ቤቴ መቅደሴን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፡፡ ሉቃስ ምዕራፍ 19 ቁ.46

መንደርደሪያ ፤  አስተያየት የመስጠትም ሆነ ትችትና ነቀፌታ የማቅረብ ባህላችን በአብዛኛው  በጎ ተግባርን አበረታትቶ ድክመትን ጠቁሞና ስህተትን ነግሮ ለመሻሻል የሚያልም አይደለም፡፡ ግለሰብንም ሆነ ተቋምን/ድርጅትን ስንደግፍ ነፋስ አይንካህ የምንል ነቀፌታችን ደግሞ መልካም ጎኖችን የማይመለከት በመሆኑ ጤናማ የመተቻቸት ባህል ማደበር አልቻልንም፡፡  እንደውም የምንወደው የምንደግፈው ነገ እድጎና ጎልብቶ ማየት የምንሻ ከሆነ እግር በእግር እየተከታተልን አስተያየታችን ልንለግሰው ይገባ ነበር፡፡ የሚሆነው ግን በተቃራኒው ሆነና የሚደግፉትን መተቸት ቀርቶ ሌሎች ሲተቹ የስድብ ጦር፣ የአሉባልታ ጎራዴ ስሎና የፍረጃ ጋሻ ይዞ መሰለፍ ነው የተለመደው ፡፡ ይህም እንደ በጎ ነገር ተለመደና ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በአብዛኛው ከውዳሴ ከጭብጨባና ሙገሳ በተቃራኒ የሆነ ነገር ለመስማት ጆሮአቸው፣ ለመቀበል ልቦናቸው ዝግጁ አይሆንም፡፡

Customer Management Tools
Everything You Need To Start Selling Start Your 30-Day Free Trial.

ስንደግፍ ስህተት ድክመት እንደማይታየን ሁሉ ሰንነቅፍም ምልካም ጎኖች አይታዩንም፡፡ ስለሆነም ነቀፌታችንም ሆነ ትችታችን ተቃውሞአችንም ሆነ ምክራችን ወደ ዳር የሚገፋ እንጂ ወደ መሀል የሚጎትት፤ የሚያራራቅ እንጂ የማያቀራርብ፣ ይበልጥ እልህ የሚያስገባ እንጂ የሚያለዝብ አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህ ነገረ ስራችን እስካሁን እንዳልበጀን ሁሉ ለወደፊቱም አይበጀንምና ትችታችንም ሆነ ነቀፌታችን እስከ ዛሬ ከመጣንበት መንገድ ወጣ ቢልና በእውነት ላይ ቢመሰረት  መልካም ነው፡፡ የትናንቱ ካልበጀን ዛሬም በዛው መቀጠሉ ለምን!

በተለይ ያልሆኑትና ናችሁ እየተባለ ባልሰሩት እየተሞገሱ ስህተትን አሳይተው ድክመትን አመላክተው ለመሻሻል በሚያግዙ ሳይሆን የሚናገሩትን ሁሉ ትክክል የሚሰሩትን ሁሉ እንከን የለሽ የሚተነፍሱትን ወርቅ በሚሉ ሰዎች እየታጠሩና እየታወሩ የት ይደርሳሉ ብለን ተስፋ ያደረግንባቸውን  ድርጅቶችንም ግለሰቦችንም አጥተናል፡፡ ይህን ተረድተን ለመውደድም ለመጥላትም ለመንቀፍም አትንኩብን ለማለትም ወዘተ ምክንያት የሚሆኑ ግላዊ ነገሮችን ሁሉ ወደ ጎን ብለን በእውነት ስለ እውነት እንደግፍ እንተች፡፡ ማንም ሰራው ማን  ትክክል የሆነውን ትክክል፣ ያልሆነውን ደግሞ አይደለም እንበል፡፡አነጋገራችን ለዛ ያለው ጽሁፋችን ከአሉታዊ ቃላት የጸዳ ቢሆንም መልካም ነው፡፡ “ ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ” የሚለው የቅዱስ መጽኃፍ ቃል ላስተዋለው ጥሩ ትምህርት ነበር፡፡(መጽሀፈ መክብብ 5.6)

በሌላም በኩል እውነት አርነት ያወጣችኋል ተብሎ የተጻፈ ሲሆን በተግባር የሚታየው ግን ሀሰት ያበለጽጋችኋል የሚል ያልተጻፈ ግን በብዙው ሰው አዕምሮ የሰረጸ ምድራዊ ቃል ያለ ነው የሚመስለው፡፡ የምትፈልጉትን ታገኙ ከምትሹት ቦታም ትደርሱ ዘንድ ብቸኛውና አቋራጩ የሀሰት መንገድ ነው፤ ትሄዱበትም ዘንድ ተፈቅዶላችኋል የተባለም ይመስላል፡፡ እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር የሚለው የአበው ብሂል ተዉኝ ልኑርበት በሚል መቀየሩ ደግሞ ለዚህ መስፋፋት መንገዱን ጥርጊያ ሜዳውን የማይጎረብጥ አድርጎታል፡፡

መንደርደሪያ ብዬ ብዙ ማለቴ የህዝብ አይንና ጆሮ ለሆነው ኢሳት አስተያየት መጻፍ ቀላል ሆኖ ስላልታየኝ ነው፡፡ እናም እንዴት ኢሳትን ብሎ ለቁጣ ሳይቸኮል ያነሳሁትን ጉዳይ እውነትነት እና እንዴትነት በርጋታ ማየት ቢቻል መልካም ነው እያልኩ አስተያየቴን ለዛሬ በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡ ጌታ ኢየሱስም ስለ እውነት እናንተ ዝም ብትሉ ድንጋዮች ይመሰክራሉ ያለውን አስታውሱልኝ፡፡

« ..ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ፣የማይታወቅም የተሰወረ ምንም ነገር የለም፡፡ (የሉቃስ ወንጌል ም.12 ቁ.2)

አስበን በቀጠሮ ሳይሆን ድንገቴ ያገናኘን ገደኛሞች እያወጋን ነው፡፡የወሬያችን ማእከላዊ ነጥብ ወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ በተለይ የአዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ተግባር ነው፡፡ በየራሳችን የእይታ አቅጣጫና የመረዳት አቅም የተገነዘብነውን እያነሳን እዛም እዚህም ስንረግጥ ኢሳት ዘንድ ደረስን፡፡ኢሳት ውስጥ የሚታየው የድጋፍና የተቃውሞ ክርክር ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በግልጽ የታየበት ነው፤ሁለቱም ወገን በየራሱ ለራሱ ትክክል ነው፤ተቋሙም አቋም ሳይዝ ጋዜጠኞቹ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ማድረጉ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ነው ወዘተ እያልን አወጣን አወረድን፡፡

በዚህ ግዜ ነበር አንዱ ሀብታሙ አያሌው ለውጡን ለመቃወም የሞራል ብቃት የመንፈስ ነጻት የሌለው ቢሆንም የሰዎችን ሀሳብን የመግለጽ መብት እናከብራለን እስካልን ድረስ  መብቱ ነው፣ኢሳት ለእሱ መፈንጫ መሆኑ ግን ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያበሳጫል አለ፡፡ እንዴት ለምን? ስንል ጥያቄ ሰነዘርን፤በፍጹም ኢሳት የእርሱ መድረክ መሆን አልነበረበትም ሲል አነጋገሩን ከረር አደረገው፡፡ እኮ ለምንና ስለምን ? ዝም ብሎ ተቃውሞ አሉባልታ ይሆናልና ፤ ይህን ለማለት ያበቃህን መረጃ ማስረጃ አምጣ ብለን ያዝነው፡፡

እኔ ሀብታሙን ከልጅነት ጀምሮ አውቀዋለሁ፤ ብሔረ ጽጌ አካባቢ አንድ ሰፈር ነው ያደግነው፤ካላቸኮላችሁ አንድ በአንድ እነግራችኋለሁ ሲል ሁለታችን አይን ለአይን ተጋጭተን  ቃል ሳይወጣን በስሜት ተስማማንና ቀጥል አልነው፡፡

ወዳጃችን ፣ ሀብታሙን ከግንቦት ሀያ ት/ቤት እስከ ኢሳት በረዥሙ ገለጸው፡፡ ምንም ሳንተነፍስ በጥሞና አዳመጥነውና ሲጨርስ ታዲያ ይህን ሁሉ ይዘህ እንዴት ዝም ብለህ ተቀመጥህ አልነው፡፡  ዝም አላልኩም የምችለውን አድርጌአለሁ፣ ከዚህ በላይ እኔ እንደሱ አንደበትም መድረክም የለኝም አለና አደረኩት ያለውንም ፡ ሀብታሙ አንድነት ገባ መባልን እንደሰማሁ ለኢ/ር ግዛቸው ስልክ ደውዬ ያስገባችሁት ሰው ማ እንደሆነ አውቃችኋል ወይ ብየ በዝርዝር ነግሬአቸው ነበር፡፡ ለመውደድ  ለመጥላት ግዜ የማይፈጀው ዲያስፖራ ሆይ ሆይ ማለት እንደ ጀመረም በቻልኩት መንገድ ለመንገር ሞክሬአለሁ አለን፡፡

ሀብታሙን በተወሰነ ደረጃ ባውቀውም ወዳጃችን የነገረን አይነት ሰው ነው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡የወዳጃችን ገለጻ ደግሞ በማስረጃ የቀረበ በመሆኑ ላለማመን የሚቻል አልነበረምና ስሜቱን አጋባብን፡፡ ይህን ሰምቼ ዝም ማለት ህሊናየ አልቀበል ብሎኝ ከሳምንት በላይ ሙግት ገጠምሁ፡፡በነጋ በመሸ የጥፋት ተባባሪ እየሆንክ ነው እያለ ጉንተላው አላስቀምጥ ሲለኝ ከህሊና ወቀሳ ትንሽ ማረፍ ብችል ብየ ይህችን ማስታወሳ ጻፍሁ፡፤

ቤቴ መቅደሴን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፡፡

ወዳጄ ቁጭቱን አጋብቶብን ነጋ ጠባ ህሊናየ ይህን ሰምተህ እንዴት ዝም ትላለህ እያለ ሲጠዘጥዘኝ “ ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፣እርሱም ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የወንበዴዎቸ ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው፡ ” የሚለው የመጽኃፍ ቃል  ነው ወደ አዕምሮየ የመጣው፡፡

ኢሳት የህዝብ አይንና ጆሮ ነው፡፡ ህዝብ ይህን በማመኑም ነው አቅፎና ደግፎ እዚህ ያደረሰው ፡፡ ይህ የህዝብ የሆነ ተቋም በስመ የወያኔ ተቀዋሚ የትናንት ማንነቱን ብቻ አይደለም በህዝብና በሀገር ላይ ያደረሰውን ጉዳት በማስመሰል ክህሎቱ ጋርዶ በምላሱ እየተከላከለ ሲተውንበት ሲታይ ቤታችን የእውነት መድረክ ነው እናንተ ግን የሀሰተኞች የሸፍጠኞች የአስመሳዩች መናኸሪያ አደረጋችሁት ማለት ብሎም መጠየቅ የህሊና ግዴታ ይሆናል፡፡

ከኢሳት የምጠብቀው፤

ወዳጄ በማስረጃና መረጃ አስደግፎ በአሳማኝ ሁኔታ የነገረንን በዝርዝር አለመጻፌ ለምን እንደሆነ ባለቤቶቹም አንባቢዎችም የምትረዱት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ነገሮች ወደ እዛ የሚገፉ ከሆነ ግን ያነሳሁት ጉዳይ የጥላቻ አሉባልታ ሳይሆን እውነት መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ሀ.ለ ብዬ አቀርባለሁ፡፡ ወደ እዛ ባይኬድ ግን እመርጣለሁ፡፡ እኔ ከሀብታሙ ጋር አይደለም ጸብና ፍቅር ትውውቅ የለኝም፡፡ ስለሆነም የኢሳት ማኔጅመንት..

1-የሚባለውን ነገር ከሀ-ፐ እናውቀዋለን፡ የነበረው ካለው ይበልጥ ሚዛን የማይደፋ በመሆኑ ነው የተቀበልነው ማለት፣

2-የምናውቀው ነገር የለም እናጣራለን፣ለዚህ የሚሆን መረጃ በዚህ በኩል አቀብሉን ብሎ አድራሻ መስጠት

3-በዝምታ ማለፍ፡፡ ሶስተኛው  ለኢሳትም ለሀብታሙም ቤታችን ለማይገባቸው ሰዎች እየዋለ ነው ለሚሉም አይበጅምና ኢሳት ይህን ምርጫው ባያደርግ መልካም ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ አይነት አስተያየቶችን  ከተጠቃሾቹ ግለሰቦች ጋር ባላችሁ ቅርበት ምክንያት ለንባብ ለማብቃት የማትደፍሩ ዌንም የማትፈልጉ የድረ-ገጽ ባለቤቶች አንድም እንታገልለታለን የምትሉትን ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት መርህ እየጣሳችሁ መሆኑን አንድታጤኑት ሁለትም ለግለሰቦቹ እየጠቀማችኋቸው እንዳልሆነ እንድትረዱት ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ከፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም አዳፍኔ መጽኃፍ አንድ አረፍተ ነገር ተውሼ ላብቃ ፡፡ “በዋናነት የመክሸፍ ምንጭ ትናንትና  ነገን አለማሰብ ነው፣ የወጣነውን ዳገትና የወረድንበትን ቁልቁለት ለይተን አለመረዳት፣ ዳገቱን እንዴት እንደ ወጣንና ቁልቁለቱን እንዴት እንደወረድን በትክክልና በእውነት አለመገንዘብ ናቸው፡፡ ክብርንና ኩራትን ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብና ሳንመዝን ለማይገባው እንሰጣለን፤ውጤቱም የሠራው እየተረሳና እየኮሰሰ ያልሠራው እየተወሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤ የተገፋው ያንጎራጉራል፤እናት  ኢትዮጵያ  ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡ እያለ