አህጉራችን አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ተላቋል ቢባልም የአስተሳሰብና የህሊና ባርነት ወረርሽኙ ጭራሽ ተባብሷል፡፡ የምዕራባውያን የባህል ወረራ ድህረ ቅኝ ግዛት ለመቀጠሉ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስም ይቻላል፡፡ አፍሪካውያን ለራሳችን ማንነት የምንሰጠው የተዛባ ግምት ያስከተለው ተፅዕኖ ነፀብራቅ በተከታዩ ትውልድም የሚያባራ አይመስልም። ወደ ተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ለመግባት ይረዳን ዘንድ በአገርኛ ቋንቋ ስያሜ አጠቃቀምና ትርጓሜ ረገድ የሚስተዋሉጥራዝ ነጠቅነት ላይ ማተኮር ፈለግን፡፡
ቋንቋ የሰው ልጅ በሀሳብ ለመግባበት የሚጠቀምበት ዓይነተኛ ስልት ነው፡፡ ሆኖም ግን የአንድን ቃል አቻ ፍች በተሟላ ሁናቴ የማናገኝበት አጋጣሚ በመኖሩ ምክንያት ብቻ አስገዳጅ የተውሶ ቃላቶች እዚህም እዚያም መሰግሰግ እንደ ጊዜያው መፍትሄ ሲወሰድ ቆይቷል፡፡
አገራችን ሰፊ የባህልና ታሪክ ስብጥርን ተላብሳ የራሷን ፊደል የምትጠቀም መሆኑ በመላው ዓለም የማይካድ ሥልጣኔ ባለቤት ናት፡፡ ሆኖም በዓለማቀፋዊነት ሰበብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለቅጥ እየተስፋፋ የመጣው መዘበራረቅ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አስከትሏል፡፡ እውቀትን ለማስፋፋት ሲባል ከሥነ ልሳንና ሥነ ጽሑፍ ሊቃውንት እውቅና ውጪ የባዕድ ወይንም ዲቃላ ቃላትን በሰፊው የመጠቀም አዝማሚያ መኖሩ አልቀረም፡፡ በተለይም የሣይንስና ቴክኖሎጂ መገለጫ ቋንቋ አመችነት ላይ አሁንም በአማርኛ ቋንቋ ረገድ እየተደረገ ያለው ሙከራና ጥረት አመርቂ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮዽያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ከትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጋር የመፍትሄ ፍለጋው ጅማሮ እምብዛም አልተሰራበትም፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ከመዝገበ ቃላት እስከ ሰዋሰው ማስተማሪያ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የህትመት ጥረቶች ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህ እና መሰል ማጣቀሻዎች ተጠናክረው ባለመቀጠላቸውና በቸልተንነት በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በወጭ የባዕድ ቃላቶች ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት አስከትሏል፡፡
ለልዩ ልዩ የግል ድርጅቶች የምናስተውለውን ለጊዜው እንተወውና በመንግስታዊ ተቋማት የሚሰጡ ስያሜዎች አገርኛ ያለመሆናቸውና አማርኛው ውስጥ እንግሊዝኛ እየተሰነቀረ ጉራማይሌነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለመሆኑ በተለይም በብዙን መገናኛ ጭምር ጥራዝነጠቅነቱ ትኩረት ያለማግኘቱ ያበሳጫል፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን ብንጠቅስና ብንተች ምን ይለናል፡- ኢትዮ-ቴሌኮም፤ የኮንስትራክሽ ሚኒስቴር፣ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ፣ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች፣ የብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽ፣ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን፣ አርሚ አቬሽ፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ ባህልና ቱሪዝም፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ትብብር፣ የማዕድንና ኢነርጅ፣ ኤሌክትሪክ ባለስልጣን፣ ስፖርት ኮሚሽን፣ ጄንደር ሜንስትሪሚንግ፣ ወዘተረፈ የመሳሰሉትን እንዳሻን ሰይመናቸዋል፡፡ ትችቱ ምን ያህል ከህሊና ጥገኝነት መላቀቅ እንዳልተቻለ የሚያስረዳ በመሆኑ የራስን ፈልጎ ከማዳበር ይልቅ በሌሎች የተውሶ ቃላት መጠቀም ስንፍናን እንድንለማመድ መንገድ ከፍቷል፡፡
ዘላቂ ስያሜዎችን በአገርኛ በሕዝብና በተጠቃሚው ዘንድ በሥርኣት እንዲለመዱ ህጋዊነቱን የሚከታተልና እርምት የሚወስድ አካል ያለመኖሩም ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ መገልገያ መሳሪዎች፣ ተቋማትን የመሳሰሉትን ለወደፊቱ ትውልድ ማቆየት የግድ ይላልና አስተያየቱ ከዚህ አንፃር መርምሮ መቃኘት ይኖርበታል፡፡ በህትመት ዝግጅት ላይ የሚገኙ፣ የብዙሃን መገናኛዎች፣ የትርጉም ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት፣ የመዛግብተ ቃላት አሰናጆች፣ ኀያሲዎች፣ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፀ መስክ ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች በሙሉ ያላቸውን ሰፊ ልምድ ከቋንቋና ሥነ ልሳን እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ አጋዥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉና ቀዳሚ ተግባርና አገራዊ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በስያሜ አሰጣጥና ትርጓሜ ረገድ አጥንቶና መርምሮ የሚያፀድቅ ራሱን የቻለ ደረጃ መዳቢና ባለድርሻ አካል መቃቃም አስፈላጊ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በዘፈቀደ መቀያየርንም ችገር ስለሚያስቀር ቋሚና ዘላቂ ስያሜዎችን ዘመን ተሸጋሪ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ ከመንዛዛታቸው የተነሳም ካላስፈላጊ መሰላቸት ይታደጋሉ፡፡ የመንግስታዊ ተቋማት አሰያየም አጠር ቢልና ባያሰለች ፋይዳው ቀላል ስላልሆ በአግባቡ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ ይህን ጠቆም ስናደርግ ትኩረት ቢያገኝ ከታሪካዊ ተወቃሽነትም ያድናል፡፡ ቸር ይግጠመን!!!
