ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሱኝ ነገሮች ሁለት ናቸው፤ አንደኛው ኢሕአዴግ ዋና ዋና የሚባሉ የሕዝብ ሀብቶችን በከፊል ወደ ሕዝብ ይዞታነት ለመቀየር ያወጣው ውሳኔና ሁለተኛ ደግሞ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ THE ETHIOPIAN ECONOMY – AT A CROSS ROAD ብለው የጻፉት ባለ25 ገጽ ሞኖግራፍ ነው፡፡ በዚህ ላይ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ነው፤ እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ የመፍትሔ ሐሳብ የምለውን ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ ድቀት፣ የብድር መብዛትና የሜጋ ፕሮጀክቶች መና ሆኖ መቅረትን በገለጹበት ጽሑፍ መፍትሔ ያሉትንም ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ቋት ባዶ መሆን በቻ ሳይሆን የአገሪቱ ብድር ከ24.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ፣ የውጭ ብድር ይመልሳሉ ተብለው የታሰቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈቅ የሚል እምርታ አለማሳየታቸው፣ የስኳር ፕሮጀክቶች መክሰራቸው፣ በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የኅዳሴ ግድብ ከዐሥር ዓመት በላይ መቆየቱ፣ ከዚህ አልፎ የውጭ ብድር የወለድ መጠን 1.8 ቢሊዮን መድረሱ ወዘተ የአገሪቱ ኢኮኖሚን ከሚገባው በላይ ማንኮታኮቱን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ጽሑፋቸው አቶ ኤርሚያስ የመፍትሔ ሐሳብ ብለው ያቀረቡት 5ቱን ታላላቅ የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል ቢዛወሩ በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 50 ቢሊዮን የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል አስልተዋል፡፡ 5ቱ ታላላቅ ወደ ግል እንዲዛወሩ ያሏቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ባሕር ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሎኮምና የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ናቸው፡፡ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደ ግል የሚዞሩትን ተቋማትና የሚያስገኙትን ጥቅም ሲዘረዝሩ የማስተላለፊያ መንገዱን አንድም ሆን ብለው አሊያም አስፈላጊነቱን ስላላመኑበት ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ በተለይ ትልልቆቹ የሕወሓት /ኢፈርት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ሼሮቹን ገዝተው ቢወስዷቸው ከድጡ ወደማጡ እንደሚወስድ ለአቶ ኤርሚያስ ጠፍቷቸው አይመስልም፡፡ ከአገራዊ ሀብት ወደ አንድ ጎሳ ወይም ብሔር ሀብትነት ወርደው ጦሳቸው የበዛ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ገዥው ቡድን ኢሕአዴግም የአቶ ኤርሚያስን የመፍትሔ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ የተቀበለ በሚመስል መልኩ ዋና ዋና የሚባሉትን ተቋሟት ማለትም ቴሌኮም፣ አየር መንገድና ባሕር ትራንስፖርት በከፊል ወደግል የሚያዞር ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የሕዝብን ሀብት ወደ ግል ማዞር የተለመደ ነው፤ ነግር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄና ግልጽነትን ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግልጽነትና ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ወደ ግል ማዞር የሚፈጥረው ቀውስ በቀላሉ ልንወጣው የምንችለው አይሆንም፡፡ ከኢትዮጵያ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው የሶብየት ሕብረት ስትፈርስ የነበረውን ይመስላል፡፡
በሶብየት ሕብረት ከ45000 በላይ የመንግሥት ተቋማት ነበሩ፡፡ የሶብየት ሕብረት ሲፈርስ እ.ኤ.አ ከ1992-94 ባለው ጊዜ በሩሲያ ዋና ዋና የሚባሉ የመንግሥት ተቋማት ወደ ግል ተዛውረዋል፡፡ ሒደቱም ለሁሉም ዜጎች እኩል የመግዣ ኩፐኖች (ቮቸር) ከታደለ በኋላ መግዛት ፍላጎት ያለው ዜጋ በተሰጠው ኩፐን ሲገዛ መግዛት የማይፈልገው ደግሞ የመግዣ ኩፐኑን መግዛት ለሚፈልግ አካል ወይ ይሰጠዋል አሊያም ይሸጣል ማለት ነው፡፡ በጊዜው ታላላቅ በሚባሉ ድርጅቶች ኢኮኖሚው በብቸኝነት (ሞኖፖሊ) እንዳይያዝና ብዙ አክሲዮን መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ ኩፐኑን መግዛት ከማይፈልጉ ወይም ከማይችሉ ዜጎች ገዝተው ሲወስዱ ድሃውን ስለሚያጠናክሩ ጥቅሙ የበዛ ነው በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ግልጽነት ይጎድለው ስለነበር ብዙ የአይሁድ ድርጅቶች ኩፐኖቹን ቤት ለቤት ሰበሰቧቸው፡፡ በዚህም ትልልቅ የሚባሉትን ድርጅቶች ወዲያውኑ በቁጥጥራቸው ስር አዋሏቸው፡፡
እኛስ ከሩሲያ ምን እንማር?
የሩሲያን ችግር ላለመድገም በእኛ የሚከተሉት ጉዳዮች መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡
1. ከሁሉም መቅደም የሚኖርበት ጉዳይ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ሪፍርም ነው፡፡ ዘላቂና የተረጋጋ ፖለቲካዊ አካባቢ ሳይፈጠር የአገር ሀብትን ለተወሰነ ቡድን ማስተላለፍ ታላቅ ኃላፊነት መጉደል ነው የሚሆነው፡፡ በፖለቲካዊ ለውጡ በነጻ የመደራጅት፥ የመናገርና፥ የፕረስ ነዓነት መረጋጋጥ ብሎም የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት መደራጀት የግዴታ ነው፡፡
2. እንደ ኢፈርት፣ ጥረትና ዲንሾ የመሣሰሉ ባለቤትነታቸው የማን እንደሆኑ በግልጽ የማይታወቁ ተቋማት ጥረት ያለ መረጃ ለሕዝቡ ቀርቦ እኩል ወደ ግል መዛወር ይኖርባቸዋል፡፡ የኢንዶውመንት ተቋማቱ ባለቤትነታቸው የክልል መንግሥታት ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ ወርሦ እኩል ወደ ግል እንዲዞሩ ሒደቱ አብሮ ቢጀመር የኢኮኖሚ አለመመጣጠኑን ያጠባል፡፡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ይፈጥራል፡፡
3. ከመንግሥት ተጽእኖ ነጻ የሆነ በባለሙያዎች የሚመራ ወደግል ማዘወርን የሚሠራና የሚቆጣጠር ገለልተኛ ኮሚሺን ሊቋቋም ይገባል፡፡ ኮሚሽኑ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ መሆን ይኖርበታል፡፡
4. ሌላው ወደ ግል የሚዛወሩት የሕዝብ ተቋማት ግምት በትክክል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በመቀጠል ሀብቱ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመካፈል የአንድ አክሲወን ዋጋ መተመን ይቻላል፡፡ የተተመነውን የአክሲዎን ዋጋ መግዣ ነጻ የመግዣ ኩፐኖች እንደ ምርጫ ካርድ በቀበሌ ለሁሉም ዜጎች ማደል፡፡ መግዛት የሚፈልጉ ዜጎች በተሰጣቸው ኩፐን መሠረት አክሲዎን ይገዛሉ፤ የማይችሉ ደግሞ የመግዣ ኩፐኑን መግዛት ለሚችል ሰው አሳልፈው መስጠት ወይም መሸጥ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ዜጎች ኩፐኑን አሳልፈው ሲሰጡ ወይም ሲሸጡ በትንሹም ቢሆን ድሃ የኅብረተሰባችን ክፍል በተዘዋዋሪ የደጎምን ሲሆን በሌላ በኩል በሽያጭ ወቅት መንግሥት አነስተኛ ታክስ ገቢ ሊያገኝ ይችላል፡፡
በተጨማሪም ሀብት በአንድ ቡድን ወይም ጎሳ ወይም ባለሐብት ቁጥጥር ሥር እንዳይውል በግለሰብ የአክሲዎን ባለቤትነት በመቶኛ ከ3 ፐርሰንት እንዳይበልጥ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከዚሁ ላይ አብሮ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ተቋማቱ ወደ ግል ሲዛወሩ መጀመሪያ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ደካማ የሆኑት የመብራት ኃይልና የቴሌኮም ተላልፈው አየር መንገድ ግን በመንግሥት ሥር ቢቆይ የሚመረጥ ይመስለኛል፡፡
ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ችግሮ ሳይሰተካከሉ ገንዘብ ላለው ብቻ ተቋማቱን ወደግል ማዛወር ከሩሲያም የባሰ ቀውስ ውስጥ ያስገባናል፡፡
(ሙሉቀን ተስፋው)