N.Ed Aba Gebramariam to sealite mih cathedral

  • በንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመድቧል
  • የኦዲት ሥራው ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የካቴድራሉ ሒሳብ ይመረመራል
  • በሕዝብ የተባረሩት ሓላፊዎች ቀርበው እንዲያስመረምሩና እንዲመረመሩ አዘዘ
  • “ሕዝቡን አስተባብረን ውሳኔውን ለማስፈጸም ዝግጁ ነን፤”/ማኅበረ ምእመናኑ/
  • የፌዴራል ጉዳዮችና የእንባ ጠባቂ፣ለጠቅ/ሚኒስትሩና ለፓርላማ አሳስበዋል፤

†††

  • ፓትርያርኩ፣“ቅሬታዎችን ለመቅረፍ አቅሙና ፍላጎቱ የላቸውም፤”ሲሉ ተቹ
  • ለሃይማኖት እና መንግሥት ግንኙነት ድንጋጌ፣የሕግ ትርጉም እንዲሰጥ አሳሰቡ
  • ከዜጎች መብትና ማኅበራዊ ቀውሱ አኳያ ጠ/ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ጠየቁ
  • ፍ/ቤቱም፣“ተቀራርባችሁ ችግሩን ብትፈቱት ነው የሚሻላችሁ፤”ሲል መክሯል
  • “ዳኝነት ግዴታችን ቢኾንም ቤተ ክርስቲያን ከአማኞቿ ስትካሰሥ ያሳፍራል፤”

†††

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ለምእመናንን ቅሬታ በወቅቱና በአግባቡ ምላሽ ከመስጠት አንጻር የሚታይበት ውስንነት የሚያስከትለው ማኅበራዊ ቀውስ ያሰጋቸው አካላት፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ያሳሰቡ ሲኾን፤ ቋሚ ሲኖዶስ በበኩሉ፣ የችግሩ መገለጫ ኾኖ ላለፉት 6 ወራት በእንጥልጥል ላይ ባለው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል ጉዳይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ኮሚሽን ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ትላንት ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፤ ካህናት፣ ልዩ ልዩ ሠራተኞችና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እያቀረቡ ያሉት ቅሬታ በአግባቡ እየተስተናገደ አለመኾኑን በመጥቀስ፣ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማገዝ መንግሥት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

በተደጋጋሚ የሚሰሙ የማኅበረ ካህናትና የማኅበረ ምእመናን አቤቱታዎች ምላሽ ባላገኙባቸው አህጉረ ስብከት፣ ምእመኑ ሰላሙ እየደፈረሰ፣ ከቤተ ክርስቲያን እየራቀ፣ ሀብትና ንብረቱ እየባከነ እንደኾነ ያለማቋረጥ የሚቀርቡት አቤቱታዎች የሚያረጋግጡ በመኾኑ፣ የከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ሳይፈጥሩ እልባት ይሰጣቸው ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡ በሀገር አቀፉ የፀረ ሙስና ትግል ለማስመዝገብ የሚፈለገው ለውጥ ያለሃይማኖት ተቋማት አጋርነት አስቸጋሪ እንደኾነና መንግሥት የዜጎችን የሃይማኖት ነጻነትና ሰላም ለማስጠበቅ ካለበት ግዴታ አኳያ፣ የግንኙነቱን ዓይነትና ድንበር(የማይገባባቸው ጉዳዮችና ምን ድረስ እንደኾነ) በመወሰን ረገድ ሕገ መንግሥታዊው የሃይማኖትና መንግሥት ግንኙነት ድንጋጌ የሕግ ትርጉም እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የአህጉረ ስብከት ማእከል በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ መፍትሔ ሳይሰጠው 6 ወራትን ባስቆጠረው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረትና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል ውዝግብ፣ መንግሥታዊ ተቋማቱ ፓትርያርኩን ተጠያቂ አድርገዋል፤ “የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ አቅሙም ፍላጎቱም የላቸውም፤” በማለት ተችተዋል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቱ፣ከማኅበረ ምእመናኑ ዐቢይ ኮሚቴ ጋራ በቅርበት እየተገናኘ ሲሠራ መቆየቱ ተገልጿል፤ ሚኒስትር ዴኤታውም፣ ከአንድም ኹለት ጊዜ ከፓትርያርኩ ጋራ ቢነጋገሩም፣ ከፍ/ቤቱ ሒደት ጋራ በተያያዘው ግትር አቋማቸው ሳቢያ የረባ ውጤት ባለመምጣቱ፣ውዝግቡ አላስፈላጊ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እንዲያሰጥ ጠይቋል፡፡

ኹለቱ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ስለጻፏቸው ደብዳቤዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በትላንትናው ዕለት እንዲያውቀው የተደረገ ሲኾን፤ ዛሬ ዓርብ፣ ሰኔ 8 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ባካሔደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ የካቴድራሉን ወቅታዊ ኹኔታ በአጀንዳ ይዞ በመወያየት ባለአራት ነጥቦች ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በውሳኔው መሠረት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ለካቴድራሉ አራት የአስተዳደር ሓላፊዎችን(አስተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም እና ቁጥጥርበጊዜያዊነት ይመድባል፤አጣሪ ኮሚቴም በመመደብ የማኅበረ ምእመናኑ አቤቱታ እንዲጣራ ያደርጋል፡፡ማጣራቱ፣ የኦዲት ሥራው ከቆመበት ጊዜ አንሥቶ ያለውን የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ጉዳዮችን የሚያካትት ሲኾን፤ አስተዳዳሪውን መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃንን ጨምሮ በሕዝብ የተባረሩት የጽ/ቤት ሓላፊዎች በአካል ተገኝተው ተፈላጊ ሰነዶችን እያቀረቡ እንዲያስመረምሩና እንዲመረመሩ ቋሚ ሲኖዶሱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ዛሬ 10:00 ላይ የካቴድራሉን ማኅበረ ምእመናን ዐቢይ ኮሚቴ አባላትንና የሰንበት ት/ቤቱን አመራሮች ጠርቶ አነጋግሯል፡፡ ሦስት የማኅበረ ምእመናኑ ተወካዮችና ሦስት የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮች የቀረቡ ሲኾን፣ ውይይቱ፣ቋሚ ሲኖዶሱ በቀኑ ስብሰባው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማሳወቅና የማጣራቱ ሒደት እንዲቃና መደረግ ባለበት ቅድመ ዝግጅት ላይ ያተኮረ እንደኾነ ተገልጿል፡፡ከግማሽ ሰዓት በላይ በዘለቀው ውይይት፣ማጣራቱ እስኪጠናቀቅ የሚሠሩ ጊዜያዊ የአስተዳደር ሓላፊዎችን መመደቡንና አጣሪ ኮሚቴውም በጠቅላይ ጽ/ቤቱ መቋቋሙ ለተወካዮቹ ተነግሯቸዋል፡፡

“ለማጣራቱ ሒደት መዘግየት ክፍተቱ የማን ነው?” በሚል ከቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ለቀረበው ጥያቄ ተወካይ ምእመናኑ፣“የእኛ ክፍተት አይደለም፤ የኾነው ኹሉ ምክንያቱ በእናንተ ምክንያት ነው፤”ሲሉ መልሰዋል፡፡“የተመደቡ አጣሪዎችን አንቀበልም ማለታችሁና ቢሮውን ማሸጋችሁ ጥፋት ነው፤”በሚል መልሰው ጠይቀው በአካሔዳቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል፡፡“ከዚህ በተረፈ እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ያጠፋነው ነገር ካለ ይቅርታ እንጠይቃለን፤ቤተ ክርስቲያኗ በዘላቂነት መጎዳት ስለሌለባት ያለፈውን ጥፋት ትተን በቀጣይ ተራርመን እንቀጥላለን፤” ሲሉ የቋሚ ሰኖዶሱን ውሳኔ ለማስፈጸም ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል፡፡

“በቤተ ክርስቲያኑ ያለው ሕዝብ የእናንተን ቃል ተቀብሎ በውሳኔው መሠረት ይሔዳል ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በሰበካው ተሰሚነት ያላቸው አባቶችና የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮች እንደመኾናቸው ብዙኃኑ ምእመን ከእነርሱ ሐሳብ የተለየ አቋም እንደሌለውና በቃላቸው እንደሚጓዝ ለቋሚ ሲኖዶሱ አረጋግጠዋል፡፡“ጊዜያዊው አስተዳደር ተመድቦ ማጣራቱ በሚጀመርበት ወቅት ሕዝቡን አሳምናችሁ ከካቴድራሉ መውጣት አለበት፤ ከተለመደው ሥርዐተ አምልኮ ውጭ ማገዱ መቆም አለበት፤ ይኼን እንደምታደርጉ ቃል ግቡልን፤” ሲባሉም “ሙሉ ሓላፊነት እንወስዳለን፤” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚመደብበትንና አጣሪ ኮሚቴው የሚላክበትን ትክክለኛ ወቅት ቋሚ ሲኖዶሱ በቀጣይ እንደሚያስታውቃቸው በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

nebured aba gebramariam gebrasillasie

በስብሰባው ላይ በይፋ ባይገለጽም፣በጊዜያዊነት የተመደቡት አስተዳዳሪ፣የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የገዳማት መምሪያ ዋና ሓላፊ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ እንደኾኑና በዋና ጸሐፊነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ፣ በተቆጣጣሪነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ስታቲስቲክስ ዋና ክፍል ሓላፊ መ/ር ዓይናለም ተጫነ እንዲሁም በሒሳብ ሹምነት የሀገረ ስብከቱ የበጀትና ሒሳብ ክፍል ባልደረባ የኾኑት ወ/ሪት የሺ ወርቅ አለነ መመደባቸው ከውስጥ ምንጮች ተሰምቷል፡፡

የአጣሪ ኮሚቴው አባላትም፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ፣ምክትል ዋና ሓላፊው መጋቤ ሐዲስ ሐዋዘ ብርሃን ጫኔ፤ የአልባሳትና የንዋየ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ ኾነው እንደተመደቡ ተጠቁሟል፡፡ በማኅበረ ምእመናኑ አቤቱታ መሠረት የኦዲት ሥራው ያለፉትን ስድስት ዓመታት ሒሳብ የሚሸፍን ሲኾን፤ ሌሎች ጥያቄዎች በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጣርተው እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል፣ የሀገረ ስብከቱን የሁከት ይወገድልኝ ክሥ የሥር ፍ/ቤት ውድቅ ቢያደርገውም ተመልሶ ዳግም እንዲታይ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በወሰነው መሠረት፣ ትላንት በዋለው ችሎት ላይ፣ “ከአሁኑ ተቀራርባችሁ ችግሩን ብትፈቱት ነው የሚሻላችሁ፤” በማለት ዳኛው ጠበቆቹን ምከራቸው ተገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱ ክሡን የማስተናገድና የመሰለውን ዳኝነት የመስጠት ግዴታ እንዳለበት የገለጹት ዳኛው፣ ቤተ ክርስቲያን ግን አማኞቿ ላቀረቡላት ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ ክሥ መሥርታ ፍ/ቤት ስትቆም ያሳፍራል፤ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ለተባረረው አስተዳዳሪ በየፍ/ቤቱ በመሟገት የታወቁትንና ሀገረ ስብከቱን በመወከል ለቆሙት ኹለት ጠበቆችም፣ “ከአኹኑ ተቀራርባችሁ ችግሩን ብትፈቱት ነው የሚሻላችሁ፤” በማለት ምክራቸውን ሲለግሱ ተሰምተዋል፡፡

በትላንቱ ችሎት የተጠበቀው ወደ ፍሬ ነገር ክርክር ለመግባት የነበረ ቢኾንም፣ ተከሣሽ ማኅበረ ምእመናኑ፣ “ባስገባነው የጽሑፍ መልስ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንፈልጋለን፤” በማለታቸው ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለመጪው ሰኔ 25 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የከሣሽ ጠበቆች፣ “ኾን ብለው ነገሩን ለማጓተት ነው፤ የካቴድራሉ አስተዳደር ባለመመለሱ በአገልግሎቱና በሀብቱ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፤” በማለት የተጠየቀው ማስተካከያው አላስፈላጊ እንደኾነ ተቃውመዋል፡፡ የማኅበረ ምእመናኑ ጠበቆች በበኩላቸው፣ የውስጥና የውጭ አገልግሎቱ በተረጋጋ አኳኋን እየተከናወነ ከመኾኑም ባሻገር ንብረቱ በአግባቡ እየተጠበቀ እንዳለና ሒሳቡም በሚሊዮኖች ጭማሪ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡ የጽሑፍ ምላሻቸውን ለማስተካከል ባቀረቡት ጥያቄ ላይ የከሣሽ ጠበቆች አስተያየታቸውን እስከ ሰኔ 15 ቀን እንዲያስገቡና ማኅበረ ምእመናኑ ለሰኔ 25 ቀን በአስተያየቱ ላይ መልሳቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ ችሎቱ ትእዛዝ በመስጠት ተነሥቷል፡፡

ይኸው፣የሀገረ ስብከቱ “የሁከት ይወገድልኝ” ክሥ ተቋርጦ በቀጥታ ወደ ማጣራቱ እንዲገባ ለማግባባት፣ በራስ መንገሻ ሥዩም የሚመራ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን፣ ፓትርያርኩ ከሩስያ ሐዋርያ ጉብኝኝት እንደተመለሱ ጥያቄውን ያቀረበ ቢኾንም፣ ለጥረታቸው ዕውቅና ባለመስጠትና “እናንተው ክሡን አቋርጧችሁ ኑ፤” በሚል ሒደቱ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሠረት መቀጠሉ ታውቋል፡፡ እነራስ መንገሻ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትን ከማነጋገራቸው በፊት፣ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ስለሽምግልናው አስፈላጊነት በማግባባት፣ ቅዱስነታቸውን እንደሚያሳምንላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡ኾኖም ለሽማግሌዎቹ የገባው ቃል፣ በክሡ ሀገረ ስብከቱ እንደሚረታ፣ ቀደም ሲል ጠበቆቹን ይዞ እየቀረበ በአቋማቸው እንዲጸኑ ካስተማመነበት አቋሙ ጋራ በመጋጨቱ ፓትርያርኩን አስቆጥቷቸዋል፤ፊት እንዲነሡት ከማድረጉም ባሻገር፣ ለአጣሪ ኮሚቴው መቋቋም ተጨማሪ ምክንያት እንደኾነ ታውቋል፡፡

በሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢው ሊቀ አእላፍ ያዝ ዓለም ገሠሠ ሰብሳቢነትና በውጭ ግንኙነት መምሪያ ጸሐፊው መጋቤ ሀብታት ቃለ ወንጌል ታደሰ ጸሐፊነት የሚመራው አጣሪ ኮሚቴው፣ በመጪው ሰኞ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአቤቱታ የቀረቡ የሀገረ ስብከቱን የአሠራር ግድፈቶችን፣ የአስተዳደር ችግሮችንና የሙስና ተግባራትን በማጣራት የሚመረምረው ኮሚቴው፣ ውጤቱን በማስረጃ አስደግፎ በአፋጣኝ እንዲያቀርብ በፓትርያርኩ ታዟል፡፡ ኮሚቴው ተልእኮውን አጠናቆ የምርመራው ውጤት እስኪደርስ፣ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ካልተፈቀደ በቀር፤ ሠራተኛ መቅጠር፣ ማዛወር፣ ዕድገት መስጠትና የደመወዝ ጭማሬ ማድረግ የተከለከለ መኾኑን፣ ፓትርያርኩ ትላንት ሰኔ 7 ቀን ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አግደዋል፡፡