
የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ብሔርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ሳቢያ ከመፈናቀል አፋፍ ላይ ያሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር አባላትን ለመጠበቅ ጣልቃ እንዲገባ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።
አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት እንደጠቀሰው በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሰዮ ወረዳ በዚህ ሳምንት በቡድን የተሰባሰቡ የአካባቢው ወጣቶች የአማሮችን ቤት መክበብ፣ ድብደባና የንብረት ዝርፊያ ፈፅመዋል ሲል ይከሳል።
በተጨማሪም ከጥቅምት ወር አንስቶ ቢያንስ 20 የሚደርሱ አማሮች በእንዲህ ያሉ ጥቃቶች መገደላቸውን ገልፆ፤ ባለስልጣናት ድርጊቱን ለማስቆም ምንም እንዳላደረጉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ብሏል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በብሔራቸው ምክንያት የጥቃት ኢላማ ሆነው ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ በተቃረቡት የአማራ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚፈፀሙትን የጭካኔ ጥቃቶች ለመከላከል እርምጃ መውሰድ አለበት” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የታላላቅ ሃይቆች ዳይሬክተር የሆኑት ጆዋን ኒያኑኪሰ ተናግረዋል።
ሪፖርቱ ጨማሮም 1400 የሚደርሱ የአማራ ቤተሰቦች ጥቃት ይፈፀምባታል በተባለችው የሰዮ ወረዳ ውስጥ የቀሩ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት ቄሮና ፎሌ በተባሉት የኦሮሞ ወጣቶት ቡድኖች በተደጋጋሚ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ሳቢያ ከሦስት አስርታት በላይ ከኖሩበት አካባቢ ተገደው ሊወጡ እንደሚችሉ ስጋት አድሮባቸዋል።
“ለልጆቻችን ህይወት እንሰጋለን። መንግሥት ጣልቃ ካልገባ በስተቀር አካባቢውን ለቀን ለመውጣት ያለንን ንብረት አዘጋጅተናል” ሲሉ አንድ ነዋሪ ለአምነስቲ ተናግረዋል።
ነዋሪው ጨምረውም ምንም እንኳን እየተፈፀሙ ስላሉት ጥቃቶች ማህበረሰቡ ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን ለወረዳና ለዞን ባለስልጣናት ቢያቀርቡም ምንም መፍትሄ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
ስለሪፖርቱ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ተጠይቀው ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በአሁኑ ጊዜ ያለውን እውነታ የማያሳይ መሰረተ-ቢስ ሪፖርት ነው” ብለዋል።
አሁን ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለናል የሚሉት ሰዎች በጥቅምት ወር በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ስጋት ውስጥ ገብተው ከቦታው የሄዱ እንደነበሩና ከመካከላቸውም የተወሰኑት እንደተመለሱም ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል።
”አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ላይ በተጠቀሰው አካባቢ እንዲህ ያለችግር መከሰቱን የሚገልፅ ምንም አይነት ነገር አልሰማሁም” ያሉት ዶክተር ነገሪ በክልላቸው ከየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ የመጣን ሰው ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንዲፈፀም የክልሉ መንግሥት እንደማይፈቅድ ተናግረዋል።
የአምነስቲ ዘገባ እንዳመለከተው በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋና ኢሉ-አባቦራ ዞኖች ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት የጀመረው በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነው።
በተጨማሪም በቤኒሻንጉል ክልል ሺናሻ ዞን ውስጥ የሚኖሩ አማሮች ተመሳሳይ ጥቃት አጋጥሟቸዋል። በዚህም ቢያንስ 20 የሚደርሱ አማሮች በሚያዚያ ወር ውስጥ በተፈፀሙ ጥቃቶች ተገድለዋል ብሏል የአምነስቲ ሪፖርት።
SOURCE – BBC/AMHARIC