መኪኖች ከከተማዋን አቋርጠው ማለፍ አልቻሉም
አጭር የምስል መግለጫመኪኖች ከተማዋን አቋርጠው ማለፍ አልቻሉም

በጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ ከትናንት ሰኔ 6/2010 ዓም ጀምሮ እስከዛሬ ረፋድ ድረስ በነበረ ግጭት የንብረት ውድመት እንደደረሰ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ግጭቱ ጋብ ብሎ የነበረ ሲሆን ዛሬ ረፋድ ላይ መልሶ በማገርሸቱ የከተማዋ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል። በዚህም ሳቢያ ወደ ወልቂጤና ከተማዋን አቋርጠው የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች የደህንነት ስጋት ስላደረባቸው ከከተማዋ ውጪ እንደቆሙ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።

ስማቸውን እንዳይገለፅ የጠየቁ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ የተፈጠረው በትናንትናው ዕለት ሲሆን፤ የግጭቱ መንስኤ በከተማው እየተካሄደ ካለው የስፖርት ውድድር ጋር በተገናኘ የጉራጌ እና የአጎራባች ቀቤና ብሄረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ነው።

“ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች የወልቂጤ ከተማ ወጣቶች ለቀቤና ወረዳ ቡድን ይጫወቱ ነበር። ዘንድሮ ግን ለመጫወት አለመፈለጋቸውን ተከትሎ የተጀመረው አላስፈላጊ ስድድብ ወደ ቤት እና መኪና ማቃጠል ደርሷል” ሲሉ ሁኔታውን ያጋሩን ነዋሪ በአሁኑ ሰዓት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማው ተሰማርተው ሁኔታውን ለማረጋጋት እየጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሀብታሙ በበኩላቸው ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ተናግረው፤ የግጭቱ መንስኤ ግን ከስፖርት ፎክክር ጋር የተያያዘ ብቻ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል።

የደረሰውን አጠቃላይ የንብረት ውድመት እና በሰው ላይ የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ በዚህ ሰዓት ለማሳወቅ እንደሚቸግር የተናገሩት አዛዡ የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት በቅርቡ ተጣርቶ ይፋ እንደሚደርግ አስታውቀዋል።

በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን በውስጡ ሦስት ብሄረሰቦችን ይዟል። እነሱም የጉራጌ፣ የቀቤና እና ማረቆ ብሄረሰቦች ናቸው።እኒህ ብሄረሰቦች ለዓመታት በአብሮነት እና መግባባት ሲኖሩ እንደነበረ የሚጠቅሱት በዞኑ የመስቃን ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን መ/ቤት ባልደረባ ሬድዋን መሃመድ፤ በጉራጌና በቀቤና ብሄረሰቦች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለተፈጠረው ግጭት ሲያብራሩ ፣

“ያለመግባባቱ ምንጭ ከወልቂጤ ከተማ ይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። የጉራጌም ሆነ የቀቤና ብሄርሰብ አባላት ከተማዋ ለእየራሳቸው እንደምትገባ ይከራከራሉ። የሁለቱ ብሄረሰቦች አለመግባባት ለከተማዋ ዕድገት ማናቆ እየሆነ ነው” ብለዋል።

ይሄ አይነቱ ግጭት የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተሰበከ ባለበት በአሁኑ ሰዓት መፈፀሙ አሳዛኝ እንደሆነ ሬድዋን አክለው ተናግረዋል።

Source     –    BBC/AMHARIC