የኢትዮጵያና የኤርትራ ነገር እጅግ አሳዛኝ የሚያደርገው በዚህ ዓለም በሰለጠነ ዓለም፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪክ ከሆነ ከአምሳ ዓመታት በኋላ በቀኝ ግዛት ውሎች ምክንያት ኩናማው፣ ትግርኛ ተናጋሪው፣ ሳሆው ኢሮብ እና አፋር በመካከሉ ባዕድ የሆነ መስመር ተሰምሮበት ለሁለት መከፈሉ ነው። ከሁሉም በላይ ኣሳዛኝ የሚሆነው ደግሞ በሻዕቢያና በህወሀት የተመራው የትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ ትግል መጨረሻው የኢጣሊያና የምኒልክ ፕሮጃክት ማስፈፀም መሆኑ ተቃርኖው የሚደንቅ ነው።

አንድ ህዝብ በጠላቶቹ ፍላጎት በመሀሉ የተሰመረን የጠላት መስመር ይከበርልኝ ብሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ህይወት መገበር፣ ለአርባ ዓመት ያህል ደግሞ በአሰቃቂ ጦርነት ውስጥ ማለፍ አይገባውም ነበር። ከቀኝ ግዛት ነፃ መውጣት ማለት በዚያ ዘመን የነበሩ አከላለሎች፣ አሰራሮችና ህጎች በመሻር በአስተሳሰብም ጭምር ነፃ መውጣት የሚያካትት ነው።

የአፍሪካ ቀንድ የቀኝ ገዢዎች ባሰመሩት የድንበር መስመር ምክንያት አፋሩ በሶስት ቦታ፣ ሶማሌው በአራት በአምስት ቦታ፣ ትግርኛ ተናጋሪው፣ ኩናማው፣ ሳሆው፣ ኢሮቡ፣ በተለያዩ አገሮች እንዲከፋፈል አድርጎታል። በዚህ መንገድ ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ማምጣትም ሆነ አብሮ ማደግ አልተቻለም። በዚህ ላይ በኤርትራ ውስጥ የኃይማኖታዊ ሽፋን ያለው የጦርነት አርማጌዲዮን በቅርብ እንደሚጀምር ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም።  በሾሻል ሚዲያዎቻቸው በትግርኛ፣ በእንግሊዘኛ በአረብኛ ጭምር እያደረጉት ያለው ሰጣገባና ቅስቀሳ ላይ  በግልፅ የሚታይ ነው። ይህ ልዩነት ፖለቲካዊ ቅርፅ እንዲይዝ እስራኤልና አረቦች በስፋት እየሰሩበት እንዳለም እንደዚሁ ምልክቶች አሉ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ለዚሁ ጉዳይ የትግራይን ህዝብ ለማገዶነት የሚፈልጉት መኖራቸው ነው። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ሆኖ፣ በተባበረ ክንድ ያለችውን አገር ለሁሉም የምትስማማ እንድትሆን ይታገላል እንጂ ከዚህ በኋላ አዲስ አገር ምስረታ የሚኳትንበት ምክንያት አይታየኝም።

በኤርትራ የኃይማኖት ጦርነት ጀመረ ማለት ነገሩ ሁሉ በዚያ ያበቃል ማለት አይደለም። የአፍሪካ ቀንዱን ሁሉ ነው የሚያበጣብጠው፣ ኢትዮጵያም አይቀርላትም። ያኔ ትግሬነት አማራነት ኦሮሞነት ወይም ሌላ የብሄር ማሰለፊያዎች ይቀሩና ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነትና እስላምነት አዳዲስ የማሰለፊያ መሳሪያዎች ሆነው ይከሰታሉ። ደግሞ አንድ ላይ የነበረው ተለያይቶ የተለያየው ደግሞ ተገናኝቶ እርስ በእርስ የመፋጀቱ ጉዳይ በሌላ መልኩ ይቀጥላል ማለት ነው። ሱማሌዎቹም እንደዚሁ አንድ ላይ ሆኖም ተለያይተውም በሰላም መኖር አልቻሉም። ሌላም ሌላም ብዙ ችግር በዚህ በአፍሪካ ቀንዱ አከባቢ ማንሳት የሚቻል ነው። ይህ ሁሉ በአፍሪካ ቀንድ ደረጃ ካልታሰበበት፣ በብሄርና በኃይማኖት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችና ፍላጎቶች መፍታትና ወደ ተሻለ የጋራ ጉዳይ ማሳደግ ካልተቻለ ችግሩ እየተባበሰ ነው የሚሄደው።

በነገራችን ላይ በቅርቡ የአቶ ለንጮ ለታ The Horn of Africa as common Homeland: The State and Self Determination in the era of Heightened Globalization እያነበብኩ ነው ያለሁት። ሰውዬው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ሊቅ ነው። የፖለቲካ አቅሙና እውቀቱ በዚህ ደረጃ ከፍተኛ አይመስለኝም ነበር።  አሁን ጊዜውና ዘመኑ ፈቅዶ ወደ አገሩ ዳግም ተመልሷል። ይህ የአፍሪካ ቀንድን የጋራ መኖሪያ የማድረግ ሀሳቡ ከልቡ የሚያምንበት ከሆነ አሁን ለመተግበር የሚችልበት የተሻለ ዘመን ላይ ያለ ይመስለኛል። እኔም የአፍሪካ ቀንድ እንደ አዲስ አዋቅሮ ሰፊ የፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ዓይነት ማዕቀፍ በመፍጠር፣ ህዝቦችና ኢኮኖሚ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት የጋራ ሰላማዊ መኖሪያ ማድረግ የተሻለ መፍትሄ ሆኖ ነው የሚታየኝ። እናም በሀሳቡ ላይ ውይይት ቢደረግ አይከፋም ባይ ነኝ። ወደፊት እንጂ ወደኋላ እያሰቡ አገር መንገባት አይቻልምና።

በዚህ ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ተፈጥሯል፣ ሁሉም ነገር አንድ ዓይነት በማድረግ፣ ልክ ጋፋት፣ ቋራ፣ ዛይ እና ናራ የተባሉ ህዝቦች በጠፉበት መንገድ፣ አርጎባው፣ ቅማንት፣ አገው፣ ኩናማው ኢሮቡ፣ መዠንገሩ፣ ሽናሻው ሌላውም ሁሉ ማንነቱና ቋንቋውን እንዲረሳ በማድረግ በኃይል አንድ ዓይነት አገር የመግንባቱ ሂደት ከሽፏል። በተለይ አሁን ኦሮምኛ ሌላኛው የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ሆኖ ሲታወጅ የቋንቋ ብዙህነቱ ጅማሮው አዲስ መልክ እየያዘ ይመጣል። ሌሎች ክልሎች እንደቅርበታቸውና ለራሳቸው እንደሚጠቅማቸው ከሁለቱም ቋንቋዎች አንዱን ወይም ሁሉቱንም መርጠው የማስተማርና የመጠቀም ነገር ይጀምራሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ወላይትኛና ሲዳምኛ ሲጨመሩበት በአንድ አይነትነቱ የአገር ግንባታ ሳጥን ላይ የመጨረሻው ሚስማር ይሆናል። የሕብረ ብሄራዊነት አገርና የብዙህነት ባህል ማሰሪያው፣ ብሎኑ ይጠብቃል። ይህ አዲስ ነገር አይደለም፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲውዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ  ወዘተ ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋዎች ያላቸው አገሮች ናቸው።

ከዚህ በኋላ በአንድ አገር ለመኖር አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ አንድ ዓይነት የታሪክ አረዳድ፣ አንድ ዓይነት ኃይማኖት ወይም አንድ ዓይነት ባሕል መኖር የግድ የሚልበት አይሆንም። የየራስህ ቋንቋ፣ ታሪክና ታሪክ በመያዝ፣ በጋራ በሆኑ ነገሮች፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የአገር አንድነትና ግንባታ ነው የሚኖረው። በዚህ መንገድ ነገሮች ሁሉ አቃፊና አሰባሳቢ እንዲሆኑ በማደረግ፣ ብሄር ተኮር የሆኑ የተስፋፊነት ፍላጎቶችን በመግራት ቀስ በቀስ የብሄርተኝነት ስሜቱ እየቀነሰ፣ ከተማነት እየተስፋፋ የህዝብ ለህዝብ እንቅስቃሴ እየጨመረ ሲሄድ በህገ መንግስታዊነት ላይ የተመሰረተ ሲቪላዊ ብሄርተኝነት (Civic Nationalism) እያበበ ይመጣል።

አንድ ወንድማችን እንዳለው፣ በፊት ያልተመረመረ ድፍን የሆነ የአንድነት ንቃት (Unconscious unity) ነው የነበረን። እኛ የተለየ ማንነት፣ ቋንቋና ባህል አለን የሚል ክፍሎች መጡ፤ በዚህ መስመር ተደራጅተው፤ ተዋግተው ድል አድርገው ስልጣን ያዙ።  አሁን ልዩነቶችን ብቻ መሰረት ያደረገ ስርዓት ነው ያለን። ከነ ብዙ ችግሩ የአገር ግንባታው በሌላ መልኩ ለማስቀጠልም እየተሞከረ ነው ያለው። ያዋጣ አያዋጣ በደንብ ተሞኩሮ አልታየም። ወይ ወደ ተሻለ አስተማማኝ ህብረ ብሄራዊ አገርነት ወይም ደግሞ ተመልሶ ወደ መፈረካከስ ሊያመራ ይችላል። ሁለተኛው እንዳይሆን በደንብ ማሰብ፣ ለእኩል ተጠቃሚነት፣ ለአብሮነትና ለመልካም ወንድማማችነት ተግቶ መስራት ያስፈልጋል።

ከዚህ በኋላ ማድረግ ያለብን ወደኋላ ወደ ድሮው አስተሳሰብ ወይም ስርዓት መመለስ አይደለም፣ ምንድነው አንድ የሚያደርገን፣ የጋራ ጥቅማችንና ፀጋችን ምንደነው? እንዴት ነው በአንድ ላይ በፍቅር በወንድማማችነት በመደጋገፍ መኖር የምንችለው ወደሚል በእውቀት ላይ የተመሰረተ አንድነት (Unconscious unity) ነው መምጣት ያለብን። አገር ማለት ደግሞ የሆነ መለኮታዊ ነገር አይደለም፤ በምድር ላይ በጋራ የምትኖርበት ቤት ማለት ነው። ስለዚህ ለሁሉም እንዲመች ሆኖ መግንባት ነው አለበት፣ ለሁሉም የማይመች ከሆነ ደግሞ ፈርሶ እንዳዲስ ሰፋ አድርጎ የተለያዩ ክፍሎች እንዲኖሩት አድርጎ ወይም ለያይቶ መገንባት ነው እንጂ ምንም አማራጭ እንደሌለ ሁሉ እየተናቆሩ መኖር መፍትሄ አይደለም። ይህ ፅድቅ አይሆንም። ምክንያቱም አገር ማለት በምድር በአፀደ ስጋ የምትኖርበት እንጂ ስትሞት ገነት የምትገባት ቦታ አይደለም።

በዚህ ጉዳይ ላይ በሰከነ መንገድ እንወያይበት፣ መራገሙና መወጋገዙ መፍትሄ አይሆንም።

 

ግንቦት 30/2010 ዓ.ም.