“ሕዝባዊ ሲኖዶስ” ስንል፣ በዘመናችን ሲኖዶስ መዋቅራዊ ደረጃና በአባላቱ ተዋፅኦ ላይ የተከሠተውን ክፍተት በማሳየት፣“ጥንታዊውና መደበኛው ይመለስልን፤ ይተግበርልን” ማለትን የሚያስገነዝብ ነው፤
በመዋቅራዊ መሠረቱ ኹለት ወገን ነው፤ አንዱ ክህነታዊ ቅዱስ ሲኖዶስ(Holy Sacramental Synod) ሲኾን ሌላኛው ደግሞ፣ አስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ(Holy Governing Synod) ነው፤
“ሕዝባዊ ሲኖዶስ”፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገልበት የነበረና በእጨጌው የሚመራ ጥንታዊና መደበኛ የሲኖዶስ ቅርፅና አደረጃጀት ነው፤
በእጨጌው የሚመራው የአስተዳደራዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ሕዝብ ያመነባቸው ምሁራንና ሞያተኞችን ያካተተና ይልቁንም ንቡራነ እዶችና ሊቃነ ካህናት በአባልነት የሚሳተፉበት ነበር፤
የፓትርያርኩ እጨጌነት፣ ለአስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰጥቶ በመንፈሳዊ ፕትርክናቸው ቢወሰኑ፤ የቋሚ ሲኖዶስ ቅርጽ፣ በአስተዳደራዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ተተክቶ ሥራው ቢሠራ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅነት፣ በምሁራን ሞያተኞች መመራት ቢጀምር፤ጳጳሳት በክህነት አገልግሎት ብቻ ተወስነው አስተዳደራዊ ሲኖዶሱ በእጨጌው በሚመራ ምሁራዊ ስብጥር ቢሠራ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ጥንቱ ወደ ታላቅነቷ ትመለሳለች፡፡
†††

ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ

(የጥንታውያን ቋንቋዎችና ጽሑፎች ተመራማሪ)

የጥንታዊ ቋንቋዎችና ጽሑፎች ተመራማሪው ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ፣ “ሕዝባዊ ሲኖዶስ ይቋቋም” በሚል ርእስ፣ በየሁለት ሳምንቱ በአዲስ አበባ ታትማ በምትወጣው ግዮን መጽሔት ያሰፈሩትን ጽሑፍ ቀዳሚ ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል እንደኾነ ያወሱት ጸሐፊው፣በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ እንደመኾኑ መጠን፣ በአሠራሩና በውሳኔ አሰጣጡ ከተለያዩ ተጽዕኖዎች ተጠብቆ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን፣ የኹሉም መብት በሕግ ፊት እንዲከበር፣ እኩልነትና አንድነት እንዲረጋገጥ መጠንቀቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በሓላፊነት በሚያገለግሉበት መንፈሳዊ ኮሌጅ በትውልድ ማንነታቸውና በሥራ መብታቸው ላይ የደረሰባቸውን በደል ተጨባጭ መነሻ ያደረጉት ዶ/ር ዘሪሁን፣ ከወገንተኝነትና ጥቅማጥቅም በጸዳ መልኩ ፍትሕ የሚሰጥ አባት ወይም የበላይ ሲኖዶሳዊ አካል በማጣት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ በኾኑ ተቋማት ዳኝነት ፍለጋ የሚንገላቱ ካህናት፣ ሊቃውንትና ምእመናን እየተበራከቱ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በአጭር ጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለትም፣የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደርና አገልግሎት በቀኖናው እንዲመራ የማድረግ፣ ሀብቷን የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ፥ መንፈሳዊነት፣ልዕልና እና ቅድስና አጠያያቂ እንደሚኾን የአባላቱ ብፁዓን አባቶችም ቅቡልነት እንደሚያሰጋ ጠቁመዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላትና አካላት ለአገልጋዮችና ምእመናን የፍትሕ ጩኸት መላሽ የሚኾኑበት ቅርበት እየተቋረጠ ከሔደም፣ የቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ህልውናና አንድነት ለከፋ አደጋ ከመጋለጡ በፊት፣ “ማኅበረ ምእመናኑ ያመኑበት፤ በዐይናቸው የሚያውቁት፤ በእጃቸው የዳሰሱት፣ በትምህርቱ የተማረኩበት፤ ለአመራሩና ውሳኔው የሚገዙለት፣ የሕዝብ ይኹንታና ተመጣጣኝ ውክልና የተሰጣቸው ሊቃውንትና ምሁራን አባቶች ተመልምለው የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይገባል፤” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በወጣችው ግዮን መጽሔት ባስነበቡት የጽሑፋቸው ተከታይ ክፍል ደግሞ፣ይህንኑ አቋማቸውን በማጠናከር፣“የሕዝባዊ ሲኖዶስን” ምንነት በስፋት አብራርተዋል፡፡“እኔን የሚያሳስበኝ የታላቋ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው፡፡ ቀኖናዋ ሲጣስ ያስቆጫል፤ ዶግማዋ ሲፋለስ ያበሳጫል፤ ሥርዐተ እምነቷ ሲራከስ ያናድዳል፤ ስለሚያሳስበው ጉዳይ አብረን ብንታገል ይሻል ይመስለኛል፤” በማለት ጽሑፋቸውን የሚጀምሩት ዶ/ር ዘሪሁን፣ በተለይ ከ4ኛው መ/ክ/ዘ አንሥቶ በኢትዮጵያ ጥንተ ክርስትና እና በቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ነጻነት ላይ የተፈጸመውን የመለያየትና የታሪክ ሐቆችን የማፋለስ በደሎች ተንተነዋል፡፡

ዛሬም፣ በጥናት የተደገፈ የፖሊቲካ ተልእኮ ባነገቡ ኃይሎች ሤራና ጣልቃ ገብነት፣ ሕገ ሲኖዶስ እየተጣሰ የሀገርን አንድነት የሚያፈርስና የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት የሚገዳደር ድርጊት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ይህንም፣ “ከዳተኝነት፤ ፖለቲከኝነትና አማሳኝነት” ሲሉ የገለጹት ጸሐፊው፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ከዚህ መታደግ የሚቻለው፣ ሁላችንም አንድ ኾነን ያገባናል ስንልና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመሰከረላቸው ዕጩዎች ጵጵስና ተሹመው የሲኖዶስ አባላት ሲኾኑ ብቻ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡ “ጳጳሳቱን የመረጠው ሕዝብ ነው ማለት፣ ሲኖዶሱ ሕዝባዊ ኾነ ማለት ነው፤ ጳጳሳቱን ከምልመላ ጀምሮ የመረጣቸው መንግሥት ነው ማለት፣ ሲኖዶሱ መንግሥታዊ ኾነ ማለት ነው፤” ይላሉ፡፡

ስለ“ሕዝባዊ ሲኖዶስ” የሚሰጡትን ትርጉም በመቀጠል፣ “በሕዝብ የተሾመ ጳጳስ ብቻ ነው ለሕዝብ እንደሚሠራ የሚታወቀው፤” ያሉት ጸሐፊው፣ “ጳጳስ የሚሾመው እኮ ሕዝብ ላይ እንጂ መንግሥታዊ ድርጅት ላይ አይደለም፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከመቀነቱ እያወጣ ለሚያሠራው ቤተ ክርስቲያን የሚሾምበትን ሰው በስሙና በመልኩ በጠባዕዩም አምኖበት የመጠቆምና የመምረጥ መብት እንዳለው በሕጉ ተጽፎ የለምን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን ቀርቶ ተሿዋሚውን ጳጳስ በሃይማኖት የማይመስሉት ሰዎች እንኳን ስለሚኖረው መልካምነት ሊስማሙበት እንደሚገባ በፍትሐ ነገሥት ተጽፏል፡፡ እንግዲህ ሕዝባዊ ሲኖዶስ ማለት በዚህ መልኩ በሕዝብ ተጠቁመው የተመረጡና የተሾሙ ጳጳሳት ያሉበት የሕጋዊ ሲኖዶስ ቅርጽ ነው፤ በማለትም ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

“ሕዝባዊ ሲኖዶስ” ሲባል፣ በዘመናችን ሲኖዶስ መዋቅራዊ ደረጃና በአባላቱ ተዋፅኦ ላይ የተከሠተውን ክፍተት በመጠቆም፣“ጥንታዊውና መደበኛው ይመለስልን፤ ይተግበርልን” ማለትን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡ ዶ/ር ዘሪሁን እንዳስረዱት፣ “ሕዝባዊ ሲኖዶስ” በመዋቅራዊ መሠረቱ በኹለት ወገን የሚዋቀሩ ሲኖዶሳትን ያመለክታል፡፡ አንዱ፣ ክህነታዊ ቅዱስ ሲኖዶስ (Holy Sacramental Synod) ሲኾን ሌላኛው ደግሞ፣ አስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ(Holy Governing Synod) ነው፡፡

በሀገራችን ያለው ክህነታዊው ሲኖዶስ ብቻ እንደኾነ ጠቅሰው፣ቀደምቱ የአስተዳደራዊ ሲኖዶስ ቅርጽና አገልግሎት በታሪክ በተፈጸመው ደባ(በግብጻውያንና ሮማውያን) ጠፍቷል፤ ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ክህነታዊ ሲኖዶስ ሕጋዊ ቅርጽና የአባልነት ተዋፅኦ ላይም ጥያቄ አንሥተዋል – “ቀሳውስት በመነኰሳት መሀል ተገኝተው የሲኖዶስ አባላት እንዳይኾኑ የሚከለክል ተቀጽላ ሕግ ከየት የመጣ ነው? በአንዲት ሴት የተወሰኑ ካህናትን የጉባኤው አባላት እንዳይኾኑ ያገለለ ሲኖዶስ አይደለምን?”

በሀገራችንም ታሪክ “ሕዝባዊ ሲኖዶስ”፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገልበት የነበረና በእጨጌው የሚመራ ጥንታዊና መደበኛ የሲኖዶስ ቅርፅና አደረጃጀት እንደኾነ ዶ/ር ዘሪሁን እንደሚከተለው አውስተዋል፡፡…

“ለማንኛውም ሕዝባዊ ስለኾነው ስለ አስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ አወቃቀርና ታሪክ ጥቂት ልንገራችኹ፤ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ታሪክ አስተዳደራዊ ሲኖዶስ ቢያንስ ዐሥራ ኹለት አባላት ያሉበት ኾኖ በእጨጌው የሚመራ ነበር፡፡ አስተዳደራዊ ሲኖዶስ በእጨጌው የበላይነት፣ በርእሰ ሀገሩ ታዛቢነት፣ በሊቀ ጳጳሱ አውጋዥነት ብዙ ጊዜ ተገልጧል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የእጨጌው መንበር ደብረ ሊባኖስ መኾኑ አልቀረም፤ እጨጌው በአስተዳደርና ዕውቀት የቤተ ክህነቱ የበላይ ሲኾን፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት የፓትርያርኩ የበታች ነው፤ ፓትርያርኩ በመንፈሳዊ አገልግሎት የበላይ ሲኾኑ እጨጌው ግን ተጠሪነቱ ቀጥታ ለሀገሪቱ ርእሰ ሀገር ነበር፤

በእጨጌው የሚመራው የአስተዳደራዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሕዝብ ያመነባቸው ምሁራንና ሞያተኞችን ያካተተና ይልቁንም ምሁራን የኾኑ ንቡራነ እዶችና ሊቃነ ካህናት በአባልነት የሚሳተፉበት ነበር፡፡ እነዚህ አባላት የኾኑበት ሲኖዶስ ለተበደለ ፍትሕን የሚሰጥ ለፓትርያርኩ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ ሲኾን መዋቅርነቱ ላዕላዊ ነው፡፡ ይኽ አስተዳደራዊ ሲኖዶስ በዜጋ አመል ደብረ ሊባኖስ ተመሥርቷል፤ በታላላቅ የሀገር ቤት ሲኖዶሶችና የውጭ ሲኖዶሶች ተገኝቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ለምሳሌ፥ ኢየሱሳውያንን ተከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት አዘዞ ሔዷል፤ “ዘጠኝ መለኰት” የሚሉትን ለመመርመርና ለማውገዝ ዋልድባ ድረስ ዘልቋል፤ራሻ እንደ ዛሬው የራሷን አስተዳደራዊ ሲኖዶስ ሳታቋቁምና ራሷን ሳትችል ከታላቋ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በፍሎሬንት ጉባኤ ተገናኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ሲኖዶስም በሮም ፍሎሬንት ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ደቂቀ እስጢፋን አሳፍሮ ተመልሷል ፡፡

ለነገሩ አባ ሆይ ወደ ሩስያ ሔደው ስለመጡ ይህን አስተያየት መርምረው፣ የአክሱም ሐውልትን ከጣልያን እንዳስመለስን፤ የአስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶሳችንንም አወቃቀር ከራሻ ቢያስመልሱልን መልካም ነበር እላለኹ! በሩስያ መስኮብ ቤተ ክርስቲያን ዐሥራ ኹለት አባላት ያሉት በእጨጌው የሚመራው አስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ መንበሩ በሴንት ፒተርስበርግ መንበረ ጴጥሮስ የተመሠረተው በ1721 ነው፡፡ ራሻውያን ይኽንንም ሲኖዶሳዊ ቅርጽ በኢየሩሳሌም ከነበሩት፣ በእጨጌው ከሚመሩት የኢትዮጵያውያን የሲኖዶስ አባላት እንደወሰዱት የታሪክ ምንጮች ያጋልጣሉ፤ የራሽያ ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ለ200 ዘመናት በዚህ መዋቅር የበላይነት እየተመራች ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን የእጨጌነቱን አስተዳደራዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዐት ጳጳሳቱ ወርሰውታል፡፡ በጥንቱ ሥርዐታችን ሥራ አስኪያጅ የሚሾመው በእጨጌው ጥናትና አቅራቢነት ጳጳስ ያልኾነ ምሁር ነበር፤የክህነታዊውን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ለማስፈጸም በሚል ቋሚ ሲኖዶስ በሚል ተቋቁሞ፣ የቋሚ ሲኖዶስ አባላትም ጳጳሳት ብቻ ኾነው ምሁራኑ ቀሳውስትና ሊቃውንት ባለመካተታቸው ቀዋሚው የአስተዳደር ቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዐትና እጨጌአዊ መዋቅር ተዘንግቷል፡፡

ሀገረ ስብከት ሲከሠስ፥ ዳኛው ጳጳስ፣ ይግባኝ ሰሚ ጳጳስ፣ የበላይ ውሳኔ ሰጪ ጳጳስ ኾነው ተሠይመውበታል፡፡ በዚህ ዓይነት አስተዳደር ማን ፍትሕ ያገኛል? ምን ዓይነት ሥራስ ይሠራል? የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጳጳስ መኾን አለበት ብሎ መወሰን የቤተ ክርስቲያን ምሁራንን ያገለለ አይደለምን? አሁን ግን ይኼ ሁሉ ቀርቶ ፓትርያርኩ እጨጌነቱን ለአስተዳደራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ቢሰጡና በመንፈሳዊ ፕትርክናቸው ቢወሰኑ የቋሚ ሲኖዶስ ቅርጽ በአስተዳደራዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ተተክቶ ሥራው ቢሠራ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅነት በምሁራን ሞያተኞች መመራት ቢጀምር፤ ጳጳሳት በክህነት አገልግሎት ብቻ ተወስነው አስተዳደራዊ ሲኖዶሱን በእጨጌው ለሚመራው ምሁራዊ ስብጥር ቢያስረክቡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ጥንቱ ወደ ታላቅነቷ ትመለሳለች፡፡

እኔም የምጮህለት የሕዝባዊ ሲኖዶስ ጉዳይ ከሚያነሣቸው ጥያቄዎች አንዱ፣ ለዚህ ጽሑፍ ርእስ ያደረግሁት፣ “ሕጋዊ ሲኖዶስ የትኛው ነው?” የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጥያቄ መነሻነት በዘመናችን ያለውን የሲኖዶስ ቅርፅና ዓይነቶቹን እተቻለኹ፣ ምናልባት ቃሉ ዓለማዊ ለመሰላችኹም አለመኾኑን ገልጫለኹ፤ እናም አሁንም እላለኹ፥ ሕዝባዊ ሲኖዶስ ይቋቋም!!! ይቆየን…

“…ኲሎ አመክሩ ወዘሠናየ አጽንዑ…”

ገለቶማ !!!

ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ፣ “ሕጋዊ ሲኖዶስ የቱ ነው?” በሚል ግዮን መጽሔት፣በግንቦት ፳፻፲ ዓ.ም. እትሙ ያስነበበው ሲኾን፤ ለጡመራ መድረኩ እንዲስማማ ተመጥኖ የቀረበ ነው፡፡ ጸሐፊውን ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱን በኢ-ሜይል አድራሻቸው <mulatuz@yahoo.com> ማግኘት ይቻላል፡፡