በማህበረሳብችን ውስጥ በተለያዩ መድረኮች፤ ማህበራዊ ድህረ ገጾችን ጨምሮ የሚካሄዱ ውይይቶችን እና የሚሰጡ አስተያየቶችን ሳይ ከዚህ የሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች ወደ አእምሮዮ መጥተው ይመላለሳሉ። ብንወያይባቸው እና በማህበረሰ ባህሪ ጥናት ላይ ምርምር ያካሄዱ፣ ልምድና እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ሃሳስብ ቢሰጡበት እና ቢያስተምሩን ደስ ይለኛል።
ያሬድ ኃይለማርያም ለ7 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጋር አብሮ የሠራና የኖቬምበር 1 እማ 2ቱን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከሃገር ብዙ ምስጢሮችን ይዞ በመውጣት ለአውሮፓ ሕብረት ያቀረበ ነው።
1. በማህበረሰባችን ውስጥ እጅግ ስር የሰደደና ከፍተኛ የሆነ የተጠራጣሪነት ስሜት ነግሶ ይስተዋላል። ይህ ችግር ከሌለ ደስ ይለኛል፤ ጥያቄውንም ወደ እራሴ አዞረዋለሁ እርሶም እንደ እኔ ካስተዋሉት ግን ከምን መነጨ ብለው ያስባሉ? በጥርራሬ ላይ ብቻ የተመሰረቱ ማህበረሰባዊ ተግዳራቶች፣ ውይይቶችና ውሳኔዎችስ የእርስ በርስ ግንኙነቶቻችንን ከምን ደረጃ ላይ እያደረሱት ነው? እየጎዱን ወይስ እየጠቀሙን? ያልጠረጠረ ብቻ ሳይሆን የጠረጠረም እኩል የሚመነጠርበት ማህበረሰብ ከሆንን ችግሩ ከወዴት ይሆን? ጥርጣሬ በራሱ መጥፎ አይደለም። የሳይንሳዊ ምርምር መነሻው ጥርራሬ (doubtful) መሆን እና ከዛ የመነጩ ጥያቄዎችም ናቸው። የእኛ ጥርጣሬ ለምን ወደ ምርምርና የማጣራት ሥራ አያድግም? መጠርጠር ብቻውን የእውቀት ወይም የግንዛቤ መሰረት ሊሆን ይችላል ወይ? በጥርጣሬ ላይ ብቻ የተመሰረቱ ውሳኔዎች ለእውቀት ምን ያህል ቅርብ ናቸው? በጥርጣሬ ላይ ብቻ ተመስርተው በሚሰጡ አስተያየቶችም ሆነ ውሳኔዎች ምን አተረፍን? ምንስ እያጣን ነው?
2. ሁለተኛው ውይይት የሚሻ የሚመስለኝና ምናልባትም ከላይኛው ጥያቄ ጋር የተያያዘ የሚመስለኝ በማህበረሰባችን ውስጥ ጎልተው የሚስተዋሉትና በብዙ ውይይቶች ውስጥ የሚጸባረቁት የአሉታዊ የሆነ ባህሪዎች (negative behaviour) እና አዳዲስ ነገሮችን ስንሰማ ወይም አዳዲስ ለውጦችን ስናስብ አሉታዊ ነገሮች ብቻ አግዝፈን ማየት (negative expectations)። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ከአዎንታዊ ነገሮች ይልቅ አሉታዊ ነገሮች በሁሉም ግንኙነቶች ውስጥ ገነው የሚወጡት መን ሲኮን ነው? በኛ ማህበረሰብ ውስጥ እነዚህ ነገሮች ለምን በስፋት ይስተዋላሉ? ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳ በምን መልኩ ልንቀንሳቸው እንችላለን? እነዚህ አስተሳሰቦች በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በሌሎች ህይወታችን ውስጥ ያላቸው ተጽእኖ ምን ያህል ነው? በነገው ተስፋችን ላይ ያላቸውስ ተጽዕኖ ምን ሊሆን ይችላል?
3. ሦስተኛው አንገብጋቢ ጥያቄ ከውይይት ባህላቸን ጋር ተያይዞ ከላይ ከተነሱት ሁለት ችግሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ይመስለኛል። የውይይት ባህላችን ምን ያህል ዳብሯል? ምን ያህልስ ለዲሞክራሲያዊ እሴቴች ተገዢ ነው? ከምንጠቀማቸው ቃላቶች አንስቶ እስከ ሃሳብ አገላለጻችን ምን ያህል ለሌሎች ሰዎች ሃሳብን የመግለጽ መብትና ነጻነት ጥንቃቄና አክብሮት እናደርጋለን? ስድብ፣ ዝልፊያ፣ የግለሰቦችን ስብዕና እና ክብረ ነክ የሆኑ ቃላቶች እና አገላለጾች የውይይት አካል ሊሆኑ ይችላሉ ወይ? ሃሳብን በሃሳብ መሞገት እና ሃሳብን በስድብ እና ዝልፊያ ማጣጣል ልዩነቱ ገብቶናል ወይ? ብዙ ጊዜ አንድ ሰው በማናቸው ጉዳይ ላይ ሃሳብ ሲሰጥ በብዙ የውይይት መድረኮች እንደሚስተዋለው ከግማሽ በላይ የሚሆነው የውይይት ተሳታፊ ዋናውን ሃሳብ ወደ ጎን በመተው የስድብ ናዳ የሚያወርድ ከሆነ ውይይት ሊካሄድ ይችላል ወይ? ሃሳብ አፍላቂዎችስ ሃሳባቸውን በስድብ ለውሰው እና ሌሎችን አንቋሸው ማቅረባቸው ለውይይት ይጋብዛል ወይ? ሙክትና ክርክር የሚፈራ መህበረሰብ የውይይት ባህል ሊያዳብርስ ይችላል ወይ? ለምንድን ነው በበርካታ መድረኮች ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ ሃሳቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ሲከራከሩና ሲወያዩ ከማየት ይልቅ አንድ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች አንድን ሃሳብ ቃላት እየቀያየሩ ሲወቅጡ፣ ሲያነሱና ሲጥሉ የሚውሉት? ክርክር የሌለብት መድረክ አዲስ ሃሳብን ያፈልቃል ወይ? ወይስ በክርክርና በሙግት መረታትን እንፈራ ይሆን? ከሆነስ ለምን?
እስኪ በእነዚህ እርዕሶች ዙሪያ ያሻችውን በሉ። በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ለመወያየት እና ጉንጭ አልፋ ያልሆን ውይይት ለማካሄድ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በቴክኖሎጂ እገዛ መድረኮች ተፈጥረውልናል። ነገር ግን በአግባቡ እየተጠቀምንበት አልመሰለኝም። የውይይት መድረኩን እናደላድል እና ብዙ ተነጋግረን የማንጨርሳቸው አገራዊ ጉዳዮች ስላሉን ውይይቶቻችንን በስፋት እንቀጥላለን። ከስድብ በስተቀር ሁሉንም ሃሳቦች ለማስተናገድ፣ ለመስማትና ለመማር ዝግጁ ነኝ። በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ ያለዎትን ትንሽም ሃሳብ ቢሆን ጠብ ከማረግ አይቦዝኑ። እንዲህ እንዲህ እያልን የውይይት ምህዳሩን ጤናማ እና ለአገር የሚበጅ ልናደረገው እንችላለን። የአገዛዝዝ ሥርዓቱ ካጠበበብን የዲሞክራሲ ምህዳር የበለጠ በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ያልተገሩ አስተሳሰቦችና ባህሪዎች መድረኩን ጥርቅም አድርገው ይዘውታል። እስቲ የራሳችንን ምህዳር እኛው እናስፋው እና በሰፋው የውይይት ምህዳር ሥርዓቱን እንሞግት።

