በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት – ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)

*** BlackLion ***

ኹለት ርዕሰ-ጉዳዮች የአገራችንን ፖለቲካ ከአርባ ዓመታት በላይ ተቆጣጠረውት ቆይተዋል፤ የመደብና የብሔረሰብ ጥያቄዎች፡፡ ከየካቲት 66 ሕዝባዊ አብዮት እስከ 1983 ዓ.ም. የመደብ ጥያቄ ከፍ ያለ ቦታ ይዞ የቆየ ሲሆን፣ ከ1983 ወዲህ ደግሞ የብሔረሰብ ፖለቲካ የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ ሆኗል፡፡

እነዚህ ኹለት አጀንዳዎች ፖለቲካችንን ፍጹም ስለተቆጣጠሩት፣ ዜግነትና በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ምንም ዓይነት ትኩረት ተሰጥቶት አያውቅም፡፡ በእኔ እምነት ትልቁ ችግራችን ይህ ነው፡፡ የመደብም ይሁን የዘውግ ፖለቲካ ኅብረተሰብን በ“እኛ” እና “እነሱ” የሚተነትን፤ ከሠራተኛው መደብ ወይም ከወዛደሩ፣ ከዚህኛው ዘውግ ወይም ከዚያኛው ወዘተ. እያለ በተካረረ የቡድን ውድድር (ብዙውን ጊዜም በወዳጅ-ጠላት ትንታኔ) ላይ የሚያተኩር የፖለቲካ ዘይቤ ነው፡፡

የመደብንም ይሁን የዘውግ ጥያቄን ዋናው የመታገያ አጀንዳ አድርጎ መደራጀት የሚፈልግን የኅብረተሰብ ክፍል መከልከል አይቻልም፡፡ እርግጥ ከኢትዮጵያ በስተቀር በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ዘውጋዊ ማንነትን መሠረት አድርጎ መደራጀት በሕግ የተከለከለ ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን ይህን ጉዳይ በሚመለከት ብዙ ርቀት ስለመጣን መከልከል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

የተሻለው መፍትሔ፣ ሌሎች በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱ ወገኖች ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ማዕከል አድርገው የሚደራጁበትን መንገድ ማመቻቸትና መደገፍ ነው፡፡ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ሲባል፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ የመምረጥና የመመረጥ፣ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በነጻነት (ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት) ተዘዋውሮ የመሥራት፣ የመደራጀት፣ ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ፣ በግሉም ይሁን ከሌሎች በሐሳብ ከሚግባባቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር ተደራጅቶ የመቃወምና ተጽዕኖ የማሳደር ወዘተ. መብት አለው ማለት ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በዘውጋዊም ይሁን በሃይማኖታዊ ወይም በመደባዊ ማንነቱ መገለል ሲደርስበትና በደል ሲፈፀምበት በደል ያደረሰበትን አካል በፍርድ ቤት ከስሶ መብቱን ማስከበር፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን አልፈው ወይም ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም በደል ሲፈፅሙ፣ በፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ወዘተ. የጠንካራ ዜጋ መሠረታዊ መለያ ነው፡፡ ዜግነታቸውንና ዜግነት የሚያስገኘውን በረከት የተገነዘቡ ወገኖች የእኔ ዘውግ ወይም ሃይማኖት አባል ሳይሉ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የማስተናገድ፣ እነሱም በዚህ አግባብ የመስተናገድ ባህል አላቸው፡፡

በአገራችን ዘውጋዊ ማንነትን መሠረት አድርገው የተደራጁ በጣም በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እንወክለዋለን የሚሉትን ዘውግ ብቻ ለይተው ስለሚያቀነቅኑ በኢትዮጵያዊያን መሀከል በከፍተኛ ደረጃ ጥርጣሬና አለመተማመን ነግሷል፤ ጥላቻ፣ ግጭትና መፈናቀልም የዘወትር ድርጊት እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የምንቀጥል ከሆነ ሁላችንም ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ በጽንፈኛ ቡድናዊ አስተሳሰብ የተከፋፈለና የተቋሰለን ኅብረተሰብ ዴሞክራሲ ሊያድነው አይችልም፤ እንዲያውም በእሳቱ ላይ ቢንዚን ነው የሚያርከፈክፍበት፡፡ ይህ ጽንፈኛ የሆነ የዘውግ ፖለቲካ ሊታረቅ የሚችለው በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ማዕከላዊ ቦታ ሲያገኝና ሚዛኑን ሲያስተካክለው ብቻ ነው፡፡

አገራችን በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱ ንቁ ዜጎችን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ መገናኛ ብዙሃንን፣ የሐሳብ ጎተራዎችን (think-tanks) ወዘተ. ትጣራለች፡፡

ምን ይመስላችኋል?
መወያየት መልካም ነው፤ እስኪ እንወያይ …