“እሱ ተከራካሪ፣ እሱ መልዕክት አስተላላፉ፣ እሱ ዳኛ ሊሆን አይችልም”  አቶ አታላይ ዛፌ የወልቃይት የአማራ ማነነት አስመላሽ የኮሚቴ አባል

“የተከሰሳችሁት በወልቃይት አማራ ማንነት ነው ወይስ በሽብርተኝነት የሚለው የሚታይ ይሆናል” ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት

“እኚህ ዳኛ  በማህበራዊ ሚዲያ ያቀረቡት የህወሓትን አቋም ነው” ዘመነ ጌቴ  የወልቃይት የአማራ ማነነት አስመላሽ የኮሚቴ አባል

ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት እና የክስ መቋረጥ ጉዳይ!

ዳኛ ለተከሳሽ መቆም እንዳለበት የህጉ መርህ እንደሚያዝ የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በተለይ ከሳሹ መንግስት ሲሆን ዳኛ ለተከሳሽ ሊወግን ይገባል። ምክንያቱም መንግስት ተከሳሹ ፍትሕ እንዳያገኝ የማድረግ አቅም ይኖረዋል። በአንፃሩ ግለሰብ ፍትሕ ያገኝ ዘንድ ዳኛው ሊያግዘው ይገባል። ጥሩ ፍትሕ በመስጠት።

ዳኛ ዘርዓይ ዛሬ በኢ ኤን ኤን ቴሊቪዥን ቀርቦ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ክስ መቋረጥ እንዳልነበረበት፣ እንዲያውም መንግስት ሀገር ውስጥ የተከሰሱበትን ጉዳይ ማቋረጥ አልነበረበትም በሚል ቅሬታውን ገልፆአል። ከዚህ አልፎ ያሉበት ሀገር ድረስ በመሄድ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊከሳቸው ይገባ ነበር ሲል ተከራክሯል።

የኢሳት ክስ ይታይ የነበረው 19ኛ ወንጀል ችሎት ነው። አቶ ዘርዓይ 4ኛ ወንጀል ችሎት የግራ ዳኛ ነው። የኢሳት ክስ 4ኛ ወንጀል ችሎት ላይ ቢታይ አቶ ዘርዓይ በምን መልኩ ሊዳኝ ነበር የሚለውን የዛሬው መግለጫ በደንብ ያሳያል።

በሌላ በኩል አቶ ዘርዓይ ዛሬ ስለኢሳት የተናገረው በትህነግ/ህወሓት ሰዎች ቴሌቪዥን መሆኑ በሚነገርለት ኢ ኤን ኤን ቀርቦ ነው። ኢ ኤን ኤን በአንድ ወቅት ኳስ እያሳየ፣ በመሃል “ሰበር ዜና” ብሎ አማራና ኦሮሞን የሚያጋጭ ዜና ሰርቷል ተብሎ በሁለቱ ክልሎች ሀላፊዎች ተወቅሷል። ጣቢያው ሰበር ዜና ብሎ የሰራውን ዜና ምስል ያመጣው ከሌላ ሀገር ቃጠሎ ነው ተብሏል። አቶ ዘርዓይ ኢሳት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይከሰስ የሚለው ገዥዎቹ “ሕዝብን ሆን ብሎ እያጋጨ ነው” ብለው ባወገዙት ኢ ኤን ኤን ቀርቦ ነው።

በሌላ በኩል አቶ ዘርዓይ “ወልቃይት የትግራይ ነው” የሚል አቋም ይዞ የወልቃይት ኮሚቴ አባላትንና ሌሎች በወልቃይት ጉዳይ የተከሰሱትን “ሲዳኝ” የነበር ሰው ነው። ስለ ወልቃይት በፃፈው 46 ገፅ ፅሁፍም “አማራ በማንነቱ የማይኮራ ነው ብሎ ስለፃፈ አማራ ላይ ጥላቻ አለበት፣ ስለዚህ እኛን ሊዳኘን አይገባም” የሚል ተቃውሞ ከአማራ ተወላጆች ሲነሳበት እንደነበር ይታወሳል። ዘርዓይ ወልደሰንበት ግን “ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቴ ነው” ብሎ ተከራክሮ አብረውት የተቀመጡት ሁለት ዳኞች ፈርደውለታል!

አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከወልቃይት ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ተከሳሾች ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ የነበር ሲሆን አቶ መብራቱ ጌታሁንን ዐቃቤ ሕግ በፃፈው “መብርኃቱ” የሚል ትግርኛ ስም መጥራት እንቀጥላለን ብሎ የተናገረ ሰው ነው።

እነ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል ብለው ብይን ማስተላለፋቸውም ይታወሳል። ተከሳሾች ከአቶ ዘርዓይ ጋር በነበራቸው አለመግባባት ችሎት አንገባም ብለው እንደነበር እነ በቀለ ገርባ፣ እንዲሆም በርካታ የአማራ ተወላጆች ላይ “ችሎት ደፍረዋል” በሚል መፍረዳቸውም አይዘነጋም። ተከሳሾች አቶ ዘርዓይ እንደሚያሾፍባቸውና እንደሚስቅባቸውም በተደጋጋሚ በችሎት ተናግረዋል። አቶ ዘርዓይ ከተከሳሾች ጋር በነበረው አሉታዊ ግንኙነት ለበርካታ ጊዜ በችሎት ተዘልፏል። ችሎቶች ተቋርጠዋል። ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ተሰጥተዋል።

በአንድ ወቅት በ”ሽብር” የተከሰሱ የአማራ ተወላጆች “በዳኛ ዘርዓይ መዳኘት አንፈልግም” ይላሉ። የኦሮሞ ተወላጆችም ለአማራ ተወላጆች አጋርነታቸውን ያሳያሉ። በመሃል ክንዱ ዱቤ “አቶ ዘርዓይ ትግሬ ስለሆነ ብቻ ሊዳኘኝ አይገባም” ይላል። እኛም ዜናውን እንሰራዋለን። የሰራነው ዋናውን ኮሚቴዎቹ ያቀረቡትን ምክንያት ነበር። ዳንኤል ብርሃነ ደግሞ ክንዱ ዱቤ ያለውን ብቻ ቃል በቃል ሰራው። ለዳንኤል ብርሃነ ይህን ጉዳይ ሊነግረው የሚችል ማንም አልነበረም። ከአንድ ሰው በቀር! አማራ በማንነቱ የማይኮራ ሕዝብ ነው ብሎ ዘርዓይ ፅፎታል ብለው ተከሳሾች ያቀረቡት ሰነድም የወጣው በዳንኤል ብሎግ ነበር!

አቶ ዘርዓይ ከበርካታ ተከሳሾች ጋር ንትርክ ውስጥ ገብቷል። ዛሬ ደግሞ የኢሳት ክስ መነሳት አልነበረበትም፣ እንዲያውም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መከሰስ ነበረበት ብሏል። የኢሳት ይፋ ሆኖ ነው! አቶ ዘርዓይ የእነ ንግስት ይርጋ፣ የእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል፣ የእነ ጎይቶም ርስቃይ፣ የእነ ጉርሜሳ አያኖ፣ የእነ መብራቱ ጌታሁንና የሌሎችም ክስ መነሳት ላይስ ምን ብሎ ይሆን?

ችሎት ስንከታተል የነበርነው ላይ “ስሜን አንስተሃል፣ ፌስቡክ ላይ ኮሜንት አድርገሃል” እያለ ያሳየን የነበረውን መከራ ብዙ ዝርዝር አለው። ፍትሕ ያለበት ሀገር ቢሆን ኖሮ የተሸማቀቅነውም ክስ አቅርበን ፍትህ ባገኘን ነበር። ይህን ጉዳይ “አሸማቃቂ ችሎቶች” ብዬ መፅሐፌ ላይ አካትቸዋለሁ! ማህሌት ፋንታሁንም አንድ ቀን የደረሰባትን እንደምትፅፍ ተስፋ አደርጋለሁ!