዎቹ ነገረ ስራ ገብቶት የታየውን ለህብረተሰቡ ለማሳየት ብዙ የጣረ ብዙም የተንገላታ ሰው ነው፡፡ ወቅታዊ ትያትሮችን እያዘጋጀ ወጣት ተዋንያንን እያለጠነ  አዳራሽ ተከልክሎ መጋዘን እየተከራየ(ግንፍሌ የነበረውን አስታውሳለሁ)ብዙ ሞክሯል፡፡ ኋላም የሩሲያ የብል ማዕከል ውስጥ የሚገኘውን ፑሺኪን አዳራሽ በኪራይ ይሁን በነጻ ፈቃድ ይዞ ሰርቷል፡፡እኔም  በጋሜ  መቅረትን ያኋት እዛው አዳራሽ ነው፡፡

ትያትሩ በዚህ ሁኔታ የታየ በመሆኑ ብዙ ሰው ስለማየቱ እጠራጠራለሁ፡፡ ትያትሩ እንደሚያሳየው የመጣ የሄደው ጸጉሯን እየላጨው በጋሜ የቀረችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ አዲስ መጪው አመጣጡ በሥርዓት ሳሆን በጉልበት በመሆኑ ከእርሱ ቀደም የነበረው ሁሉ የማይጥመው በመሆኑ ሁሉን አፍርሶ ከዜሮ ይጀምራል፡፡ በኢትዮጵያ የስርዓተ መንግሥት ቅብብሎሽ አለመኖር ያደረሰውን ጉዳት አሳይቶ ወቅታዊውን የወያኔዎች የጥፋት ጅምሮ በሚገባ አመላከቶ ከዛ መስመር በአፋጣኝ መውጣት እደሚገባ የሚያስገነዘብም የሚያጠነቅቅም ነበር ትያትሩ፡፡ ለዚህም ነው በወያኔዎች እመቃና ክልከላ የገጠመው፡፡

ዙሪያ ገባ ሄድኩ መሰል ፣  አዲሱ ጠቅላይ ማስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በነበረው መሰረት ላይ ጡብ ማስቀመጥ ሲገባ የሚመታው የነበረውን መሰረት እየናዳ በአዲስ በመጀመር…ወዘተ እያሉ በቁጭት መንፈስ የሚያሰሙት ንግግር ነው ድሀ አደግን አስታውሶ የአያልነህ ሙላት ጥረት ቢዘገየም ዛሬ ምላሽ አገኘ በማለት በዚህ ሰአት አስፈላጊነቱ ታይቶኝ አፋልጉኝ ብዬ የመጣሁ፡፡

አያልነህ ዛሬ ወደ መድረክ የሚወጣበት ግዜ ይመስለኛል፡፡ የቀደሙትን በጋሜ መቅረትን ድሀ አደግን ወዘተ ትያትሮቹን  ብቻ ይዞ ሳይሆን አዳዲስ ስራዎችንም ለማቅረብ፡፡ጠቅላይ ማኒስትሩም በየሙያ ዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች ኃላፊት ሲሰጡ፣ አደራ ሲያሸክሙ የሰማሁ መሰለኝ፡፡

ቴዲ አፍሮም ቢሆን አሁን ወቅቱ የሚሻው አርቲስት ነው፡፡ የተወገዘበት ኢትዮጵያዊነት፣ ሰንደቅ ዓላማ አንድነት ፍቅር ወዘተ ዛሬ ክብር አግኝተዋል፡፡የቴዲ ስራ ለወያኔዎች ምን ያህል የእግር እሳት ሆኖባቸው አንደኖረ ያ ማነው ስሙ የብሮድካስት ባለሥልጣን ኃላፊ የነባራ ሰውዬ ያለምንም ሀፍረትና ይሉኝታ በመድረክ የተናገረው በቂ ገላጭ ነው፡፡ እሱ ያለውን መድገም አያሻም፡፡ አሁን ቦታውን ያገኘ ይመስለኛል፡፡ እናስ ታዲያ ቴዲስ ቦታውን ማግኘት የለበትም፡፡

ያለማንም ከልካይ ያለምንም ስጋት በኳስ ሜዳ በአዳራሽ ሚሊኒየምን ጨምሮ በተለያዩ ኢትዮጵያዊያኖች በዛ ብለው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ እየተገኘ የቀደሙ ስራዎቹንም ሆነ አዳዲስ እየፈጠረ ይህን ቀና ማለት የጀመረ ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ የማቃናት እየተጠገነ ያለውን አንድነት ይበልጥ የማጥበቅ እየተሰበከ ያለውን ፍቅር የማጽናት ወዘተ ሥራ መስራት ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፡፡