መንግስቱ ሙሴ
መደራጀት መሰረታዊ የዴሞክራሲ መብቶች አካል ነው

ዜጎች መደራጀት ሲጀምሩ እና የመደራጀትን ጥቅም ሲያውቁ ጨቋኞች እና ጭቆናቸው ቦታ ቦታውን ይይዛሉ። በጸረ ኢትዮጵያ ጎራ የተሰባሰቡት ለአለፉት 50 አመታት በዋነኛነት ባተሌውን እና ደበሎ ለባሽ አርሶ አዳሪውን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው በማያውቀው እና ባልሰራው ወንጅለው ጉድጓድ ቆፍረው ሲቀብሩት፣ በገደል ሲወረውሩት፣ ከቀየው ተነስ ብለው በትውልድ ሀገሩ ስደተኛ ሲያደርጉት ከልካይ እና ሀይ ባይ አላገኙም። ሚጢጢዋ የትግራይ ጠባብ ቡድን አማራ ጠላቴ ብላ በኢትዮጵያ ምድር እና ታሪክ፤ ያውም የስልጣኔ ምንነት በማይታወቅበት ዘመን ያልተሰራ በደልን ስትፈጽም ይህ ሕዝብ በቋንቋው እና ቀየው ተደራጅቶ አይመክተኝም ከሚል እምነት በመነሳት ነበር። የጭቆናው ዳር ግን አሁንም እየቀጠለ ያለው ያውም በተከታታይ ጦር ሰብቀው ከገፉት ደርቡሾች እና የአውሮፓ ወራሪወች ተዋግቶ ያስከበረውን ዳር ድንበሩን የአባት አያቶቹን ባድማ ያንተ አይደለም ተነስ ብለው ሲያፈናቅሉት ብዙወቻችን ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ፋይዳ አልሰራንም። ድጋፍ ለማሰባሰብ እና እንዲደርስለት ለማድረግ እንኳን አቅሙ እና መንገዱ ተዘግቶብን በተስፋ ቢስነት ተቀምጠን አይተናል።
የተበደለው አማራ ቢደራጅ ኖሮ በሰሜን ወሎ የተካሄደበት ጭፍጨፋ። የባሕርዳር እልቂት፤ በጎንደር፣ በዳባት፣ በወልቃይት፤ በአርማጭሆ፣ በመተማ የተካሄደው ሁሉ ወንጀል ባልተፈጸመበት። ቢያንስ በዳይ እና ገዳይ መልስን ስለመፍራት እራሱን እና ወታደሩን በሰበሰበም ነበር። የዘር ፖለቲካ ቦታውን በያዘበት እና መንግስታዊ እና ህገመንግስታዊ ስልጣን በእጁ ባስገባበት አንዱን ለምን ትደራጃለህ ስጋት ነህ ማለት ከባድ ፍርደገምድል እና አድላዊነትም ይሆናል። ስለብሄራዊ አንድነት ስናወራ፣ ስለዴሞክራሲ እና እኩልነት ስንሰብክ የዜጎች መብት የተገደበነቱን ከሰበክን ስህተት እንፈጽማለን።
የዴሞክራሲ መብትን በገደብ እና ያለገደብ በሚለው የዛሬ 43 አመት በኢሓፓ እና በመኢሶን የተካሄደው ክርክር እና በኋላም ያስከተለውን ልዩነት እያስታወስን ነው። መብት ገደብ እና ድንበር የለውም ያሉት የኢሕአፓ ታጋዮች ምልአተ ሕዝቡን ከጎናቸው ማሰለፋቸውን እናስታውሳለን።
መደረግ ያለበት የዘር ፖለቲካ አጥፊ እና አፍራሽ ነው ካልን ሁኔታወችን በትግል መለወጥ ይኖርብናል።፡የአንድነቱ ጎራ እውነተኛ የአንድነት ኃይል ሆኖ መውጣትን ይጠበቅብናል። ከተበደሉ ዜጎች ጎን እየሞተም መሰለፍን እና በተግባር ማሳየትን ያስገድዳል። ዛሬ ከወደመተከል የሚፈልሰው ዜጋ በእርግጥም የት የሌለ እና ማቆሚያው የት እንደሆነ የማይገመት እስከመሆን ደረጃ ደርሷል። ይህ ክልል ደግሞ በአጭሩ የጠላት ጦርነት እንኳን ለኢትዮጵያ አርበኞች መከለያ ወንዝ እና ሸንተረሩ ተስፋ እና መከታ የነበር ብሎም የነጻነት ጮራ ቀድሞ የፈነጠቀውም ኦሜድላ እና፣ ጉባ፣ በለያ፣ ማቡክ፣ የስመጥር አርበኞች ጀርባ የነበር አካባቢ ዛሬ የልጅ ልጆቻቸው አገራችሁ እይደለም ተብለው ሲገፉ፣ ሰለባ እና ግድያ ሲደረግባቸው። አገር ለቀው ሲንጓለሉ ታዲያ ምን እንዲሆን ይጠበቅ ነበር? እኔ ነኝ ያለ ምሁር የማይመልሰው ጉዳይ እና ፈተና ነው።
በነገራችን ላይ ኢሕአፓ የመጨረሻ ውጊያውን ከህወሓት ጋር ያደረገበት አካባቢም ነበር። ስመጥሯ የሴት ኮማንደር አያልነሽ በዚህ አካባቢ እና በጎጃም ሕዝብ እንደአለኝታ የተጠራችበት መነሻውም ከዚህ ነበር። አሁን ህወሓት በፈጠረችው የዘር ክልል ግን ዜጎች መኖር ያልቻሉበት እና የቀን ተቀን ሰቆቃ የምንሰማበት ሆኗል።
የልቅ በወግ እና በክብር እንደመሰረታዊ መብትም መደራጀትን ደግፎ ተባብሮ በአንድነት ጭቆናን ለማስወገድ መስማማት የተሻለ በይበልጥም አመች የሆነ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ሕወሓት አላሸለበችም። ህወሓት ግዜ እና ቦታ እየጠበቀች ነው። እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ህዝባዊ ማድረግ ተገቢ ነው። ቄሮ በመደራጀቱ ለመፍትሄ መንገድ ጠረገ፣ በክልሉ ቢያንስ የህወሓትን የበላይነት አስወገደ። ባጭሩ ዜጎች ሲደራጁ እሰየው በርቱ ማለት ተገቢ ስለሆነ በርቱ ተመንደጉ እንላለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
