ስዩም ተሾመ
በእግር ኳስ ውድድር የጀመረው ግጭት ትላንት ማለዳ ላይ በጉራጌው የቀቤና መኖርያዎችን ማፍረስና የወረዳውን አስተዳደር; ቢሮዎች ማቃጠል የጀመረው አመፅ ለሊቱን ሙሉ በሁለቱም ብሄሮች ቀጥሎ በርካታ ቤቶች ሲቃጠሉ ማደራቸውንና ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለጹት ” ትላንት ማለዳ የጀመረው ችግር ከጉራጌው ከተወሰደው እርምጃ ቀጥሎ ወልቂጤን ዙርያ ከቦ የሚገኘው የቀቤና ማህበረሰብ “ጉራጌ ወደ ሀገሩ” ከሚሉ መፈክሮች ጋር አፀፋ ሲወስድ እንደነበር ነው የታየው። በምላሹም ምሽቱን ጉራጌው የቀቤናውን የግለሰቦች ቤት ማቃጠል ሲጀምር ቀቤናውም በተመሳሳይ አፀፋ ሲመልሱ ነበር ያደሩት! በሂደቱም የከተማውን #ፓሊስ_አዛዥ ቤት ጨምሮ በርካታ መኪናዎችና ቤቶች ከሁለቱም ብሄሮች ሲቃጠሉ ሁለት ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል። ማለዳ አካባቢ ፌዴራል ፖሊስ ወደ ከተማው ገብቷል። በከተማው ውስጥ ግን ውጥረቱ ነግሷል።” ብለዋል::
በወልቂጤ ከተማና ዙሪያዋ የተቀሰቀሰው ግጭተና ሁከት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል:: ጠዋት ላይ የፌደራል_ፖሊስ በአከባቢው ቢደርስም በተገቢው ሁኔታ ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ እንዳልሀነ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዛት ያላቸው መኪኖችና መኖሪያ ቤቶች በእሳት ጋይተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሰጠው መምህር ስዩም ተሾመ “ምንም እንኳን የፀጥታ ሃይሎች በቸልተኝነት ሁኔተውን ለመቆጣጠር ጥረት ባያደርጉም የሀገር ሽማግሌዎችና የአከባቢው ታዋቂ ግለሰቦች ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስትና ፖለቲካ አላፊ ናቸው! የጉራጌና ቀቤና ማህብረሰቦች ግን ለቀጣይ ዘመናት አብረው ይኖራሉ፡፡ ለሚያልፍ ነገር የማያልፍ ጠባሳ መተው ተገቢ አይደለም፡፡ ከማንም በፊት ሰላሙን ማስከበር ያለበት ህዘቡ ነው፡፡ ስለዚህ የጉራጌና ቀቤና ማህብረሰብ አባላት ሀገር ሲቃጠል ዳር ቆመው መመልከት የለባቸውም፣ ግጭቱን ለማስቆም ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡” ብሏል::
በዚህ ግጭት ሳቢያ ከአዲስ አበባ ጅማ ያለው መንገድ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዝግ ነው:: በአሁኑ ሰዓት ወልቂጤ ከተማ መከላከያ ሰራዊት የተቆጣጠረው ሲሆን ” ችግሩን ያስነሱት የታጠቁ ሀይሎች ሲሆን ሕወሓት በደኢህዴን ካድሬዎች በኩል የጉራጌን ሕዝብ ለመከፋፈል፣ የወቅቱ ሁኔታ ላይ ጫጫታ ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ማሳያ ነው” ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከሚሰጡት አስተያየት ለመረዳት ተችሏል::
በሌላ በኩል “ተአምር ከሰማይ የወረደ ያሕል ስናጋንን አገራችን ወደ ከባድ አደጋ እያመራች ነው።” በሚል ጋዜጠኛ ምኒልክ ሳልሳዊ እንደጻፈው:
ልንክደው የማንችለው = አትኩሮት የነፈግነው = በራሳችን ድክመት ኢሕአዴግ የፈጠረው
– የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚያደርጉት ግድያና ማሳደድ
– የኦሕዴድ ካድሬዎች አማራውን እያፈናቀሉ ቤቱን እያቃጠሉ እየገደሉ ማሳደድ
– በቤንሻንጉል ጉምዝ በአማራው ላይ አሰቃቂ ግድያና ማፈናቀል እስከ ብልት መስለብ
– በአፋር ሕዝብና በ አማራ ሕዝብ መካከል የተከሰተው ግጭት
– በጌድዎ ሕዝብና በጉጂ ኦሮሞዎች መካከል በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ግጭት
– በኦሮሞና በሲዳማ ሕዝብ መካከል የሚደረገው ግጭት
– በሲዳማና በወላይታ ሕዝብ መሓል የተከሰተው ግጭት
– በጉራጌና በቀቤና መካከል የተከሰተው ግጭት
– በሀረር በክልሉ ካድሬዎች መካከል የተለኮሰው እሳት
– በትግራይ በሐገር ሉአላዊነት ስም የተሰራጨው አደንዛዥ አጀንዳ … ወዘተረፈ …
አደግመዋለሁ ስለ እውነት እንቁም ስለሕግ እንቁም ስለ ሕዝብ መብት እንቁም። ከላይ በዝርዝር የተከሰቱና የቀተሉ ወደፊትም የሚከሰቱ ግጭቶች በዋናነት ስፖንሰር ሆኖ የሚያካሂደው የሚያስፈጽመው ኢሕአዴግ የተባለ ስልጣኑን መነጠቅ የማይፈልግ ስለ ሕዝብ ደንታ ቢስ የሆነ ድርጅት ነው። ኢሕአዴግ በሆዳም ካድሬዎቹና በጥቅም በገዛቸው ወሮበሎች ሃገር እየበጠበጠ ነው። ሕዝብን እየገደለ እያፈናቀለና እያሳደደ ነው። ለዚህ ደግሞ የተቃዋሚውን መዘናጋት ተጠቅሞበታል። ተቃዋሚው ከመታገልና በሕዝብ ውስጥ ስራ ከመስራት ይልቅ ተዓምር የወረደ ያሕል የኢሕአዴግን አጀንዳ በቅንነት ሲያስፈጽም ሕዝብ አደጋ ላይ ሆኗል።ተአምር ከሰማይ የወረደ ያሕል ስናጋንን አገራችን ወደ ከባድ አደጋ እያመራች ነው። የስርዐቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግ ስልጣኑን ላለመነተቅ የሸረበው ሴራ ነው። ሕዝብ ባለው አገዛዝ ሴራ ከመጠቀም ይልቅ እንዲጨፋጨፍ ግፊት እየተደረገበት ነው። በዙሪያችን ያለውን ነገር በመገምገምና ከኢሕ አዴግ የፖለቲካ ባሕርያት አንጻር በመለካት ልንታገልል ይገባል። ለዚህ ደግሞ መፍትሔ የሚሆነው ባለው አገዛዝ ላይ ጫና በመፍጠር በህዝብ መሃል ገብቶ በማስተማርና የትግል ፍሬዎች እንዲያብቡ በመታገል ነው።” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል::

