አቶ በቀለ ገርባ
አቶ በቀለ ገርባ

አመሳክረን ማድመጥ ከቻልን አቶ ለማ መገርሳ የማናውቀው እስር ቤት ካለ ጠቁሙንም ሲሉ ሰምተናል።ከዚያ የምንረዳው የደረሱበት የማይታወቅ እስረኞች መኖራቸውንና ምናልባትም አቶ በቀለ በስም የሚያውቋቸው ሊሆኑ ይችላሉ።ስለዚህ ዶር አብይ ጠመንጃ አንስተው ስርአቱን የሞገቱት አቶ አንዳርጋቸውን ፈትተው ሌሎች ሃገር ውስጥ በተለያየ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የታሰሩ ምናልባት የኦፌኮ አባላት አሁንም በእስር ቤት መኖራቸው አቶ በቀለን ቢያስገርማቸው ወይም ሊገባቸው ባይችል እንዴት ይደንቀናል። አቶ በቀለ ለምን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ተፈቱ አላሉም። እንደ ፖለቲከኛ አንፃራዊ በሆነ መልኩ የራሳቸው የድርጅት አባላትን አለመፈታት ለማሳየት ንፅፅር ውስጥ ገቡ እንጂ። አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ይህን ቁም ነገር ጠንቅቀው እንደሚረዱ ሙሉ እምነት አለኝ።

ስለ አህያና ዳውላ ማውራት የፈለኩት አቶ በቀለ እኛ በሞትንበት ለምን አቶ አንዳርጋቸው ተፈቱ ቢሉ እንኳን ፍፁም ሊያስገርመን አይገባም ብዬ ስለማምንም ጭምር ነው።።ለምን ብንል ከጎሳ ፖለቲካ የሚጠበቅ ስለሆነ። ከዚህ በፊት ስለሃገራችን የጎሳ አደረጃጀት አንዳንድ ፅሁፎችን አቅርቤ ነበር።የኢትዮጲያ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች በራሳችን ቋንቋ እራሳችንን እናስተዳድር ባህላችንን እናሳድግ ማለታቸው በምንም መልኩ በአሉታ ሊታይ አይገባም።አሁን ባለንበት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ማንም ለማንም ቋንቋ መራጭ መሆን አይችልም። የኢትዮጲያ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች በየአካባቢያቸው ቋንቋ ቢናገሩ በየቋንቋቸው ቢማሩና ቢዳኙ ፤የየራሳቸውን ባህል በስነ ፅሁፍ በሙዚቃ ወዘተ ቢያጎለብቱ ለኢትዮጲያ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ ሊሆን አይችልም።ያ ደሞ በራሱ የጎሳ ፖለቲካ አይደለም።የጎሳ ፖለቲካ ማለት አንድን ጎሳ ማዕከል አድርጎ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁሞ መንቀሳቀስ ነው። የብሄረሰቦችን መብት ማክበርና የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችን መፍቀድ በጣም የተለያዩ ናቸው።

ሃገራችን ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ደሞ እጅግ በጣም የከፋ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ህወሃት የብሄረሰቦች መብት የሚለውን ሃሳብ ይዞ ሲመጣ በውስጡ ያስቀመጠው መርዝ አለ። ይህም አንደኛ አማራውን በጠላትነት መፈረጅ። ሁለተኛ ብሄረሰቦችን በጎሳ ማደራጀት።  ሶስተኛ  አማራውን ከኦሮሞው ትምክህተኛና ጠባብ በሚል ከፋፍሎ ሁለቱን የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ግራ ማጋባትና ማጋጨት። አራተኛ አማራው በራሱ የራሱን መብት እንዳያስከብር የአማራ ድርጅት የተባለው ብአዴንን ምናልባትም ለአማራው ከፍተኛ ጥላቻ ባላቸው አማራ ባልሆኑ ሰዎች ለብሄረሰቡ ምንም ጥቅም በማይሰጥ መንገድ እንዲመራ ማድረግ። አምስተኛ ለሌሎቹም የብሄር ድርጅቶች በላያቸው የህወሃት ሰዎችን በሞግዚትነት በማስቀመጥ ማሽመድመድና የህወሃትን ልዩ ጥቅም ማስከበር ሲሆኑ እነዚህም በህቡዕ መስመር እያሉ የሚጠሩት የዝወራ ዘይቤ ነው። መስመር የሚሉት  የብሄረሰብ መብት ማክበርን ሳይሆን እነዚህን መርዞች ነው።አሁንም ሰዎች የሚፈናቀሉት በዚህ መስመር ተብሎ በሚጠራ ዝውር ነው።

ፖለቲካ ድርጅት ስለ ፍትህ፤ ስራ ፤ እንጀራ፤ ውሃ፤ መጠለያ፤ልብስ፤ትምህርት፤ ህክምና፤ መንገድ ወዘተ ለአጠቃላይ ለኢትዮጲያውያን መደባዊ በሆነ መልኩ  ለማዳረስ  በሚደረግ ትግል የፖሊሲ ልዩነት የሚያንፀባርቅ ስብስብ   እንጂ የአንድን ብሄረሰብ መብት በማስከበር ስም ብሄረሰቡን ከሌላው ብሄረሰብ በተለየ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚቋቋም የአድሏዊነትና የወነጀለኝነት ስብስብ አይደለም።ያ ዘረኝነት ነው። ዶር አብይ እነዚህን አምስቱን መርዞች ከፓለቲካው ሰማይ ማፅዳት ከቻሉ የሁሉም የግለሰብና የብሄረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት የፖለቲካ ስርዓት ለማምጣት እድል ይኖራል።ብሄረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው ያሰተዳድሩ የሚለው ህሳቤ ሊታጀቡባቸው የሚገባ ህሳቤዎች፤ የጎሳ የፖለቲካ ድርጅቶችን ፀረ ፍትሃዊነትና ፀረ ዲሞክራሲያዊነት መረዳት፤ ዜጎች በመጀመርያ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው በጋራ የሞቱላት ብዙ ዋጋ የከፈሉባት ኢትዮጲያ የምትባል የጋራ ባለ አኩሪ ታሪክ  ሃገር እንዳለቻቸው እንዲረዱ በፅኑ መስራት፤ዜጎች በፈለጋቸው የሀገሪቱ ክፍላት በነፃ ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸውን ማረጋገጥ፤በጎሳ አድልዎ የሚያደርጉ ሰዎችን ድርጅቶችንና ማህበራትን የሚቀጣ ጠንካራ ህግ ማውጣት የመሳሰሉት ናቸው።

ዘረኝነትና ፖለቲካ ፍፁም የተለያዩ ናቸው።አማራጭ አጥተን የጎሳ ፖለቲካ እንለዋለን እንጂ የጎሳ ፖለቲካ እያልን የምንጠራው በሃይል ሃጋዊነት የተላበሰውን ያው ዘረኝነት ነው።ፓለቲካ ድርጅት በጎሳ በሃይማኖት ተንተርሶ ከተደራጀ ፍትህ ቦታ አይኖራትም።ምክንያቱም ከራስህ ጎሳ የወጣን ሙልጭ ሌባ፤ ከሌላው ጎሳ ከወጣ ነብይ ማስበለጥን ግድ ይላል።አፍሪካን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሃገራት ይህን የፖለቲካ ሀ ሁ ተረድተው በጎሳና በሃይማኖት ህሳቤ የፖለቲካ መደራጀትን ከህገ ወጥ ወይም ከወንጀል ይመድቡታል። የብሄረሰቤ መብት ይከበር ብሎ መንቀሳቀስ እውነታ ነው። አንዴ ግን ያ መብት በህገ መንግስት ከፀደቀ የህዝብንም ይሁንታ ካገኘ በኋላ የዕለት ተዕለቱ የፓለቲካ ስራ ከጎሰኝነት የፀዳ መሆን ይኖርበታል።

አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አረንጓዴ የሚባል ፓርቲ አደራጅተው የኦሮሞውንና የአማራውን ብሄረሰብ መብት በጋራ ሊያስከብሩ የማይችሉበት ምክንያት የለም።የሱማሌ ፓርቲ ብለህ ስትደራጅ ግን ሌላውን ሁሉ ማግለል ግድ ይላል። ጎሰኝነትና ዲሞክራሲ በፍፁም አብረው አይሄዱም።ጎሰኝነት በይዘቱ አድሏዊ ነው።ጎሰኝነት ባለበት ፍትህና ዲሞክራሲ ቦታ አይኖራቸውም።በጎሳ ፖለቲካ ወይም በዘረኝነት በአባላቶችህ ተወዳጅነትህና ተመራጭነትህ የሚለካውና የሚመዘነው ሌሎችን በማግለል ብቃትህ ነው።አንዱን ጎሳ መርጠህ ቆሜልሃለሁ በማለትህና ሌላው ላይ በምታደርሰው ጥቃት መጠን ተመራጭነትህ ይጨምራል።

ስለዚህ አሁን ሊያስጨንቀን የሚገባው ዶር አብይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችን አቅፈው በሃገሪቱ ዲሞክራሲ ይሰፍናል ብለው ያስባሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ነው ።ያ ከሆነ ኢትዮጲያውያን እርስ በራሳችን ወደ ምንተላለቅበት መጥፎ መንገድ እየነጎድን መሆናችንን ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል።ጎሰኝነትን አድሏዊነትን ዲሞክራሲያዊ መብት ካደረግነው ትልቅ አደጋ አለው።ይህንንም የምለው እስካሁን በኢትዮጲያ ዲሞክራሲ እንዳልነበረ ስለምረዳ ነው። ጎሰኝነትን በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከማካሄድ አንድ አምባገነናዊ የፓለቲካ ድርጅት ተጠያቂ በሚሆንበት ስርዓት ማካሄድ እጅግ እጅግ በጣም ይሻላል።አምባገነናዊው ፓርቲ ሳይፈቅድ ጥቃቶች አይካሄዱም።የሚደርሰውን ጥቃት መጠን  እንዳስፈላጊነቱ የሚቆጣጠር ተጠያቂ አምባገነናዊ  ፓርቲ ስለሚኖር።

የጎሳ ፖለቲካና ዲሞክራሲ በጣም መጥፎ ጥምር ናቸው። እሳትና ጭድ ማለት የጎሳ ፖለቲካና ፍትህ ናቸው።እሳትና ጭድ ማለት የጎሳ ፓለቲካና ዲሞክራሲ ናቸው።ስለዚህ አቶ በቀለ ገርባን ለቀቅ እናርግና አስተሳሰቡን ስለሚቀፈቅፈው ባጠቃላይ ስለ ጎሳ ፖለቲካ ወይም በትክክለኛ ስሙ ህጋዊነት ስለተሰጠው ዘረኝነት መወገድ ግንዛቤ እንፍጠር።ያኔ እኛና እነሱ የሚባለው ነገር ከስር መሰረቱ ሲጠፋ ፖለቲከኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የጎሰኝነት ከፋፋይ መርዝ አይረጩም። የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችን ህገ ወጥ ማድረግ ማለት ብሄረሰቦች በቋንቋቸው አይጠቀሙ ማለት አይደለም።

አቶ በቀለ ገርባ አሁንም በእስር ላይ አሉ የሚሏቸው በሙሉ ይፈቱ።

መላኩ ከአትላንታ