ጋምቤላና የዘውግ ፖለቲካ ተግዳሮት
***
ቴዎድሮስ ኀይለ ማርያም (ዶ/ር)
(የታሪክና የብሔርተኝነት ጥናት ምሁር)
***
በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተንጣልላ የምትገኘው አረንጓዴዋ በረሃ ጋምቤላ በውስጧ አምስት ዋና ዋና ተወላጅ ብሔረሰቦችና፣ ቀድሞ ደገኛ የሚባሉ ዛሬ ደግሞ በመጤነት የተመደቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖሩባታል። ከአገሬው ብሔረሰቦች ዋነኞቹ አኙዋ፣ ኑዌርና መጀንግር ቢሆኑም፣ ባለፉት መቶ ዓመታት የጋምቤላ ውስጣዊ ፖለቲካ ወሳኝ ጉዳይ በአኝዋና በኑዌር መካከል የነበረው ክፉም ሆነ ደግ መስተጋብር ነበር። እነዚህ ወንድማማች ብሔረሰቦች በአሰፋፈር፣ በባህል፣ በኤኮኖሚ ዘይቤና ማኅበራዊ አደረጃጀት ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ ለረዥም ዘመናት በጋራ ልማድ፣ በጋብቻ፣ በታሪካዊና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ተሳስረው አንዴ ሲጋጩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲታረቁ ኖረዋል።
በአስተዳደራዊ ቅርፅ ከወረዳነት እስከ ክልላዊ መንግሥትነት የዘለቀችው ጋምቤላ፣ ከ1890ዎቹ ጀምሮ ባለፉት መቶ ምናምን ዓመታት ሦስት የኢትዮጵያ አገዛዞች ተፈራርቀውባታል። እነዚህ መንግሥታት የተከተሉት ከበርቴያዊ፣ ኅብረተሰባዊና ጎሳዊ የአስተዳደርና ፖለቲካ መርሆዎች የክልሉን ማኅበራዊ ግንኙነት ከሚዘውሩ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ነበሩ። ዛሬ በጋምቤላ የሚታየውን ግራ የሚያጋባ የደም መፋሰስ አዙሪት ለመረዳት፣ በነዚህ ዘመናት የታዩትን ታሪካዊ ሒደቶች መተንተን ያስፈልጋል። በነዚህ ዘመናት የሕዝቦች አሰፋፈርና እንቅስቃሴ እንዴት ነበር? በቡድኖች መካከል ያለውን ግንኙነት የቀየሩ ውስጣዊና ውጫዊ መንስኤዎች ምንድናቸው?

ዘውዳዊ አባታዊነት
***
ከመነሻው ታላቁ የጋምቤላ ችግር ውስጣዊና ውጫዊ የመሬት ወረራ ነው። ውስጣዊ ወረራ በክልሉ ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረግ መገፋፋት ሲሆን፣ ውጫዊ ወረራ ደግሞ ከክልሉ ውጭ ባሉ መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶቸና ቡድኖች የሚከናወን ነው። ኢትዮጵያና እንግሊዝ የድንበር ስምምነቱን በፈረሙበት በ1895 አኙዋኮች ከሞላ ጎደል በምዕራብ ከፒቦር ወንዝ እስከ ምሥራቅ ባሮ ቀላ ድረስ በሙሉ ጋምቤላ በተለይም በዋነኞቹ ወንዞች በባሮ፣ ጊሎና አኮቦ ዳርቻ ሰፍረው ይኖሩ ነበር። በአንጻሩ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ከጅካኒ ኑዌር ክፍል የሆኑ ጥቂት ጋጃኮች በአዱራና በላሬ፣ ጥቂት ጋጆኮች ደግሞ በኮቻር ይኖሩ ነበር።
በአጠቃላይ በዘውዳዊው ሥርዓት በኹለቱ ጎሳዎች መካከል የድንበር መገፋፋቱ እየተጠናከረ ቢመጣም፣ ግጭቶቹ አካባቢያዊ ገጽታ ያላቸውና በማኅበረሰቦች መካከል በሚደረጉ ዘልማዳዊ ድርድሮችና ውለታዎች የሚዳኙ ነበሩ። በአብዛኛው መንስኤያቸውም እንደ ድርቅና የመሬት መራቆት፣ የሕዝብና ከብት ብዛት መጨመር የመሳሰሉ ተፈጥሮአዊ ችግሮች ነበሩ። ውጥረቶችም በምዕራባዊው የጋምቤላ ድንበር አካባቢዎች በተለይም በባሮ፣ በጊሎና በአኮቦ ወንዞች ጫፎች የተወሰኑ ነበሩ።
ዘውዳዊው አገዛዝ በአውራጃው የዘረጋው አስተዳደር ደካማ ቢሆንም፣ ሁለቱን ዋና ዋና ጎሳዎች ለመዳኘት፣ በመካከላቸው ሠላም ለማምጣትና ቡድናዊ ስሜቶች እንዳይጋነኑ በብሔራዊ የዜግነት መንፈስ ለማነጽ የበኩሉን ጥረት አድርጓል። የጋራ የሆኑ የፖለቲካና ማኅበራዊ አማራጮችን ለመፍጠር፣ በሲቪል አገልግሎቱ፣ በውትድርናው፣ በአስተዳደሩ፣ በትምህርት፣ በገበያና በፍርድ ቤቶች ተጓዳኝ መስተጋብሮችን መሠረት ጥሏል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ጅማሮዎች መቅኖ ሊያገኙ አልቻሉም። ከሁሉም በላይ የመጀመሪያው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት (ከ1948 እስከ 1964) በወቅቱ እስከ 30 ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞችን ወደ ጋምቤላ እንዲጎርፉ በማድረግ የክልሉን ሠላም አደፍርሷል። ጦርነቱ በድንበር አካባቢ የሚገኙ አኙዋክና ኑዌር ኢትዮጵያውያንን ከመጉዳት አልፎ፣ ለወትሮ ወቅታዊ ሰፋሪ የነበሩ የሱዳን ኑዌሮች በአኙዋክ መንደሮች ላይ ከፍተኛ ግፊት እንዲያሳድሩ አድርጓል። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያና ሱዳን በ1958 ያደረጉት ስደተኞችን ከድንበር አካባቢ ወደ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ያህል አዝልቆ የማስፈር ስምምነት፣ ግጭቱን ከአኮቦ፣ ጅካዎና ጆር ወረዳዎች አሳልፎ ወደ ማዕከላዊ የአኙዋክ መሬቶች ወደ ኢታንግ፣ ጎግና ጋምቤላ ድረስ ለማስፋፋት ረድቷል።
በአኙዋክና ኑዌር ጎሳዎች መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ በዚህ ምክንያት የሻከረ ቢሆንም፣ እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ድረስ መስተጋብራቸው በዘልማዳዊ ውለታ ላይ የተመሠረተ፣ በእንግዳና በተቀባይ ደንብ መግባባት የሚፈፀም ነበር። ይህ ማለት የተለያዩ የኑዌር ጎሳዎች በአኙዋክ መሬቶች ላይ በድርድር መስፈራቸውን ቢቀጥሉም ባለርስቶቹ ማን እንደሆኑ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።
ኅብረተሰባዊ ኢትዮጵያዊነት
***
ወታደራዊው ደርግ በ1966 ጀምሮ አስተዳደሩን ጋምቤላ ላይ ሲዘረጋ ፣ በመጀመሪያ ከቀድሞው የተለየ መሠረታዊ ለውጥ አላመጣም ነበር። ሆኖም አኙዋኮች በሽግግሩ ዓመታት በመኸል ወረዳዎች ሰፍረው በሚገኙ ስደተኞችና ኢትዮጵያውያን ኑዌሮች ላይ ያላቸውን ቅሬታ በአመፅና በግጭት መግለጻቸው ለአገዛዙ የችግሩን አሳሳቢነት አስገንዝቦታል። ስለዚህም ደርግ የስደተኞችን ሁኔታ መቆጣጠር የጀመረው ከታኅሣሥ 1968 አንስቶ ነው። በዚያኑ ዓመት ኹለቱን ጎሳዎች ለይቶ ማስፈር ከመጀመሩም በተጨማሪ፣ በ1969 የጠረፍ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በመመሥረት እርምጃውን አጠናክሯል።
በተለይም አብዮታዊው መንግሥት ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአውራጃው ውስጥ ከፍተኛ ሕዝብ የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ዘመቻ በማካሄድ፣ የሁለቱን ጎሳዎች መሪዎች በአውራጃው አስተዳደር ውስጥ በማሳተፍ፣ የጋራ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ የዜግነት መንፈስን በማስረፅና ልዕለ ጎሳዊ የሆኑ መስተጋብሮችና ማንነቶችን በብሔራዊ ደረጃ ለማሳደግ ሞክሯል። ደርግ ኹለቱን ጎሳዎች በተለያዩ ሕዝባዊ ማኅበራት፣ በባህል ቡድኖች፣ በፓርቲ፣ በወታደራዊና ሲቪል መዋቅሮች ለማቀላቀል ከመሥራቱም በላይ፣ በተለይ በከተሞች ውስጥ በጎሳ ላይ የተመሠረቱ ማናቸውንም ማኅበራትን እስከ መከልከል ደርሶ ነበር።
ስለዚህም ጎሰኝነት የቱንም ያህል ስሜታዊ ኀይል ቢኖረውም ይፋ ተቋማዊ መፍሰሻ ሊያገኝና መላውን ብሔረሰቦች ሊያፋጥጥ አልቻለም። ለአብነትም ከፍ ያለ መጠን ያለው የኑዌር ሸንግ ረንግ ንዑስ ጎሳ ከሱዳን ተነስቶ በኢታንግ አካባቢ ካሉ አኙዋኮች ጋር በመደራደር የሰፈረው በ1975 ነበር። ይህ ወቅት በአጠቃላይ በአውራጃ ደረጃ ታይቶ የማይታወቅ መስተጋብር የተፈጠረበትና፣ ኹለቱ ማኅበረሰቦች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደጋራ አመለካከት መራመድ የጀመሩበት ነበር ለማለት ይቻላል።
ሆኖም ይህ ጅምር በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ሊደናቀፍ በቃ። አንደኛው እስከ 300 ሺሕ የሚደርሱ ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ጋምቤላ ያጎረፈው የኹለተኛው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት (1975 እስከ 1997) መቀስቀስ ነበር። ይህንን ተከትሎ ደርግ የስደተኞችን ፍሰት ለመቆጣጠር ካለመቻሉም በላይ፣ በኤርትራና ትግራይ የሽምቅ ውጊያው እየበረታበት ሲሄድ ጋምቤላን ከናካቴው ለሱዳን ሕዝብ አርነት ንቅናቄ አሳልፎ ተወለት። የክልሉ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ እንደገለጹት አኙዋኮች በገዛ መሬታችን በስደተኞችና በአማፂ ኑዌሮች ተበደልን የሚል ቁጭት አደረባቸው።
በዚህ ውጥረት ላይ ወታደራዊው መንግሥት ሌላ የአኙዋኮችን ቅሬታ የሚያባብስ ፕሮጄክት ነደፈ። በግዙፍ የመልሶ ማስፈር መርሐ ግብር በታኅሣሥ እና በየካቲት 1977 ባሉት ወራት ብቻ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደገኞችን ከትግራይ፣ ከወሎና ከሸዋ አምጥቶ በአኙዋክ መሬቶች በአቦቦ፣ ኢታንግ፣ ጋምቤላ፣ ጎግ እና ጆር መንደሮች ሠርቶ ተከላቸው። ይህ እርምጃ አኙዋኮች ከሁለት ወገን እየተጠቃን ነው የሚል ስሜት እንዲያድርባቸውና በ1980 የጋምቤላ ሕዝብ አርነት ንቅናቄን በመመሥረት ለትጥቅ ትግል እንዲነሱ አስገደዳቸው። ይባስ ብሎ ደርግ በአውራጃው ዋና ዋና ወንበሮች ላይ የኑዌር ባለሥልጣናትን በመሾም ነገሩን አከረረው።
ዞሮ ዞሮ የደርግ የአያያዝ ዕቅዶች በአብዛኛው ከማዕከል ወደታች የሚፈስሱና አውቅልሃለሁ ባይ በመሆናቸው፣ አንዳንዶቹ ጎሳ ዘለል እርምጃዎቹም ነባር ዘልማዶችን፣ ስጋቶችንና ጥያቄዎችን ባለማገናዘባቸው፣ በተለይ ደግሞ በአውራጃው በነጻ የመንቀሳቀስና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን የመጋራት ዜግነታዊ ዕቅዶቹ በአኙዋኮች ዘንድ በጥርጣሬ መታየታቸው አልቀረም። ስለዚህም በቀናነት ሳይሆን በተጨባጭ የፖሊሲ ውጤቶች ከተመዘነ፣ የወታደራዊው መንግሥት ማሕደር አጥጋቢ አልነበረም።
ዘውጌ ብሔርተኝነት
***
ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጣው ኢሕአዴግ ሕልውናውን የመሠረተው ጎሰኛነትን መፍታት የሚቻለው እንደ ዋና ፖለቲካዊ ኀይል በመቀበልና መዋቅራዊና ሕጋዊ መገለጫዎቹን በመመሥረት ነው በሚል አስተሳሰብ ላይ ነው። ለተቀናቃኞቹ ደግሞ ይህቺን የተከፋፈለች አገር መግዛት የሚቻለው ማኅበራዊ ስንጥቆችን በማጠናከርና ሁሉም ወገኖች በውስጣዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲጠመዱ በማድረግ ነው የሚል ነው። በዚህም አለ በዚያ ኢሕአዴግ ጎሰኝነትን ብቸኛው የፖለቲካ መደራጃና የቁሳዊና ትዕምርታዊ ጥቅማጥቅሞች ማግኛ መንገድ አድርጎ መሠረተው።
በተለይ በጋምቤላ ረገድ ከ1983 እስከ 1987 ያለው የመሸጋገሪያ ወቅት ከኢሕአዴግ በመቀናጀት በትጥቅ ትግል ገፍተው በመጡት በአኝዋኮች የፖለቲካ የበላይነት ሰፈነ። ኑዌሮች በፊናቸው የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ የሚል ድርጅት መሥርተው ሥልጣን ለመጋራት ቢታገሉም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው። ኢሕአዴግም ጉዳዩን ለመፍታት በመጀመሪያ ክልሉን በኹለት ዞኖች ከፈለው። በሐምሌ 1987 የተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት አንደኛ ጉባኤም ጎሳዊ የሥልጣን ክፍፍል ቀመር አፀደቀ። ከዚህ በኋላ ፕሬዚዳንትነቱ ለአኙዋክ፣ ምክትልነቱ ለኑዌር፣ አፈጉባኤነቱ ደግሞ ለመጀንግር ተደለደለ።
የሚገርመው ነገር አብነት ይሆናል የተባለው የጎሳ ቀመር ጭራሽ አፋጂ ሆኖ አረፈው። ከ1988 እስከ 1992 የነበሩት ዓመታት በጎሳ መስተዳድር አከላለል፣ በወረዳዎችና ቀበሌዎች ስርጭት፣ በሥልጣንና በጀት ክፍፍል፣ በስኮላርሽፕ ዕድሎች ኮታ፣ በልማት ዕቅዶች ድልድል፣ በትምህርት ቋንቋ፣ ወዘተ. በተለይ በአኙዋክና ኑዌር ጎሳዎች መካከል ከፍተኛ ግጭቶችና ደም መፋሰሶችን አስከተለ። እነዚህ ግጭቶች በመጠናቸው በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖረውን መላውን ማኅበረሰብ ያቀፉና፣ በኀይለኝነታቸውም ታይተው የማይታወቁ ነበሩ። በኢታንግ ብቻ እንኳን በ1990 እና 1994 ክረምቶች የተካሄዱት ኹለት ታላላቅ ጦርነቶች በዘግናኝነታቸው የሚታወሱ ናቸው።
ኢሕአዴግ ከነሐሴ 1989 ጀምሮ ጉዳዩን ምናልባት ከሶማሌ ክልል ውጭ በየትኛውም ክልል ባልተደረገ የጎሳ መሐንዲስነት ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉ አልቀረም። የሁለቱን ጎሳዎች ፓርቲዎች በግጭት አራጋቢነት በመክሰስ፣ መሪዎቹን ከማባረርና በአዲስ ጥላ ማኅበር ሥር የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብሎ ከማሰባሰብ በተጨማሪ፣ በግልጽ የአኝዋክ፣ ኑዌርና መጀንግር ዞኖች ብሎ ለይቶ እሰከማስመር ደረሰ። አጨቃጫቂዋን ኢታንግ ወረዳንም በልዩ ዞንነት ደለደላት።
የኹለቱ ጎሳዎች ውጥረት ማዕከላዊ መንግሥትን በእጅጉ ስላስደነገጠው በ1995 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር መሥርቶ በአስቸኳይ ‹አማካሪዎቹን› ወደክልሉ ላከ። የኢሕአዴግ የጎሳ መርሕ በግልጽ ድክመቱ የተመሰከረው በአዋጅ ቁጥር 359/1996 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን በክልሎች ላይ ሲሰጠው ነበር። የጎሳ ግንኙነት አያያዙም ራሱ እንደሚያንቆለጳጵሰው ሳይሆን ከፍተኛና ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ከደርግ እምብዛም ያልተለየና ልኂቅ ተኮር የሆነ፣ በአውቅልሃለሁ ከላይ ወደታች፣ ከማዕከል ወደክልል የሚፈስስ ነው። በዚህም ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሳይሆን ወቅታዊ ትኩሳቶችን በማብረድ ዘይቤ የሚዋዥቅ በመሆኑ የትኛውንም ቡድን በቅጡ አላረካም። እንዲያውም የነበራቸውን ተስፈኝነት አለቅጥ አጎለበተው። ይባስ ብሎ ኢሕአዴግ ከጠቅላላ ነዋሪው ሩብ እጅ የሆኑትን ሌሎች ኢትዮጵያውያንን መጤዎች ብሎ በመፈረጅ ከክልሉ ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ስላገለላቸው በመሃል የነበራቸው የገላጋይነት ሚና እንኳን ፈፅሞ ጠፋ።
የኢሕአዴግ የጎሳ ቀመርና ባንቱስታን አከላለል በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሐቅ ጥንቅቅ አድርጎ ለማካተት አልቻለም። የማይጨበጥ ሕልም ነበር። በተለይም ደግሞ መንግሥት በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ተሻጋሪ የሆኑ፣ ልዕለ ጎሳዊ መስተጋብሮችንና ድልድዮችን ለመሥራት የረባ ጥረት ባለማድረጉ የተነሳ በረዥም ጊዜ አደገኛ ልዩነቶችን አስከተለ። የጎሳ ፓርቲዎች ዘልማዳዊ ባላንጣነትን ለማራመጃ ምቹ ጎዳናዎች በመሆን ግጭቶችን ከማርገብ ይልቅ ማባባስ ጀመሩ። በየደረጃው ያሉ አኙዋክና ኑዌር ባለሥልጣናት መንግሥታዊውን መዋቅርና ሀብት ለጎሳ ጦርነት ማካሄጃ እስከማዋል ደረሱ። ቢያንስ ሦስቱ ፕሬዚዳንቶች እና ዋና ዋና ሹማምንቶቻቸው በዚህ ጉዳይ ከወቀሳ እስከ እስር እርምጃ ደረሰባቸው።
በሒደት በኹለቱ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረጉ ግጭቶችም መላውን ብሔረሰብ ያሳተፉና በአመላመላቸውና በጭካኔያቸው ዘልማዳዊ ደንቦችን እንኳን የገሰሱ፣ ለምሳሌ ሕፃናትና ሴቶችን ጭምር በመግደል፣ ሆኑ። ጥላቻን በማባባስ ግንኙነቱ መልሶ የማይጠገንበት ደረጃ እስከመግፋት ደረሱ። ዘመነ ኢሕአዴግ ‹ሞኖፖላዊ ተከርቸም› የሚባለውንና እጅግ በተካረሩ ልኂቃን ፣ የተሽመደመዱ ተቋማትና መዋቅራዊ ግጭቶች የገነኑበት ሁኔታ ፈጠረ (ማልሴቪች 2006፤ ወልፍ 2006)።
በተለይም አኙዋኮች የደርግን የመጨረሻ ዘመን የሚያስታውሱ ግፎች እየተፈፀመብንና በኹለት ወገን እየተከበብን ነው እስከማለት ደረሱ። ከታኅሣሥ 1996 የደፈጣ ጥቃት በኋላ ክልሉ በተደጋጋሚ የግጭት አውድማ በመሆኑ ለተወሰነ ጊዜ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቢሮ ዕዝ ሥር እስከመዋል በቅቶ ነበር። ይሁንና የአኝዋኮችን ቅሬታና አመፅ የሚያባብሱ ጉዳዮች ቀጠሉ። ሰፋፊ የአኙዋክ መሬቶች በልማት ስም ለአገር ውስጥና ለባዕድ ባለሀብቶች ተሸነሸኑ። በምላሹም የደፈጣ ቡድኖች በተለያየ ጊዜያት መንገዶችን በመቁረጥ፣ የሕዝብ ማመላለሻዎችን በማጥቃት፣ ሌሎችም እንደ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ቢሮዎችን፣ የነዳጅ ፈላጊዎችንና የግል እርሻዎችን የመሳሰሉ ተጋላጭ ዒላማዎችን መምታት ቀጠሉ።
ፌዴራል መንግሥትም በበኩሉ የአፀፋ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ፣ ከ2005 ጀምሮ የክልሉን ፕሬዚዳንት ወንበር ለኑዌሩ ጋትሎዋክ ቱት ኮት በመስጠት ውጥረቱን አከረረው። የክፋቱ ክፋት ደግሞ ከ1997 በኋላ ረግቦ የነበረው የደቡብ ሱዳን ችግር እንደገና በ2005 በማገርሸቱ፣ በየዓመቱ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደጋምቤላ ክልል መጉረፍ ቀጠሉ። ቀለበቱ መልሶ በይበልጥ ጠበቀ ማለት ነው።
ታዲያ የጋምቤላ ዕጣፈንታ ምንድነው?
***
በቀድሞይቱ ጋምቤላ ዘልማዳዊ ጎሰኝነት ባሕላዊ መልክ ያለውና በቋንቋና ትዕምርታዊ መንገዶች የሚገለጽ ነበር። በተጨማሪም አካባቢያዊና ውሱን፣ በማኅበረሰቦች መካከልም መደጋገፍ፣ መዋሐድ፣ መረጋጋትና ቁጥብነትን የሚያሰፍን ነበር። ይህ ጤናማና ተፈጥሯዊ ሒደት የተናወጠው ከሃያኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ በኋላ በክልሉ የተከሰተውና በአካባቢያዊ እውነታዎችም ሆነ በዕድሜ ጠገብ ልማዶች የማይገዛው የሕዝብ ማዕበል በጎረፈበት ወቅት ነበር። በውጤቱም ሁለቱ ማኅበረሰቦች ከክልሉ ጫፍ እስከ ጫፍ እንዲፋጠጡ ዕድል በመክፈት፣ ዘመናዊና ቡድናዊ የሆነውን ለሥልጣን፣ ለግዛትና ለሀብት የሚደረግ ጎሰኝነት ወለደ።
ታሪካዊ ትንታኔ እንደሚያመለክተው ሁለቱ ማኅበረሰቦች በኤኮኖሚያዊ ሀብቶች አንፃር ያላቸው ግንኙነት፣ በተለይም ኑዌሮች ዋነኞቹን የክልሉን ወንዞች ለመጋራት ያደረጉት ግፊት፣ በአኙዋክና በኑዌር ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ጎሰኝነት ባሕርይ፣ መጠንና መገለጫ መንገዶቹን የሚገዛ ዋነኛ መንስኤ ነው። ከላይ እንደተገለጸው ይህ ሒደት ዝግተኛ፣ ነጠላና አነስተኛ እስከሆነ ድረስ የክልሉን ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ ሥርዓት አላናጋም።
ሌላው ዐቢይ ገዥ መንስኤ የኢትዮጵያ መንግሥትና የአዘማኝነት ተጽዕኖው ነው። ማዕከላዊው መንግሥት በአኙዋክና በኑዌር መካከል ያሉትን አለመግባባቶች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማስታረቅ ባለመቻሉ፣ ለአኙዋኮች ተገቢ የዕጣ ፈንታ ፍርሐት አስተማማኝ ዋስትና አለመስጠቱና እያደርም በአንዱ ወይም በሌላው ዐይን ሕጋዊነትና ቅቡልነቱ እየተሸረሸረ መሄዱ ችግሩን የከፋ አድርጎታል። ግጭት የህልውና ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል።
ጋምቤላ ከማዕከል ለሚወረወሩ ርዕዮተ ዓለማዊ ማነቆዎች ተመችታ አታውቅም። በዘውዳዊውና በአብዮታዊው መንግሥታት የተተገበረው ጎሰኝነትን የማጣጣልም ሆነ በጉልበት የማዋሐድ መርሕ፣ እንዲሁም በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የተያዘው ጎሰኝነትን የማንቆለጳጰስና በጉልበት የመለያየት ሥራ ከክልሉ እውነታ ጋር ፍፁም ሊሰምር አልቻለም። ከመሃል የሚፈበረኩ ፖሊሲዎች የማኅበረሰብ ዘለል መስተጋብሮችን መሠረታዊ አመክንዮ የሳቱና፣ ግባቸውም ‹በአስገዳጅ የበላይነት፣ በሽንገላ አገዛዝና በውሱን ራስ-ገዝነት› የተደመደመ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ነው። ስለዚህም በክልሉ ውስጥ ያለው የማኅበረሰቦች ሠላም ይበልጥ እየደፈረሰና ደም አፋሳሽ እየሆነ፣ ጥላቻውም ጠቅላላውን የማኅበረሰቦች ሕይወት እየመረዘ፣ የማይቀለበስበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል።
