ለሀገር ግንባታ ይበጃል በማለት ከዚህ በታች በቅን ልቦና የሰነዘርኩትን አስተያየት እንድመለከተልኝና አስፈላጊዉን እርምጃ እንድወስዱ በትህትና እጠይቃለሁ።
መንደርደሪያ፤
በ20ኛዉና 21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሌሎች አገሮች ከጊዜ ወደጊዘ በእድገት ጎዳና ወደፊት ሲራመዱ፤ የተሻለ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሲገነቡና በሰላም ሲኖሩ እኛ ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ስንራመድ ሁለት እርምጃዎች ወደኋላ እንረግጣለን። ዉድ አገራችን ከራሷ ተርፋ ሌሎች አገራትን መመገብ የሚያስችል የተዋበና የበለፀገ የተፈጥሮ ኃብት ተችራለች፤ እጅግ በጣም ከፍተኛ ትምህርትና ልምድ ያሏቸዉ ብዙ ልጆች አፍርታለች፤ ህዝቦችዋም ታታሪዎችና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸዉ ናቸዉ፤ በዚህም ምክንያትና በእግዚአብሔር ቸርነት አንድነቷንና ነፃነቷን ጠብቃ እስከ አሁን ደርሳለች፤ ቸሩ እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋና ይግባዉ። ነገር ግን ዛሬ የሕዝባችን አላስፈላጊ መከራና ሰቆቃ እየከፋ መጣ። ህዝባችን በኑሮ ዉድነትና በርስ በርስ ግጭት እየተተራመሰ ይገኛል። አገሪቷ ራሷ እስከ ህልዉናዋ ድረስ በከባድ ፈተና ዉስጥ ሆና ሳያት አንጀቴ ክፉኛ ይቆስላል። እጅግ በጣም ያስገርመኛል፤ ያሳዝነኛል፤ ያበግነኛል። ይሄ መሆን ከቶዉንም የለበትም፤ ልናስቀረዉና ልናሻሽለዉ እንችላለን። የተሻለ ዲሞክራሲያዊ የፖሊቲካ አስተዳደር ለመገንባት፤ ሰላምና እርጋታን ለማስፈን፤ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ለመንከባከብ፤ የአካባቢያችንን የአየር ብክለት ለመቀነስ እና ዘለቄታ የሚኖረዉን የአገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በቂ ችሎታና እግዚአብሔር የቸረን ሰፋፊ የተፈጥሮ ሀብቶች አሉን።
የአገሪቷን ሉዓላዊነትና ህልዉና ለመጠበቅ ሆነ አላስፈላጊ የህዝብ ሰቆቃ ለማስወገድ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለዉ የኢሕአደግ አስተዳደር ከባድ ኃላፊነት ይጠበቅበታል። ሆኖም ግን በአገሪቷ ላይ የተሻለ የፖሊቲካ ለዉጥ ለማምጣት ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች፤ የሲቪክ ማህበራትና ግለሰቦችም ጭምር ብዙ ነገሮች እንደሚጠበቁ ለመርሳት አይደለም (ይሄንን በሌላ ጽሑፍ አብራራለሁ)። ላለፉት 40 ዓመታት ገደማ ለዶሞክራሲ፤ ለእኩልነትና ዕድገት ትንሽም ብትሆን የግሌን አስተዋጽኦ ከማድረግ ተቆጥቤ እንደማላዉቅ ታሪኬ ይመሰክራል፤ የዚህችም ተጨማሪ መልእክት መንፈስ የዚያዉ ረዥም ትግልና ፀሎት ተቀጥያ ነዉ። እነዚህን ማሳሰቢያዎች እንደሚከተለዉ ሳቀርብላችሁ በጥሞና ተመልክታችሁ የሚቻላችሁትን ሁሉ መሻሻል እንድታደርጉ በሕዝባችንና በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃችኋለሁ። ከስህተቶች መማርና ማሻሻል ፀጋ እንጂ ደካማነት አይደለም።
፩ኛ/ ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲ ስለመሸጋገር አስፈላጊነት፤ ተጋድሎና ግዴታ
ባለፉት ረዥም ዓመታት በኢትዮጵያና በተመሳሳይ የአፍሪቃ አገሮች ዉስጥ የአምባ ገነን ሥርዓቶች የሚሊዮኖችን ሕይወት እንዳጠፋ፤ ንብረቶች እንዳወደመ፤ ህዝብ እንዳፈናቀለና እንዳሰደደ፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳቀጨጨና አላስፈላጊ ርሃብና እርዛት እንደጋበዘ ማንም የማይስተዉ ሃቅ ነዉ። በደርግ ዘመን የገጠመንን ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ ታሪክ ለዘለዓለም ሲያስታዉሰዉ የሚኖር ሃቅ ነዉ። ከደርግ ዉድቀት በኋላ ሁሉም ዜጋ የተሻለ አስተዳደር ነበር የጠበቀዉ። ዛሬ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች በዲሞክራሲ ጎዳና መልካም መሻሻል ሲያሳዩ ኢትዮጵያ አሁንም በከባድ ጣጣ ዉስጥ ትገኛለች። ዲሞክራሲ ለምን ይጠላል? ለምንስ ይፈራል? በየአራት ወይም አምስት ዓመቱ በሚደረገዉ ምርጫ መልካም ራዕይ ይዞ የሚቀርብ ይመረጣል፤ ሌላዉ ደግሞ ተቃዋሚ ሆኖ ይሠራል። እንደዚህ እያሉ እየተፈራረቁ አገሪቷን ቢመሩ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፤ ሰላምና አገራዊ እርጋታ ይሰፍናል፤ ኢኮኖሚ ያድጋል፤ ህዝብ በሰላም ይኖራል። ህያዉ ሆኖ የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነዉ። የሰዉ ሕይወት አጭር ናት፤ ለሁሉም ጊዜ እንዳለዉ ባንዘነጋ መልካም ነዉ። እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ልባችንን ንፁሕ አድርገን እንፀልይ፤ ንስሐ እንግባ፤ አገራችንን፤ ልጆቻችንና ወገኖቻንን ለማዳን እንሞክር።
ዲሞክራሲ፤ አገራዊ ህብረትና ሰላም ሳይኖሩ ዘለቄታ የሚኖረዉ እርጋታ፤ ዕድገትና የህዝብ ደህንነት ሊረጋገጡ አይችሉምና።
፪ኛ/ የመሬት ባለቤትነትና፡አጠቃቀም ችግሮች
በአፍሪቃ፤ በእሲያ፤ በፓሲፊክ፤ ወዘተ ዐለማት ላይ ከነበሩት ችግሮች ዋነኛዉ የመሬት ባለቤትነትና አጠቃቀም ነዉ። ነዋሪዎች የሆኑ ባለቤቶች ሲነጠቁ፤ ሲፈናቀሉ፤ ሲራቡና ሲያልቁ የዉጪ ባለጉልበቶችና ወራሪዎች ይፈነድቁባቸዋል። ይሄ ችግር የደረሰባቸዉ ብዙ አገሮች መሻሻል ሲያሳዩ በኢትዮጵያ አገራችን ግን ዛሬ ከባድ ችግሮች እንዳሉ ይሰማል። በተጨማሪም በአገራችንም ካሁን በፊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ተብለዉ የተቆጠሩት ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲታረሱ የቆዩ ከፊል የሰሜን ኢትዮጰያ ምድሮች ነበሩ። ዛሬ ግን በተለይ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ደኖች ተጨፈጨፉ፤ አፈር እየታጠበ ሄደ፤ መሬት ካለዕረፍት በተደጋጋሚ ታረሰ። ሃይቆች እየደረቁ ናቸዉ፤ እየተበከሉም። አፈሮቻችን ታጥበዉ ሄዱ፤ መሬቶቻችን ለምነታቸዉንና ምርታማነታቸዉን እያጡ ናቸዉ። በነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች የተቀሩትም የአገሪቷ መሬቶች ጠፍ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ላይ የሰሀራ ምድረበዳ በረሃዉን ወደደቡብ እየገፋ ይገኛል። በተጨማሪም የአካባቢዉ አየር ብክለት ዓለምን በሙሉ እያሰጋ ይገኛል። የነዚህን ተጽፅኖዎች ለመቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች አሉ። በኔ አስተባባሪነት በሚመራዉ አግሮፎሬፕ በሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ትንሽ ድርጅት አማካኝነትና በኢትዮጵያ ማእከላዊ፤ የክልልና የወረዳ አስተዳደሮችና የገጠር ገበሬዎች ማህበራት ትብብር በአርሲ ዞን የሠራናቸዉን ተዓምራት ከዘገባዎችና ከዌብ ሳይታችን ላይ ማየት ይቻላል (www.agroforep.org.uk):: ጠፍ መሬቶችን መልሶ ማልማት እንደሚቻል፤ የገጠር ገበሬዎችን ማደራጀት፤ ሥልጠና መስጠትና ድጎማ አድርጎ ምርታማነታቸዉን እንዲጨምሩ ማብቃት፤ የገጠር ሴቶችን አደራጅቶ፤ ሥልጠናና የገንዘብ ድጎማ በማድረግ (ለምሣሌ Credit and Saving Revolving Fund Scheme) ዘለቄታ የሚኖረዉን ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚቻል፤ ወዘተ አስመስክረናል፡፡ በተለመደዉ ግብርና ጎን አትክልትና ፍራፍሬ በመትከል፤ የንብ እና የዶሮ እርባታ በማስፋፋት፤ ከብት በማደለበ፤ ወዘተ የገቢ ምንጮቻቸዉን በማብዛት ርሃብ እንዳያጠቃቸዉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ህይወት እንዲኖሩና ልጆቻቸዉን በጤና፤ በደስታና በትምህርት ዓለም እንዲያሳድጉ ማብቃት ይቻላል፡፡ ከትምህርትና ከዓለምአቀፍ የሥራ ልምዶች የገነባናቸዉን ተመክሮዎች ከአገራችን ባህል ጋር በማጣጣም ብዙ ተዓምር በመሥራት ርሃብንና መከራን የማስወገድ ችሎታ አለን፤ በማናቃቸዉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንችላለን፤ ሰላሙን፤ እርጋታዉንና መንግሥታዊ ትብብር ካገኘን።
በአገር ዉስጥ ያሉት ወገኖች የሚቻላቸዉን እያደረጉ ይገኛሉ፤ ነገር ግን ከፍተኛ ዕዉቀትና ረጅም የሥራ ልምዱ ያሏቸዉ ብዙ ወገኖች በስደት ዓለም ያሉ ስለሆኑ አገሪቷን ለመታደግ እንዲበቁ ሁኔታዎችን በከፍተኛዉ ማመቻቸት ይጠበቃል፤ ይሄ ጥያቄ ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጠዉ መሆን አለበት፡፡ ሌሎች አገራትና ዓለማት አክብረዉን፤ እጆቻችንን ስመዉ ሸልመዉ በሙያችን ይጠቀማሉ፤ እግዚአብሔር ይስጣቸዉ፡፡ ሆኖም ግን ዉድ አገራችን እየተጎዳች ባእዳን አገሮችን እየዞርን ብናቀና ሙሉ የመንፈስ እርጋታ ልናገኝ አንችልም፡፡ ሁሉም ባገር ነዉና፡፡
፫ኛ/ ችጋር፤ ርሃብ፤ በሺታና ቸነፈር ለማስወገድ ገና ብዙ ይቀረናል
ብዙ የዓለም ህዝብ ችጋር፤ በሺታና ቸነፈር ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ በመቆየቱ ምክንያት መልካም ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛል። ቸሩ አምላካችን እጅግ ምስጋና ይግባዉና ያቺ የተቀደሰች አገራችን እጅግ በጣም ሃብታም ሆና የተፈጠረች ነበረች።በምድራችን ስፋት፤ በአፈሩ ለምነት፤ በወንዞቻችንና በሃይቆቻችን ብዛትና በተሟላ የተፈጥሮ ሀብት የተገጎነጸፈችና እጅግ የላቀች ቅድስት አገር ናት። እንኳን ለህዝባችንና ለሌሎችም የምትተርፍ አገር ነበረች። በዚህ ላይ በየዓመቱ ብዙ የዉጪ እርዳት እንደሚገባ ይነገራል፡፡
ሆኖም ግን መድረስ ከሚገባት የእድገት ደረጃ ልትደርስ አልቻለችም፡፡ ርሃብና ችጋር ቶሎ ቶሎ ይጎበኟታል፤ በቶሎም አይለቋትም፤ ሚሊዮኖች በየዓመቱ ይጠቃሉ፤ ሺህዎች ይሰደዳሉ፤ ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ሰላምና እርጋታ ኖሮ የተፈጥሮ ኃብታችንን ተንከባክበን ለመጠቀም ብንችል ምንኛ የዕድገት ደረጃ በደረስን ነበር፡፡
፬ኛ/ ለወጣቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት ስለመስጠትና ስደትን ስለመቀነስ ዘመቻ አስፈላጊነት
ዛሬ በኢትዮጵያ ብዙ አያሌ ዩኒቬርሲቲዎች ተከፍተዋል፤ አበረታች እርምጃ ነዉ፡፡ ሆኖም ግን ዛሬም ወጣቱ በተለያዩ ምክንያቶች አገሩን ጥሉ ለመሰደድ ይገደዳል፡፡ በስደቱ ጉዞ ላይ ስንቶች ለጋ ወጣቶች በየበረሃዉና ባህሩ ላይ እንደቀሩ ቤት ይቁጠራቸዉ። ከተሻገሩም በኋላ በዐረብ አገሮች የሚገጥሟቸዉን አሰቃቂ ችግሮችና የባርነት ኑሮ ሁላችንም የሰማናቸዉ ናቸዉ፡፡ በዐለም ላይ እጅግ ተንቀናል፡፡ ወጣቶች በዉድ አገራቸዉ ተምረዉ አድገዉ ተመንድገዉ በሰላም ካልተዘጋጁ የሚቀጥለዉን ኃላፊነት ማን ሊረከዉ ይችላል? የአገራችንን ድንበርስ ማን ሊከላከልልን? ትልቅ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡፡ እነዚህን ወጣቶች ማስተማር፤ የሙያ ስልጠና መስጠት፤ ማደራጀትና ሥራ የማስያዝ ግዴታም ሆነ ችሎታ አለን፤ ብዙም ሳይመሽብን በጥልቁ አስበንበት ለወጣቱ ትዉልድ የሚገባዉን ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፡፡
፭ኛ/ የፈተናዎቹን ክብደት ለማጠቃለል ለመንግሥት ያለኝ ቅን መልእክት
እንኳንስ አገራዊ ሁከት ተጨምሮበትና በሰላምም አየር እያሉ እላይ ባጭሩ የተቀመጡትን ፈተናዎች መወጣት ቀላል ሥራ አይሆንም። የዉጪ መንግሥታት የየራሳቸዉን ጥቅም ነዉ የሚያስቀድሙት። አንዳንዶቹ መከፋፈል የመሳሰሉትን ቀዳዳ መንገዶች ይጠብቁና ሊያጠቁን፤ ሊቆጣጠሩን ይፈልጋሉ። አንዳንዶቹም አገራትን ከፋፍለዉ በመግዛት ነዉ የሚነግዱት። ከሁላችንም ዜጎች ብዙ የተቀናጀ ጥረት ይጠበቅብናል። ሰላምና እርጋታ ከተገኘ ግን ለብዙዎቹ ፈተናዎቻችን መፍትሔ መንገዶች ይኖራሉ። የአገሪቷ መዉደቅ ለማንም አይበጅምና ሁሉም ዜጋ ሊያስብበት ይገባል፤ ከመንግሥት እስከተቃዋሚ፤ ከከተማ እስከገጠር፤ ፊደል ከቆጠረዉ እስካልቆጠረዉ ድረስ። እግዚአብሔር ይጨመርበት።
የአገራችን ታሪክ እታች ባጭሩ እንደተመለከተዉ እራሱን ይደጋግማል፤ አሁን ደግሞ በአሳሳቢ ደረጃ ዉስጥ እንገኛለን።
በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ወቅት ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ወጣ፤ ብዙ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች፤ ክልኒኮች፤ ሆስፒታሎች፤ ወዘተ ተገነቡ። ካገርም ዉጪ አፍሪቃ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ታላቅ ዕርዳታ ተለገሰ። ሰሜንና ደቡብ ሱዳኖች እንዲስማሙ ታላቅ አስተዋጽኦ አደረጉ። ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ቁልፍ ሚና ተጫወቱ። ከዐለም መንግሥታት ምሥረታ በፊት በነበረዉ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ዉስጥም አገራችንን አባል በማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን አገዛዙ የባላባታዊ ሥርዓት ስለነበረ በተለይ ጪሰኞች ክፉኛ ተጨቆኑ። ድህነትና ርሃብም ተደጋገሙ። የመሬት ይዞታንና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን መመለስ አቃታቸዉ። ያገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈለገዉን ያህል ሊንቀሳቀስ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የታሪክ ሂደት ሆነና የባላባታዊ ሥርዓት አክትሞ መሬት ላራሹ እንዲሆንና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በተደረገዉ ረጅም ትግል የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ሊወድቅ ቻለ።
በወቅቱ የተጠናከረ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ የሕዝቡ ትግልና ድል በወታደሮች ተቀማ። ነገር ግን ምንም እንኳን የፖሊቲካ አስተዳደር ብቃት ሳይኖረዉ በእጁ ባለዉ ጠብ መንጃ አማካኝነት ሥልጣን ላይ ቢቆናጠጥም በጦር ኢኮኖሚ ዉስጥ እንኳን ሆኖ ብዙ መልካም ለዉጦች አሳይቶ ነበር፤ የመሬት አዋጅ ሙከራ፤ መሠረተ ትምህርት ማስፋፋት፤ የመንገዶች፤ ድልድዮች፤ ክሊኒኮች፤ ሁስፒታሎችና ኮሌጆች ግንባታዎች። በዚህም ላይ እጅግ በጣም ብዙ ወጣቶች ለከፍተኛ ትምህርት ወደዉጪ ተልከዋል። ነገር ግን ዲሞክራሲ ታፈነ። ሕዝብ ለሚያሰማዉ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሹ ርሸና ሆነ። በዓለም ታይተዉ የማይታወቁ ፋሺስታዊ እርምጃዎች ተወሰዱ፤ ማሰር፤ መደብደብ፤ ማሰቃየት፤ መረሸን፤ ወዘተ። አብዮት ልጇን ትበላለች እየተባለ ፤ የፊዬል ወጠጠ ተዘፈነብን። ከዚያም በኋላ ደርግ ልቡ አበጠበት፤ በሥልጣን ሰከረ። ብዙ ጄነራሎችንም ጭምር እንደጠላት ቆጥሮ በላቸዉ። ከዚያ በኋላ አዉራ ያጣዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሃሞቱ ፈሰሰ፤ ተስፋ ቆርጦ አፈገፈገ። በሂደቱም ደርግ በገዛ ኃጢአቱና በሕዝባችን የረጅም ጊዜ ቆራጥ ትግል ኃይሉ ተደመሰሰ።
ለመሬት ላራሹ፤ ለብሄሮች እኩልነትና ለዲሞክራሲ የወቅቱ ትዉልድ የከፈለዉን ከፍተኛ መስዋእትነት ታሪክ ሲያስታዉሰዉ ይኖራል። ከደርግ የባሰ መንግሥት አይመጣም በማለት ብዙ ዜጋ በቀና ፊት ተቀብሏችሁ ነበር። ሥልጣን ላይ ከወጣችሁበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ግንባታዎች ተዘርግተዋል፤ ትልልቅ ፎቆችና ሰፋፊ መንገዶች ተሠርተዋል፤ በየክልሉ ብዙ ዩኒቬርሲቲዎች ተገንብተዋል። በጎኑ ግን ዕጣ ፈንታችን ሆነና እታች ባጭሩ ለማመልከት እንደሞከርኩት የተጠበቀዉ ያህል አዝላቂ ለዉጥ ሊመጣ አልቻለም።
(ሀ) አንዳንድ ጊዜ የአገሪቷ ሕልዉና ራሱ ያሳስበናል
እኔ በመሠረቱ ዲሞከራሲያዊ የሆነ ፈዴራላዊ ሥርዓት ጠቃሚ ነዉ ብዬ አምናለሁ። በአብዛኛዉ ግን በተግባር የታየዉ ጎሣ ከጎሣ፤ ወገን ከወገን ጋር ሲጋጭና ሲፈናቀል ነዉ። በተለይ በአማራ፤ በኦሮሞና በሶማሌ ህዝቦች አካባቢ ብዙ ግጭቶች ሲፈፀሙ ይታያሉ፤ ይሰማሉ። ወገን ተወገን ጋር ተታርቆ፤ ተፈቃቅሮና ተባብሮ እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል። ማንም ዜጋ በገዛ አገሩ በነፃ ተንቀሳቅሶ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ መብቱ እንዲጠበቅለት ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል።
(ለ) ብዙ ሕዝብ መሬቱን በተመለከተ ብዙ ችግሮች እንደገጠሙት ይሰማል
እላይ በተራ ቁጥር 2 ስር እንደተጠቀሰዉ ዛሬ በአገራችን የመሬት አጠቃቀም ከዋና ችግሮች አንዱ ነዉ። በብዙ ታዳጊ አገሮች እንዳሁት የዉጪዉ ስምምነት በአብዛኛዉ የሚፈፀመዉ ከአካባቢዉ የመሬቱ ባለቤቶች/ተጠቃሚዎች ፍላጎትና ይሁንታ ዉጪ በመፈጠራቸዉ ምክንያት ነዉ። የአገሬዉ ነዋሪና ተጠቃሚ ሕዝብ ካለፍላጎቱ ከመሬቱ ሲፈናቀል ብዙ መዘዞች ይፈጠራሉ፤ በጉልበት የተፈናቀለዉ ወገን ሰብዓዊ መብቱን ይነጠቃል። ርሃብ ላይ ይወድቃል። ገበሬ መሬቱን ከተነጠቀ ሕይወቱም ታሪኩም ጠፋ ማለት ነዉ። በዚህም ላይ ጥሩ ስምምነትና ከፍተኛ ቁጥጥር ካልተደረገ ብዙ የዉጪ ኢንቬስተሮች የሚሮጡት ለትርፋቸዉ እንጂ ለአካባቢዉ ሕዝብ ሆነ ለአየሩ ጥራት አይደለም፤ ደኑ ሊጨፈጨፍ፤ አየሩና ወንዙ ሊበከል ይችላል። ይህ ብክለት አካባቢዉን ብቻ ሳይሆን ወንዙንና አየሩን ተከትሎ በሩቁ የሚኖሩትንም አያሌ ዜጎች፤ ከብቶችና አራዊት ጭምር ሊያጠቃና ሊያጠፋ ይችላል። ስለዚህ መሬቱን የተነጠቀዉ ዜጋ መብቱን ለማስጠበቅ ሲል ትግል ዉስጥ እንዲገባ ሲገደድ ሰላም፤ እርጋታና ዘለቄታ የሚኖረዉ ዕድገት ሊናጋ አይችልም ወይ? ስለዚህ ማንኛዉም የዉጪ ስምምነት የአካባቢዉን ህዝብ ይሁንታና ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል። የጥቅሙም ተካፋይ መሆን ይኖርበታል፤ ለምሣሌ፤ በትምህርት ቤቶችና ክሊኒኮች ግንባታ፤ ንፁህ ዉሃ አቅርቦት፤ መንገዶች ማሻሻል፤ የሥራ ዕድል መክፈት፤ ወዘተ።
በዚህም ላይ፤ እላይ ባጭሩ እንደተገለፀዉ፤ ለአያሌ ዘመናት በተደጋጋሚ ሲታረሱ የቆዩ መሬቶቻችን ጠፍ እየሆኑ መጥተዋል። የህዝብ ቁጥር መጨመር፤ የዛፎች መጨፍጨፍና የአየር ብክለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ጥሎናል። ጠፍ መሬቶቻችንን መጠገን፤ አፈርን መቆጠብና መከላከል፤ የዛፍ ተከላን ማብዛት፤ በአመቺና አስፈላጊ ቦታዎች ላይ ግብርናንና ደንን ማጣመር (ለምሣሌ AGROFORESTRY SYSTEMS አጠቃቀም)፤ ወዘተ። እንደዚሁም ሃይቆችንና የዝናብ ምንጮችን መከላከል (ለምሣሌ PROTECTION OF CATCHMENT AREAS) እና የመስኖ አጠቃቀምን ማብዛት እጅግ በጣም አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸዉ። ከትምህርትና ከልምድ ያገኘናቸዉን ፀጋዎች በተገቢዉ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል። በማናቃቸዉ ችግሮች ላይ ደግሞ ጥናቶችና ሣይንሳዊ ምርምሮች ማድረግ ይኖርብናል። በተለይ ይሄኛዉ ክፍል የኔን ሙያና ልምድ ስለሚመለከት ብዙ ማለት እችላለሁ።
(ሐ) ፍትሃዊ ያልሆነ የአገሪቷ ሀብት ክፍፍል
የኑሮ ዉድነት እጅግ አሰቃቂ ደረጃ እንደደረሰ ይሰማል። ወጣቱ ስደትን መርጦ እንዳይንገላታና እንዳይጎዳ ለማድረግ የሚያስችል ተገቢ ጥናት ሲደረግ አይታይም። እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የወጣቱ አእምሮ እንዳይነካ ተገቢዉን እንክብካቤና ትምህርት መስጠት ይጠይቃል። ዝሙት አዳሪነት እንዳይጨምር መጠንቀቅ ይገባል። ከመፍትሄ ሀሳቦች መሃል እኩልነትን ለማምጣት መሞከር፤ የአገር ንብረት የህዝብ መጠቀሚያ መሆኑን ማረጋገጥና ዘለቄታ የሚኖረዉ የኢኮኖሚ ዕድገት መዘርጋት ነዉ ብዬ አምናለሁ።
(መ) ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በሰለጠነ መንገድ አለመነጋገር
በዲሞክራሲ በዳበሩ አገራት ዉስጥ የተለያየ አመለካከት ያሏቸዉ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ይቻቻላሉ፤ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ይነጋገራሉ፤ ለመስማማትም ላለመስማማትም ተስማምተዉ ተጨባብጠዉ በሰላም ይለያያሉ። እጅግ በጣም ያስቀኑኛል። ሁሉም ወገን ከነዚህ ወርቃማ ሁኔታዎች መማር ይኖርበታል። ዲሞክራሲ ሳያብብና ሰላምና እርጋታ ሳይኖር ዘለቄታ ያለዉ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። መጨረሻዉ ተያይዞ መጥፋት እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። ወርቃማ አማራጮች እያሉን እንደዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ዉስጥ መዘፈቅ አይኖርብንም።
(ሠ) የተማረዉ ወገን በደንብ ሲታቀፍ አይታይም
ላለፉት 40 ዓመታት ገደማ ከገዢ ቡድኖች ጋር ያልወገነዉ አብዛኛዉ የተማረ ክፍል ተገለለ፤ አገሪቷ እጅግ ለፍታ ያስተማረቻቸዉ ልጆችዋ ካላገለገሏት ማን ሊያሳድጋት ይችላል? ባገሩ መኖርና መሥራት ያልቻለዉ ንፁሕ ዜጋ ተበትኖ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና መዕራባዉያን አገሮችን ሲያገለግልና ሲያቀና ይገኛሉ። የአገሩ ሠርዶ ግን ባገሩ በሬ ቢሆን መልካም ነበር።
(ረ) ለወጣቶች ችግሮች የሚገባዉን ትኩረት አለመስጠት
እላይ እንደተገለፀዉ፤ ካለምንም የፖሊቲካ አድልዎ ማንኛዉም የአገሪቷ ወጣት በነፃ የመማር፤ የመመረቅና የመሥራት ዕድል ሊሰጠዉ ይገባል። በርሃብና በችጋር የተጠበሰዉ ዜጋ ከባርነት ለማይሻል ሁኔታ እንዳይዳረግ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ መስጠት ይጠበቃል። በዚህም ላይ በተለያዩ የጎረቤት አገሮች ሲቀጠቀጡ፤ ሲደፈሩ፤ ሲሰቃዩና ሲገደሉ እጎናቸዉ መቆም እጅግ በጣም ያስፈልጋል።
፮ኛ/ መደምደሚያ
ዉድ አገራችን ያለችበትን ጣጣና ወዴት እያመራች እንዳለች ሁሉም ዜጋ እኩል የሚረዳና የሚጨነቅ አይመስልም። የዉድ አገራችን መጎዳት፤ መከፋፈልና አያድርገዉ እንጂ መከፋፈል ለማን ይበጃል? ባባቶቻችንና በአያቶቻችን ደምና አጥንት ተገንብታ ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከብራ ኖራ በዓለም አቀፍም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋ እስካሁን የደረሰችዉን ያቺን ቅድስት አገር ዉድቀት ቁጭ ብለን ማየት በምድርም በሰማይ ሊያስጠይቅ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። አስተዉሎ ለተመለከተ ዜጋ ሁሉ እነዚህን ጥያቄዎች መረዳት ከባድ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
የአገሩን ሠርዶ በአገሩ በሬ የሚል ጥሩ አነጋገር አለ (ችግሮቻችንን እኛዉ በእኛዉ በህብረት መፍታት ይኖርብናል ማለት ነዉ)፡፡ አባቶቻችንና አያቶቻችን የነበራቸዉን ዐቅም ሁሉ ተጠቅመዉ አገሪቷን ጠብቀዉ ለኛ አስረክበዋል።። እኛ ግን ያን ሁሉ ለፍተን የተማርን፤ የታገልንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ አዲስ ቴክኖሎጂ በተስፋፋበት ዘመን ዉድ አገራችንን ማንሳትና ማሳደግ እንጂ ጉዳቷን ማየት ከቶ አይገባንም፡፡ በዓለም እንደአሸዋ የተበተነዉ ወገን ተመልሶ በኩራት እየኖረ ሕዝባችንን እንዲያገለግል ጥርጊያ መንገድ ማበጀት ይኖርብናል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት ለወገኖቻችን ማብቃትና ርሃብን፤ ጥማትን፤ እርዛትን፤ ስደትንና እንግልትን ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል። ቁርጥ ያለዉ የዲሞክራሲና ራስን የመቻል አማራጭ ይሄን ይመስላል፤ በኔ ቅን እይታ።
አሁንም ካለፉት ስህተቶችና ጥፋቶች መማር አንችልም ወይ?
ዛሬ በዉዲቷ አገራችን ላይ ጥቁር ደመና የተጋረጠባት ይመስላል። ቁጭ ብለን ሁኔታዎች እስከሚባባሱ ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም።አሁን የደረስንበት ዉድቀት ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ባለሥልጣናትንም እኩል ማሳሰብ ይኖርበታል። ሥልጣን ይመጣል፤ ይሄዳል። ገንዘብ አብሮ ጉድጓድ አይገገባም። አገር ግን ለእኛ ብቻ ሳትሆን ለልጆቻችንና ለሚቀጥሉትም ትዉልዶች መትረፍ ይኖርባታል። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ደማቸዉን አፍስሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩዋት ቅድስት አገር በሁላችንም ትብብር ህልዉናዋ ተረጋግጦ አብባ ለዘለዓለም እንድትኖር ለማድረግ ኃላፊነቱ የሁላችንም መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።
ምርጫዉ ለሁላችንም ክፍት ነዉ፤
- የተጣላዉ ወገን እርስ በርሱ እንዲተራረቅ ማመቻቸቱ የተባረከና የተቀደሰ ተግባር ነዉ። ከኒልሰን ‘ማዲባ’ ማንዴላ ጥረቶች ትንሽ ብንማር መልካም ነዉ። እርሳቸዉ ለአገራቸዉ ነፃነትና ሰላም ሲሉ ከአፓርታይድ ጠላቶቻቸዉ ጋር እንኳን ታርቀዋል። አሁን ያለፈዉ አለፈ። ይቅር መባባል አለብን። ለወደፊቱ መልካም ራዕይ ፈጥረን አገራችንን ከጥፋት ማዳን አለብን።
- መቻቻልና ንጹሕ ዲሞክራሲን በህብረት መገንባት ይጠበቅብናል።
- በዓለም እንደአሸዋ የተበተነዉ ወገን ተመልሶ በኩራት እየኖረ ሕዝባችንን እንዲያገለግል ጥርጊያ መንገድ ማበጀት ያስፈልጋል።
- እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት ለወገኖቻችን ማብቃትና ርሃብን፤ ጥማትን፤ እርዛትን፤ ስደትንና እንግልትን ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል።
- የኔ ትምህርትና የሥራ ልምድ በተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም፤ መንከባከብና ዘለቄታ በሚኖረዉ እድገት ላይ ነዉ። የሚቻለኝን ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ እስከ ህልፈተ ሕይወቴም ድረስ ይሄንን የግሌን አስተዋጽኦ ከማድረግ እንደማልቆጠብ ቃል እገባለሁ። ከሁሉም ቅን ዜጋ የምጠብቀዉም ይሄንኑ ነዉ።
ቸሩ አምላካችን ቅን ልቦና ይስጠን፤ ይታረቀን፤ ወገኖቻችንና ውድ አገራችንን ይጠብቅልን፤ አሜን
ከአክብሮት ሰላምታጋር።
በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)
