ግንቦት 27ቀን 2010ዓም(04-06-2018)
ስለ ኢትዮጵያ አገራዊ አመሠራረት ሁለት ተጻራሪ ሃይሎች፣አገር ወዳዶችና ጎሰኞች የሚሰጡት አስተያዬት እንደ አቋማቸው የተለያዬ ነው።
በኢትዮጵያዊ አገር ወዳዶች በኩል ታሪክን መነሻ በማድረግ የሚቀርበው አመለካከት፣- ኢትዮጵያ የሰው ዘር መነሻ፣ ከብዙ አገራት በፊት ስርዓት ገንብታ የኖረች፣ የብዙ ዘመናት ታሪክ ያላት፣ከቀይ ባሕር ማዶና መለስ የተንሰራፋ ሰፊ ድንበር የነበራት፣ለሌሎች አገራት ስልጣኔና ምስረታ ምሳሌና ምልክት የሆነች አገር ናት።እንደማንኛውም አገር የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ፣የተለያዩ እምነቶች ተከታይ፣የብዙ ባህል ባለቤት የሆነ ህዝብ የኖረባትና የሚኖርባት አገር ናት።አገራዊ ግንባታዋም ሌሎች አገሮች ከተከተሉት አይለይም።ምንም እንኳን በሂደቱ ወቅት በአንድነትና በጸረ አንድነት ሃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱ ባይካድም፣ከአንዳንዶቹ ፍጹም አረመኔያዊ ከሆነ አገራዊ አመሰራረት በተሻለ መልኩ፣በመከባበርና በመግባባት ብሎም በመፈቃቀድ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆምና አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም ዜጋ የሚችለውን መስዋእትነት ከፍሏል።በተደጋጋሚ ከውጭ የመጡ ጠላቶቹን ተባብሮ በመመለስ ነጻነቱን አስከብሯል።በዚህ የጋራ እርብርቦሽና የእኛ ባይነት መንፈስ የተገነባች አገር በየወቅቱ በተነሱ የውጭ ጠላቶችና የሥልጣን ፍቅር ባሳበዳቸው መሪዎች ተንኮልና በሚፈጥሩት ውዝግብ የሕዝቡ ሰላምና አብሮነት ፈተና ውስጥ ሲገባ፣ ያገሪቱም እድገት ተሰናክሎ፣አንድነቷም ተቦርቡሮ በቀበኞች እየተቆራረሰች ከአገራት በፊት የነበረችና የነጻነት ምልክት የሆነች አገር አሁን ከአገራት ሁሉ ዃላ ቀርታ፣ ለዓለም ሕዝብ በርሃብ፣በግጭትና በስደት የመቀጣጫና የማስፈራሪያ ምሳሌ ለመሆን መብቃቷን በቁጭት ይናገራሉ።
በጠባብ ጎሰኞችና በጠላቶቿ ዓይን ደግሞ ፣- ኢትዮጵያ ማለት ያልሰለጠነ፣ካውሬ የማይሻል፣የማይግባባ፣የማይተዋወቅ፣እርስ በርሱ የሚፋጅ፣ሃይማኖት የሌለውና ፈጣሪን የማያውቅ አረመኔ፣ አንዱ ሌላውን ውጦና አስገብሮ ፣በባርነት ይዞ የኖረባትና የሚኖርባት፣ደሃና ዃላ ቀር አገር ናት።ስለተፈጥሮ ሃብቷ፣ስለእረጅም ታሪኳ፣በዓለም ታሪክ ውስጥ ስለነበራት ቦታና ድርሻ፣ሕዝቡ ያለውን ሰብአዊ ስነምግባርና አብሮ የመኖር ትስስሩንና ታሪኩን ይክዳሉ።ለነሱ ኢትዮጵያ ማለት ሌሎች በነጻነት ይኖሩ የነበሩትን አገሮች(Nations) አፈራርሶ የበላይነት ባገኘ ጎሳ የተፈጠረች አገር ናት፣ስለሆነም እያንዳንዱ ጎሳ የራሱን ክልል ከልሎ ከሌላው ተነጥሎ ነጻ መንግሥት ማቋቋም አለበት ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አገርና ዜግነት(Nation and Nationalities)የሚለውን ዓለም አቀፍ ግንዛቤ ብሔር ብሔረሰብ የሚል የተሳሳተ ትርጉም ያለው ትንታኔ በመስጠት የተዛባ አመለካከታቸው ሕጋዊነት እንዲኖረው ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው።ይህ በውጭ አገር ሰርጎ ገቦችና በአገር ውስጥ ተባባሪዎቻቸው በዴሞክራሲና በእኩልነት ስም ጎሳን የጠቀመ መስሎ ኢትዮጵያን በማፈራረስ ሴራ ከሰባ ዓመት በፊት የዘሩት የጥፋት ችግኝ ጎምርቶ ኢሕአዴግ የሚባል ፍሬ ካፈራ ሃያ ስምንት ዓመት ሆኖታል።በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተወለደው ትውልድ ስለነባሩ ያገሩ ታሪክ ሳያውቅ ለሚረጭለት አጥፊ ታሪክ ሰለባና ጭፍራ በመሆን የረጅም ዘመናት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን አገሩን እንዲጠላና ለነጮች መሰሪ የምዝበራ ዓላማ መሣሪያ ለመሆን ላይ ታች ሲል ይታያል።እራሱን ከሌላው ወገኑ ነጥሎ በጠላትነት መስመር ውስጥ አሰልፎ ሌላውን ወገኑን መጤና ሰፋሪ እያለ ሲገልና ሲያፈናቅል ያሳለፈው ጊዜ ለወደፊቱ ሊጠፋበት የሚችል አደጋ እንደሚሆንበት ለማዬት ከከለለው የጎሰኝነት እንቅልፉ አልነቃም።አሁንም የነገሩትን እራስን የመጥላት ዘመቻ እያስተጋባ በራሱ ላይ ቢላዋ እዬሳለ ነው።ለኢትዮጵያዊ ማንነቱ ምሰሶና አጋር የሆነውን ወገኑን በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ እንደ ዋና ጠላት በመቁጠር ሃይሉን ንዶና አመንምኖ አገሩን ለማፈራረስና ለውጭ ሃይሎች ዘረፋ የተመቼ ደካማ የጎሳ መንደር ለመፍጠር በነጻነት ስም የሚያደርገው ትግል ስህተት መሆኑን አሁንም አልተረዳም።ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት አገር ከሶማሊያ አልተማረም።
በጸረ ኢትዮጵያነት የተሰለፉት የየጎሳው መሪዎች ነን ባዮች እራሳቸውን የአንድ ትልቅ አገር ዜጋ ከማድረግ ይልቅ የተወሰነ ቁራሽ መሬት ባለቤት ወይም ምስለኔ ለመሆን፣ለዚያ ትንሽነት ሲሰግሩ ማዬትን የመሰለ ዃላ ቀርነት የለም።በዚህ ላይ ነጮች ዃላ ቀር ብለው ቢሉ ስህተት አይሆንም፤ከትልቅነት ትንሽነትን ከመምረጥ ሌላ ምን ዃላ ቀርነት ይኖራል?ሰብአዊ ፍጡርን ለዚያውም በመዋለድ በእትብት የተሳሰረን ወገኑኑንና ዘመዱን፣ የአንድን አገር ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋና በሚከተለው እምነት የተነሳ ከመጥላትና ከመሸንሸን ሌላ ምንስ አውሬነት ይኖራል?እኛና የእኛ የሚለው መንፈስ ተዳክሞ እኔና የእኔ በሚለው ከተተካ ምን አይነት ጠንካራና ነጻ አገር፣ምንስ አይነት እድገት ይታሰባል?
ኢትዮጵያዊ በዘመናት መስተጋብር ያተረፈውን ውህደትና ታሪክ ሽረው ፣ሕዝቡን በቋንቋው እረድፍ አሰልፈው፣ የመሬት ድንበር ከልለው፣ እርስ በርሱ በማናከስ ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ሂደት ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት “ሕገ መንግሥት” በሚል ሽፋን “ሕገ በትን” አውጆ ከመንቀሳቀስ ሌላ ምን የአገር ጠላትነት ይኖራል?ያንንስ ሕግ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ እኩልነት ይጠቅማል ብሎ የሚቀበል ምን አይነት አእምሮ ያለው ዜጋ ነው?ለምን ከሌሎቹ አገሮች ስርዓት መማር አልተቻለም?ነገሩ አውቆ የተኛ ቢጠሩት ወይ አይልም ነው።ይህንን እራስ ጠል ድክመት ተሸካሚና ወጣቱን ትውልድ የሚበክሉት ተምረናል የሚሉ የስልጣን ጥመኞች የሆኑ የየጎሳው ተወላጆች ናቸው።የሚገርመው ነገር ግን ፣ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ፣ ልዩ ልዩ ባህልና እምነት ያለው ሕዝብ በአንድነትና በሰላም በሚኖርበት አገር ውስጥ እየኖሩና በእኩልነት እንዲታዩ፣መብታቸውም እንዲከበርላቸው እየጮሁ ተወለድንበት ለሚሉት አገር ሕዝብ ግን የዘረኝነትና የልዩነት መርዝ መርጨታቸው ነው።ይህ ደግሞ ከወንጀል በላይ ወንጀል ነው።የጎሰኝነት ውጤትና ጣራው ፋሽዝም ነው። የፋሽዝም ጸረ አንድነትና ኢሰብአዊነት ነው።በአገራችን የተከሰተው ጎሰኝነት የሂትለርን ተከታዮች በዓለም ፍርድ ቤት ካስቀጣው ወንጀል ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም።የሚበልጥበት ምክንያት ባልታጠቀና የጦር ሃይል በሌለው ደሃ ገበሬ ሕዝብ፣ህጻንና አዛውንት ላይ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋና በደል በመሆኑ ነው።
ሰፊው ሕዝብ የእርስ በርስ ጥላቻ የለበትም፤ለዘመናት አብሮ በሰላምና በአንድ አገር ልጅነት መንፈስ ባህልና ቋንቋውን እምነቱንም ጭምር ተወራርሶ የኖረ ነው።ከሃምሳ ዓመት ወዲህ በስሙ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚሹ የጎሰኝነት ፍልስፍና በሚከተሉ ጥቂቶች ሲረጭ የኖረው እርኩስ መንፈስ አሁን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ድል እየሆነ መጥቷል፤ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ የሚለው አገራዊ መለያ ጎልቶ በተቀናቃኞቹ አንደበት ሳይቀር እየተነገረለት ነው።ይህ ግን በቂ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል።ጎሰኝነትን የሚያጎላውና የሚንከባከበው፣የጥፋት እውቅና (licence to distroy)የሚሰጠው “ሕገ መንግሥት”ተብዬው የጎሰኞች መሳሪያ በኢትዮጵያዊነት ላይ መሰረት ባደረገ፣የአገርን አንድነት በሚያረጋግጥ ፣የዜጎችን ደህንነት በሚያስከብር፣የዜጎችን መፈናቀል በሚከላከል፣መንግሥትን በሚቆጣጠርና ከስሩ ባደረገ፣ሕዝብ በተሳተፈበትና ባጸደቀው እውነተኛ ሕገመንግሥት መተካት ይኖርበታል።ያ እስካልሆነ ድረስ ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመራ ሂደት አለብሎ ለማመን ያስቸግራል።
ጥላቻ መንዛት ወንጀል ነው፣መከፋፈልና ማጋደል ወንጀል ነው።አንዱን መጉዳትና ሌላውን መጥቀም ወንጀል ነው።አገር መናድ ወንጀል ነው።ሕዝብን ማሳደድና ማፈናቀል ወንጀል ነው። የአገርን ሃብት መዝረፍና ማዘረፍ ወንጀል ነው።ያገሩን ባለቤት እያፈናቀሉ መሬቱን ለባዕዳን መሸጥና አሳልፎ መስጠት ወንጀል ነው።እነዚህን ሁሉ በሕግ ሽፋን የሚፈጽም መንግሥትም ይሁን ቡድን ወንጀለኛ ነው።ዘረኞች በዚህ “ሕገ መንግሥት” ድጋፍ አገር አፍርሰው ሌላ አገር ለመፍጠር ሲሞክሩ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ዜጎች ደግሞ አገር ለማፈራረስ የተሰናዳውን ” ሕገ መንግሥት” በመቃወምና ባለመቀበል ነባሯን ኢትዮጵያን፣ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን በተሻለ መልክ ለማስቀጠል የሚረዳ ፣ሕዝብ የመከረበትና የተቀበለው ሕገ መንግሥት እንዲኖር ይጥራሉ።የነሱ ኢትዮጵያ በጎሰኝነት ካስማ ላይ የተገነባች ሳትሆን፣ በሕዝብ ጥረትና ህብረት፣በመስዋዕትነት ዋጋ የተገነባች አገር ነች።
ዘረኞች የደቀቀችና የደከመች ብሎም የተበታተነች፤ለወራሪ ጠላት የተመቸች ኢትዮጵያን ማዬት፣እነሱም የደከመ ፣ቁርጥራጭ ክልል ይዘው በውጭ እርዳታና በልመና እናድጋለን ብለው ሲመኙ፣አገር ወዳድና በራሳቸው የሚተማመኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ታፍረውና ተከብረው የሚኖሩባትን፣ ይበልጥ የተባበረችና ጠንካራ አገር ለመጭው ትውልድ ማስረከብን ይመርጣሉ።ይህንን ምርጫቸውን ለማደናቀፍ የሚወጠነው ሴራ ግን ቀላል አይደለም።በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ዜጎች ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ የግዴታ የራሳቸውን ዓላማ በቅጡ ተረድተው በአንድ ጣራ ስር መሰባሰብ ይኖርባቸዋል።ከጠላት ወረዳ ምህረት፣ ከአፍራሽ ጎራ ጥንካሬ ይገኛል ብለው መጠበቅና መዘናጋት አይኖርባቸውም።ወይም በአንዳንድ ሽርፍራፊ ጥቅም ትጥቃቸውን ሊፈቱ አይገባም።ትጥቃቸውን ባጠበቁ ቁጥር የሚያገኙት ድል ይበዛል፤ትጥቃቸውን ካላሉና ከፈቱ ግን ያገኙትንም ያጣሉ።የአንዳንድ የታወቁ እስረኞች መፈታት በጎ ገጽ ቢኖረውም፤ አሁንም በሽህ የሚቆጠሩ ዜጎች በየቦታው እስርቤት ውስጥ እየማቀቁ ነው፤አገር እራሷ በጎሰኞች ገመድ ተተብትባለች።አሁንም ማፈናቀሉ፣ማሳደዱ ግድያው እየተፈጸመ ነው።ይህ ሁሉ ግፍ በሚፈጸምበት ወቅት ላይ ሆኖ ” ጉሮ ወሸባዬ”! ብሎ መጨፈር ጨለምተኝነት ነው።የትግሉንም ዓላማ ማሳነስ ይሆናል። አሁን ትግሉ ከወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል።ጎሰኞች ስርዓቱን ለማዳን እየተሰባሰቡ ናቸው።በተቃዋሚው በተለይም ዲያስፖራ በሚባለው ጎራ ውስጥ ያለው ወገን እገሌ ወጣ !እገሌ ወረደ! ዶር አብይ ይህንን አለ! እያለ በትዝብት ከማዬትና በጆሮው የሚሰማውን ከማድነቅ የተለዬ እራሱን ሲያጠናክር አይታይም።የተገኘው መለስተኛ ውጤትና የጠላቶቹ መፍረክረክ ብዙ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት የህይወት ዋጋና የእስራት ስቃይ የተዋቀረ የትግል ውጤት መሆኑን ዘንግቶ የተወሰኑ ሰዎች ፍላጎትና ስጦታ አድርጎ ቆጥሮ ያጨበጭባል።በሌላም በኩል የአንድ ድርጅት የትግል ውጤት አድርጎ የመቁጠር ወገንተኝነት ሲሰነዘርና ለግለሰቦች የሥልጣን ጎዳና ጠራጊ የመሆኑ ጭፍን ጀሌነት ሲያንጸባረቅ ይታያል።
ወቅቱ ፈታኝ ነው፤በፖለቲካው መስክ በውዥንብር የደፈረሰ የሃሳብ ጎርፍ ይወርዳል፤ጎርፉ ደካማውን እያግበሰበሰ በመስገር ላይ ነው።እዚያ ውስጥ ላለመስመጥ ብርታትና ብስለትን ይጠይቃል።ጎርፉ እየተመመ ከሚገባበት አደገኛ ውቅያኖስ ለመዳን አቅጣጫ አመላካች(compass) ያለው የራስን ታንኳ ወይም ጀልባ ሰርቶ መቅዘፍ ያዋጣል።በሰው ጀልባ ላይ መሳፈር ዋስትና የለውም፤ከጀልባው ባለቤት ጋር ካልተስማሙ መሃል መንገድ ላይ ጥልቀት ካለው ውሃ ውስጥ ተወርውረው ሊሰጥሙ እንደሚችሉ ማሰብ መልካም ነው።ኮምፓስ ያለው ጀልባ ማለትም ኢትዮጵያዊነት እራዕይና የፖሊሲ መመሪያ ያለው ድርጅት ማለት ነው። ዘሎ በሌላው ድንኳን ውስጥ ገብቶ አጫፋሪ መሆንን እንደ ባህል አድርገው የያዙ ድርጅቶች ካለፈው ውድቀታቸው ሊማሩ ይገባል። በአሁኑ መልክ ተበታትኖ መነሻና መድረሻውን ሳያውቁ መንጎድ ለተደራጀ ጥቃት ያጋልጣል።አሁን በመሽመድመድ ላይ ያለው የጎሰኝነት አከርካሪ እስከነጭራሹ በኢትዮጵያዊነት ክንድ ካልተሰበረ ሰላምና አንድነት አይኖርም።ዜጋ ተነጥሎ የሚጠቃበትና የሚፈናቀልበት ሕግና ስርዓት እስካለ ድረስ ለውጥ አለብሎ ማጨብጨብጨብ ሞኝነት ነው። ለውጡም የጌታ እንጂ የስርዓት ለውጥ አይሆንም። በልዩነት ክር የተሰፋው ባንዲራም ተወግዶ የደም ዋጋ ተከፍሎበት ፣ ለሌሎች አገሮች ሳይቀር የነጻነት አርማ የሆነው አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከዳር እስከዳር እስኪውለበለብና መሰረታዊ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ትግሉ መቀጠል ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!
አገሬ አዲስ
