1985፡ ኤርትራ Vs ኢትዮዽያ (የመለያየት ጨዋታ) ውጤት 1 ለ 0

ኤርትራውያን ወደባችንና ባህራችን ብቻ አንደላቆ ያኖረናል አሉ፡፡ በዚያ ላይ ዕድሜ ለጌታችን ጣሊያን ስልጡን ነን ብለውም አመኑ፡፡ስለዚህ ለቀቅ አድርጉን አሉን፡፡ ብለውም አልቀሩ 30 ዓመት የፈጀ ጦርነት ከወገኖቻቸው ጋር አካሂደው ነጻነት ወይም ባርነት ተብሎ በሚጠራ ሕዝበ ውሳኔ መለያየት ሞት ነው ሳይሆን መለያየት አንዲህ ነው በማለት ለመቶ ፈሪ በሆነ ድምጽ ቻው አሉን፡፡ ይህንንም ለአለም አወጁ፡፡በነገራችን ላይ ነጻነት የተባለው ኢትዮዽያ ቅኝ ገዥ ናት ተብሎ ነው፡፡ አይ ፖለቲካ፡፡ይህን ካመኑ ደግሞ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዳደረጉት ነጻ ሲወጡ ወሰናቸው በቅኝ ግዛት ወቅት የነበረው መሆን ነበረበት፡፡የአልጀርሱ ስምምነት ለምን አስፈለገ፡፡አፌዙብን፡፡አይሁድ ጌታን ንጉስ ነህ ለማለት የእሾህ አክሊል እንዳደረጉለት አይነት፡፡ቀሪወቹን ኢትየዽያውያንን የሚመሩት መሪወች ደግሞ መሄዳቸው መልካም ነው ለምን ቢባል ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ጥይት በአገራችን አይጮህምና ነው ብለው ተነበዩ፡፡ ድንቄም ትንቢት! እንደ ዕውነቱ ከሆነ ኢትዮያና ኤርትራ ሲለያዩ የልጆች ጨዋታ ይመስል ነበር፡፡በቃ ቻው ቻው፡፡ ባልና ሚስት እንኳን እንደዚህ አይለያይም፡፡ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ አንድ አገር በነበሩ ጊዜ የጋራ ሃብት፤ድንበር፤መገበያያ ገንዘብ፤ዕዳ(ብድር) ወዘተ…ነበራቸው፡፡በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሳይመሠረት፤የሁለቱ አገር ዜጎች ድምጽ ሳይደመጥ ሁሉም ነገር ጫካ ውስጥ አልቆ ስለነበር የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ስለወደፊቱ ግንኙነትም ፖለቲከኞቹ ቤታችን ቤታችሁ ነው ከማለት ያለፈ ህግና ስርዓት አልተበጀለትም ነበር፡፡እንኳንና አንድ ሃገር የነበረ ህዝብ ይቅርና ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት እያደረገች ያለውን እልህ አስጨራሽ ድርድር ለተመለከተ በዕውነቱ ኢትዮጵያ በወቅቱ ተወካይ የሌላት አገር ትመስል ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጦሱና ዳፋው ግን ውሎ አድሮ ለእኛ ለተራው ዜጋ ነው የሆነው፡፡ በነገራችን ላይ የስኮትላንድ ሪፈረንደም ጊዜ ሁሉም ስኮትላንዳዊ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ብሪታንያዊ የወቅቱን ጠ/ሚ/ር ዴቪድ ካሜሩንን ጨምሮ ድምጽ ሰጭውን ለማሳመን ብርቱ ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል፡፡መለስ ዜናዊ ኤርትራን በጓሮ በር ሸኝተው ለቀሪወቹ ደግሞ ታዋቂውን አንቀጽ 39ን ደነቀሩ፡፡ታላቁ መሪ የአንድነት አባት ናቸውና ይህንን አንቀጽ በማቆም አንድ ላይ በትነውን እሳቸው ደግሞ መበተን ወደ ሌለበት በጊዜ ተለዩን፡፡የከፋው ካለ አሁንም ሂደቱ ብዙ ከባድ አደለም፡፡አማራን ለመስደንገጥ ታስቦ ከሆነ ከስረዋል መሪያችን፡፡ለምን ቢባል እያደገ የመጣው የመገለልና የመከፋት ስሜት ከሁሉ ቀድሞ ልገንጠል እንዳይል ያሰጋል፡፡በአዲሱ ትውልድ ለውጥ እያየሁ ነው፡፡እንደ እናቱ እንደ እቴጌ ጣይቱ ነገ አርገው በዚህ የሚደነግጥ የለም የሚል ድምጽ እየተሰማ ነው፡፡አንድን ቤት የሚያቃጥል ዕሳት አንዱን ልብስ ከሌላው አይለይም፡፡ እናም አማራ በስሙ የተነገደበት የእስከ አሁኑ ይበቃል የሚሉ እየሰማሁ ነው፡፡ስለሆነም እሳቱ የጋራ እንጂ ለአማራ ብቻ የተላከ መቅሰፍት አይሆንም፡፡አንድ ክልል የመገንጠል ጥያቄ ቢያቀርብ 2/3 የም/ቤት ድምጽ ማግኘትና ሌሎች ሂደቶች መሟላት አለባቸው፡፡ ለኤርትራዊያን ይህን ማድረግ እንኳን ቢከብድ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን በደልናችሁ ብሎ እንዲጠይቃቸው ዕድል መሰጠት ነበረበት ካልሆነ ደግሞ ቻይና ታይዋን ላይ እንዳደረገችው ሂጂ ግን ዕውቅና ስጡን አትበሉን ማለት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ለብዙ ድርደር በር ይከፍት ነበር፡፡ ኧረ ስንቱ…፡፡ የባሰ አታምጣ እንዲሉ…

1990፡ ኤርትራ Vs ኢትዮዽያ (የመንግስታት ጦርነት) ውጤት 1 ለ 0

ንግግሩም ጽሁፋም የማይጠገበው ዘነበ ወላ በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንዳለው ጦርነት የነገስታት ነው እኛ ወታደሮች ተዋጉ ስንባል መዋጋት ብቻ ነው እንዳለው ነበር የሆነው፡፡የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዘዳንት የአቶ ገብሩ  አስራት ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጰያ መጽሀፍ የ1990 ኤርትራ Vs ኢትዮዽያ ጦርነት ስለነበረው ሁኔታ የተወሰነ መረጃ ይሰጣል፡፡ኤርትራ ድንበሩን ሁሉ በቦምብ ስታጥረው፤የዕድሜ ልክ ምሽግ ቆፍረው ሲጨርሱ የእኛወቹ መሪወች ሁሉን አፍነው እንኳንና ተራው ዜጋ ይቅርና አሻንጉሊቶቹ የግንባሩ መሪ ፖለቲከኞችና ጄኔራሎችም አያውቁም ነበር፡፡መለስና ስየ በር ዘግተው ሲታገሉና ሲያታግሉ ነበር፡፡ ነገር ከአለቀ ከደቀቀ በኋላ መጨረሻ ላይ አሰምተውን የማያውቁትን ሁሌም ግን የማይሰለቸንን የጥላሁን ገሠሠን ኢ….ት….ዮ….ጵ…..ያ የሚለውን ዘፈን ጋብዘው፤ኮከብ የሌለውን ባንዲራ እንድንለብስ ፈቀዱልን፡፡ይህንስ ማን አየብን እያልን ወደ ባድመ ተመምን፡፡የአገሬ ልጆች ቦንቡን ተንከባለሉበት፤ምሽጉን እየዘለሉ ገቡበት፡፡ሰጋቸው ደማሚት እንደመታው ድንጋይ ሰማይ ላይ ብትን አለ ለሃገር፡፡ህይወት ከንቱ፡፡ነፍሳቸውን ይማር፡፡አሁን የኢቲቪ እንግዶች ለዘላቂ ሰላም ሲባል መስዋዕነታቸውን እንዳናነሳ በምሁር ካባ እየነገሩን ነው፡፡መሀል አገር ማኪያቷቸውን እያጣጣሙ የሚቀልዱትን ቀልድ ቢያቆሙ ጥሩ ነው፡፡ ሻብያ ምሽጉ ሲደረመስ ሽምጥ ሲሮጥ የኢትዮዽያ ጦር እየተከተለ በማሳሳደድ ላይ እያለ ሻብያ ዳግም ተመልሶ እንዳያገግም አቅሙን ሁሉ ማውደም ሲቻል እያጠቃ የነበረን ጦር እስከ አሁን ድረስ በማናውቀው ምክንያት ጦሩ ማጥቃቱን እንዲያቆም ታዘዘ፡፡ሻብያም ሃይሉን በሰላም አሰባስቦ አፈገፈገ፡፡ቀጥለን ደግሞ በአለም ቀፋ ፍርድ ቤት ተሟግተን እናሸንፋለን በማለት ብዙ የህግ  ምሁራን  እየጮሁ ነብይ በአገሩ እንዲሉ አለም አቀፍ ልምድ ያላቸውና ከጄኔራል የሚስተካከል አገር ፍቅርና ታማኝነት ያላቸውን እነ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምን ገፍተው የፈረንጅ ጠበቃ ቀጥረው ባድመን ጭምር አስረክበን በዝረራ ወጣን፡፡ እና  1 ለ 0 አደለም እንዴ?

2010፡ ኤርትራ Vs ኢትዮዽያ (የጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ ጨዋታ) ውጤት ——–? ገምቱ!

አሁንም የኤርትራ ጉዳይ የጓዳ ጉዳይ ሆኗል፡፡የጓዳ ስል የኢህአዴግ ወይም የመንግስት ማለቴ ነው፡፡ በደንብ ፀሐይ ሊሞቀው ፤ ሁሉም ሊሰልቀው ይገባል፡፡የችግራችን አልፋና ኦሜጋ ጥንትም ዛሬም ኤርትራ ናት፡፡ የኤርትራ ጉዳይ የቅርብ ጊዜ ምልክት መታየት የጀመረው በዚያ በውጥረቱ ወቅት በዘመነ ቄሮ አስተዳደር ጊዜ ነበር፡፡ ህዝብ ለህብ ግንኙነት በሚል ማን አንደሚያሰተባብረው ግልጽ ባልሆነ መንገድ(Celebrity Events?) ሁለት ስብሰባወች አዲስ አበባ ተካሄዱ፡፡ይህም ስብሰባ የኢቲቪ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ እነ ፕ/ር መድሃኒ ታደስም ቃለ መጠይቅ ይሰጡ ነበር፡፡ጠ/ሚ/ር ደ/ር አብይም በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ሾላ በድፍኑ የሰላም ጥሪ አቀረቡ፡፡ትክክል ነበር፡፡በመቀጠል አጭሩ አሜሪካዊው ዲፕሎማት አስመራንና አዲስ አባባን ጎብኝተው ተመለሱ፡፡የኢህአዴግ አቭሪ ጥይት ኢቲቪ ትግራይ ድንበር አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ቃለ መጠይቅ በመስራት አሁን ያለው ሁኔታ በቢዝነስና ደህንነት ላይ እያሳዳረ ያለውን ተጽኖ ለማሳየት ሞከረ፡፡ይሄ የሰፈር ጸብ አይደለም የሁለት አገሮች እንጂ፡፡በመጨረሻ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ  በ28/09/10 የምሽት ሰበር ዜና የዚህን ሁሉ ዳር ዳርታ አረዳን፡፡በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲም ቢሆን አንድን አገር ወክሎ ቀጥታ ለሌላ አገር ጥሪ ማድረግ ይችላል ወይ የሚለውን ለህግ ባለሞያወች ትቼ ጉዳዩ አሁንም በተለመደው ሁኔታ መቀጠሉ ግን በጣም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡የዚህ የፓርቲና የመንግስት ዳር ድንበር ባለመኖሩ አገሪቱ በህግ ሳይሆን የረባ ስልጣን የሌላቸው እነ በረከት ስምዖን ሲያሾሯት ኖረዋል፡፡ አሁንም ለውጥ እናምጣ ከተባለ ፓርቲ ስለቀጣዩ ምርጫ ቢሰራ አገሪቱን ግን በህግ ስልጣን ያላቸው ሰወች በህግ መሰረት ቢመሯት፤ ግድ ከሆነም ፓርቲውም በህግ በተሰጠው ስልጣን ብቻ ቢሰራ፡፡ሃላፊወችን ምደረ ካድሬ ግምገማ በሚባል የፓርቲው ስልት አላሰሯቸውም፡፡መወሰን አይችሉም፡፡ህገ-መንግስቱ ውስጥ ገዢ ፓርቲ እንዲያ ያደርጋል እንዲህ ይሠራል የሚል አላስታውስም፡፡ ፖሊሲው የዕሱ ነው የምትለዋን ተገን አርገው አገሪቱን ወደ ስርዐት አልበኝነት ቀየሯት፡፡ እናም ይሄ መደበላለቅ ከኤርትራ ያላነሰ ጦስ አስከትሏልና ድንበሩ አብሮ ቢሰመር ጥሩ ነው በዘመነ አብይ፡፡ለነገሩ ህወሀት ብቻውን ወደብ ሰጥቶ አይደል! ፀሐይ ይሙቀው ስንል እንዲያው መንጠራራት ቢሆንም ብሪታንያ በፓርላማዋ  ስንት ጊዜ እንደተጨቃጨቀችበት አይነት ውይይት ማለት ነው፡፡ ሁሌም አድሮ ጥጃ የሆነው ኢቲቪ ግን እንደለመደው አንዳንድ ምሁራን፤ አንዳንድ ነዋሪወች እያለ እየመረጠ በዕጣ ፈንታችን ላይ የሚተላለፋ ውሳኔወችን በህዝቡ ቅቡል እንደሆኑ ለማሳየትና ለማስረገጥ  የተለመደ ሸፍጡ አገርሽቶበታል፡፡ይህ አደገኛና ለውጡን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው፡፡በነገራችን ላይ ጠ/ሚ/ር ደ/ር አብይ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተሸላሚውን የኢትዮጵያን አየር መንገድ ለጨረታ ማውጣት ሳይሆን የሚቀድመው የኢትቪን ውሽት ማርከሻ የሚሆን በርካታ የግል ቴሌቨዠኖች በአስቸኳይ አገሪቱ ላይ ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ ነው ያለባቸው፡፡ያኔ የሁሉም ድምጽ ይሰማል፡፡ህዝብም ለውሳኔ የሚያበቃ መረጃ ይኖረዋል፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ የአሁኑ ሁኔታ ጠ/ሚ/ር መለስ የጀመሩትን ደ/ር አብይ ጨረሱት አንደማለት ይሆናል፡፡ጠ/ሚ/ር ደ/ር አብይ በአሁኑ ሰዓት በመላው ህዝብ እራሴን ጨምሮ ተስፋ ያሳደሩ መሪ ናቸው፡፡ ይህ ግን አይተቹም ማለት አይደለም፡፡እሳቸውም ቆንጥጡን ብለዋል፡፡ እንግዲህ ኤርትራውያን ዳር ድንበሩ ወዳጅም ጠላትም የሚያውቀውና የተቀበለው ካርታና ባንዲራ ያለው አገር ለራሳቸውም ለልጆቻቸውም ይኖራቸዋል፡፡እኛ ግን ከዚህ ሁሉ ሂደት ያተረፍነው ልጆቻችንን በኤርትራ በረሃ ለአሞራ ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ጠ/ሚ/ር መለስ የጀመሩትን ያልሁት መለስና ህወሀት ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ አንዲሉ ለኤርትራ ነጻነት አንዳንዴ ከሻብያ በላይ መሆን ሲሞካክራቸው ታይተዋል፡፡ የኤርትራ ህዝብ ትግል አይቀለበስም የሚለውን የመለስ መጽሀፍ ያስታውሷል፡፡ለነገሩ ዛሬም ድረስ በኩራት የሚናገሩት ገድል ነው፡፡ ሻብያ ግን ለውለታቸው የሰጠው ምላሽ መሬታቸውን በዕብሪት መያዝ ብቻ ሳይሆን የአይደር ህጻናትን ጨዋታቸውን ሳይጨርሱ መቅጠፍ ነበር፡፡ ኢቲዮጵያውያን ግን ህወሀቶች ከሻብያ ጋር ብን ያለ ፍቅር ውስጥ በነበሩበት ወቅት ቡና ጠጡ እንኳን ባይሏቸውም የቁርጡ ቀን ወረራ ወቅት አብረዋቸው ወድቀዋል፡፡ይህንን ፍርድ ለፈጣሪ መተው ነው፡፡ መለስና ህወሀት ለሻብያ የዋሉት ይህን ብቻ ሳይሆን ኤርትራን እንደ አገር በማወቅ ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ በመጻፍ ቀዳሚ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሃገር አዲስ አገር ከሆነ የተባበሩት መንግስታት ዕውቅና እንዲሰጠው እናት አገሩ ዕውቅና መስጠት አለበት፡፡በዚህ ምክንያት እንደ ሃገር የሚኖሩ ግን ተ.መ.ድ የማያውቃቸው ቅርባችን ሁሉ አሉ፡፡ጠ/ሚ/ር ደ/ር አብይ ደግሞ ድንበራቸውን አሰመሩላቸው ማለት ነው፡፡አሁን ኤርትራውያን የልጆቻቸው ሞት ትርጉም አለው፡፡ የአኛ ልጆች ሞት ግን የኤርትራውያንን አሞሮች አስደስቶ እንደሆነ እንጂ ለኢትዮያውን እናቶች ፈውስ የሌለው የዕድሜ ልክ ሃዘንና የአዕምሮ ህመም ነው፡፡ በጦር ሜዳ የአሸነፍነውን ጦርነት ጦሩ ሰንት ዋጋ ከከፈለ በኋላ ማጥቃቱን እንዲያቆም መታዘዙ እስከ አሁን የሚጠዘጥዘን ህመም ነው፡፡ ከውጭ ወራሪ ኤርትራን ለመከላለከልም  አባቶቻችን እንደ ቅጠል ረግፈዋል ይህም መዘንጋት የለበትም፡፡ብቻ ለኤርትራ ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡የቀድሞ ነገስታት ለማባበል በሚመስል መልኩ ከሌላው በተለየ ልዩ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ተዋልደናል እናም ዘመድ ነን፤ ባህልና ሃይማኖትስ አያገናኘንም ወይ በማለት የአንድ ወገን ልመና ለምነናል፡፡ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የሆነው በቅሎ አጎቴ አጎቴ ይላል ፈረስ ግድ የለውም ነው፡፡ለወደብ ነው የምትፈልጉን የሚል ፌዝ ነው የሚሰማው፡፡ኤርትራዊው ፕ/ር በረከት ፍስሃ ለርዕዮት አዘጋጅ ቴድሮስ ጸጋየ የሰጡት ቃለ ምልልስ አንድ ማሳያ ነው፡፡አዝኜባቸዋለሁ፡፡ጋዜጠኛውን ግን ባርኔጣየን አንስቼለታለሁ፡፡መስቀለኛ ነበር ጥያቄው፡፡ፕ/ሩን አጋለጣቸው፡፡ አብረው መብላታቸው መኖራቸው እንጥፍጣፊ ሃዘኔታ ለኢትዮጵያ አልሰጣቸውም፡፡እሳቸው ደንበኛ የወልኣብ ወልደማርያም የመስፈስ ልጅ ናቸው፡፡ እነ ተስፋየ ገብረዓብ የህወሀት አባል በነበረ ጊዜም ሆነ ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ የሰሩትን የዘር ማጥፋት ወንጀል…ሁሌም አንዘነጋውም፡፡ ግን አነ አብርሃም ደቦጭ፤ ሞገስ አስገዶም፤ ዘርዓይ ድረስ ፤አቡነ-ድሜጥሮስ ፤ ፕ/ር ተስፋጽዮን ፤የአገር ፍቅር አባላት በሙሉ ስለነበሩ ስላሉም ሁሉንም በልኩ ማየት ግዴታችን ሳይሆን ደማችን ግድ ይለናል፡፡

እሺ ድንበሩ ተካለለ እንበል፡፡ ሁሉ ነገር ወደ ቀድሞ ነገሩ ተመለሰ እንበል፡፡ ከዚያስ ከዚያማ ኤርትራውያን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ሸማች፤በቢሊዮን ዶላር የሚያሳፍስ የወደብ አገልግሎት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ፤ኢትዮጵያ ውሥጥ እንደ ልብ መንቀሳቀስና እንደ በፊቱ በቂ የደህንነት መረጃ ያገኛሉ፡፡ እኛ በአብዛኛው ሸማች ሆነን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ያለ ቅድመ ሁኔታ የአለማቀፋን ፍ/ቤት ውሳኔ በራሳችን ተነሳሽነት ስንቀበል የትኛውን ብሔራዊ ጥቅም እንደምናስከብር በኩራዝ ፈልጌ አጣሁት፤ ይልቅ ኤርትራ ሃትሪክ ሶሰተኛ ድል ታስመዘግባለች፡፡ምናልባት ሰላምን እናገኛለን፤ ከእንግዲህ ወዲህ ተቃዋሚወችን አትደግፍም ሊባል ይችላል፡፡ሰላማችንን በዋናነት ያጣናው ከህግና ዴሞክራሲ በተጣላው  ፖለቲካችን ነው፡፡ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በሰሞኑ ለውጥ ምክንያት እንኳን አንጋፋወቹ ፖለቲከኞች እነ ሌንጮ ለታ ጠቅለው ገብተዋል፡፡ሌሎችም ሁኔታውን በጥሞና እየተከታተሉ ናቸው፡፡ሚዲያውና አክቲቪስቱ ምን ያህል ተስፋ እንዳደረገ ማየት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሰላማችን እኛ ጋር ነው፡፡ዋናው ፖለቲካችንን የምር ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሻብያ ቢፈልግ እንኳን ትርጉም ያለው ጉዳት ማስከተል አይችልም፡፡ህወሃት ስለሚርመጠመጥ እንጂ ይህንንም ማስቆም ይቻል ነበር፡፡

እና  ምን ይጠበሥ ለምትሉኝ…

በመለስ ጊዜ ሥርዐት የሌለው መለያየት አሁን እንደገና የሚንጸባረቅበት ዕድል ሊኖረው ይገባል፡፡

  1. ብሄራዊ ጥቅማችን ላይ መደራደር አንችልም፡፡ ስለዚህ ከድንበሩ ማካለል ጎን ለጎን የአሰብ ጉዳይ እንደገና ሊነሳ ይገባል አውነተኛ ሠላም ከተፈለገ፡፡ አብይ ቢተው…የሚቀጥለው ሌላ አብይ ይመጣል፡፡ ህወሀት ምዕራፋን እንደዘጋው ደጋግሞ ነግሮን ነበር በፓርላማ ጭምር፡፡ ግን ደምና አጥንት የተከፈለበት ብቻ ሳይሆን ህጋዊም ታሪካዊም ፖለቲካዊም መነሻወች ስላለው ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ይቀጥላል፡፡ልጆቻችን፤ የልጅ ልጆቻችን ገና ያነሱታል፡፡ሰው ተከፍሎበታልና! ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አገር ወደብ አልባ ሆና፤በአገጯ የምትነካውን የአሰብን ወደብ የይገባኛል ጥያቄ ለአለም አቀፋ ማህበረሰብ ሳታቅማማ ማቅረብ አለባት፡፡ የምኖነረው መንግስተ ሰማያት አይደለም እዚች ጣጠኛ ምድር ላይ ነን ገና! ሁለቱም ሃገራት በጋራ በነጻ መጠቀም አስታራቂ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡
  2. ባድመና ድንበር ማካለሉን በተመለከተ- ቦታው ላይ ያለውን ዕውነት መቀበል ብንችል ጥሩ ነው፡፡ግን በባድመ መደራደር የሚሆን አይሆንም፡፡ህዝቡም እሺ የሚል አይመስለኝም፡፡ፀሀይ ግባት ስለሆነ…
  3. የዝምድናችን ነገር…ሃቁ ተዋልደናል፤አብረን ክፋም ደግም አሳልፈናል፡፡አነሱ ምኒልክ ሸጦናል ብለው ይከሳሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ቅኝ ገዝታናለች እንዳሉት የሽፍጥ ክስ ነው፡፡ምኒልክ አቅም ካልገደባቸው የዘመኑ ነገስታት ግዛት በማስፋት የሚታሙ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ የጋራ ታሪካችን ላይ ክፋውንም መልካሙንም ድርሻ ድርሻችንን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ሁለታችንም ተበዳድለናል፡፡ ስለዘህ ከልብ ይቅር መባባል አለብን፡፡ዕውነት ያድነናል፡፡

ከነዚህ ውጪ ያለው ሌላው ተጨማሪ ነው፡፡ በዚህ ካልተስማሙ ፍቅር የጋራ ነው ከማይሆን ወዳጅነት   አትድረሱብን አንደርስባችሁም የሚል ስምምነት ብንፈራረም ይሻላል፡፡

***************************የያዘውን የወረወረ ፈሪ አይባልም፡፡አበቃሁ፡፡***************************