(ዘ-ሐበሻ) በሕወሓት አቅራቢነት በኢህ አዴግ ሥራ አስፈጻሚ የተሰጠውን ” የአልጀርስ ስምምነትና የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለናል” ውሳኔ በመቃወም በዛሬው ዕለት በአዲግራት ከተማ ተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ::
ትናንት ህወሓት ባወጣው መግለጫው “ኢትዮ-ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያየዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢህአዴግ ምክርቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያይበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ አንድ ጉድለት እንደሆነ ማእከላዊ ኮሚቴዉ ደምድሟል።” የሚል እርስ በ እርሱ የሚላተም መግለጫ ቢያወጣም በትግራይ የሚደረገውን ተቃውሞ አላቆመውም::
በአዲግራት ከተማ በዛሬው ዕለት በተደረገው ሰልፍ “እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኤርትራዊ አንሆንም” “ዕቃ እንጂ ሰው አይሸጥም” “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት የኢትዮጵያ አፈር እንሆናለን” እና ሌሎችንም መፈክሮች ሲያሰሙ ነበር::

በሌላ በኩልም በመቀሌ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ በሮማናት አደባባይ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ከፍተኛ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ከስፍራው ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ::
በሌላ በኩል ሕወሓት ትናንት እርስ በ እርሱ የሚላተም መግለጫ ካወጣ በኋላ የተለያዩ አክቲቭስቶች እየተቹት ይገኛሉ:: የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ “የህወሓት መግለጫ (በቀላል ቋንቋ)” በሚል ባቀረበው አስተያየት ” ህወሓት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን “የአልጀርሱ ስምምነትንና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለናል” የሚለውን የኢህአዴጉ ውሳኔ ተቀብሏል። የህወሓት ባለስልጣናት ከፌደራል ስልጣን መባረራቸው ግን ተቃውሟል። በዚሁ መሠረት ህወሓት የህዝብን ጉዳይ ችላ ብሎ የስልጣን ጉዳይ ግን አንገብግቦታል። ከህወሓት የሚጠበቅ ነው፤ ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለግል ስልጣን የሚኖር ድርጅት ነውና።
ዓረና ፓርቲ “… ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ …” የሚለውን የኢህአዴግ ውሳኔ አይቀበልም ብቻ ሳይሆን አጥብቆ ይቃወማል። ለዚህም ነው ዓረና የትግራይ ህዝብ ተቃውሞውን በሰልፍ እንዲገልፅ ጥሪ ያቀረበው። የትግራይ ህዳሴ በተጋሩ አንድነትና ትግል ይረጋገጣል።” ብሎታል::

አክቲቭስትና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዳይሬክተር ጀዋር መሐመድ ‘ ሕወሓትን “ጸባይ ገዝተህ ቁጭ በል አልያም ጥፋ” ብሎታል:: “ሕወሓት እውነታውን መቀበል አቅቶታል:: በፌዴራል መንግስቱ ያጡት ስልጣን ተመልሶ አይመጣም:: በትግራይ ራሱ በሚቀጥለው ምርጫ ይሸነፋሉ:: የነሱ ቀን አብቅትውል:: በ እብሪተኝነታቸው ከቀጠሉ ከኢህአዴግ አባልነትም ሊባረሩ ይችላሉ” ያለው ጀዋር ለ ኦህዴድ እና ባአዴን አመራሮች ባስተላለፈው ጥሪም “ህወሀት የክብር አሸኛኝቱን ጠልታ አሻፈረኝ ካለች አትለማመጧት ልቀቋት። ለመጨረሻው ግጥሚያ ከቄሮ ጋር ተላትማ ወደመቃብሯ ትገፍተር” ብሏል::
ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው “ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክርቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ” መጠየቁን ተከትሎም ኤርሚያስ ለገሰ በሰጠው አስተያየት ዶ/ር ዓብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮንን የሕወሓትን ጥያቄ መቀበል የለባቸውም ብሏል::
ቬሮኒካ መላኩ የተባሉ ጸሐፊም የሕወሓትን መግለጫ ከተመለከቱ በኋላ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል::
“የህውሃትን መግለጫ ምንም አዲስ ነገር የለውም የሚሉት ሰዎች ኢህአድግ የሚባለውን ድርጅት ባህሪይ ካለማወቅ የሚሰነዘር አስተያየት ነው።
ኢህአዴግ ” ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ” በሚባል ጠርናፊ አስተሳሰብ የሚመራ ግትር ግራ ዘመም ፓርቲ ነው። አንድ ድርጅት የፈለገ የሀሳብ ልዬነት ቢኖረው ኢህአድግ ከተባለው ጃንጥላ ወጥቶ ድርጅቱን የሚቃረን መግለጫ አያወጣም።
…
ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ህውሃት ፣ኦህዴድና ዴኢህዴን ለሁለት እንደ ጣቃ ጨርቅ የተተረተሩት “ቦናፓርቲዝም ” በሚባል ተራ ፈረንሳይ ወለድ ተረት ተረት ነው። የአሁኑ የህውሃት መግለጫ ኢህአድግ የቆመበትን ዋና መሰረት (Base) የደረመሰ ነው።ለምሳሌ የአልጄርሱን ስምምነት ኢህአዴግ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሲቀበል ህውሃት ግን ወደ ድሮው አቋሙ ተመልሶ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
የድርጅቱንም ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የአደረገውን ምደባ በይፋ በመግለጫ ተቃውሟል
።
ይሄ ከባድ ወንጄልና ህገመንግስቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጠውን ስልጣንና ተግባር የሚቃወም ነው።
ህውሃት በተጨማሪም በመግለጫው በ40 ሚሊዮን የአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት አውጇል ። ህውሃት ትናንት ባወጣው መግለጫ ራሱን ወደ ሽብርተኛ ድርጅት አውርዶ በፌደራል ስርአቱ ላይ በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት አውጇል።
የዛሬ 16 አመት ህውሃት ለሁለት ሲሰነጠቅ ብአዴን የሚባል በድን ድርጅት ኦክስጅን ቀጥሎላቸው መተንፈስና መትረፍ ችለዋል።
…
አሁን ሶስቱም ድርጅቶች ኦህዴድ ፣ዴኢህዴንና ህውሃት መግለጫ አውጥተዋል። ኦህዴድና ዴኢህዴን በአንድ መስመር ተሰልፈዋል ህውሃት አፈንግጧል። አሁን የሚጠበቀው የብአዴን ነው። ብአዴን አሁን ህውሃት በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት በአወጀችበትና እናት ድርጅቴ በሚለው ኢህአድግ ላይ ባፈነገጠችበትና ህገመንግስቱን በተቃረነችበት በዚህ የሽብር ተግባሯ እንደ 1993ቱ ወደ ገደሉ በብርሃን ፍጥነት እየተምዘገዘገች ወዳለችው ህውሃት ጎን የሚቆምበት ምክንያት የለም።
የኢትዮጵያ ህዝብም ህወሃትን ለመቅበር ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለምና ከዶ/ር አቢይ አህመድ ጋር በመሆን በፖለቲካ Sucide ራሷን በራሷ ያጠፋችውን ህውሃትን ኑ እንቅበር ።”
