እንዴት ሰነበቱ መቸም ትልቁን የኢትዮጵያ መሪነት ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምእራብ እስከ ምስራቅ በህዝቡ ዘንድ ጥሩ የሚባል አይነት ተቀባይነት እያገኙ ነው በበኩሌ ስልጣን ያዳብር ብያለው::
ወደ ዋናው አሳቤ ስገባ በሚድያዎች አንድ ነገር ሲናገሩ ሰማው ሊቢያ ሂጄ በግፍ ታርደው የተጣሉ ወገኖቸን አፅም ይዤ እመጣለሁ ሲሉ እጅግ በጣም ደስ አለኝ ምክንያቱም እንዲህ አይነት ነገር በእድሜየ አይቸ ሰምቸ ስለማላውቅ በሀገሬ በኢትዮጵያ መሪ አንደበት እናም ሊቢያ ሄደው የወንድሞቻችንን አፅም ማምጣትዎት ትልቅ የሀገር አንድነትን የሚያጠናክር ሰራ ነው ግን ይህ ነገር ለአንድ ወቅት ብቻ እንደፋሽን ተወርቶ የሚቀር ነገር እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ ::
እናም ከልጅነቴ ጀምሮ አንድ በአእምሮየ የሚመላስሰ ጥያቄ ነበረኝ ዛሬ ላይ ይህን ነገር ስሰማ ሊቢያ የወንድሞቻችን አፅም ውቂያኖስ ላይ እንደተጣለ ነው የሰማነው ካለም እሰየው ነው ነገር ግን እንግሊዝ ሀገር በክብር የተቀመጠ የተቀበረበት ቦታ የሚታወቅ ሀገሩን እንደናፈቀ በባእድ ሀገር የቀረው የሃበሻው ንጉስ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ ነገርስ እንዴት ነው::
እርግጥኛ ነኝ ለናፈቃት ለእናት ሀገሩ አንደሚያበቁት እርግጠኛ ነኝ ስለ ልዐል አለማየሁ ትንሽ ልበል እና ላብቃ::
እንግሊዞች ከመቅድላው ጦርነት ፍፃሜ በሇላ ወደ ሃገራቸው ከወሰዷቸው ውድ ነገሮች መካከል አንዱ የዓጼ ቴዎድሮስ ወንድ ልጅ የነበረው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ነው። ልዑል አለማየሁ ወደ እንግሊዝ አገር ሲወሰድ ገና ስምንት አመት አልሞላውም ነበር፤ በመሆኑም ኣብዛኛውን የህይወት ዘመኑን ያሳለፈው ከእናት አገሩ ዉጪ ነበር ለማለት ይቻላል።
ልዑል አለማየሁ በእንግሊዝ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩ መምህራን ሁሉ መልካም ወዳጆች ሆነውለታል፡፡እርሱ ግን ከትምህርት ይልቅ ለስፖርት የተሻለ ፍቅር ነበረው፡፡እግር ኳስ እና ራግቢም ይጫወት ነበር፡፡መምህራኑ ወታደራዊ ሳይንስ እንዲያጠናም ግፊት አድርገዋል፡፡እናም እ.ኤ.አ. በመስከረም 1878 ወደ ሳንድረስት ወታደራዊ ትምህርት ቤት ካለ ፈተና እንዲገባ ተደረገ፡፡በወታደራዊ ትምህርት ቤት ደስተኛም ሆነ ውጤታማ አልነበረም፡፡እናም ለእረፍት እንደወጣ አልተመለሰም፡፡አለማየሁ ከኢትዮጵያ ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውት ነበር፡፡አንዱ ከእናቱ እናት ወይም ከአያቱ ሲሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ላኪ ማንነት አይታወቅም፡፡ሁለቱም ደብዳቤዎች የአለማየሁን መመለስ የሚናፍቁ ነበሩ፡፡
እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 14 1879 በጥቂት ቀናት ህመም ከዚህ አለም በሞት ሲለይ እድሜው 19 ብቻ ነበር፡፡በንግስቷ ፈቃድ በዊንድሶር የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ የቀብር ስነስርዓቱ ተፈፀመ፡፡የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሲከበር የልዑል አለማየሁን አፅም ወደ ኢትዮጵያ ለማስመጣት ጥረት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ስኬታማ አልሆነም፡፡፡
ልዑል አለማየሁ እ.ኤ. አቆጣጠር በ April 29, 1861 ዓ.ም. ተወልዶ እ.ኤ. አቆጣጠር በ November 14,1879 ዓ.ም. በእንግሊዝ አገር በሞት ተለይቷል። በመቃብር ሃውልቱም ላይ የሚከተለው ፅሁፍ ተፅፏል።(ፅሁፉ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተመለሰ ነው) … ” እንግዳ ሆኜ መጣሁ፤ ተቀበላችሁኝ”

