የቀድሞ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት ዝምታውን ሰበሩ
የደረሰውን በደል ተናገሩ
============

© ግዮን መፅሔት ዛሬ (ሰኔ 2/2010 ቅፅ 1 ቁጥር9)

የተዳፈነው የሙስሊሙ ሐቅ!

ከቀድሞው መጅሊስ ፕሬዘዳንት ሸይኽ ኺያር ሙሐመድ አማን ጋር የተደረገ ቆይታ።

በ2005 በተደረገ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ የምርጫው ዘመን ሳያልቅ እና የጠቅላይ ምክርቤቱ ደንብ ሳይፈቅድ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ በ2007 እንዲበተን እና እዚህ ግባ በማይባል በሌላ ቡድን እንዲተካ መደረጉ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ የዚህ ህገ ወጥ ግልበጣ ዋና ተዋናኞች ደግሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር እና ሚኒስትር ዴታው፣ የኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ዴታው የነበረው አቶ ሽመልስ ከማል (ለዚሁ አፍራሽ ስራው እንደ ሽልማት ከመንግስት የመንግስት ቤት በስሙ ካርታው ዙሮለታል)፣ የፔትራም ድርጅት ባለቤት፣ የአዲስ አበባ መጂሊስ ፕሬዝዳንት የነበረው ዶ/ር አህመድ፣ ከውጭ ሀገር ደግሞ አቶ ሳላሀዲን ወዚር የአህባሾቹ መሪ እንዲሁም በአንዳድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተጽእኖ ስር በወደቁ የመጅሊስ ኡለማ ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡

የግልበጣው ዋነኛ ሰበብና ሽፋን የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትና ለሐቅና ለትክክለኛ ሥራ ቁርጥ አቋም የነበረን አብዛኞቹ የሥራ አስፈጻሚዎች “ወሀብያ ናቸው ተብለን ” በተደጋጋሚ በሕዝብ ጆሮ እንዲናፈስ የተደረገው ውሽት እውነት እንዲመስል ተደርጐ መቅረቡ ነው፡፡ በመሰረቱ “ወሀብያ” የሚለው ቃል እና ጽንሰ ሀሳብ እስልምና የማያውቀው፣ በኢትዮጵያ መኖሩ ያልተረጋገጠ፣ ተረጋግጦም ከሆነ ያረጋገጠው አካል በሕግ እንዲታገድ አድርጎ፣ ይህን በዋህብያ የተፈረጀ ቡድን ወይም ግለሰብ እንድናውቀው አልተደረገም፡፡ እንዲህ አይነቱ ህገ መንግስታዊ አሰራር በሌለበት ሁኔታ እምነታችን፣ አስተሳሰባችንና ግብራችን ‹‹ዋህብያ›› የሚሉት የአስተሳሰብ መንገድ የማይገልጸንን ሰዎች ‹‹ዋህብያ›› የሚል ታፔላ ሲለጥፍሉን አጀንዳው ምን እንደሆነ ለማንም አመዛዛኝ አእምሮ ላለው እና አርቆ ለሚያይ ሰው ግልጽ ነው፡፡ ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› እንደሚባለው ሆኖ እንዳይቀር፣ ሀቁን ሁሉም እንዲረዳው ከብዙው በጥቂቱ ማሳያ የሚሆኑ ነጥቦች ብቻ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግስትን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ለሚገቡት ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ አይቻልም በሐይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን አንፈቅድላችሁም በማለት በይፋ ስለተቃወምን፣ ሕገ መንግስቱ ተጥሶ እና ተረግጦ ለደረሰብን የመብትና የፍትሕ ገፈፋና ረገጣ በሚድያም ሆነ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በጊዜው ግልጽ በማድረጋችን እና በመውቀሳችን ፣ ለምን ጊዜም ቢሆን ሳንሰለችና ሳናቋርጥ የመብት ጥያቄ በማቅረባችን ማለትም ፣ ሕልውና፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕና አንድነት መብታችን መሆኑ ታውቆልን ችለን መኖር ብቻ ሳይሆን ተቻችለን እንኑር፣ የተለያዩ ጐራና ሴክቶችን ፈጥራችሁ አትለያዩን፣ መጠቀሚያ አታድርጉን የሙስሊሙ አንድነት ሐይሉ ነው እና አትበታትኑን፣ አንድነታችን ይጠበቅ ብለን በአንድነት ጉዳይ ላይ የጠነከረ አቋም ስለያዝን ስለ አንድነት የሚሰብክና የሚያቀነቅን እንደ ወንጀለኛ የሚቆጠር በመሆኑ እርምጃ ተወስዶብናል፡፡

የ2005 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ አስችጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መካሄዱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ አስቼጋሪ ሁኔታ በርካታ እና የሚታወቁ ምክንያቶች ስለነበሩ ወደ ሙሉ ዝርዝሩ ሳንገባ፡፡ ከነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል ከቁጥጥር ውጭ የተፈጠሩ እውነታዎች ለሕገ-ወጥ ግልበጣው መንሰኤዎች እንደሆኑ በማሳየቱ ላይ እናተኩር፡፡

1. በእነ ሸኽ ኺያር መሐመድ አማን አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት የሀገሪቱን ሙስሊሞች ለመምራት ጠቅላይ ምክር ቤቱን እንደተረከበ የተጣለበትን ተግባር እና ኃላፊነት መሠረት አድርጐ የሙስሊሞችን እና የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ግራ ቀኙን አይቶ ከገመገመ በኋላ ከቀጣይ የስራ ትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ም/ቤቱ ከውጭ እና ከውስጥ ስውር ፍላጐቶች እና ተጽእኖች ነፃ ሆኖ ሕዝበ ሙስሊሙን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እና በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድም ተአማኒነት እንዲኖረው ማስቻል፣ ከሀገርም ሆነ ከውጭ ከሚገኙ አቻና አጋር አካላት ጋር ሕግና ሕግን በተከተለ አግባብ ጤናማ ግኑኙነት ለመፍጠር ፣ የጠ/ም/ቤቱን የስራ ትኩረት አቅጣጫዎች በጊዜው ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር ለክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ለፖርላማ እና ለፌዴሬሽን አፈጉባዔዎች፣ እንዲሁም ለሌሎች ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአካል በመገኘት በማስረዳት ተቀባይነትንም አግኝተን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብተን ነበር፡፡ በተጨማሪም ወደ ስራ ከገባን በኋላ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል የማይገቡ ፍላጐቶች እና እነዚን ፍላጐቶች ለማስፈጸም ሲባል ልዩ ልዩ ተጽኖች እና ግፊቶች ይደረግብን ስለነበር እንዲህ አይነቱ ጫና እንዲነሳልን፣ እንዲሁም በአክሱምና በሌሎች ቦታዎች መስጅድ የመስራት እድሉና መብቱ እንዲሰጠን ጠይቀን፣ አስረድተን ተግባብተንም ነበር፡፡

በዚሁ ከመንግስት ከፍተኛ መሪዎችና ኃላፊዎች ጋር በተወያየንባቸውና በተስማማንባቸው ጉዳዮች አንጻር ፊታችንን ወደ ስራ መልሰን ፣ የመጅሊሱ ምርጫ የተካሄደው ህዝበ ሙስሊሙ በመጅሊሱ ላይ እምነት ባጣበት፣ በዚህም ምክንያት ጥያቄው ለመንግስት ቀርቦ ሙሉ ስምምነት ባልተደረሰበት፣ ይህም ህዝበ ሙስሊሙ በምርጫው ሂደት ላይ የተከፋፈለበት ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ቀዳሚ የስራ ትኩረትና የእንቅስቃሴ አቅጣጫችንን ህዝበ ሙስሊሙ እንዲረጋጋና ወደ አንድነት እንዲመጣ ማድረግ ነበር፡፡ ለዚህም ስኬት ሁለት የእንቅስቃሴ ስልቶችን ቀየስን፡፡ የመጀመሪያው በጠቅላይ ምክር ቤቱና የሙስሊሙን ህብረተሰብ አንድነት በማይፈልጉ ሃይሎች የተፈጠረውን የተዛባ አመለካከትና አሰራር እንዲሁም ጣልቃ ገብነት መልክ እንዲይዝ፣ ህገ መንግስታዊ የሆኑ የመጅሊሱና የህዝበ ሙስሊሙ መብቶች እንዲከበሩ፣ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነበር፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፣ መጅሊሱ ለሁሉም ህዝበ ሙስሊምና የእስልምና አስተሳሰቦች ጥላ እንዲሆን፣ በተለይም መጅሊሱ ሌሎችን አግልሎ የአህባሽ አስተሳሰብ እንዲያራምድ የሚፈለገው ተጽእኖ እንዲነሳ፣ ልዩ ልዩ እስላማዊ ስልጠናዎች በአገር ውስጥ ዑለማዎች እንዲሰጥ፣ የአክሱም ሙስሊሞች መስጅድ የመስራት መብት እንዲከበር፣ በአክሱምም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ለሚኖሩ ሙስሊሞች የመቃብር ቦታ እንዲሰጥ፣ በአገራዊ ጉዳዮች የሙስሊሞች ተሳትፎ የህዝበ ሙስሊሙን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ እንዲሆን፣ ወዘተ በመሳሰሉ መሰል የመጅሊሱና የህዝበ ሙስሊሙ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡
በመጅሊሱ ውስጥ በቆየንባቸው ጥቂት የስራ ጊዜያት እነዚህን ጉዳዮች ለማስፈጸም ቀርቶ፣ ለሚነሱት ጥያቄዎች ሁሉ ጉዳዮን ‹‹ከዋህብያ›› ጋር በማያያዝና ታፔላ በመለጠፍ፣ በስራ አስፈጻሚው መካከልም ጣልቃ ተገብቶ የመከፋፈል ስራ በመሥራት፡፡ በተለይ በወቅቱ የነበሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስቴርና ሚንስቴር ዲኤታው የአህባሽ አስተምህሮ የመጅሊሱ ግዴታ እንዲሆን በግልጽ ጣልቃ ገብነት ግፊት ሲያደርጉ ቆይተው፣ ይህ አልሳካ ሲላቸው የትግራይ ክልል ተወካይ በነበሩት በሸኽ ኸድር ማህሙድ አመካኝነት አብዛኛውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከኃላፊነት ለማስነሳት እስከ መጨረሻ ተጉዘዋል፡፡ ሸኽ ኸድር ማህሙድ በየጊዜው ባካሄዷቸው የስልጣን ግልበጣና ሌሎች ያልተገቡ የመጅሊሱን ህገ ደንብ የጣሱ ተግባሮቻቸው የተነሳ በተደጋጋሚ ቢመከሩም ሊታረሙ ባለመቻላቸው የስራ አስፈጻሚው ከስራ ሲያግዳቸው ውሳኔው ከብሔር ጋር ተያያዞ፣ ‹‹የዋህብያ›› ስራ እንደሆነ ተደርጒ ተወስዷል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የህዝበ ሙስሊሙን የተከፋፈለና በመጅሊሱ ላይ የነበረን ፍርሃትና ስጋትን ለመቅረፍ የተከተልነው ስልት ከልዩ ልዩ የህዝበ ሙስሊሙ አካሎች ጋር ውይይት ማድረግ ነበር፡፡ ባቀድነው መሰረት ከዑለሞችና አሊሞች፣ ከወጣቶችና ከሴቶች፣ ከምሁራንና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር ተከታታይ ውይይቶች አድርገናል፡፡ ባደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶች ጠቅላይ ምክር ቤቱ የሕዝበ ሙስሊሙ ማዕከል እንዲሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ ሕዝበ ሙስሊሞች ጋር ጤናማ እና የተረጋጋ ግኑኙነት ለመፍጠር በቅተናል፡፡ ለዚህም በ2005 እና 2006 የሐጅ ጉዞ ላይ የታየው እና የማይደገም ታሪካዊ ክዋኔ ህያው ተጨባጭ እና በአደባባይ የተመሰከረለት ምሳሌ ነው፡፡

2. በወቅቱ የተረዳነው እና የተገነዘብነው ሌላው የምክር ቤቱ አብይ ጉዳይ የጠቅላይ ምክር ቤቱን ተልዕኮ ለመወጣት የሚረዱ ተቋማት ውስን አቅማቸው ስስ መሆኑ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ እንዲዘጋ የተደረገው እስላማዊ የባህል ማዕከል በወቅቱ በሰው ኃይል እና በአደረጃጀት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጐ ነበር፡፡ መስጊዶች ፣ ሕዝበ ሙሰሊሙ የሚደራጅባቸው ተቋሟት፣ በምክር ቤት በሙሉ ያዞታቸው እውቅና ተሰጥቷችው የሚተዳደሩባቸው ደንቦች እና ሕጐች ማንዋሎች ተዘጋጅተው ሙስሊሙ ሕብረተሰብ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው እንዲሆኑ በእቅድ ደረጃ መቀመጣቸው ሌላኛው የ‹‹ዋህብያ›› ታፔላ መለጠፊያ ሰበብ ነበር፡፡

3. ለተወሰኑ ግለሰቦች የግል ንብረት መስሎ የሚታያውና ከተመሰረተበት አላማ ውጭ የውጭ ሃይሎች ያልተገባ ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንደሆነ የሚነገርለት የዑለማና ፈትዋ ምክር ቤት በውክልናውና በአደረጃጀቱ ተጠናክሮ የስሙን ያህል ቁመናና ክብር እንዲኖረውና ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ አቅም እንዲፈጥር በጥናት ላይ የተመሰረት እንቅስቃሴ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ፣ የዑለማ ምክር ቤት መጠናከር በጣልቃ ገቦቹም ሆነ የዑለማ ምክር ቤቱን የግል ንብረታቸው ያደረጉ ግለሰቦች፣ የዑለማ ምክር ቤቱን በዋህብያ ሊያስይዙት ነው በሚል ውንጀላ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ህገ ደንብ ውጭ የተለመደውን ምክር ቤቱን የማፍረስ ተግባር አስፈጻሚ ሆኑ፡፡

4. ከላይ እስከ ታች የተዋቀረው የሸሪኣ ፍርድ ቤት ብቃትና የሰው ሀይል አደረጃጀቱ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡ በርካታ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች የሚቀርቡበት መሆኑ በፌዴራል የዳኞች ጉባኤ የሚታወቅና የሸሪአ ፍርድ ቤቱ እራሱን ‹‹የገዥ ወገን ተወላጅ ነኝ›› እያለ በሚጠራና የሸሪአ ፍርድ ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የእውቀትም ሆነ የስነ ምግባር ብቃት በሌለው ግለሰብ ይመራ ስለነበረ፣ ሁኔታውን ለመለወጥና የሸሪአ ፍርድ ቤት እስላማዊ ቁመናውን የሚመጥን ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረ ቢሆንም፣ በዋህብያ ሊያሲዙት ነው በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ሥራ አስፈጻሚውን ማጥቂያ ተደረገ፡፡

5. ወጣቶች በእድሜያችው፣ ምሁራን በሙያቸው ተደራጅተው ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር ተቀራርበው የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ማንዋሎች እና ደንቦች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቶ የነበረ ሲሆን ሕዝበ ሙስሊሙን መአከል ያደረጉ በመንግስት እውቅና የተሰጣቸው የመንፈሳዊ እና የልማት ድርጅቶች ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር ተቀራርበው እና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ቢደረስም፣ ይህ በሌሎች የእምነት ተቋማት የሚሰራ ድርጊት እኛ ዘንድ ሲደርስ ‹‹የዋህብያ›› ስራ ተደርጎ ተወሰደ፡፡

6. የጠቅላይ ምክር ቤቱ የልማት ኤጀንሲ የነበረው ‘’ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ’’ በመፍረስ ላይ ስለነበር፣ በሀገሪቱ ከሚገኙ የውስጥ እና የውጭ የልማት ድርጅቶች እና ወኪሎች ጋር ሰፊና ተከታታይ ውይይት በማድረግ እነዚህ የልማት ድርጅቶች እና ወኪሎች ከጎናችን እንዲሰለፉና በልማት ስራ አብረውን ለመስራት ፈቃደኛ እንዲሆኑ አስችለን ነበር፡፡ በወቅቱ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገበት ጊዜ ስለነበር፣ በመንግስት የተዘረጋውን ስደተኞቹን ወደ ሀገራቸው የመመለስ እና የማቋቋም መርሃ ግብር ለማገዝ እኛም ከስደት ተመላሾችን የመመለስና የማቋቋም ግብረ ኃይል አቋቁመን፣ ይህን ኃይል የሚመራ ከልዩ ልዩ የህዝበ ሙስሊሙ ክፍሎች የተውጣጣ ቦርድ ሰይመን ስራ ጀምረን ነበር፡፡ ይኸም እንቅስቃሴ ‹‹ዋህብዮችን›› የማደራጀት ስራ ሆኖ በአደባባይ አስወቀሰን፡፡

7. የአወሊያ እስላማዊ እርዳታ ድርጅት ጉዳይ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከአወልያ በተጨማሪ ሰሜን ወሎ የሚገኘው የወልዲያ መስጂዶችና እስላማዊ ትምህርት ቤቶች ማእከል የሚባለውም ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት የመንፈሳዊና የልማት ተቋማት ከሃምሳ አመታት በላይ የቆዩና በየጊዜው በውሰጣዊና በውጫዊ ሃይሎች አሉታዊ ተጽእኖና ጡጫ ሲያርፍባቸው የቆዩ አንጋፋ የህዝበ ሙስሊሙ ሃብቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን የመንፈሳዊና የልማት ተቋሞት የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ህልውናቸውን ለመጠበቅ፣ ቁመናቸው ወቅቱን የተከተለና የመጠነ ለማድረግ አቅማችን የፈቀደልንን ጥረት አድርገናል፡፡

በተለይ የአወሊያ እስላማዊ እርዳታ ድርጅት በአንድ በኩል የወቅቱ አጀንዳ በሌላ በኩል ተቋሙም እየተዳከመ ስለነበር ሁለቱንም ተግዳሮቶች ያማከለ አቅጣጫ በመያዝ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ፣ ይህንንም የሚያስፈጽም ከፖርላማ፣ ከምሁራን፣ ከታዋቂ ግለሰቦችና ከባለ ሀብቶች በተወጣጣ ራሱን በቻለ ቦርድ እንዲመራ ተደርጓል፡፡ በሰሜን ወሎ የሚገኘውን የወልዲያ መስጂዶችና እስላማዊ ትምህርት ቤቶች ማእከል ለማጠናከር ጥናት አስጠንተን ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ ስንጀምር ባጭሩ እንዲቀጭ ተደርጓል፡፡

8. ስራ እንደጀመርን የተረዳነው ሌላኛው ተጨባጭ ሁኔታ፣ የሀጅ መንፈሳዊ ጉዞ አገልግሎቱና ገቢው በውጭና በውስጥ ፍላጎቶችና ችግሮች የተጠላለፈ መሆኑ ነበር፡፡ ለዚህ ማሳያ ያህል ብቻ አንዱን ብንጠቅስ፣ የመንፈሳዊ ጉዞ የአውሮፕላንና የትኬት አገልግሎት የጠቅላይ ምክር ቤቱን ስነ ምግባር በማታከብር ግለሰብ የተያዘ ነበር፡፡ ይህችው ሴት በሁለት የጉዞ ወኪል ስም የትኬት አገልግሎት እንድታቀርብ በማድረግ የም/ቤቱ ገንዘብ እንዲዘረፍ የተደረገበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ በኩል የመንፈሳዊ ጉዞ የትኬት አገልግሎቱ በግልጽ ጨረታ እንዲሆን፣ በግለሰቧ እጅ የሚገኘው 10,000,000.00 /ከአስር ሚሊዮን ብር/ በላይ የሚሆን ገንዘብ እንዲመለስ ወደ ህግ እንዲቀርብ አድርገን ነበር፡፡

9. ከዚሁ ከሀጅ የመንፈሳዊ ጉዞ ጋር በተያያዘ የተረዳነው ሌላው ጉዳይ የጠቅላይ ም/ቤቱም ሆነ የክልል እስልምና ምክር ቤቶች የገቢ ምንጭ በሐጅ ወቅት ከሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን ነበር፡፡ ገቢ ለማግኘት ሲባል በሐጃጆች ላይ የሚጫነው ክፍያ ያልተገባ፣ እንዲያውም ከእስልምና መሰረቶች አንዱ በሆነው ሐጅ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደር እንደሆነ በማመን ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሌሎች የገቢ ምንጮች ላይ ትኩረት አድረገን ነበር፡፡ ከእነዚህ የገቢ ምንጭ አማራጮች መካከል የ/ጠ/ም/ቤቱ ጽ/ቤት አካባቢ፣ አንዋር መስጂድ ዙሪያ፣ ፒያሳ የሚገኘውን የአወልያ ት/ቤት፣ ወሊሶ የሚገኘውን የህጻናት ማሳደጊያ ማእከል፣ ለህዝበ ሙስሊሙ የተሠጡ ቦታዎችን ማልማት ነበር፡፡

የእነዚህ ቦታዎች ባህሪውንና አዋጭነቱን ካስጠናን በኋላ ቅደም ተከተል አዘጋጅተን ወደ ስራ ገብተን ነበር፡፡ ለምሳሌ የአንዋር መስጂድ ዙሪያ ካርታ እንዲወጣለት ተደርጎ ህዝበ ሙስሊሙን ማእከል ባደረገና ባሳተፈ መልኩ እንዲለማ ባለ ሀብቶችን፣ ምሁራንንና ተዋቂ ግለሰቦችን ባካተተ ቦርድ እንዲመራ ተደርጎ ነበር፡፡ የጠቅላይ ም/ቤቱ ጽ/ቤት የሚገኝበት ቦታ ያለ አግባብ ተቆርሶ ተወስዶበት ስለነበር፣ ቦታው እንዲመለስ እና ለልማት እንዲውል የአዲስ አበባን አስተዳደር ሳይታክተን ደግመን ደጋግመን ጠይቀናል፡፡ በሼኸ መሀመድ አማን አህመድ ተጀምሮ በሼኸ አብዱረህማን ሁሴን ሙዳ ጊዜ የተጠናቀቀው በተለምዶ የሙስሊም አደባባይ የሚባለውን 174 ሺህ ካሬ.ሜትር እንዲያስረክቡን በተለይም ለእስላማዊ ዩኒቨርስቲ፣ ለኢድ አደባባይና ለመሰል የልማት ተቋሞች እንድናለማ፣ የልማቱን ዝርዝር መግለጫ አዘጋጅተን አቤቱታችንን ለጠቅለይ ሚኒስተሩ ሳይቀር ያለመሰልቸት በአካል አስረድተን በማመልከቻም ጠይቀን እሳቸውም መፍትሔ እንድናገኝ መመሪያ ሰጥተውልን ነበር፡፡

ለምሳሌ ያህል በተለያዩ ክልሎች ያሉትን የፌዴራል መጅሊስ ይዞታዎችን እና ወሊሶ የሚገኘውን የህጻናት ማሳደጊያ ቦታ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር፣ ፒያሳ በሚገኘው የአወልያ ትምህርት ቤት የሚገኝ ይዞታን የንግድ ማእከል ለማድረግ ከኢስላሚክ ዲቨሎፕመንት ባንክ ጋር ሰፊ ስራ ተሰርቶ ነበር፡፡ በተለይም ፒያሳ የሚገኘውን የአወልያ ትምህርት ቤት ይዞታ የንግድ ማእከል ለማድረግ የተደረገው ጥረት ኢስለሚክ ዲቨሎፕመንት ባንክ በራሱ ባለ ሙያዎች አስጠንቶ ከባንክ ወለድ ነጻ የሆነ ከ25 ሚሊዮን ዶላር ወይም ባሁኑ ምንዛሬ ከ700,000,000.00ብር /ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር/ በላይ በረዥም ጊዜ በሚከፈል ብድር ፈቅዶልን ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢስላሚክ ዲቨሎፕሜንት ባንክ ተዘዋዋሪ ፈንድ በልዩ ልዩ አገሮች ባስገኘነው እስኮላር ተምረው በስራ ላይ የሚገኙ ምሩቃንን በማሰባሰብና በማወያየት፣ በተዘዋዋሪ ፈንድ የተማሩበትን ከ200,000,000.00ብር /ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር/ በላይ የሚሆን ገንዘብ ለጠቅላይ ም/ቤቱ እንዲያስገቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ይህም ‹‹የዋህብያ›› ሆነና ወደ ተግባር እንዲለወጥ አልተፈለገም፡፡

10. ከተለያዩ ሀገሮች ማለትም ከሳውዲ፣ ከጀርመን፣ ከቱርክ፣ ከሱዳን፣ ከግብጽ፣ ከማሊዥያ፣ ከኢንዶኒዥያ ከመሳሰሉ ከተለያዩ የሀገር መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረግነው መግባባት መሠረት ለ500 የማስተርስ እና የፒኤችዲ በተለያየ የትምህርት መስክ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች የነፃ ትምህርት እድል አግኝተን ይህም ጉዳዩ በሚመለከተው የመንግስት አካል በኩል እዲፈቀድልን እና እንዲተገበርልን ጠይቀን ነበር፡፡ ይህም የሙስሊሞች በልዩ ልዩ የሳይንስ ዘርፎች መማር የማይዋጥላቸው ወገኖች ከ‹‹ዋህብያ›› ጋር አያይዘው ተፈጻሚ እንዳይሆን የቤት ስራቸውን ሰሩብን፡፡

በአጠቃላይ እቅዶቻችን እንዳይሳኩ በርካታ ምስጢራዊ ድራማዎች ተካሂደውብናል፡፡ በህዝብና በመንግስት ከበሬታ የተሠጣቸውን ሰዎች እኛ ለቦርድና ለልማት ስራዎች ስንመርጣቸው <<ዋህብያ>> የሚል ታፔላ እየተለጠፈባቸው አብረውን እንዳይሰሩ ጫና ይደረግብናል፡፡ ኢስላሚክ ዲቨሎፕሜንት ባንክ ከመሳሰሉ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ስናገኝ ከ <<ዋህብያ>> ጋር ያዛምዱብናል፡፡ በዚህ የተነሳ ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን አገሪቷም እንድታጣ ተደርጓል፡፡ ሌሎችም በእንጥልጥል ላይ የነበሩ በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ከተለያዩ ሀገራት ድጋፍ የተገኙ ፕሮጀክቶች እንዲመክኑ ሆነዋል፡፡ ከመጨረሻው ድራማ በፊት ከአራት ጊዜ በላይ የተናጠል እና የቡድን የግልበጣ ሙከራ ተደርጎብናል፡፡ የፍትህና የደህንነት ሰዎች በፌዴራል ሚኒስቴር አስተባባሪነት በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ያገኘነው ተቀባይነት ስላሳሰባቸው ከክልል እስከ ቀበሌ አባሎቻችንን በማስፈራራት ያደረጉት ደባና ሴራ አስመልክተን ብንጮህም ሰሚ በማጣት ኢስላማዊ እቅዶቻችንና ልማታዊ ግቦቻችን እንዲመቱና ደግም እንዳያንሰራሩ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በላይ ባጭሩ ለመግለጽ የሞከርናቸው አንኳር ጉዳዮች፣ የአገራችን መጅሊስና የህዝበ ሙስሊሙ ፍላጎቶች እንደሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በየትኛውም መስፈርት ‹‹ዋህብያ›› ጠንከራ መንፈሳዊ ተቋም የሚጠላ፣ ትምህርትና ልማትን የማይወድ ወዘተ ከሆነ፣ ከላይ የተዘረዘሩ ጉዳዮች ይህን መስፈርት የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑ የመጅሊስና የህዝበ ሙስሊሙን ጉዳዮች ይዘን ስለታገልን ብቻ ለየካቲት 29/2007 የጠቅላይ ምክር ቤቱን መደበኛ ጉባዔ ጠርተን በዝግጅት ላይ እያለን፣ የካቲት 15/2007 ባላወቅነውና ባልተገኘንበት፣ ተመርጠን ሁለት አመት ተኩል እንደቆየን፣ የአምስት አመት የምርጫ ዘመናችንን እንኳን ሳንጨርስ ከኃላፊነት መነሳታችንን ከራዲዮ ፋናና ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንድንሰማ ተደርገናል፡፡