ከባርናባስ ገብረማሪያም/
Bega22601@comcast.net
ጨቋኙን የህወሓት ሰው በላ ስርዓት ከነግሳንግሱ ተጠራርጎ ካልተወገደ በኢትዮ}ያ
ምድር ላይ የተረጋጋ ሰላምና አስተማማኝ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም
የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት መጨረሻው ገደል ነው እንደሚባለው ሁሉ በኮሜዲ የተጀመረውን የህወሓት ጉዞ በትራጀዲ መደምደሙ የሚገርም አይደለም:: ዛሬ ወደዱም ጠሉም ራሳቸው በቆፈሩት ጉድጓድ የሚገቡበት ፣ ራሳቸው በለኰሱት እሳት የሚለበለቡበት ፣ ራሳቸው በዘሩት የከፋፍለህ ግዛ መርዝ የሚያጭዱበት ፣ የባዕድ ሎሌ በመሆን በሀገርና በህዝብ ላይ በሰሩት ክሕደት የሚጋለጡበት ፣ ለልጅ ልጆቻቸው ይተርፋል ብለው የዘረፉትን የህዝብና የሀገር አንጡራ ሃብት እንዲሁም በጥላቻ ላይ የተመሰረተ በወገኖቻችን ላይ የፈፀሙትን ግፍና ያፈሰሱትን ንፁህ ደም ይዋል ይደር እንጂ የሚጠየቁበትን ቀን ሩቅ እንደማይሆን በውል የተረዱ የህወሓት መሪዎች ገመናቸውንና ሽንፈታቸውን ለመሸፋፈን ሲባል ጥርስ የሌለው አንበሳ መስለው ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውን ሰሞኑን በመቀሌ ተሰብስበው ያወጡትን አስቂኝ መግለጫ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል:: መግለጫውን ስናየው “ዛሬ አይደለም አጎንብሶ ማልቀስ ድሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ” የሚለውን የሀገርኛ አባባል ያስታውሰናል::
ህወሓቶች በሻዕቢያ አጃቢነት ደርግን ጥለው አዲስ አበባ ገብተው በዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ዙፋን ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ በአንድ በኩል ስማቸውን እንኳን ሳይቀይሩ የትግራይ ነፃ አውጪ ነን እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ደርግን ማሸነፍ ማለት ኢትዮ}ያውያንን ማሸነፍ ማለት አድርገው ቆጥረውታል:: ከዚህ ትዕቢትና ድንቁርና በመነሳትም ህዝቡን እንደ ጠላት እንደ ሞርኰኛ እንደ ተስፈኛ በማየትና በመናቅ ከኛ በላይ ጀግና የለም:: ከኛ በላይ መተኰስና መግደል የሚችል ሰው የለም :: ከኛ በላይ አገርን ማስተዳደር የሚችል ዜጋ የለም:: ትግራዋይ በተፈጥሮው ጀግና ነው:: ወዘተ በማለት ሌላውን ህዝብ ግን ራሱን ነፃ ማውጣት ፣ መብቱን ማስከበርና ሀገሩን መጠበቅ የማይችል በተፈጥሮው ፈሪና ደካማ አድርገው በመገመት የልብ ልብ ተሰምቷቸው 100 ሚሊዮኑን ህዝብ አንገት አስደፍተው እንዳሻቸው እየመዘበሩ እኖሆ አሁን ላለንበት ጊዜ ደርሷል::
ካሁን በሗላስ የህወሓት ዕድል ምንድን ነው?
በአንድ ወቅት ዶክተር መራራ ጎዲና ሲናገሩ “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል” ብለው እንደነበር ይታወሳል:: በዚያን ጊዜ እንደ ተረት ይታይ የነበረው አባባል ዛሬ በተግባር ህያው ሆኖ ታይቷል:: የናቁትን ድንጋይ ማዕዝን ይሆናል እንዲሉ ዛሬ ህወሓቶች ያለሙትን ዘላለማዊ ስልጣን በህዝባዊ ዓመፅ ተንዶ እግሬ አውጭኝ ብለው ወደ መጡበት ወደ ትግራይ ሲፈረጡጡ ማየት “አምላኬ ሆይ ይህን ሳላይ እንኳን አልገደልከኝ” የሚያሰኝ ነው:: ወደ ትግራይ ሂደውም አልቀናቸውም:: ዛሬ ትግራይ በህዝባዊ ተቃውሞና ሰላማዊ ሰልፍ ተጥለቅልቃለች:: ከዚህ ፍርሃትና ጭንቀት በመነሳትም ሰው በላ የህወሓት መሪዎች በሜዳ ላይ እንደነጋበት ጅብ በመደነባበር የሚገቡበትን መላቅጡ ጠፍቶባቸው የቀቢፀ ተስፋ መግለጫ ቢያወጡ የሚገርም አይደለም:: ከድጡ ወደ ማጡ የገቡበት ጊዜ ስለሆነ ሲሞቱ መንፈራገጥና አጉል መላላጥ የበለጠ እንድንጠነክር ያደርገናል እንጂ ሊያስደንቀን ወይም ሊያስነግጠን አይገባም:: ሐቁም እንደሚከተለው ነው
- የመጨረሻ ምሽጋችን ብለው ሲተማመኑበትና እንደብረት አጥር ሲያዩት የነበረው የትግራይ ምድርና ህዝብም ከጥቂት ካድሬዎቻቸውና ከግል አጃቢዎቻቸው በስተቀር አንድም የሚከተላቸው አያገኙም:: ህወሓት የከሰረ የህዝብ ደምና ሃብት ነጋዴ መሆኑን ህዝቡ በሚገባ ተረድቶታል:: ዛሬ የትግራይ ህዝብ መድህን ብለን መጥራት የምንችለው ራሱን ማዳን ያቃተው የህወሓት አጭበርባሪ ቡድን ሳይሆን እንደ ዓረና ትግራይና ሌሎች ሀቀኛ ልጆቹ በከፈሉት መስዋእትነት የመጣውን ለውጥ ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ መሆኑን በሚገባ ተረድቶታል::
- ህወሓቶች እንደገና የለመዱትን ብጥብጥ ለመፍጠር ቢሞኩሩ ከማንም በላይ ተጎጂ የሚሆኑት እነርሱ ራሳቸው ናቸው:: ህዝቡም በተለይም ወጣቱም ቢሆን እንኳን ዛሬ ፈርጥጠው በመቀሌ በመሸጉበት ሁኔታ ቀርቶ በአዲስ አበባ ቤተ መንግስት በዙፋን ላይ በነበሩበት ጊዜም ቢሆን አልፈራቸውም:: አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ የህወሓት ዓፈናና ግዲያ ያንገሸገሸው የኢትዮያ ወጣት በአንድ ወር ባልሞላ ውስጥ ከሚሊዮን በላይ ወታደር መሆን እንደሚችል ማወቅ አለባቸው:: ጀግንነት ማለት አላማ ነው:: ጅግንነት ማለት ህዝባዊ ወገንተኝነት ነው:: ጀግንነት ማለት ለሀገርና ለወገን ጥብቅና በፅናት መቆም ማለት ነው :: ጀግንነት ማለት እምቢ ለባርነት እምቢ ለዓፈና እምቢ ለሀገሬ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ በቁርጠኝነት መነሳት ማለት ነው:: ይህ ደግሞ ከአያት ቅድመ አያት የወረስነው የአልገዛም ባይነት ባህል ነው:: የአሸናፊነት ሚስጢርም ጠመንጃና ዱላ አይደለም:: የድላችን ዋስትና አንድነታችንና ሕብረታችን ነው:: በመሆኑም ዛሬም እንደ ትላንቱ ወጣቱም ሆነ ህዝቡ ከህወሓት በላይ ጥበቡም ሞራሉም ወኔውም የበላይነቱን ያረጋገጠበት ጊዜ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው:: ስለዚህ ድርድራችን ከወደቀ ግንድ ጋር ሳይሆን እንዴት አድርገን የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንችላለን ነው::
- ህወሓቶች ከእንግዲህ ወዲህ የፈለጉ ቢፅፉና ቢናገሩ ከመላላጥ በስተቀር የዶክተር ዓቢይን እጅ ጠምዝዘው ወደ ስልጣን የሚመለሱበትን ዕድል አብቅቷል:: የህወሓት የስለላና የዓፈና መዋቅር ከትግራይ በስተቀር በሌሎች ክልሎች ተንኰታኩቶ ፈርሷል:: በትግራይም አሁን ጀምሯል:: በራሳቸው በህወሓት ውስጥም በተለያዩ ጎበዝ አለቆች ተከፋፍለው በጎሪጥ እየተያዩ ያሉበት ሁኔታ ነው:: አለኝታችን ናቸው ብለው እንደጋሻና መከታ ሲመለከቷቸው የነበሩት ከመለስ ቀጥሎ ስልጣን የነበራቸው እንደነ ሳሞራ የኑስና ጌታቸው አሰፋም ከስልጣን ወርዷል :: ይህ ማለት ደግሞ ትርጉሙ የግለ ሰቦቹን ከስልጣን መውረድ ሳይሆን የህወሓት ንግስና እየፈራረሰና እየተንኰታኰተ ቁልቁል እየወረደ እንደሆነ የሚያመላክት ሂደት ነው:: ዛሬ ህወሓቶች ኤርትራን ጨምሮ አካባቢያቸውን ሁሉ በጠላት የተከበበ ነው:: ከእንግዲህ ወዲህ ከኤርትራ ጋር ያላቸው የመደራደር ዓቅምም ሆነ ሕጋዊነት የላቸውም ተነጥቋል:: የዳር ድንበር ጉዳይ የፌዷራል መንግስት ጉዳይ እንጂ የአንድ ራሱን ነፃ አውጪ ነኝ የሚል ጠባብ ቡድን ጉዳይ አይደለም:: ህዝቡ በተለይም የትግራይ ህዝብን ነጋ ጠባ በሬ ወለደ እያሉ የሚያታሉሉበት የፓለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርዳቸውንም አልቋል:: ዛሬ ህወሓቶች ተራ እረኛም ሳይቀር የቀን ጅቦች ሌቦች ውሸተኞች ከሓዲዎችና ሀገር ሸያጮች መሆናቸውን ያውቃቿል::
- በዲፕሎማሲ አካባቢም ቀንደኛ ተዋናይ መስለው ለመታየት የሚያደርጉትን ጥረት ከእንግዲህ ወዲህ ምንም እጅና ዓቅም እንደሌላቸው ተገንዝቧል:: በተለይም በአጎራባች ሀገሮችም ቢሆን ተቀባይነት የላቸውም:: ብዙ ሀገሮች 100 ሚሊዮን የህዝብ ድጋፍ ያለው የዶክተር ዓቢይን አስተዳደር ትተው በመክሰም ላይ ያለውን ጎጠኛ የማፍያ ቡድን ይደግፋሉ ብሎ ማሰብ የማይሆን ነው::
- አሁን በእጃቸው ላይ ያለው ከህዝቡ አፍ የነጠቁትና የዘረፉትን የሀገራችን አንጡራ ሃብት ነው:: በአሁኑ ጊዜ የሀገራችን ኢኮኖሚና ልማት የተከፋፈሉት አራት አካላት ናቸው:: እነሱም መንግስት ኢፈርት መከላኪያና አላሙዲን ናቸው:: ከነዚህ ውስጥ በህወሓት ቁጥጥር ስር ያለው ኢፈርትና መከላኪያ በድምር ከጠቅላላ የሀገሪትዋ ኢኮኖሚ ከሲሶ በላይ እጅ አላቸው:: ይህ በያንዳንዱ ካድሬና ባለስልጣን እጅ ያለው እንዲሁም በተለያየ መልክ ከሀገር ሸልኮ የወጣ ገንዘብንና ወርቅን አይጨምርም:: ይህ ሀብት ደግሞ ሌሎች ኢትዮያውያንን በማባረር በመሰወርና በመግደል በሀይል በመንጠቅ የተሰበሰበ የዜጎቻችን ደም ስለሆነ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደ ህዝቡ መመለሱ አይቀሬ ነው:: ምን የት እንዳለ ጥናቱ ቀደም ብሎ እንደተጠናቀቀ ሰምተናል:: ስለዚህ ሌባና ዘራፊ ከሕግ በላይ ሆኖ እንደፈለገ የሚፈነጭበት በአንፃሩ ንፁሃን ዜጎች የሚሸማቀቁበትና የበይ ተመልካች ሆነው የሚኖሩበት ዘመን እያከተመ ነው::
- ከአንድ አካባቢ የወጣው ህወሓት ዛሬም እንደለመደው ሌሎች 80 ብሄር ብሄረሰቦችን በሃይል በማንበርከክ እየበጠበጥኩ ፀረ ሰላምና ፀረ ሕገ መንግስት ሁኘ እንቀሳቀሳለሁ የሚል የጥፋት መንገድ ከተከተለ ደግሞ ከኢሕአዴግ አባልነት ማባረርና ፍቃዱን መንጠቅ ብቻ ሳይሆን እንደ ፀረ ሰብኣዊ ፍጡር የሆነ ሽብርተኛ ታይቶ ከነግሳንግሱ ከምድረ ገፅ እንደሚጠፋ ጥርጥር የለውም:: ሽብርተኛን መታገል ደግሞ የኢትዮያውያን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአካባቢያችን ሀገራት ከዚያም አልፎ የዓለም ማሕበረሰብም ጭምር ሃላፊነት ነው:: ስለዚህ ህወሓት “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ አሊያም ድንጋይ ነው ተብለህ ትጣላለህ ” የሚለውን አባባል ተገንዝቦ ከያዘው የጥፋትን መንገድ ተመልሶ ልኩን አውቆ እንዲኖር ይጠበቅበታል:: ካልሆነ ግን እጁን ከመሰጠት አልፎ ምንም ሌላ አማራጭ የለውም:: ኢትዮያውያን ከህወሓት በላይ ነቅቷል አልፈው ሄዷል:: መንገዱንም ያውቁበታል:: አሁን ያለው ለውጥም ድንገት የመጣ ሳይሆን ቀደም ብሎ ብዙ ተሰርቶበታል::
የተጀመረውን ለውጥ እንዳይቀለበስ ከሁላችን ምን ይጠበቃል?
ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ እንዲመጣ ለማመቻቸት ይቻል ዘንድ ለህወሓቶች ለዶክቶር ዓቢይ አስተዳደርና ለህዝቡ ያለኝን ምክርና አስተያየት አንድና አንድ ብቻ ነው:: እሱም የተጀመረውን ለውጥ ነቅቶ መጠበቅ ፣ በልጦ መገኘትና የተበተነውን ሓይል በማሰባሰብ የሁሉም ድምር እንቅስቃሴ አቅጣጫውን ወደ አንድ ሀገራዊ ጉዳይ እንዲያመራ ማድረግ ነው::
- ለህወሓቶችና አጃቢዎቻቸው በሙሉ በያሉበት
ህወሓቶችን መምከር ከድንጋይ ጋር እንደመላተም ያህል ነው:: ምክንያቱም “ በዘመነ ምኒሊክ የታወረ በምንሊክ አምላክ እያለ ይኖራል” እንደሚባለው ሁሉ ህወሓቶችም በመለስ ዜናዊ }}ና በአእምሯቸው ውስጥ የተገጠመላቸው የዘመነ ደደቢት አደንዛq ሶፍት ዌር እንደ ወባ በሽታ በደማቸው ውስጥ ሰርፆ ሌላ አማራጭ መንገድ እንዳያዩና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ አመለካከት እንዳይቀበሉ ጠፍሮሮ ስለያዛቸው እነሱ የሚናገሩትን እንጂ ሌላው የሚናገረውን የማዳመጥና የመስማት ተፈጥሮ የላቸውም:: ተፈጥሮን መለወጥ ደግሞ አይቻልም እስከ መቃብር የሚዘልቅ ባህርይ ነው::
ህወሓቶች የሚሰማ ጀሮ የሚያይ ዓይንና የሚያስተውል አእምሮ ቢኖራቸውና አሁን ያለንበትን ጊዜ በጥልቀት ቢገመግሙት ኖሮ ይህን ዓይነት አሳፋሪና የቀቢፀ ተስፋ መግለጫ ባላወጡት ነበር:: መግለጫውም ትክክለኛው ባህሪያቸውን ነው ጋሃድ ያደረገው:: አንደኛ ድንቁርናቸውንና ውሸተኝነታቸውን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል:: ሁለተኛ ምን ያህል ተስፋ የቆረጡና የዘቀጡ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው:: ሶስተኛ ህዝቡን ለማደናገር የሚጠቀሙበትን የማፍያነት ባህሪያቸውን በግልፅ ያሳያል:: ህወሓቶች እውነት ከራሳቸው በላይ ለሀገርና ለህዝብ የቆሙ ቢሆኑ ኖሮ ይህ ለውጥ እነሱንም ጭምር ለማዳን የሚችል መሆኑን በቅን ልቦና በተረዱትና ለተግባራዊነቱም ትብብር ባደረጉት ነበር :: ነገር ግን ዓይናቸውን በፍቅረ ንዋይ፣ አእምሯቸውን ደግሞ በትዕቢትና በንፃሃን ደም ስለሰከሩ አላስተኛ ብሏቸው ይኸውና አሁንም እኛ የማንገዛትና የማንግጣት ሀገር ገደል ትግባ የሚል አጥፍቶ የመጥፋት መንገድ ይዟል:: ዶክተር ዓቢይ የሚሰራቸውን ስራዎችን ለማጣጣልና ከነርሱ ውጭ ሀገሪቱን ማስተዳደር እንዳልቻለ ስራውን ለማጉደፍ ሲባል ሆን ብለው የህፃናት የእንቆቁልሽ ጨዋታ ሲጫወቱ እናያለን::
ይህ ዓይነቱ የድብብቆሽ ጨዋታ ደግሞ ተመልሶ የራሳቸውን ሞትና ውድቀት የሚያቀላጥፍ እንጂ ጭቆናና ጊዜ የወለደውን ትግል ወደሗላ መመለስ አይችሉም:: ከእንግዲህ ወዲህ ህወሓት ወደ ስልጣን ተመልሶ በኢትዮያ በበላይነት ቁጭ ብሎ ዳግም የኦሮሞን የአማራንና ሌላውን ህዝብ ረግጦ ይገዛል ብሎ ማሰብ መለስ ዜና ከጉድጓድ ተነስቶ ይነግሳል ብሎ መናገር ይቀላቿል:: ይቅርና አማራና ኦሮሞ ሊገዙ ለአርባ ዓመታት በስሙና በደሙ እየነገዱ በሞኖፓል ሲገዙት የነበሩት የትግራይ ህዝብም ቢሆን ከእንግዲህ ወዲህ የህወሓት ሰው በላ ስርዓት የጭቆና ቀንበር የሚሸከም ትክሻ አይኖረውም:: በቃኝ ብሏል:: ስለዚህ ህወሓቶች ከእሳት ጋር ከመጫወት ይልቅ የዘረፉትን ሀብት ይዘው አርፈው ቢበሉ ይሻላቿል:: ካልሆነ ግን የጋዳፊንና የሳዳም ሁሴንን አሟሟት እንመርጣለን ካሉ ደግሞ ምርጫው የራሳቸው ነው:: በዚሁ አፍራሽ ተግባራቸው ከቀጠሉ ደግሞ ነገ እንደ ደርገ ኢሰፓ የቀይ ሽብር ወንጀለኞች ከያሉበት እየተለቀሙ እነሱም በተራቸው ቃሊቲ መግባታቸው አይቀሬ ነው:: የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳምና:: ስለዚህ ለራሳቸውም ሆነ ለህዝባቸው ሲሉ ከወዲሁ የጥፋት መንገዳቸውን አስተካክለው የሰላም መንገዱን እንዲከተሉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሬን አቀርባለሁ::
- ለኩቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አራት ነጥቦችን መናገር እፈልጋለሁ::
አንደኛ እስካሁን ድረስ ባደረጉት መልካም ጥረት የህዝቡን ልብ ለማግኘት የቻሉበት ዋናው ምክንያት ጥሩ ተናጋሪ ስለሆኑ ብቻ አይደለም:: ከፊትዎ በሚነበበው ቅን ልቦናዎናና ከበሰተጀርባዎ የሚፈነጥቀው የኢትዮያዊነት ፋና ተጨምሮበት የህዝቡን የትግል ውጤት ስለሆኑም ጭምር ነው:: ስለዚህ የሰማእታቱን ትልቅ አደራ እንደማይረሱ እምነቴ የፀና ነው::
ሁለተኛ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት ህዝቡን ወጣቱንና ተፎካካሪ ሐይሎችን ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ይጠበቅ ዘንድ በፓሊሲና በሕግ ማዕቀፍ ካልተካተቱ አሮጌውን ስርዓት እንዲያንሰራራ በር የሚከፍት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል:: ለውጥ ሲባል ደግሞ በመንግስት አካባቢ የሚደረገው የጉልቻ መቀያየር አይደለም:: ዋናው መሰረቱ መጀመሪያ የጠራ ራእይ ያስፈልጋል:: ከዚያም ራእዩ ወደ ፓሊሲ ሕግና ስትራተጂ መመንዘር ያስፈልጋል:: ከዚያም ይህን ራእይ ፓሊሲና ሕግ ተግባራዊ የሚያደርጉና ሚዛንን የሚጠብቁ መንግስታዊና ህዝባዊ ተቋማት እንዲያብቡ ማድረግ የግድ ይላል:: የቀድሞ የአሜሪካ ፕረዚዳንት ባራክ ኦባማ ስለለውጥ ሲናገሩ “ለአፍሪቃ ጠንካራ መሪ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት ነው የሚያስፈልጋት” ብለው እንደነበር ይታወሳል:: በመሆኑም ለውጡ መነሻውንና መድረሻውን የማይታወቅ ፣ ሁሉንም የለውጥ ባለድርሻ አካላትን የማያሳትፍ ፣ በአየር ላይ የተንሳፈፈና በአንድ መሪ ብቻ የተንጠለጠለ የዳበሳ ትግል ከሆነ ግን የትም አይደርስም:: ስለዚህ ዶክተር ዓቢይ ማድረግ የሚገባቸው የፈለገውን መስዋእትነት ይጠይቅ ቤት ለመገንባት መጀመሪያ ሞሶሶ ማቆም እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሀገር ለመገንባትም መጀመሪያ የፓሊሲና የሕግ ሞሶሶ መሰረት መጣል እንደሚያስፈልግ በውል በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ ቅድሚያ ሰጥቶ መረባረብ ያስፈልጋል:: ህዝቡ የሚጠቅመውን የፓሊሲና የሕግ ዋስትና ካገኘ ራሱ ዘብ ሆኖ ይጠብቋል::
ሶስተኛ ህወሓቶች ልካቸውን አውቀው አርፈው እስከሚኖሩ ድረስ እንዳበደ ውሻ መቅበዝበዛቸው የማይቀር ነው:: ለብትና ከሚጠቀሙበት ስልቶች አንዱም ቤት ዘግተው ስብሰባና ግምገማ እያሉ የግለ ሰዎችን ሞራልና ስነ ልቦና መስበር፣ አጀንዳ ማስቀየስና ማሰልቸት ነው:: ይህ ዓይነቱ ጭንቀላት ገዳይ የሆነ ስልት ደግሞ ካርባ ዓመት በላይ በትግራይ ምድር በሚገባ ሰርተውበታል:: ዛሬም ዶክተር ዓቢይን ለመፈታተን ከትግሉ ፈር ለማላቀቅና ለማዳከም ሲባል ስብሰባ እያሉ ማስፈራራትና መጎትጎት የጀመሩበት ምክንያት ለጤና እንዳልሆነ ህዝቡ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለው ይገኛል:: ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ በፓርላማም ሆነ በኢህኣዴግ ደረጃ የሚደረገውን ስብሰባ እንዳለፈው ቤት ዘግቶ የሚቦካ የጓሮ ሽኩት ሳይሆን ለህዝቡ ይፋ በሆነ መልኩ በዜና መገናኛ የተደገፈ ሆኖ መካሄድ አለበት:: ህዝቡ ማን ምን እያለ እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል:: ህዝቡ የሚጠቅመውን ሃሳብ ለመደገፍ የማይጠቅመውን ሃሳብ ደግሞ ለመቃወም ይችል ዘንድ ስብሰባው ግልፅ መሆን ያለበትን ግልፅ በሆነ መንገድ በይፋ መካሄድ አለበት:: ካልሆነ ግን በህዝቡ መስዋእትነት የተጀመረውን ለውጥ በጥቂት በህወሓት/ኢሕአዴግ የስልጣን ባላባቶች መካከል በጓሮ በሚደረገው ዝግ ስብሰባ የዶክተር ዓቢይን እጅ ጠምዝዞ ለመቀልበስ የሚደረገው ሙኮራ ተቀባይነት የለውም:: ጉዳዩን ህዝቡ ሳያውቀው ሾላ በድፍን ሆኖ ከቆየ በሓላ ድንገት መርዶ ሆኖ የሚመጣ ከሆነ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆነው ህዝቡ ሳይሆን የዶክተር ዓቢይን አስተዳደር ነው::
ህወሓቶች በዚሁ አካሄድ የተካኑ ናቸው:: ሌላውን ትተን የኢትዮ ኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት ሰሞኑን በኢሕአዴግ ውስጥ በጓሮ የተወሰነውን ውሳኔ በኢሕአዴግ መንግስት ላይ አሜኔታን የሚያላላ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል:: ህወሓቶች ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ በትግርኛ ቋንቋ ለህዝቡ ሲናገሩ ዶክተር ዓቢይን ተጠያቂ አድርገው ነው እያቀርቡት ያሉት:: በተለያየ ቋንቋ በተለያየ ይዘት እየተመነዘረ በተለያየ ሚዲያ አደናጋሪ በሆነ መንገድ እየተገለፀ ህዝብንና ሀገርን ማተራመስ የቻለው ውሳኔ ከጅምሩ ግልፅነት ስላልነበረው ነው:: አጀንዳው ያቀረበው ማን ነው? ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ ለምን አሁን አጣዳፊ ሆነ? ከአጀንዳው በስተጀርባ ያለው ሶስተኛ ሐይልስ ማን ነው? መንግስት እያለ ለምን በድርጅት እንዲወሰን ተደረገ? የማን ፍላጎት ለማርካት ተብሎ ነው በጥድፊያ እንዲወሰን የተደረገው? የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ነው እንዳይባል ህዝቡ አልተጠየቀም:: ስለዚህ ሚስጢሩ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ለብዙዎቻችን እንቆቁልሽ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው:: ለዚህም ነው የዳር ድንበሩን ጉዳይ አካሄዱ ግልፅነትን ቅንነትንና ህዝባዊ ታማኝነትን የጎደለው ውሳኔ ስለሆነ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ብለን እየተቃወምን ያለነው::
አራተኛ ለዶክተር ዓቢይ ማሳሰብ የምፈልገው ዓቢይ ጉዳይ መንግስትንና የፓለቲካ ድርጅቶችን መለየት አለበት:: በሕገ መንግስቱ የተደነገገው ለሁሉም የፓለቲካ ፓርቲ እኩል ተጠቃሚነትና እንቅስቃሴ የሚሰጥ ቢሆንም እንደ ህወሓት የመሳሰሉት ድርጅቶች ግን የበኩር ልጆች አድርጎ የሚያይ ሌሎች ደግሞ እንደ እንጀራ እናት ወይም እንደ ሁለተኛ ዜጋ አድርጎ የሚመለከት ነው:: በሃብት ክፍፍልም ሲታየ ኢፍትሓዊ ነው:: ህወሓት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥሮ በሁለት እጁ እየፈተፈተ ሲበላ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ግን በልመና የተሰማሩ ናቸው:: በምን ሂሳብ ነው የአንድ አካባቢ ነፃ አውጪ ነኝ የሚል ድርጅት ከሕግ በላይ በመሆን አንዴ ጦርነት ያውጃል ሌላ ጊዜ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ክብርና ስም ያጎድፋል ሌሎች ድርጅቶችንም ይሳደባል ያስፈራራል ይንቃል ይገድላል ያስራል:: በምን ሂሳብ ነው ህወሓት ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ድርጅቶች በተለየ መልኩ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እየገባ እየፈተፈተ እንዲኖር እሽሩሩ እየተባለ የሚኖረው እስከመቼ ነው:: ስለዚህ ይህ ሕገ ወጥና አጉራ ዘለል ድርጅት ልኩን አውቆ እንዲኖርና አደብ እንዲገዛ ማድረግ ያስፈልጋል:: ስለሆነም ሕጎቻችንን በአስቸኳይ በመፈተሽና በማስተካከል የህወሓት መረኑን የለቀቀ ውንብድና በሕግ የሚገዛበት መንገድ እንዲፈለግ የአክብሮት ጥሬን አቀርባለሁ::
- ለህዝቡ ለወጣቱና ለተፎካካሪ የፓለቲካ ድርጅቶች ያለኝን ጥሪና መልእክትም አጭር ነው::
ሁላችንም በጋራ መስማማት ያለብን ዓቢይ ጉዳይ የችግሩን ጠንቅና የጭቆና ምንጭ የሆነውን የሻገተና አሮጌ የህወሓት ስርዓት በፍፁም የመፍትሄ አካልና የለውጥ አጋር መሆን አይችልም:: በተግባርም እያየነው ነው:: ስለዚህ ትግሉ በለውጥ ፈላጊው ሐይልና በአሮጌው ስርዓት መካከል መሆኑን በማመን አሰላለፋችንንና ሚናችንን በመለየት ጥርት ያለ አቋም ይዘን የለውጥ ሂደቱን መደገፍ ይጠበቅብናል:: ምርጫው የባርነትና የነፃነት ጉዳይ ነው:: ምርጫው በሰላም የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ነው:: ምርጫው የሀገራችንን አንድነትና ድህንነት የመጠበቅና የመበታተን ጉዳይ ነው:: ምርጫው በህወሓት ስር ወድቆ ያለፈውን ዓሰርቱ ዓመታት የሰቆቃ ዘመን እንደገና መድገም ወይም ሰብሮ የመውጣት ጉዳይ ነው::
ዶክተር ዓቢይ አህመድ በህወሓት በጎ ፈቃድ የመጣ ሳይሆን የኦሮሞ ቀይሬዎች ፣ የአማራ ፋኖዎች፣ የትግራይ የአሉላ አባ ነጋ ልጆችና እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን ማዕዝናት ያሉት ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የከፈሉትን መስዋእትነት ድምር ውጤት ነው:: በመሆኑም ይህ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በዋዛ ፍዛዛ ልክ እንደ 97ቱ በማዘናጋት ተመልሶ በሰው በላው የህወሓት ስርዓት እጅ ከወደቀ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆነው ዶክተር ዓቢይ አህመድ አይደለም:: ዋናው ተጠያቂው የሚሆነው የትግሉንና የለውጡን ባለቤት የሆነውን ህዝቡ ወጣቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የቆሙ ወገኖች ሁሉም ጭምር ነው:: ስለዚህ ለውጡ ግቡን ሊመታ የሚችለው በአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥረትና መልካም አሳቢነት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም የትግሉንም የመፍትሄውንም አካል በመሆን የነቃና የተደራጀ ተሳትፎ ስናደርግ ብቻ ነው:: በሌላ አነጋገር ሚሊዮኖች ዓቢይ ሲፈጠሩና ሲደራጁ ብቻ ነው ለውጡ የሰመረና ቀጣይነት የሚኖረው::
የለውጥ አጋር ሲባል ደግሞ ምኞት ብቻውን በቂ አይደለም:: ለውጥን ከፈለጉ በተግባር የለውጥ ሰው ሆኖ መገኘት የግድ ይላል:: ራስን ሳይለውጡ ስለለውጥ መናገር ይከብዳል:: ለምሳሌ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ብዙ የፓለቲካ ድርጅቶች እንዳሉን ይታወቃል:: ነገር ግን ስንቶቹ ናቸው የጥላቻ ፓለቲካ ፣ ጠባብ ቡድናዊ እምነት ፣ የዘር ፓለቲካና የመጠላለፍን አዙሪት ሰብረው በመውጣት በለውጡ የተሃድሶ ጎዳና ለመራመድ የሚያስችላቸውን ጥርት ያለ ድርጅታዊ የፓለቲካ ቁመና ይዘው የሚገኙት? ስንቶቹ ናቸው አሁን ያለውን የሀገራችን ውስብስብ ሁኔታና እውነታ በአግባቡ አጢነው ከጭራነት ወጥተው ወደ ግንባር ቀደም መሪ ድርጅትነት የተሸጋገሩት? እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ራሱን የቻለ የመጀመሪያው የትግል ምዕራፍ ነው:: ስለዚህ “ፈረሱም ሜዳውም አለ“ ተብሏልና ይህንን ወርቃማ ጊዜ ሳያመልጥ ብቁ ሆኖ በቦታው መገኘትና በትግሉ ሜዳ ላይ መጋለብ ያስፈልጋል:: በመሆኑም ዛሬ የፓለቲካ ድጅቶች ነን የሚሉት ሐይሎች ሁሉም በህዘብ ፊት በተግባር የሚፈተኑበት ጊዜው አሁን ነው::
በማጠቃለል በሀገርኛ አባባል “ የነብር ጅራት አይዙም ከያዙም አልቁም ” ይባላል:: ምክንቱም ነብሩን ይዘውና አቁስለው ከለቀቁት ተመልሶ የሚበላቸው መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ነው:: ህወሓት ነብር ነው ማለቴ አይደለም:: ድመትም ብትሆን ተመሳሳይ ፀባይ ነው ያላት:: ያም ሆነ ይህ ዛሬ ዕድሜ ለታጋዩ ህዝባችን የህወሓት ቡድን ሓፍረትንና ውርደትን አከናንቦ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ትግራይ እንዲፈረጥጥ አድርጎታል:: ይሁን እንጂ ህወሓት አከርካሪውን ተመታ እንጂ ገና አልሞተም:: ህወሓት ከመሞቱ በፊት መንፈራገጡና መላላጡ አይቀርም:: ስለዚህ በዋዛ ፍዛዛ ተመልሶ ዳግም ህይወት እንዳይዘራ ሁላችንም በያለንበት እንደ አንድ ሰው ዘብ በመቆም ዋጋ የከፈልንበትን የለውጥ ጎዳና አቅጣጫውን እንዳይስት ነቅተን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለብን እኛው ራችን ነን:: በምንም መልኩ ከእንግዲህ ወዲህ ህወሓት እኛን በጎሳ በዘርና በሃይማኖት እርስ በራሳችን እየከፋፈለ በማባላት ዳግም ወደ ስልጣን የሚመጣበትን ዕድልና ቀዳዳ ማግኘት የለበትም:: ስለዚህ ለውጡ ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆንና የተከፈለውን የደም መስዋእትነትም ደመ ከልብ ሆኖ እንዳይቀር በተለይም የዚሁ ወጣት ትውልድ ፈተናና ሃላፊነት መሆኑን ቆም ብለን በሰከነ አእምሮ ማሰብ ይኖርብናል::
በሌላ ቀን በሌላ ርሰ ጉዳይ እስከምንገናኝ ደህና ደህና ሰንብቱ
