ዩሱፍ ያሲን / ኦስሎ ኖርዌይ

በዛሬይቷ ኢትዮጵያችን ተስፋም ፣ ስጋትም ፣ ሰፍኗል ፡፡ ጎን ለጎን እርግጥ ተስፋ መሰነቁ ሚዛን እየደፋ መምጣቱ አይካድም ፡፡ መዳረሻችን በውል ባለመታወቁ ጉዟችንን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱ ወገኖች በዚያኑ መጠን እንዳሉ መቀበል የግድ ይላል ፡፡ ደስ በሚያሰኙ ቸር ወሬዎች እየተንበሸበሽን ነን ፡፡ ባንጻሩ ተስፋን የሚያደበዝዙ ዜናዎች ያንገላቱናል ፣ ያላጉናል ብንል ማጋነን አይሆንብንም ፡፡ There is Good news ብለው በኋላ There is bad news በማለት አሜሪካኖቹ እንደሚጠርቁት መሆኑ ነው ፡፡ በየቱ እንጀምር ከነጸሎቱ « ቸር ወሬ ያሰማን » ስለሆነ ወጉ ደግ ደጉን ላስቀድም ፡፡

ትልቁ ብሥራት የበርካታ የፖለቲካ እስረኞች ክሶች መቋረጥና መፈታት ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊነት መሰበኩ ነው ፡፡ የመግባባትና የእርቅ ድባብ እንዲወርድ ፍላጎት መታየቱ ነው ፡፡ «ተፎካካሪ ፓርቲዎች» ስለ ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅ ማውረጃ ንድፎች ላይ ሃሳብ  ለሃሳብ  እንዲወያዩ  መጀመሩ  ነው፡፡  ባጭሩ  የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ ሂደት በምር መጀመሩ ፍንጭ መታየቱ ነው ትልቁ የዶክተር ዓቢይ የእስካሁኑ ስኬት፡፡ በሁሉም ዘንድ ተስፋችን መለምለሙ ብቻ ሳይሆን በእርስ በእርስ መበጣበጥና መመሰቃቀል አፋፍ ላይ የነበረችው አገር ወደ መረጋጋት ፊቷ መመለሱ ነው ትልቁ ነገር ፡፡ ምንም እንኳን ለዶክተር ዓቢይና ለቲም ለማ ሁሉም በተራውና ከየአቅጣጫው የፍላጎቱ መመዝገቢያ ሊስት (Wish list) ቢያዥጎደጉዱለትም፣ ዕድልና አዲስ ተስፋ መፈንጠቁን እናቶች ተቀብለው ነው ቱፍ፣ ቱፍ እያሉ የከፉ አይንካብን  ምርቃት የሚቸሩት፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ለዶክተር አቢይ ቴ” የሚል አዲስ ስም አወጡለት እየተባልንም ነው፡

ባንጻሩ ጥርጣሬው ለከት የለውም ፡፡ ዋናው ዶክተር ዓቢይን የወያኔኢሃዴግ ሴራ ተቀባይና ወኪል አድርጎ መመልከቱ ነው አንዱ የጥርጣሬ ስጋት፡፡ በስርአቱ ተኮትኩቶ የተመነደገ የጉዲፈቻ ልጅ እስከማለት ፡፡ እነዚህ ምክንያቶቻቸውን እንደሚደረድሩት ሁሉ የዓቢይ ደጋፊዎችም በተራቸው ከሙሴ እስከ ጎርባቾቭ ከስርአቱ ሆድ እቃ ለውጥ ፈላጊው ብቻ ሳይሆን ነጻ አውጪው ነቢይ ተመዞ የወጣ  እንደ  ሆነ  ሁሉ ያስተምራሉ  ፡፡  አንድ  የሃይማኖት  አባት  የሙሴ  በፈርዖን ቤተ መንግሥት ማደግ የእስራኤል ህዝብ መሪነንና ሀራ የማውጣት ተልእኮውን አልጋረደበትም ይሉናል ፡፡ ሌሎቹ የጎርባቾቭ ስም ከሶቪየት ህብረት ኮሚንስት ፓርቲ ውስጥ አድጎና ተመንደጎ በግላስኖትስና ፣ በፐርስቶሪይካ አማካኝነት ታላቋን የሶቭየት ህብረት ከስር መሰረቱ  ውልቅልቋን አውጥቶ የለውጥ ኃይል ይሆናል ብሎ የገመተ የለም ይሉናል ፡፡ የዚህ ሁሉ ምሳሌ ዳራ ፣ ለዶክተር አቢይ ዕድል እንስጥው ነው መልዕክታቸው ፡፡

እርግጥ ለውጡ በሃገር ቤት እየፈጠነ ነው ፡፡ እንደ ደርጉ ባቡር እያራገፈ ብቻ ሳይሆን እያፈናጠጠ ነው ፡ ገሚሱ ዶክተር አቢይና ቲም ለማን እንርዳ በማለት ሲቀላቀሉዋቸው ፣ ገሚሱ ደግሞ በተለመደው አፈ ጮሌነት  ማዕበሉን  መፈናጠጥ ተያይዘውታል ፡፡ ዓረቦቹ – አርከብ አል ሞጃ (ማዕበሉን ተፈናጠጥየሚሉት አይነትእሩጫ ነው ፡፡ ያም ሆነ ይህ የትግሉ ማዕከል ወደ ሃገር ቤት እየተመለሰ ነው፡፡ ዲያስፖራው ሚናውንና ድርሻውን ብቻ ሳይሆን የትግል ስልቱንም እየፈተሸ ነው ፡፡ ሌላም ቸር ወሬ አለሁሉም ሰከን ማለት ጀምሯል ፡፡ አንዳንዶች ለስልጣን አለመታገላቸውንም እየማሉና እየተገዘቱ ባለድርሻናታቸውን ተቀብለው ከሌሎች ጋር ለመሥራት ዝግጁነታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው ፡፡ በዶክተር አቢይ ቋንቋ ለመደመር” እየተዘጋጁ ናቸው ፡፡ ይበል ! የሚያሰኝ ነው ፡፡ ወርቃማ ዕድል የማስመለጡም አባዜም ሆነ እርግማን እንዳይለጠፍበት ሁሉም ጥንቃቄ እየወሰደ ነው፡፡ በዲያስፖራው ካለው ኢትዮጵያዊ አብዛኛው

 

ዘውዱን በኪሱ ይዞ ይዞራል እንዳልተባለ ሁሉ፣ አሁን አሁን የተወሰነ ትህትና እየተመለከትን  ነን፡፡ ልካቸውን ፣ ሚናቸውን ፣ የትግል ድርሻቸውንም እየተረዱ እንዳሉ ሁሉ ፀሃይቱ ጎህ ቀዳ በጧት ብቅ የምትለው  ጩኸቴን  (ትዕዛዜን) ሰምታ ነው ብሎ ይኩራራል እንደሚባልለት አውራ ዶሮ ፣ ቄሮም ፋኖም፣ ዘርማም ፣ ሁሉንም ከኋላ የማዞረው እኔ ነኝ ባይ ግብዝ ታጋይም ዛሬም አልጠፋም ፡፡

በሰከን ማለቱ ግንባር ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች ቢኖሩ ከእስር ቤት የተፈቱት ታጋይ መሪዎች ናቸው፡ ትህትናቸው አስተማሪ ነው፣ የትግል ወኔያቸውም እንዲሁ ፡፡ የትግላችን መዳረሻ ያው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት ጠፍቶህ ነው ወይ የትግላችን መዳረሻው የት ነው ብለህ ጉንጭ አልፋ ጥያቄ የምትሰነዝረው ለምትሉኝ አንባቢያን መዳረሻ መንገዱ ነው አስቸጋሪውና ውስብስቡ እላለሁ ፡፡ ከሁሉ የተሻለ ሲናርዮ ብትጠይቁኝ በሽግግር መንግሥት አማካኝነት የሚካሄድ የሽግግር ሂደት ነው ፡፡ በዚህ ሂደት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ እስከ ምርጫው የሚዘልቅ የሽግግር ሂደት ነው እላለሁ ፡ ግን ይህ አማራጭ  በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ መሳካት መቻሉን እጠራጠራለሁ፣ ስለዚህ አብዛኛዎቹን ባለ ድርሻ አካላቶች ያሳተፈ ማንንም ያላገለለ የሽግግር ሰነድ የሚነድፍ አካል መስርቶ አንድ ሽግግር ሳይሆን በርካታ ሽግግሮች  እንደሚያስፈልገን  አምኖ  መቀበል  ነው  ፡፡  አዲስ  ህገ  መንግስትን  የመንደፉን ተግባር ለሁለተኛው ሽግግር በመተው ያሁኑ ሽግግር በብሄራዊ መግባባትና  ዕርቅ  ማውረዱ  ላይ  ትኩረት እንዲያደርግ  ስምምነት  መድረስ  ነው ፡፡ ምክንያቱ እምብዛም አያመራምርም ፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተፋጠው እንዲደራጁ የተደረጉ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ አገራዊ አሰባሳቢ ማንነት ዙርያ ማቀራረቡ ለነገ የማይባል ነው ፡፡ ጥርጣሬው ሞልቶ ፈሷል ፡፡ የዶክተር አቢይን ጥረቶች እንደ ኦሮሞ አንግስ ጥረቶች አድርገው የሚመለከቱ   አሉ፡፡   አይፈረድባቸውም፡፡   ተራው   የኦሮሞ   እንደሆነ የሚያስመስሉ  ወገኖችም  አሉ  ፡፡  የኦሮሞው  ብሄረተኝነት  ተግዳሮቶች  ተደቅነውበታል  ፣  የአማራም  ፣ የትግሬም  እንዲሁ  ፡፡  በሁሉም  ተሳትፎ  ተረቆ  በሁሉም ይሁንታ መታጀብ ባለበት የሽግግር ሰነድ የፌዴራል ስርአቱ አወቃቀር ሊያወዛግብ ይችላል ፡፡ የአማራ ብሄረተኞች የፌዴራል አወቃቀር ስርአቱን ከሟቹ  ጠቅላይ  ሚንስትር  መለስ  ውርሶች  አንዱ  የሆነው  ፀረ  ነፍጠኛ (አማራ ?) ግንባር አድርገው እስከተመለከቱት ድረስ የሁሉ ስምምነት    ምልአተ  ስምምነት  (Consensus)  በፌዴራል  ክፍፍሉ  ላይ መገኘት  ሊያስቸግር  ይችላል  ነው  እያልኩ  ያለሁት፡፡  በሌላ  በኩል  የአማራ  ብሄረተኞች  ያልተማከለው የስልጣን ድልድል (decentralization) የፌዴራል ቅርጸ መንግስትን በመርህ ደረጃ  እስከተቀበሉት ድረስ የራሳችን የሚሉት እይታ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ የህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን ወደ ሁለተኛው ሽግግር ለማሸጋገር የፈለግሁበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ፡፡

በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የብሄራዊ መግባባት ውይይቱ ተጀምሯል እስከተባለ ድረስ  በውይይቱ መጠናቀቂያ  ላይ  የሚወጣው  ሰነድ  አቅጣጫ  አመልካች  ነው  የሚሆነው፡፡  አስማሚም  ነው  መሆን ያለበት፡፡ ለድርድሩ መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ ሰነዶችም ያሉ ይመስሉናል፡፡ የባለሙያዎቹ (conflicmanagment  resolution experts) የጥናት ድርሻንም በግምት መውሰድ ሊያስፈልግ ነው ፡፡ ከአምባገነን ስርአት  ወደ  ዲሞክራሲ  የተደረጉ  ጉዞዎችን  አስመልክቶ    በርካታ  ተሞክሮዎች  አሉ፡፡  ከተሳኩትም ከከሸፉትም፡፡  ከሩቅም  ከቅርብም፡፡   እኛ ከተጨናገፉትም ሆነ ከተሳኩት ዲሞክሪያሳዊ ሽግግሮች ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል ፡፡ መካድ የማንችለው አንድ እውነታ ፍንትው ብሎ ይታያል ፡፡ እሱም ኢትዮጵያ በለውጥ ዋዜማ ላይ መገኘቷ ለክፉም ለደግ የምትለውን ሃረግ ልጨምር መሰለኝ  !! ፡፡