ሰሞኑን ጠ/ሚ አብይ ሀገራችን የራሷ የባህር ሃይል እንደሚኖራት መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡ በእርግጥ ዶ/ር አብይ የባህር ሃይል ስለማቋቋም በይፋ የተናገሩት አንድ ተጨባጭ ምክንያት ቢኖራቸው ነው፡፡ እንደ እኔ ግመት ዶ/ር አብይ አቡ ዲያቢ ላይ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ ኤርትራ ውስጥ የጦር ሰፈር መገንባት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከባህር ጠረፍ ላይ የጦር ሰፈር ከሌለ የባህር ሃይል ማቋቋም ትርጉም የለውም፡፡ ጅቡቲ ላይ ፈረንሳይና አሜሪካን የጦር ሰፈር አላቸው፡፡ በሶማሊላንድ በኩል የተሻለ ዕድል ቢኖርም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ውስን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የኢትዮጲያን ባህር ሃይል መልሶ ማቋቋም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሚኖረው ቀይ ባህር ላይ የጦር ሰፈር መገንባት ሲቻል ነው፡፡
በመሠረቱ የኢሳያስ አፈወርቂ መደራደሪያ ሃሳብ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጠኝነት “የአልጄርሱን ስምምነት ተቀበሉና ባድመን አስረክቡን” የሚል ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር አብይ ደግሞ የራሱን መደራደሪያ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ የመጀመሪያው የአሰብ ወደብን መጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን፣ የአሰብ ወደብን መጠቀም ጥቅሙ ከኢትዮጲያ ይልቅ ለኤርትራ ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከአንደ የወርቅ ማውጫ በአመት የሚያገኘው $100ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጲያ የአሰብ ወደብን ብትጠቀም በአማካይ በአመት $300ሚሊዮን ዶላር ያገኛል፡፡
በነገራችሁ ላይ በዚህ አመት በሱዳን በኩል የመጣች ኤርትራዊ እንደነገረችኝ ከሆነ ኤርትራ ከተገነጠለች ወዲህ አስመራ ውስጥ የተገነቡትን ህፃዎች ብዛት 4 (አራት) ብቻ ናቸው፡፡ አስመራ ከተማ ስሟ እንጂ ትልቅ ስፋቷ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከተማዋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ብትለኳት 7 ኪሎ ሜትር ናት፡፡ ስለዚህ የከተማ እድገትና መስፋፋት ብሎ ነገር የለም፡፡ በመጨረሻ አስመራ ውስጥ ስንት ፋብሪካ ያለ ይመስላችኋል? በደንብ የሚንቀሳቀሱት ሁለት (2) ፋብሪካዎች ሲሆኑ እነሱም አንድ ቢራ ፋብሪካ እና አንድ ውሃ ማሸጊያ ናቸው፡፡ ኢትዮጲያ የአሰብ ወደብን ብትጠቀም በአንድ አመት አስመራ ውስጥ ስንት ህንፃና ፋብሪካ እንደሚገነባ አስባችሁታል?
አሁን የጅቡቲ ወደብን እንደምንጠቀመው ወደፊት የአሰብ ወደብን ከፍለን ነው የምንጠቀመው፡፡ ስለዚህ የአሰብ ወደብን መጠቀም ለኢትዮጲያ መደራደሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ “አሰብ ወደብ ላይ የጦር ሰፈር ማቋቋም” የሚለውስ? ይሄ ትክክለኛ መደራደሪያ ነው፡፡ ኤርትራ ይህን አልቀበልም አትልም፡፡ እንኳን ለእኛ ለግብፅና ኳታርም ፈቅዳለች፡፡ ኢሳያስ የሚፈልገው የውጪ ምንዛሬ የሚያገኝበት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የትኛውም ሀገር ሊሰጠው ከሚችለው የገንዘብ ድጋፍ ከኢትዮጲያ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚያገኘው ይበልጣል፡፡
ከዚያ በተጨማሪ የኢትዮጲያ ህዝብና መንግስት ከኳታርና ግብፅ ይቀለዋል፡፡ ምክንያቱም ከፖለተካ አንፃር የአረብ ሀገራት ኤርትራን መጠቀሚያ የሚያደርጏት ሲሆን ከኢትዮጲያ ጋራ ግን የጋራ ጥቅም ይኖራታል፡፡ ኢትዮጲያ አሰብ ላይ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም መፍቀድ በኢኮኖሚ ሆነ በፖለቲካ ረገድ ለኤርትራ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ይመስለኛል ዶ/ር አብይ “የባህር ሃይል አናቋቁማለን” ብሎ በተናገረ ማግስት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጄርስ ስምምነትን የተቀበለው፡፡
እነአንቶኔ የድንጋይ ፍትፍት የሞላትን ባድመ “ሄደች፥ ቀረች” እያሉ ይቃዣሉ፡፡ እኛ ቀይባህር ላይ የቀድሞውን የኢትዮጲያባህር_ሃይል መልሰን ስለማቋቋም እያሰብን ነው፡፡ ለማንኛውም ይህን በቀድሞ የኢትዮጲያ ባህር ሃይል (Ethiopian Navy Force) ባልደረባ የተዘጋጀ የቪዲዮ ቅንብር በመጋበዝ እሰናበታለሁ፡፡
አሰብ ወደብ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የጦር ሰፈር ሊገነባ ነው።
በአቡዳቢ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መወያየታቸውን ተከትሎ በሀገራቱ ዙሪያ አዳዲስ ለውጦችን በማየት ላይ እንገኛለን።
ሁለቱ መሪዎች በተስማሙት መሰረት ኢትዮጵያ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ባድመን ጨምሮ አስራ ሰባት አወዛጋቢ የነበሩትን ወረዳዎች ለኤርትራ ለማስረከብ የተስማማች ሲሆን ኤርትራ በበኩሏ የአሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ በክፍያ እንድትጠቀምበት እንዲሁም የባህር ሀይል ጦር ሰፈር እንድትገነባበት ተስማምተዋል ፤ በስምምነቱ መሠረት ባህር ኃይሉ በአከባቢው በሚገኘው ኢምሬት የጦር ኃይል ቁጥጥር እንዲያደርግ ዋስትና ከኤርትራ አግኝቷል።
በቀጣይም የኤርትራ በጎ ፈቃደኝነት ከታከለበት በፖለቲካ በኢኮኖሚ እና በሌሎችጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል ። (ቆንጂት ስጦታው )