በዚህ በኩል “ሕዝብ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ መውደቁን እየሰማን ባለንበት ተመሣሳይ ሰዓት የጎንደር ሕዝብ ለአቶ መላኩ ፋንታ የ2 ሚሊዮን ብር መኪና ገዛ የሚባል ነገር እንሰማለን። ገንዘቡ ያለው አካል የቢሊዮን ብር መኪና ገዝቶ የመሸለም መበቱ የተጠበቀ ቢሆንም ፣ ይህ በሕዝብ ስም የተበረከተ ሽልማት ያስገረመን፣ ለተፈናቀለው ሕዝብ በግሎባል አሊያንስ አማካይነት ከ800 ሺህ ብር በላይ ያበረከቱት እነ ታማኝ በዬነ አሁንም ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያፈላልጉ ጥያቄ እየቀረበላቸው እንደሆነ እየሰማን ባለበት ወቅት የተሰጠ መሆኑ ነው።

በወዲህ በኩል ደግሞ ጉምቱው ፖለቲከኛ ኦቦ በቀለ ገርባ “..ከኛ ወገን ወደ ስልጣን መምጣቱን ጠልተን አይደለም…ለኛ ግን ጠብ ያለልን ነገር የለም” ማለታቸውን እያዬኹ ነው። (ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ጥንቅቅ ያለ ትርጉም ነው የወሰድኩት)

መለስ ዜናዊ የአንድ አካባቢ እንጂ የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆኑ ባለፉበት ሀገር ዛሬም እነ ኦቦ በቀለና አንዳንድ ወገኖች እነ ዶክተር አብይን ” የኛ ወገን” ቢሏቸው አይገርመንም። የዚህ አመለካከት ምንጭ ምን እንደሆነ ይገባናል። የነገውን ባላውቅም እስካሁኗ ሰዓት እኔ ካለኝ እምነት ተነስቼ ስናገር ዶክተር አብይ የአንድ ወገን ወይም ኦሮሞ ብቻ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁሉም ወገን ናቸው። ሰውን በዘር ከሚፈርጅ ፓርቲ የወጡ የሰው ልጅ ናቸው።ስለዚህ “ዘሬ ኢትዮጵያዊ ነው” ያለን ሰው ፣”የኛ ወገን” ብሎ በአንድ ዘር ውስጥ ማስገባቱ በነመለስ ጊዜ ያለፈበት ፖለቲካ መሆኑን መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ለእኔ ፣እንኳን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር አብይ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳር የሆኑት ለማ መገርሳ የኦሮሞዎች ብቻ አይደሉም- እደግመዋለሁ-እስካሁኗ ሰዓት ባለኝ፡እምነት እርሳቸውም የሁላችንም ናቸው።(የነገውን እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው)

ሌላው፦ “እኛ ታግለን.. ጠብ ያለልን ነገር የለም” የሚለው አባባል ነው።

የህወኃት ካድሬዎች አንድ የመነቸከ አባባል ነበራቸው። የመታገል ዋነኛው ግን ለመደላደል የሆነ ይመስል፣እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ” ሥልጣን ልቀቁ ” ሲባሉ፣ “እኛ በታገልነው ማን ሊሾም?” ሲሉ ቆይተዋል። የታገሉት፣ ሁሉም በእኩልነት ለሚተዳደርበት ፍትሀዊ ስር ዓት ሳይሆን ወንበር ላይ ተቀምጠው ለመዝረፍ እንደሆነ በሚያመላክት መልኩ በግልጽ ሲከራከሩ ከርመዋል። ዝርፊያን እንደ ትግል ደመወዝ በመቁጠርም ሀገሪቷን ጥገት ላም አድርገዋታል። ይህ ትግልን በደመወዝና በጥቅም የማስላት አመለካከት ከእንግዲህ ከሥሩ ሊነቀል ይገባል። ቄሮም ሆነ ፋኖ፣ ዘርማም ሆነ ግንቦት 7… ሌሎችም ሁሉ የታገሉት ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲያዊት ሀገር ግንባታ እንጂ መስዋዕትነታቸውን በቁጥርና በመጠን እያሰሉ ጥቅም ሊያጋብሱ አይደለም!!

“ይህን ያህል ሺህ ወጣት የገበርንበትን አንሰጣችሁም! እኛ በታገልነው… ምናምን” የሚለው የህወኃት ዐይነት የሻገተ አመለካከት እስከመጨረሻው ሊቀበር ይገባል።