
ወደ መቶ ሺ የሚጠጉ ሰዎች ያለቁበት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ቁርሾን ይሽራል ተብሎ የተገመተው የአልጀርስ ስምምነት የነገሮችን ውል አጥፍቶ ለባሰ መቆራቆዝ ሰበብ ሆኖ ቆይቷል። በአልጀርስ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ያልተስማሙትን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይቀይራል የተባለለት ውሳኔ ግን ከሰሞኑ ተሰምቷል።
የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል። በዚህም መሰረት ባድመን ጨምሮ ለኤርትራ የተወሰኑ የድንበር ቦታዎችን ኢትዮጵያ ለኤርትራ ታስተላልፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውሳኔው ማግስት በነበረው የፀረ – ሙስና ጥምረት ላይ ተገኝተው ፣ “በአስመራ እና አዲስ አበባ መካከል አውቶቢስ፣ ባቡር፣ ኢኮኖሚ እንዲስፋፋና ወንድማማች ህዝቦች እንዲገናኙ ለማድረግ ቀዳሚውን ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ያስፈልጋል” ሲሉ የውሳኔውን ቀናኢነት ለማስረዳት ሞክረዋል።
ሆኖም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ ከጠንካራ ትችት አላመለጠም። የአልጀርስ ስምምነት በተፈረመበት 1993 ዓ.ም. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት የአሁኑ መድረክ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ውሳኔው ካላስደሰታቸው መካከል አንዱ ናቸው።
“በዚህ ጉዳይ ላይ የፓርላማ አባል በነበርንበት ዘመንም ቢሆን አቋም ይዘንበታል። የአልጀርሱ ስምምነት የኢትዮጵያዊያንን ጥቅም የማያስከብር ስለሆነ እንደገና ለድርድር ሊቀርብ ይገባል የሚል አቋም ነበር (በወቅቱ) የወሰድነው፣» ሲሉ የሚያስታውሱት አንጋፋው የፖለቲካ ሰው፣ አሁንም ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው እና የተሰጠው ውሳኔ ኢትዮጵያዊያንን የሚያስማማ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።
በትግራይ ክልል ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው አረና ትግራይ ሊቀ-መንበር አቶ አብርሃ ደስታ በበኩላቸው ፓርቲያቸው አሁን በተሰጠው ውሳኔ እንደማይስማሙ ለቢቢሲ ይናገራሉ። አቶ አብርሃ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔው ላይ የደረሰበትን ሂደትም ይነቅፋሉ፣ «ህዝብን ማማከር ይገባ ነበር፣ ከፓርቲዎች እና ከሌሎች አካላት ጋር ንግግር መደረግ ነበረበት። ጉዳዩ አንድን ክፍል ዘግቶ በሚደረግ ስብሰባ የሚፈታ አይደለም። የተወሳሰበ ነገር አለበት፣» በማለት።
ሊቀመንበሩ አክለውም፣ “ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበትን” መሬት በዚህ ሁኔታ አሳልፎ በመስጠት የሚገኝ ሰላም እንደሌለ በማንሳት አስጠንቅቀዋል።
የውሳኔው ማግስት በፖለቲከኞች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በነዋሪዎች ዘንድም ቅሬታን ፈጥሯል። ይሄንን ቅሬታ ወደ አደባባይ በመውጣት ለመግለፅ ከተሰናዱት መካከል ደግሞ አንዿ በትግራይ ክልል እና ኤርትራ መካከል ላይ የምትገኘው የኢሮጵ ወረዳ ናት። አቶ ወ/ማሪያም ብስራት የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ህዝቡ ማንነቱን ለማረጋገጥ እስከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደረሰ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ፣ «የሁለቱንም መንግስታት እና የተባበሩት መንግስታት ይህን ጉዳይ በማየት መፍትሄ እንዲሰጡን እየታገልን ያለን ሰዎች ነን። ለእኛ ይህ ጉዳይ (የሞት እና ህይወት ጉዳይ ነው) ውሳኔውን አልተቀብልነውም፣ ተቃውመነዋል» ሲሉ ለቢቢሲ ምሬታተቸውን ይገልፃሉ።
ለኤርትራ ተላልፋ እንደምትሰጥ እየተነገረላት ያለችው የባድመ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ገ/መድህን በበኩላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ሲሉ ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈሉ በማውሳት የአሁኑን ውሳኔ እንደተከፉበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ጥላሁን «ባድመ ለድርድር የምትበቃ አይደለችም። ከድሮ ጀምሮ በትግራይ ክልል ስር ስትተዳደር የነበረች ስፍራ ናት። አሁን ማን ድርድር ውስጥ እያስገባት እንዳለ አይገባንም» ይላሉ።
በአልጀርሱ ስምምነት ማግስት የተወሰነውን ውሳኔ የማይቀበሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ ደግሞ «የሚያዋስነን መረብ ወንዝ ነው፣ ከመረብ ምላሽ የኛ ቦታ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ሰላም ይፈልጋል። ሰላም ግን በሁለቱም ህዝቦች ፍላጎት እንጂ ከአንድ ወገን በሚመጣ ብቻ ፍላጎት አይሰምርም» ብለዋል።