ሰኔ 6፣ 2010 (ጁን 13፣2018)
ጆርጅ ቡሽ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ በተደጋጋሚ ይጠቀሙበት ከነበሩት ቃላት ውስጥ አንዱ “ፖለቲካል ካፒታል” የሚለው ነው። ፖለቲካል ካፒታል የሚባለው አንድ የፖሊቲካ ሰው ያለውን የህዝብ ተወዳጂነት ደረጃ የሚያመለክት ነው።አንድ የፖለቲካ ሰው ወይም ድርጅት የህዝብ ድጋፉ ከፍ ያለ ሲሆን የፖለቲካ ካፒታሉ ብዙ ነው ይባላል። በተጻራሪው ሲሆን ደግሞ ፖለቲካ ካፒታሉ ዝቅተኛ ነው ይባላል።
የፖለቲካ ሰወች ጥረት ምን ግዜም የፖለቲካ ካፒታላቸውን ማሳደግ ያን የፈለጉትን ካፒታል ሲያገኙ ደግሞ ባግባቡ መጠቀምና ቀጣይ ካፒታል መገንባት ማለትም ቀጣይ ድጋፍን መገንባት ነው። የፖለቲካ ካፒታልን ባግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ወይም ከህዝብ ፍላጎት ተጻራሪ በሆነ ተግባር ላይ ማዋል እንደማባከን የሚቆጠር ሲሆን ውጤቱም የእምነትና ድጋፍ መሽርሽርና አይንህ ላፈር ወደሚያሰኝ ደረጃ መድረስ ሊሆን ይችላል።በኢትዮጵያም የተከሰተው ይኸው ነው ። የኢትዮጵያ መሪወች ከህዝቡ ፍላጎት ተጻራሪ የሆነ ተግባር ሲሰሩ ፣ በህዝቡ ዘንድ ያላቸው አመኔታም ሆነ ከበሬታ እየተቦረቦረ መሄዱን እንመለከታለን።
ለ17 አመታት በስልጣን ላይ የነበረውን የኮሎኔል መንግስቱን አምባገነን መንግስት መገርሰስ የሚያረካ ቢሆንም ወደስላጣን የመጣው ህወሀት/ኢህአዴግ ይህን የህዝብ በጎ አመለካከት ለቀጣይ ገንቢ ተግባር ሊያውለው አልቻለም። ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ የገጠመው ችግር በዋናነት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ህወሀት መራሹ መንግስት ገና ስልጣን ከጨበጠበት ቀን ጀምሮ በድፍን ቀኖናዊ ርእዩተ አለም እና በማን አለብኝነት ትምክት የህዝባችንን ፍላጎት ሳይሆን የድርጅቱን የፖለቲካ ስልጣን እድሜ ማራዘሚያ አጀንዳ እንደፈለገ ሲተገብር ኖሯል። ይህ ጭፍን አካሄድ በመጨረሻ የወለደው በታንክም በጥይትም ቢደበድቡት ወደዃላ የማይል ታጋይ ትውልድን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ ወደስልጣን እስከመጡበት ቀን ድረስ የተከሄደውን የህዝብ እንቢተኛነት ማንም በቀላሉ የሚረሳው አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ወደ ስላጣን እየተቃረሁ ከመጡበት ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ማግኘታቸው ማንም የሚክደው አይደለም። እንኳንስ ህዝቡ ፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ተግባራቸውን በበጎ አይን ነው የተመለከቱት። ብዙወች ከዚህም አልፈው ድጋፋቸውን በተለያየ መልክ ገልጸዋል።ይህ ሁሉ ሲደመር ለዶክተር አብይ ከፍተኛ የፖለቲካ ካፒታል ሰጥቷቸዋል ።
ህዝብም ተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ የታወቁ ምሁራን ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ድጋፋቸውን ሲቸሩ ኢህአዴግና ህወሀት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ያደረሱትን በደል ግፍና ፣ አዋራጅ ተግባር ወዘተ ረስተው ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒኦስቴር አብይ የህዝብን ብሶት በመረዳት፣ የህዝብን ጥያቄ ተገቢነት በማመን አበረታች ምላሽ መስጠት በመጀመራቸው፣ ህዝብ በሚፈልገው አቅጣጫ እንደሚጓዙ አመላካች የሆነ ራእይ በማቅረባቸው ነው።
አሁን ጥያቄው ዶክተር አብይ ይህን የፖለቲካ ካፒታል ለቀጣይ መልካም ተግባር ሀገርን ከፍ ለሚያደርግና ጥቅሟን ለሚያሰጠብቅ አዲስ ጅምር ይጠቀሙበት ይሆን ወይንስ ያባክኑት ይሆን የሚለው ነው።
በዚህ አኳያ ባለፈው ሳምንት በግንቦት 2008 መጨረሻ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ሰብሳቢነት በተካሄደው ጉባኤ መጨረሻ የኢህአዴግ ስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ በተለይ በኤርትራና በኢትዮጵያ ግንኙነት አንጻር ያሰተላለፈው “የአልጀርሱን ውስኔ እንዳለ የመቀበልና የማስፈጸም ” ውስኔ የሚኖረው እንደምታ ምንድን ነው የሚለውን በቅርበት መመርመር የሚገባው ጉዳይ ነው።
ሲጀመር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ እንድትሄድ የተደረገበት የህወሀት መራሹ መንግስት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እጅግ ብዙ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት አላገኘም። ብዙ ኢትዮጵያውያን ገና ከመጀመሪያው የሚሉት ኤርትራን በተመለከተ ደብዳቤ ጽፎ እባካችሁ ግንጠላውን አጽድቁልኝ ብሎ የጠየቀው ህወሀት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ጥቅም በምንም መልኩ አላስጠበቀም፣ ሻአቢያ የፈለገውን ሁሉ ነው እንዳለ የሰጠው የሚል ነው።ይህ ደግሞ ተራ ግምት ሳይሆን በመገንጠሉ ሂደት በአደራዳሪነት ተሰይመው ከነበሩት ከእነ አምባሳደር ኸርማን ኮኸን ፣ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከነበሩት ካአቶ ታምራት ላይኔ፣ ቀጥሎም የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ከነበሩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በይፋ የተነገረና ለታሪክ በመረጃነት የሰፈረ እውነታ ነው። ኢትዮጵያ ቢያንስ ታሪካዊና ህጋዊ መብቷ የሆነውን የአሰብን ወደብ ማግኘት እንደሚገባት ሲነገራቸው አሻፈረኝ ያሉት የሕወሀት/ኢህአዴግ መሪ መለሰ ዜናዊ አንደነበሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቁጭት የሚያሰታውሰው ሀቅ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ነገር አናውቅም በማለት የአፋር ቤተሰቦቻችን ቢናገሩም ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ ፍላጎታቸውን (ኢትዮጵያዊነታቸውን ) ከማስከበር ይልቅ በጉልበት ኤርትራዊ ናቸው የሚለውን የሽአቢያን ፍላጎት ነው ያሰፈጸመው።
ከዚያም ወዲህም ህወሀት/ኢህአዴግ በተከታታይ የሰራውን ስህተት ለማረም አጋጣሚወች የተፈጠሩለት ቢሆንም አንዱንም እድል ሳይጠቀምበት ቀርቶ የኢትዮጵያን ጥቅም በተደጋጋሚ ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቷል።. እንዚህንና ሌሎችም እውነታወች መሰረት አድርገን ስንመለከት ኢህአዴግ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከቶውንም የሚታመን ድርጅት አንዳልሆነ ዶክተር አብይም ጠንቅቀው ይገነዘቡታል ብየ አስባለሁ። እንዲያውም ባአብዛኛው ህዝብ ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ ጥቅም የቆመ የሽአብያ ወኪል ነው የሚለው ድምዳሜ በሰፊው የሚታመን መሆኑን ማንሳት ለቀባሪው አረዱት እንደማለት ይሆናል። በአልጀርሱ ስምምነትም ቢሆን ህወሀት መራሹ መንግሰት የኢትዮጵያን ጥቅም በበቂ ከመከላከል ይልቅ ሻአብያን የሚያግዝ ስራ ተግባረዊ ያደረገ ስለመሆኑ ተደጋጋሚ መረጃወች እንደቀረቡ የሚታወስ ነው።
በአጠቃላይ የኢህአዴገግ የ27 አመታት የኤርትራ ፖሊሲ የክህደት ፣ የማጭበርበርና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የመስጠት እንጂ የኢትዮጵያውያን ጥቅም የማስጠበቅ ኢትዮጵያን ጥቅም የመንከባበብ እንዳልነበረ ግልጥ ነው።
ይህ በሆነበት ሁኔታ አሁን ዶክተር አብይና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያንኑ በህዝብ የተጠላ የኢህአዴግን የቆየ “ስምምነት” ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለታቸው ህዝብን እጅግ ግራ ያጋባ፣ ቁጣን የቀሰቀሰ “ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ምን ነካቸው” በማለት በሰፊው እያነጋገረ የሚገኝ ጉዳይ ነው።
ይሀ እርምጃ በትግራይ ህዝብ እንዲሁም እጅግ ብዙ በሆኑ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲወችና (ተፎካካሪወች) ተንታኞች እንደተገለጠው ጠቅላይ ሚነስቴሩን በተለይም የሀገር አንድነት ከሚያስጨንቃቸው ክፍሎች ጋር እጅግ ሰፊ ቅራኔ ውስጥ የሚከታቸውና ምናልባትም በህዝብ የተሰጣቸውን ሰፊ የፖለቲካ ካፒታል ለመቦርቦር ታላቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ነው።
አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ካንድ ወር በፊት በመቀሌ ጉብኤ ውይይትና፣ ቀደም ሲልም ካንድ አመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀይለማርያም ወደ ሁመራ በተጓዙ ጊዜ በአካባቢው ያገኟቸውና ያነጋገሯቸው ሰወች የጠየቁትን ነው ተግባራዊ ያደረጉት የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። በተጨማሪም ህወሀትም ለጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ በቅርቡ ያቀረበው ጥያቄ የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ ከሽአቢያ ጋር ስምምነት ማስፈንን ስለሆነ ነው ያሁኑ ውሳኔ የተላለፈው ይላሉ።
መመልከት የሚያሰፈልገው ግን በመቀሌ ስብሰባም ሆነ በሁመራ ጉብኝት ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስቴሮች ያነጋገሯቸው ባብዛኛው የህወሀት አባሎችና ካድሬወችን ሲሆን ያቀረቡትም ሀሳብ በድርጅታዊ አሰራር ተቀነባበሮ “አድርጉ” የተባሉትን እንጂ የህዝብን ስሜት አለመሆኑን ነው። ይህም ስለሆነ ነው በትግራይ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።
ከላይ እንደጠቀስኩት በድርጅቱ ውስጥ ጉልህ ድምጽ ያላቸው የ ሕወሀት መሪወች ደግሞ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ሻአቢያ የሚያጋድሉ እንደሆነ ስለሚታወቅ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የህወሀት ባለስልጣኖችን አመለካከትና የውስኔ ሀሳብ በጥንቃቄ ሊመረምሩት በተገባ ነበር እላለሁ። በዛሬው እለት ይፋ የሆነው የህወሀት ጉባኤ ውሳኔም ይህንኑ ነው የሚያሳየው። አሁንም ህወሀት የሚለው አፋችንን ዘግተን ለሻቢያ የፈለገውን እንስጥ ነው። ይህ ሁሉ ሲትይ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የህወሀትን ምክር እንዳለ ተግባራዊ ማድረግ ለ27 አመታት ህወሀት/ኢህአዴግን ከህዝብ ጋር ያላተመውን ስህተት መድገም ነው።
ሌላው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መመልከት የሚገባው የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጰያውያን ዘንድ ያለውን እጅግ ጥልቅ ስሜት የሚገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የአልጀርስ ስምምነትን ተቀብየ ተግባራዊ አደርጋለሁ ከማለታቸው በፊት ከተቃዋሚ ፓርቲወችና፣ ከሌሎች የታሪክና ክህግ አዋቂ ኢትጵያውያን ጋር ምንም ምክክር አለማድረጋቸው ነው። የጠቅላይ ሚኒስቴሩ በእንደዚህ ያለ እጅግ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን ካላማከሩ መቼ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ህልውና ላይ ሀሳባችን የሚደመጠው?
ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ ለ27 አመታት ያደርግ የነበረው ህዝብን ወደጎን በመግፋት የሚፈልገውን መወሰንና ይህንንም በህዝብ ላይ መጫን ነበር። ይህ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌለበት የህወሀት/ኢህአዴግ አሰራር ህዝብን ያሰመረረው አንዱ ጉዳይ ነው። ይህ አሰራር ህዝብን ያዳምጣሉ በማለት ታላቅ ተስፋ የተጣለባቸው በዶክተር አብይ ጊዜ አሁንም ተደግሞ ማየት ለብዙወቻችን እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ያለፉት 26 አመታት የኢህአዴግ መገለጫ ልዩ ምልክት ተቃውሞ ሲጠነክርበት ተሳስቻለሁ ፣ እለወጣለሁ ወዘተ ብሎ ሲምል ሲገዘት ይቆይና ህዝብ እስኪ የሚለወጡ ከሆነ እድል እንሰጣቸው ( ትንሽ እንያቸው) ብሎ ተቃውሞውን ለዘብ ሲያደርግ ያንኑ የተሳሳተና የህዝብን ፍላጎት የሚጻረር ፖሊሲ በአዲስ መልክ አጠናክሮ ለመቀጠል መሞከሩ ነበር። በዚህ አኳያ መረጃ ካሰፈለገ የቀድሞው ጠ/ሚኒስቴር አቶ ሀየወለማርያም ባለፉት ሁለት አመታት የደረጉትን ንግግሮች ማዳመጥ በቂ ነው። ህወሀት መራሽ ኢህአዴጎች ይህ አያዋጣም ተብለው በተደጋጋሚ ቢነገሩመረ ጀሮ ዳባ ልበስ ብለው በመጓዙ ከቀውስ ወደ ቀውስ በመሽጋገር ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን እኛንና ሀገራችንንም እጅግ የከፋ አደጋ ላይ አድርሰውናል። ይሀ እንዲደገም ሁላችንም አንፈልግም።
የአልጀርስ ስምምነት የሚባለው ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ ያመጣብን እዳ በህዝብም ገና ከመጀመሪያው ተቀባይነት ያጣ “ስምምነት” ነው።
ይህን ጉዳይ ከኔ ከተራው ሰው ጀምሮ ከሞላ ጎደል ሁሉም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መከበር የሚታገሉ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች የተቃወሙት ነው። ይህን የአልጀርስ ስምምነት የተቃወምነውም በመርህ ደረጃ የኢትዮጵያን ታሪካዊም ህጋዊም መብት ስለማያስከበብር ነው። ስለሆነም ይህን ስምምነት ማንም ግለሰብ ወይም ድርጅት በተለያየ መልክ አምጥቶ ተቀበሉት ቢል ገና ከመጀመሪያው ውድቅ እንደሚደረግ መገንዘብ ያሰፈልጋል።
አንዳንዶት ሁሉንም ነገር ከጎሳ መነጽር ውጭ ሊያዩ ስለማይችሉ የኢትዮጵያ ና የኤርትራ ጉዳይ የትግራይ ጉዳይ ግፋ ቢል የሰሜኑ የሀገራችን ነዋሪ ሀዝብ ጉዳይ አድርገው ሊያቀርቡት ይሞክራሉ። ይህ ታላቅ ስህተት ነው። ኢትኦጵያውያን ለሀገራቸውና ለታሪካቸው ታላቅ ፍቅር እንዳላቸው ባለፉት ጥቂት ወራት በተግባር የተመለከትነው ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ምንም እንኳ ላለፉት 27 አመታት በመንግስት ደረጃ የተቀነባበረ ከፍተኛ ጥቃት የተፈጸመበት ቢሆንም እጅግ ጥልቅና ሰፊ መሰረት እንዳለው በተግባር አይተናል።እያንዳንዷ የኢትዮጵያ ምድርም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ ሀገራችን በገጠማት የባእድ ወረራ ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የከፈሉት ዋጋ ምስክር ነው። ይህን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ በሚጥም ሁኔታ ደግመው ደጋግመው ተናግረውታል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ወደስልጣን የመጡት የህዝብን አልገዛም ማለት የህዝብን የለውጥ አጀንዳ ተመርኩዘው እንጂ ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ በጎ ፈቃድ እንዳልሆነ ምን ጊዜም መረሳት የለበትም። ይህም በመሆኑ የእርሳቸው ሀላፊነትም (ማንዴት) በህዝብ የተጠላውን የህወሀት/ኢህአዴግን አጀንዳ ማስፈጸም ሳይሆን የህዝብን የለውጥ አጀንዳ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የ ኤርትራን ጉዳይም የበተመለከተ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዶክተር አብይ የቸራቸው የፖለቲካ ካፒታል የሚመነጨው ከዚህ እውነታ ነው።
በዚህ አኳያ በአሁኑ ሰአት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የህዝባችንን የለውጥ አጀንዳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ሊወስዱት የሚገባው እርምጃ ብሄራዊ የመግባባት ጉባኤ መጥራትና ሁሉም ባለድርሻወች (ኢህአዴግን ጨምሮ ) በሀገራችን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩና የጋራ የለውጥ እቅድም እንዲነድፉ ማድረግ ዋነኛው ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የኤርትራም ጉዳይ ሆነ መሰል ታላላቅ አጀንዳወች በተናጠል ኢህአዴግ ውስኔ የሚሰጥባቸው ሳይሆን ከላይ የተጠቀሰውን ምክክር ፣ የሚሻ ነው።
ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ይህን ጉባኤ ባስቸኳይ በመጥራት በቅንነት ሁሉም ባለድረርሻወች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት አድርገው ብሄራዊ መግባባት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ የፖለቲካ ካፒታላቸውን የኢትዮጵያንና የህዝቧን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የህዝቡንም የለውጥ አጀንዳ ወደተግባር ለመለወጥ ባግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል።
ጊዜው የህዝብን አጀንዳ ማስፈጸሚያ ነው። ተፈትሾ ውድቅ የተደረገውን የኢትዮጵያን ጥቅም በግምት ውስጥ ያላስገባውን የጥቂት የህወሀት/ኢህአዴግ መሪወችን አመለካከት፣ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባለውን ለውጥ አጋች አካሄድም ሆነ የባእዳኑን ግፊት መቋቋም የሚቻለውም ህዝብን ያማከለ ጉዞን ፈጠን ብሎ በመጓዝ ነው።
