አብይ ከወታደራዊ አዛዦች ጋር ያደረገውን ሙሉ ውይይት ባልሰማውም የተሰሩ ዘገባዎችን አይቻለሁ። አብይ ከቅርንጫፍ ቆረጣ ወደ ስር ነቀላ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያመለክት ነው። አልጋው እየረጋ በራስ መተማመኑም እየጨመረ ይመስላል። በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሞት ሽረት ትግል ይካሄዳል።
ቀልባሹ ሃይል የባቡሩን ጉዞ ለማደናቀፍ ያለ የሌለ ሃይሉን እያሰባሰበ ነው። ቀልባሾች ስር የሰደደ ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው በመሆኑ፣ የለውጡ አራማጆች ህዝባዊ ድጋፋቸውን ይዘው እስከቀጠሉ ድረስ፣ የማሸነፍ እድላቸው አነስተኛ ነው።
የህወሃት ጄኔራሎች የአካባቢያቸውን ልጆች “ ውድብክን አድን” ብለው በእነ አብይ ላይ ሊያስነሱባቸው ይችላሉ። ያም ቢሆን 70 በመቶ የሚሆነው ተራ ወታደር እንደ ድሮው የማይታዘዝ በመሆኑ በጉልበት የማሸነፍ እድላቸው አነስተኛ ነው።
ደም መፋሰስ ሊኖር ይችላል፤ የተጀመረውን እንቅስቃሴ እስከመግታት ደረጃ ይደርሳል ብዬ ግን አላስብም።
በዚህ መሃል ከራስ በላይ ለአገሩ ቅን የሚያስብ ዜጋ ሁሉ፣ ቀልባሹ ሃይል አሸናፊ ሆኖ እንዳይወጣ እንዲሁም ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ሃይሎች ለውጡ ህዝብ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንዲሄድ የተለያዩ ሚናዎችን መጫወት አለባቸው። ይህ እድል ካመለጠን፣ ትግል ባይቆምም፣ የትግሉ እድሜ ግን ሊራዘም እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። የትግሉ እድሜ ሲረዝም ደግሞ መከራና ስቃዩም አብሮ ይራዝማል። በእኔ እምነት የሚቀጥሉት 2 ወራት የትግል ትኩረት በህወሃት/በረከት በሚመራው ቀልባሽ ቡድን ላይ ቢያነጣጥር መልካም ይመስለኛል።