በአስፋ እንደሻው (ለንደን)*

ዶ/ር አቢይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተመረጠ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚቀርቡበት ጥያቄዎች የተለያዩ ነበሩ፡፡ (1) መቼ ነው የራሱን ሚኒስትሮች የሚሾመው? (2) መቼ ነው ስራ የሚጀምረው? (3) ለምንድነው እስረኞችን በሙሉ የማይፈታው? (4) መቼ ነው በሙስና የተጨማለቁትን ሁሉ እየለቀመ እስር ቤት የሚያስገባቸው? ከነዚህ የከበዱት ጥያቄዎች ደግሞ (5) መቼ ነው የጸጥታውንና የመከላከያውን ዘርፎች በጁ የሚያስገባው? (6) መቼ ነው የህዝቡን በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚጀምረው? መቼ ነው…?

ብዙዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ስለተመረጠ ብቻ ወዲያው ስልጣኑን ተጠቅሞ አገሪቱን ያስተካክላታል ብለው አስበው ነበር፡፡ የተማሩ የሚባሉት ጭምር፡፡ ሁሉም ሊገነዘቡት ያልቻሉት ግን የአቢይ ስልጣን ላይ መውጣት የጉዞው የመጀመሪያ እርምጃ ማለትም እግሩን ቤተመንግስት ለማስገባትና በወንበር ላይ ለመቀመጥ ያስቻለው ድርጊት እንጅ ስራ ለመስራት የሚያበቃው አልነበረም፡፡ ምናልባት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጀምሯቸው የነበሩ ተራ ነገሮች ወይም የየእለት የጽ/ቤቱ ተግባሮች እንዳይደናቀፉ ፊርማውን መስጠት ችሎ ይሆናል፡፡ ከዚያ በላይ አንዳችም ትእዛዝና ቀላጤ ለማውጣት ሆነ በስሩ ያሉትን ሚኒስትሮችና ሰራተኞች እንዲያከናውኑለት የመጠየቅና ማስፈጸም ስልጣን አላገኘም፣ አልነበረውም፡፡ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚገምተውን በድፍረት ወረቀት ላይ አስፍሮ ለበታቾቹ ቢሰጣቸው እምቢ አንቀበልም ባይሉትም (ሞክሮም ይሆናል) እሱ ለቦታው ባይተዋር ስለሆነና መዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ የጠባብ ቡድኖች አባሎች (በተለይ ህወሃቶች) ዞር በል ሊሉት ስለሚችሉት ዝምታን መርጦ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሮች መስመር እስኪይዙ! እስከዚያው ግን በሱ ስም ይህን አደረገ፣ ያንን ወሰነ እየተባለለት ሰነባበተ!!

ጉዳዩን ከመሰረቱ ስናየው አቢይ ወደስልጣን የመጣው ከጓደኞቹና አባሪዎቹ ጋር ሆኖ ኢህአዴግን ለማሻሻል ይሁን ለመለወጥ ካደረጉት ጥረት ጋር በተያያዘ አኳኋን ነው፡፡ ህዝቡ ያገሪቱን አገዛዝ እያራገበ በየትም ቦታና ሰአት መንቀሳቀሻ እያሳጣ ስለሄደ በሃይል ከመጠቀም ሌላ የሚያደርጉት ጠፍቶባቸው ሲናወዙ የነበሩት የህወሃት መሪዎች የሱን መመረጥ እንደውድቀታቸው ተመልክተው ከማሰናከል ወይም ከዚያ የከፋ ነገር ከማድረግ ይልቅ ቤተ መንግስት ገብቶ የት እንደሚደርስ እናያለን በሚል መንፈስ ለቀቅ ያደረጉት ይመስላል፡፡ በተመረጠ በመጀመሪያው ሰሞን በነሱ ሙሉ ቁጥጥር ስር ያሉት የመንግስትም ሆነ የግል የዜና አውታሮች የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ንገግሮችና ድርጊቶች እየተከታተሉ ማስተጋባት እምቢ ብለው ባንድ ወይም ሁለት መስመር ብቻ ይጠቅሱት ነበር፡፡ ለውጭ ዜናዎችና መሪዎች ከሚሰጡት ስፍራና ርዝማኔ ጋር ሲተያይ ምን ያህል እንደተደናገጡና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደዞረባቸው አመልካች ነበር፡፡ አንደበተ ርቱእና ውብ አገላለጽ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳያቋርጥ እያከታተለ የሚያዘንበው ንግግር ግን በመንግስቱ መገናኛዎች ቢከለከልም በማህበራዊ መድረኮች አማካይነት ባለም ዙሪያ እየተሰራጨ ሲሄድ እነሱም ከምንተፍረታቸው ማስተጋበት ጀመሩ፡፡ ባገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያካሂዷቸው ውይይቶችና ጫወታዎች ያንኑ ዱሮ የሚታወቀውን አስቀድሞ ቀድተው ያስቀመጡትን መደጋገም ብቻ ስለነበር እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸው?  አዲስ ሁኔታ መፈጠሩን አልሰሙምን? ያስብል ነበር፡፡

ባጭሩ የመንግስት መገናኛ አውታሮችና ከህዝብ እይታ መሸሸግ የጀመሩት ያገሪቱ እውነተኛ ገዥዎች ወይም አምባገነን መሪዎች ያቢይን አዲስ ክስተት በውስጥ ለውስጥ አሰራራቸው አፍነው፣ አቀጭጨው፣ መላወሻ ለመንሳት ቢሞክሩም አቢይ በየቀኑ እያየለባቸው ሄደ፡፡ በተለይ ህዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ ችሎ እያንዳንዷን ካፉ የምትወጣ ቃሉን እየተጠባበቀ የሚሄደው ሰው በርክቶ ፈረንጆቹ ሳይቀሩ ላገሪቱ አዲስ ተስፋ እንደፈነጠቀላት ማውራት ጀመሩ፡፡ ተራው ህዝብ ግን “አይ ያሰሩት ይሆን ዎይ?” የሚል ጥርጣሬያቸውን እየገለጹ ብዙው በጸሎት፣ በጎዳናና በቡና ላይ ወግ መከተል ጀመረው፡፡ የህወሃት የበላይነትና በአገዛዙ ላይ ያበጀው ማነቆ እንዳለ ሆኖ፡፡

ያገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚባሉት ሳይቀሩ ለአቢይ አዳናቂና ቀስ ቀስ እያሉ ደጋፊ እየሆኑ በመምጣታቸው መሰረታዊ በሆኑት ያገሪቱ ችግሮች አንጻር ትልቅ ፈተና ተደቀኖባቸዋል፡፡ አቢይና ጓደኞቹ ኢህአዴግን ከውስጥ ለመለወጥ ወይም ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት ከመደገፍ ወይም አዲስ ነገር እንዳላመጡ በመቁጠር እንደዱሮው የጅምላ ጸረ-ኢህዴግ ትግል ከመቀጠል አንዱን መምረጥ ይገደዳሉ፡፡ ህወሃት እያፈገፈገ፣ አንዲያውም ድምጹን አጥፍቶ የነአቢይን ሁኔታ እየተከታተለ አማራጭ ስልት እየፈለገ እያለ አቢይ መቀሌ ላይ ከፍተኛ የብልጠት ስራ አከናወነ፡፡ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ምናልባት በመጎዳት ይበልጥ እንደሆነ እንጅ በሃገር ፍቅር፣ ላገሩ በመሞት፣ ከሌላ አካባቢ ለሚመጣው ህዝብ በሚያደርገው መስተንግዶ ምንም እንደማያንስ፣ በራሱ ቋንቋ አናገረው፡፡ መቀሌ የተሰበሰበው ሆነ በቴሌቪዥን የሚከታተለው ህዝብ ባልጠበቀው አኳኋን በትግርኛ ቋንቋ እያሽሞነሞነ ሲያሽበለብላቸው እንዴት አይወዱት? ህወሃት በደጃፉ ላይ ተረታ! የራሴ ነው ብሎ የሚፎክርበት ህዝብ እየተነሳ የህወሃቱ መሪ አይኑን አፍጥጦ እየታዘባቸው አንተ የምታደርግልንን ንገረን እኛ በከንቱ ሰሚ አጥተን ስንጠብቅ ኖርን፣ የመቀሌ ውሃ፣ የአክሱም ውሃ… ይኸና ያኛው ለዘመናት ይሰራላችኋል እየተባልን በመከራ ኖረናልና የመፍትሄ ያለህ? አሉት፡፡

የአቢይ የመቀሌ ድል ትልቁ ውጤት አቢይ በትግራይ ህዝብ ላይ እምነት እንዳለው፣ አገሪቱን ለማስተካከል ለተጀመረው አዲስ ትንቅንቅ ያለማወላወል እንደሚደግፉትና እንደሚረዱት ማረጋገጡ ነበር፡፡ ህወሃት ለፈጠራቸው በደሎችና ወንጀሎች እነሱ ተጠያቂ እንደማይሆኑ አፍ እውጥቶ ባይናገርም “ወርቅ ህዝብ ነህ” በሚለው አነጋገሩ እውስጣቸው ገብቷል፡፡ ገና ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመደብ በፓርላማ ቀርቦ ንግግር ሲያደርግ በታሪካችን “ተጋሩ” ተብለን የማናውቀውን ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ ባደባባይ ስለጠራን ያ ብቻ እንድንወደው ያደርገናል ያሉት ሁሉ በትግርኛ ከፊታቸው ቆሞ እያለሳለሰ ሃሳቦቹን መደርደሩ ምንኛ ከልቡ እንደቀረባቸው አንደሚያምኑት አድርጓል፡፡ ህወሃት ውስጥ የህዝብ ወገን ነን የሚሉ ቢኖሩ ያ ብቻ ይበቃቸው ነበር የአምባገነንነቱ ዘመን መጠናቀቁን ተቀብለው የለውጡን ንፋስ ከመሰሎቻቸው ከነአቢይ ጋር አብረው ለማራገብ፡፡

ምንም ሆነ ምን ግን ህወሃት እያፈገፈገ፣ እንዲያውም ድምጹን አጥፍቶ የነአቢይን ሁኔታ መከታተሉን ቀጠሏል፡፡ ዝርዝር ሁኔታውን ለማወቅ ባንችልም የነሱ አደግዳጊና አሽከር ከሆኑት ግልሰቦችና የመገናኛ አውታሮች የሚወጡትን ስንመለከት እስካሁን በነአቢይ ላይ ጦር እንስበቅ የሚሉት አነስተኞች ናቸው፡፡ ህወሃት እነአቢይን ማሰናከልና ወደሚፈልጉት ግብ እንዳይደርሱ ማዘግየት እንጅ መጋፈጥ ብሎም በሃይል ማጥፋት እንደማይቻለው የተገነዘበ ይመስላል፡፡ አቢይ አገር ላገር የሚዞረው፣ በህዝብ መሃል እየተገኘ ከሱ በፊት ያልተለመደና እጅግ ያስመሰገነውን መልካም ንግግርና ውይይት ላይ የተሳፈረበት ትልቁ ምክንያት አገዛዙን ከህወሃት ተርክቦ ለመዘወር፣ ለማስተካከል፣ አፈራርሶ ለመገንባት ስላልቻለ ነው፡፡ ያስተሳሰብ ድክመት ኖሮበት ወይም የህወሃት ድብቅ ተላላኪ ወይም መሳሪያ ሆኖ አይደለም፡፡

ህወሃት ስልጣን ከደርግ እንደተረከበ አገዛዙን መልሶ ሲያዋቅር ከላይ እስከታች በራሱ ሰዎች ስለሞላውና ለሱ ብቻ እንዲያመች ስላደረገው በድንገት የሃይል ሚዛኑ ከጃቸው ሲያፈተልክ ምንም ለውጥ ቢመጣ በግንባሩ አመራር ላይ ብቻ እንዲከሰት ወስኖታል፡፡ ያውም ከአራቱ ድርጅቶች ለበላይ ምክር ቤቱ በአባልነት የሚውጣጡት 40 ሆኖ አንድ ላይ ሲሰበሰቡና ድምጽ በግላጭ (እየተያዩ) ሲሰጡ በድፍረት ከ“በላይ አካል” የሚሰጠውን መመሪያ መጣስ ተችሎ “ያልተፈለገ“ ሰው ብቅ እንዳይል ቀመሩ እንዳያመች ተደርጎ ተሸርቦ!  በቅርቡ አቶ ሃይለማርያምን ለመተካት በተደረገው ምርጫ ወቅት በብልጠት ይህን አሰራር አስለውጠው ነው አቢይ ወደአመራር የመጣው! ህወሃት እንዴት እንደተታለለ ገና ወደፊት እስኪነግሩን እንጠብቃለን፡፡ ግን የሚመስለው የምርጫውን አፈጻጸም ከግልጽነት ወደ ምስጢርነት እንዲለወጥ ካልተደረገ ህወሃት በተለመደው መንገድ ባሽከርነት የሚያገለግለውን ግለሰብ ለማስቀመጥ እንጅ ለወቅቱ ችግሮች መፍትሄ የሚያቀርብና የተቆጣውን ማህበረሰብ የሚወክል እንደማይሻ ተገንዝበው እነአቢይ በእምቢታ ተጋትረውት ኖሯል፡፡ በተለያዩ መንገዶች እንደሚተረከው የህወሃት እቅድ ጭራሽ አቢይን ቀርቶ ሌላ ግልሰብ እንኳን ሳይታሰባቸው ፊት ለፊት ከተጋፈጣቸው ከሁለቱ ድርጅቶች (ብአዴንና ኦህዴድ) ሙሉ የድምጽ ክምችት (90) ጋር የሚወዳደር ሌላ የድምጽ ሃይል መፍጠር አላስቻላቸውም፡፡ እንዲያውም የሚመስለው ከደቡቡ ድርጅት እንኳን ህወሃትን ለመካድና ሌላ ተፎካካሪ እንዲወጣ የማድረግ ፍላጎት ኖሮ አቢይ ባሸናፊነት ብቅ እንዲል አስችሏል፡፡

የአቢይ መመረጥና ቃለመሃላ መፈጸም ለብዙው ተመልካች (የነጻነት ታጋይ ነን ለሚሉት ጭምር) ሁሉም ነገር ያለቀና ከእንግዲህ ሁሉ ነገር በአቢይ እጅ እንደገባና መፍትሄዎችን እንደሚያዥጎደጉድ ነበር የሚጠብቁት፡፡ ከሃይለ ማርያም ስራ መልቀቅ ጀምሮ አቢይ እስከተሰየመበት ጊዜ ድረስ በአፈና አዋጁ ሲታመስ የነበረው ህዝብና በጉጉት የሚጠብቀው ሁሉ ወደተረጋጋ ሁኔታ እንገባለን ብሎ ያስብ ጀመር፡፡ ነገር ግን ቢጠበቅ ቢጠበቅ አቢይ አህመድ ሚኒስትሮችን እንኳን ለመሾም ሳይችል ሰነባበተ፡፡ ልክ ሃይማርያም ደሳለኝ እንደነበረበት አጣብቂኝ እውነተኛው ባለስልጣን እሱ እንዳልሆነ ገሃድ እየወጣ ሲሄድ የህዝቡ እይታ ተስፋ ወደመቁረጥና ወደተለመደው አመጽ መመለስ አስፈላጊነት መዞር ጀምሮ ነበር፡፡

የአቢይ ካቢኔ የራሱ እንዳልሆነ ማለትም እሱ መልምሎ ያስገባቸው አለመሆናቸው ቀስ በቀስ በጣም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ተከታታዮች ውስጥ ሲታወቅ ደግሞ ከአቢይ ጋር ተሰልፎ ምን ሊደረግ ይቻላል? የሚለውም ጥያቄ ብቅ አለ፡፡ አስገራሚው ነገር ህወሃት በበኩሉ ከአንድ ሚኒስትር በስተቀር ሌሎችን ቦታዎች በሙሉ ለቆ የኩርፊያ አይነት ሁኔታ ፈጠረ፡፡ (ሚኒስትር ባያሾሙም በመንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋሞች በየርከኑ የተሰገሰገው የህወሃት ሰራዊት አቢይን ምንም ንቅንቅ እንደማያስደርግ የታወቀ ቢሆንም፡፡) የህወሃት ከሚነስትር ሹመት ማፈግፈግ ኦሮሞዎች ሁሉንም ይዘውታል ተብሎ በአቢይና ጓደኞቹ ላይ አመጽ እንዲነሳ ታስቦ ይሆን? ብቻ ባደባባይ ላይ የህወሃት መኖርም እየጠፋ ሲሄድ ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ ከማድረግ ይልቅ ወደህቡእ መግባታቸውን አበሰረ፡፡ የት ሊደረስ? ለረዥም ጊዜ ዝም ብሎ እየተያዩ ተቆይቶ መንግስቱን መዘወር ሲሳን (ለምሳሌ ግብር ሳይሰበሰብ ቀርቶ ለወታደሩና ለመንግስት ተቀጣሪው ደመወዝ መክፈል ቢያቅት) የህቡኡ የህወሃት መንግስት እራሱን ብቅ ሊያደርግ?

በዚህ ሁሉ መሃል የአገሪቱ ፖለቲካ ዋና አንገብጋቢ ጥያቄ እየተለዋወጠ ሄዷል፡፡ እነአቢይ ጥረታቸው እንዲሳካላቸው ከነሱ ጋር አብሮ መሆን ወይም መሰለፍ የህዝቡን ምኞት ማሳኪያ ብቸኛ መንገድ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ይህን አስተሳሰብ የሚቀበሉና የማይቀበሉ፣ ተግባራዊ ለማድረግም አስፈላጊውን ርምጃ የሚወስዱና የማይወስዱ በተለያዩ ሰፈሮች መከፈል ይዘዋል፡፡ ህወሃት ከበላይነቱ ወርዶ በዴሞክራሲያዊ አሰራር አራቱ ድርጅቶች (ሌሎችም አዳዲስ ተጨምረው?) ኢህአዴግን እንዳዲስ ቢያዋቅሩት (ወይም ተመሳሳይ ሌላ ድርጅት ቢፈጥሩ) አገሪቱም ህዝቡም ይጠቀማሉ፡፡ ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ አሰራር ተስተካክሎ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጎን ሆኖ በእኩልነት፣ በተፎካካሪነት ቢሰለፍ ሰላማዊ የስልጣን ሽግሽግ ለማድረግ ይበጃል፡፡ ህወሃት ይህንን አቅጣጫ አሰናክሎ የቆየውን የበላይነቱን አላስነካም ካለ ግን ኢህአዴግ መፍረሱ አይቀርም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የነአቢይ ቡድን አጋሮች አብጅቶ በፓርላማው ውስጥ የህወሃትን የበላይነት እንዲያስወግድ ከተገደደ ኢህአዴግም ያንን ተከትሎ መንኮታኮቱ ይቀጥላል፡፡ ከዚያ ውጭ የሚከተለውን ለመተንበይ ያስቸግራል፤ ነገር ግን አቢይ አገር ላገር የሚዞርበትን ምክንያት እያገባደደ በሄደ ቁጥር፣ ባገሪቱ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ችግሮች የሱን ውሳኔ እየፈለጉ ሆኖም ስልጣኑ ከጁ ውስጥ ስላልገባ መንግስቱ ተንከረባብቶ እንዲወድቅ የማይፈልጉ ወገኖች ወደህዝቡ ዞረው ለ“ማያዳግም መፍትሄ” እስከመዘጋጀትና እርምጃ እስከመውሰድ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡

ህወሃት የበላይነቱን አላራግፍም ብሎ በአገዛዙ ላይ ተሳፍሮ እንደኖረው ለመቀጠል በሩን ከውስጥ ቆልፎ ከተቀመጠ የት ይደረሳል ለሚሉ መልሱ ቀላል አይደለም፡፡ ለጦር አመራሩ መልክም ንግግር መድረግና በመከላከያውና በጸጥታው አመራር የተቀመጡትን ማንሳት ብቻቸውን እነዚህን ክፍሎች በአቢይ እጅ የሚያስገቡለት ከሆነ ተአምር ይሆናል፡፡ በርግጥ አቢይና ጓደኞቹ በህዝብ መሃል ባጭር ጊዜ ተደማጭነትና ድጋፍ አብጅተዋል፡፡ በአንድ ወጥ ድርጅት ዙሪያ ወይም መልክ ባይሰባሰብም፡፡ ይህ ድጋፍ ባለመቀናጀቱም አቢይን ካለበት ማነቆ አውጥቶ በህገመንግስቱ የሰፈረውን ስልጣን የሚያጎናጽፈው ሃይል አይሆንም፡፡ እንዲያውም ያንን ሃይል ለመፍጠር ቢሞከር እንደክህደት ቆጥረው የጦር ሃይሉን ይዘው ሊገለብጡት ቢሞክሩ አያስገርምም፡፡ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” አደጋ ላይ ነው በሚል ዝባዝንኬ ታጅበው በገሃድ እየዛቱ ያሉ ወገኖቹ መኖራቸውን ያልሰማ አለ? በገሃድ ይህን ሮሮዋቸውን የሚያሰሙት ጥቂቶች ቢመስሉም ውስጥ ለውስጥ ግን በርካቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከጸጥታውና ከመከላከከያው አካባቢ አዳማጭ ጆሮ እስኪያገኙ ወይም ተከታይ እስካበጁ ድረስ በህዝብ መሃልና ባደባባይ ይህ “የአደጋ” ወሬ አለመነሳቱና አለመሰበኩ ለአቢይና ጓደኞቹ ስጋት እንዳስቀረላቸው ማሰብ አይገባም፡፡

ካሁን በፊት የአቢይ መመረጥ እንደተሰማ ደራሲው ይህን ብሎ ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ ቶማስ ሳንካራዋን በዛሬው እለት አግኝታለች። የሚጥም ንግግሩን በመከተል አካሄዱና ፍጻሜው እንዲያምርለት ምኞቴ ነው።” ቶማስ ሳንካራ በውጭ ሃይሎች (ፈረንሳይ) ሴራ ጠንሳሽነት የተነሳበትን መልካም አላማ ከነህይወቱ ማጣቱ ከኛ አገር ሁኔታ የራቀ አስመስለው የሚሞግቱ አይጠፉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚያዋጣውንና የሚያስተማምነውን የመፍትሄ መንገድ ሳይዙ በመልካም ምኞትና ፍቅርና መግባባትን በመስበክ ብቻ መንቀሳቀስ የሳንካራን እጣ አያርቀውም፣ ኣያስቀረውም፡፡

የአቢይ አጋሮች ከዳር ሆነው አይዞህ አይዞህ ከማለት አልፈው ህዝቡን ወደማደራጀት፣ ባካባቢ አስተዳደሮች ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎና የበላይነት እንዲኖረው መደገፍና ማበረታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለፈው በኦሮሚያና በአማራው ክልሎች ገዥ ፓርቲዎች የሹመት ጋጋታ ማድረጋቸውንና በወረዳና በቀበሌ ጭምር እነሱ ይረዱናል ብለው የሚያስቧቸውን ወገኖች እንዳስገቡ ተዘግቦ ነበር፡፡ የአቢይ አጋሮች ባንድ በኩል እሱ የሚለፍፈውን የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እያጨበጨቡ ሲያስተጋቡ በሌላ በኩል ግን በተግባሩ ሜዳ ላይ ምንም ውጤት አልታየባቸውም፡፡ አዲስ አበባና ባህር ዳር ተቀምጠው በቀጭን ትእዛዝ ለያካባቢው ገዥዎችና አድራጊ ፈጣሪዎች ሲመድቡ የህዝቡን መኖር ጭራሽ እረስተውታል፡፡ ወይስ ህወሃት ሲሰራ የቆየውን ድራማ ተከትለው ከባህር ማዶ ተላልከው ገና በፈረንጅ አስጠንተው ህዝቡን ከተመልካችነት አውጥተው ሊገላግሉት? ቢያንስ ቢያንስ በቀበሌና በወረዳ ያለው ህዝብ በነጻነት ራሱን እንዲያስተዳድር በር ካልከፈቱለት እነሱ ላይ አደጋ ቢቀሰር በምን ሰበብ ሊሞትላቸው ነው?

ለነገሩ አቢይ አህመድም በትልልቅ ጉዳዮች ላይ ያልተጠናና ህዝብ ያልመከረበት ውሳኔ መስጠት ውስጥ ገብቷል፡፡ ህዝቡ በተመልካችነት የተፈረደበት፣ በዱላ ለመነረትና በእስራት ለመማቀቅ በቀላሉ የሚወሰንበት ሆኖ መኖሩ አይበቃም? የኤርትራው አበሳ መቋጨት ለኢትዮጵያም እንደሚያሻት አስፈላጊ ቢሆንም ባንድ በኩል በተራ ድርጅታዊ ውሳኔ የባድመን ሁኔታ ማራገፍ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በአሰራር ደረጃ ህዝቡ ሳይሰማና ሳይወስን፣ በተለይ ባካባቢው የሚኖረው (በተለይ የኢሮብ) ህዝብ ሮሮ ሳይደመጥ ወደቀጭን ውሳኔ መግባት ጥፋት ነው፡፡ ህወሃት የፈጸመውን ፈርጀ ብዙ ስህተቶች ለማረም ሲባል ሌላ ግዙፍ ጥፋት መጨመር አይገባም ነበር፡፡

አቢይ ስለኢኮኖሚው መስተካከያ ሃሳቦች በየጊዜው ሲወረውር ቆይቶ ቢያንስ ቢያንስ ሌሎች በቀጥታ የሚመለከታቸው ክፍሎች ምንም እንዲወያዩበት ወይም ምላሽ እንዲሰጡበት ሳይደረግ ወደተግባራዊ እርምጃዎች መሸጋገሩ የተሳሳተ ይመስለናል፡፡ ከሚነሱት ትልልቅ ጥያቄዎች ውስጥ የመንግስትና የግል ዘርፎች ግንኙነት ላይ መመሪያ እንዲበጅ መጠየቁ ጥሩ ሆኖ አሜሪካኖችና አውሮፓውያን የመንግስት ድርሻ እያሳደጉ እያሉ ድሆች አገሮችን ካሉበት እንዳይነቃነቁ ለማድረግ የሚሰብኩትን የሚያንጸባርቅ እርምጃ አጠያያቂነት አለው፡፡ እነሜቴክ ጉቦኛ የሆኑት የመንግስት ስለሆኑ አይደለም፡፡ የአየር መንገድና ቴሌ በመንግስት እጅ (ባለቤትነት) መሆን በምን መልክ ጉዳት እንዳስከተለ ተለቅሞ ሳይጠናና መስተካከያ ሳይሞከር በአክሲዮን ሽያጭ ስም ትልልቆችን ላሞች ለአራጅ ማቅርብ ይሆናል፡፡ ኮሪያ ዛሬ ታላቅ የሆነችው የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ግንባታ በወታደራዊ አሰራር ስር አስገብተው እንደነበር አልተሰማ ይሆን? በጥቅሉ ያገሪቱ ኢንዱስትሪያዊ አደረጃጀትና አሰራር ብዙ የሚነቀፍ ቢኖረውም ነቀፌታው ጭራሽ ያለውይይትና ህዝባዊ ተሳትፎ ቅጽበታዊ እርምጃ እስከመውሰድ አያደርስም፡፡ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይስ ነዎይ?

ይልቅስ ለነአቢይ ከህዝቡ ጋር ለመጣጣም ብሎም ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ ለዲሞክራሲ በር ለመክፈት የሚያስችላቸው ግልጽነት፣ መረጃዎችን በቶሎና በሰፊው ማሰራጨት፣ የህዝብ ስሜትና ብሶት ያለገደብ እንዲወጣ መገናኛ ብዙሃኑን (በተለይ በመንግስት ስም ያሉትን) ለህዝቡ አገልጋይና ልሳን እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ነው፡፡ የአገዛዙን ዋና ዋና አካሎች በተለይ ጸጥታና መከላከያ፣ ፍትህና ትምህርት የመሻሻያ ጎዳና ላይ እንዲሳፈሩ መጣር ከአቢይ አህመድ በፍጥነት የሚጠበቅ ቢሆንም የህዝቡን አጋርነትና የፖለቲካውን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ግን የመረጃውን መረብ ነጻ ማድረግ ዛሬ ነገ የማይባል ነው፡፡ ህዝቡን ለትግል የሚያበረታታ፣ በነጻ ለመንቀሳቀስና ለመደራጀት የሚያስችለው አሰራርና ህግ በፍጥነት እንዲበጅለት ማድረጉ ምንም ቀን የሚጠብቅ ነገር አይደለም፡፡ ሳንካራም ንክሩማም ለውድቀት የተጋለጡባቸው ድክመቶች እነዚህ ነበሩ፡፡

በፖለቲካው ሂደት ላይ የአቢይ ንግግሮች ያስከተሉት መልካም ውጤቶች እንዳሉ ሆነው ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ብዙ አሳሳቢ ጉዳዮች አሁንም አሉ፡፡ ትልቁ ጉዳይ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖችና ድርጅቶች የሚያሳገትፍ አገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ መጥራት ነው፡፡ የጉባኤው መጠራት ትክክልና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው እርምጃ ሲሆን አገሪቱን የሚመራ ብሄራዊ የተውጣጣ መንግስት ወይም የሽግግር መንግስት የሚባሉት ግን አቅጣጫ የሚያስቱ ይመስለናል፡፡ ባንድ በኩል ህወሃት ስልጣኑን ለአቢይ አላስረክብም ብሎ ገትሮ ይዞ ለምን ይህን ይፈቅዳል? እንደገናም ህዝቡ ተወያይቶና ተደራጅቶ ወደምርጫ መግባት ሲጠበቅበት ባለአደራ ወይም የሽግግር መንግስት ይቋቋም አይቋቋም አላስፈላጊ ውዝግብና ንትርክ ይፈጥራል፡፡ ባጠቃላይ፣ ህዝቡ ከህወሃት ራሱን ነጻ ለማውጣት እየተጠባበቀ እያለ ኢህአዴግ ነፍስ እንዲዘራ የሚያስችል መንግስት በአዲስ መልክ ይቋቋም ማለት ዱሮ የብሄራዊ እርቅ ምናምን የሚባለውን ሙግት ማስቀጠል ነው፡፡

በአገሪቱ በሙሉ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ለአጠቃላይ መፍትሄ ማዘጋጀት ራሱን የቻለ አስተሳሰብና አሰራር ይጠይቃል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በኩል ግን ቁርጥ ቁርጥ ያሉ ትርኢቶች እየተካሄዱ ይመስላል፡፡ በሚያደርጋቸው ትንንሽ ስራዎች ውስጥ ጥልቅ አስተሳሰብና ብልጠት ባይጠፋባቸውም፡፡ የነሌንጮ ወዳገር ውስጥ መመለስ፣ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ቤተመንግስት በር ላይ ፎቶ መነሳት፣ ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች ፈር ቀዳጅ ናቸው፡፡ በነዚህ እርምጃዎችም ፖለቲከኛውን ሁሉ ጉድ አፍልቶበታል! በተለምዶ በሳሩ በስንጥሩ እየተጣላ፣ “ተቃዋሚ ነኝ፣ ያለኔ ማንም ስላገሪቱ የሚያውቅ የለም” እያለ ጎጆ ጎጆ ሰርቶ ካመት አመት ያለውጤት ህዝቡን ሲያደናግር የቆየ ሁሉ “በፍቅር፣ በመከባበር አገር እንገንባ”፣ እሱው ባወጣው ቃል “እንደማመር” የሚል የፖለቲካ ተቀናቃኝ መጥቶባቸዋል፡፡ አሜሪካ ድረስ መጥቼ ላነጋግራችሁ ብሏል ተብሎ ልክ ትራምፕን አስረህ ላክልኝ ያለ ያህል መወራጨቱ ልክ አልነበረውም፡፡ በሙሉ ድምጽ ያለማቅማማት እንኳን ጥያቄ አቅርቦ (እውነት ከሆነ) ቀርቦ ማነጋገሩ ይገባ ነበር፡፡ ማነጋገር እኮ ነው!! ምላሱን ፈርተው ነው ያ ሁሉ ጦር የተሰበቅበት? ጉድ ነው!!

አብይ ያገሪቱን ፖለቲከኛ በደካማ ጎኑ ነው የገባበት፡፡ ማለትም ሳይነጋገር ብቻ ብቻውን ቡድን ፈጥሮ በሜዳ ላይ ሆኖ መጮህ ነው ልምዱ፡፡ አይ ብልጠቱ!! አንዳርጋቸውን በመፍታቱ ብቻውን ስንት ምስጋናና ክብር ሲገባው (የህወሃት አቀንቃኝ አንድ ግልሰብ–ቪዛ የሌለው ሰው ወንጅል ቢፈጥም ምናምን ብሎ–የደረደራቸው ነጥቦች በሙሉ በጥሬው ትክክል ቢሆኑም ቅሉ!!) እሱ ግን ከዚያ አልፎ የብስለት ስራ ሰራ፡፡ “አስተሳሰብህ ምን ሆነ ምን እኔና አንተን በግል ሊያቃቅርን አይገባም፡፡ እንዲያውም ወንድማማችነታችን ስለማይፋቅ እስቲ ተደማምጠን እንወያይ” ብሎ ይመስላል ቤተመንግስት ያስጠራው፡፡

ሌሎችንም ተራቸውን እየጠበቁ እንደሚቀርባቸው የታወቀ ነው፡፡ በነሌንጮ ተጀምሮ የተቀሩት ሁሉ እድል እንደሚያገኙ ጥርጥር የለውም፡፡ ሰሞኑን ደግሞ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ በገለልተኛ ወገን አማካይነት ለ“ድርድር” ቅረቡ ተብሎ ተጽፎላቸዋል ተባለ፡፡ ታዲያ አንድ አንድ እየተባለ “እጅ ሊያሰጣቸው” ይመስላል፡፡ ነገር ግን እላይ እንዳሰፈርነው ያገርቱን የፖለቲካ ሃይሎች በምክክር ጉባኤ ላይ እንዲገኙና ለአገሪቱ ምስቅልቅል ሁኔታዎች መፍትሄ እንዲያፈልቁ ማድረግ የተሻለና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይመስለናል፡፡ ዛሬ አንዱ ሲጠራ ሌላው በሌላ ቀን ቤተመንግስት ሲገባ ለተመልካቹ ጉድ ጉድ ያሰኝ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ጀርባ የቆመ የሚጠብቀው ሃይል ሳይኖር በጊዜ መጫወት አያዋጣም፡፡ ስልጣኑን በስም ብቻ እንደያዘ ሁሉም ያውቃል ወይም መረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን በመቀሌ ውይይት ላይ ስዩም መስፍን እንዳሳወቀው ግብግቡ አላለቀም፡፡ እንዲያውም ስዩም መስፍን ባደባባይ ያን ያህል በድፍረት ሲናገር በምስጢር ስለነአቢይና ጓደኞቹ ምን ሊባባሉና እንዴት ለማይቀረው ግብግብ እንደሚደራጁ መገመት አያቅትም፡፡ የኛ ፖለቲከኞች ሁሉ ጋሽ መስፍን ወልደማርያም እንዳለው ለብቻችሁ ስልጣን ካልተሰጣችሁ ወይም ባዶ ወንበር ካልተዘጋጀላችሁ ባገሪቱ ላይ እለት በእለት ያለውን መተሻሸትና ፍትጊያ እየሰማችሁ እንዳልሰማችሁ ዝም ብትሉ ለህዝቡ ነጻነት የተከፈተውን በር መልሶ ጅብ ይገባበታል፡፡ የሰማ ያሰማ፡፡

*አስተያየት ካለ  a_endeshaw@yahoo.co.uk