«እኔን ጀሃዳዊ ሐረካት ላይ እኔን ካላሳዩ የመጨረሻ ደደቦች ናቸው!»

ስራ ላይ ነበርኩኝ። ጅሃዳዊ ሐረካትን እናሳያለን ሲሉ ስራዬን አቋርጬ ወደቤት አቀናሁኝ። ጀሃዳዊ ሐረካት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ ትግልን ለማጠልሸት የተዘጋጀ ቀጣፊ ፊልም መሆኑን ባዉቅም፤ የህዝብ ወኪሎች በእስር ቤት ቆይታቸው ምን ይመስላሉ? የሚለውን ለማየት ጉጉት አደረብኝ። ኢቲቪን ከመክፈቴ በፊት የለበስኩትን ሱሬና ሸምዝ ቀየርኩኝ።ሰላምን ለማስፈን ሲሉ የታሰሩ ወንድሞቼን በክት ልብስ ነው ማየት ያለብኝ አልኩኝ።በሱና (በነብያዊ አለባበስ) ሶፋው ላይ መሰየም አለብኝ ብዬ ወሰንኩ።ጀለቢያዬን አዉጥቼ ለበስኩ።የእስላም ኮፊያዬን ደረብኩ። በጣም እየወደድኩት ያጣሁት ነገር ቢኖር ሽቶን ነው።አለርጂ (ሐሳሲያ) ስላለብኝ ሽቶ አልቀባም።ግን የዚያን ቀን የኡድ ሽቶን እጄንና ጀለቢያዬን ቀባሁ።እንደተለመደው አላስነጠሰኝም። ሶፋው ላይ ተቀመጥኩ።
ከህወሃት የደህንነት ሰዎች ጋር እራሴው በራሴው ተወራረድኩ። «እኔን በዛሬው ጀሃዳዊ ሐረካት ላይ ካላቀረባቹ የመጨረሻ ደደቦች ናቹ!» አልኩኝ። ወንድሞቼን ተራ በተራ አየሁ። የፊልም እስክሪፕት ጸሃፊው በጣም አማተር መሆኑን መረዳት ተረዳሁ።አራንባና ቆቦ የሆኑ ነገሮችን በማገኛነት ስሜት የማይሰጥ ነገር ደርድሯል። ፊልሙ የደህንነቱን መስሪያቤትና ህወሃት የሚመራዉን መንግስት ኪሳራ እንደሚያመጣበት አስተዋልኩ።እንደ ጋዜጠኛም ስራ አልፈታሁም እስክሪፕቶና ወረቀት ይዤ ማስታወሻዬ ላይ ጽፋለሁ። ቪዲዮው ዳዉንሎድ እስኪሆን ድረስ ድምጹን መያዝ ስለነበረብኝ በመቅረጼ ድምጼ ቀዳለሁ።
ወደ ፊልሙ መገባደጃ አካባቢ የኔን ምስል ፊልሙ ላይ ስመለከት ከትከት ብዬ ሳቅኩኝ። በርግጥም እኔን በማቅረባቹ ደደብ እንደገመትኩትም ደደብ አይደላቹም። ግን ሌላው ደደብነት የኔን መልእክት ለኢትዮጵያ ህዝብ ማድረሳቹ ነው አልኩኝ። ቆርጠው ያስገቡት መልእክቴ ይህ ነበር… «እነሆ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት ድምጻችንን እናሰማለን አላሁ-አክበር» ስል አጠገቤ ያለው ወጣት በጁ የያዘውን ትልቅ መስቀል ከፍ አርጎ ያሳያል። ይህ የሙስሊሞችና የክርስቲያኖችን ህብረት ያሳያል።ድምጻችን ይሰማ የሚለውን ንቅናቄ የኢቶጵያ ህዝብ መፍራት እንደሌለበትም ያመላክታል። አሜሪካ ያሉት ኢትዮጵያዉን ሙስሊም፣ክርስቲያን ሳይባባሉ ባንድነት ተነስተዋል የሚል አንደምታን ያሳያል። ጅሎ ኢትቪ ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ አወጣና መልክቱን ዘረገፈው።
ፊልሙ ቀጠለ። «ድምጻችን ይሰማ የሚሉት ለመሆኑ የትኛው ድምጽ ነው?» ሲል ናሬተሩ (አንባቢው) ይጠይቃል። የኔ ንግግር ደግሞ «ነጻ የፖለቲካ እስረኞች እንላለን አላሁ-አክበር፤ ከፍ ባለ ድምጽ ኢማም እንጂ ካድሬ አንፈልግም፣ ቄስ ፓስተር እንጂ ካድሬ አንፈልግም በማለት እነሆ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት ድምጻችንን አናሰማለን አላሁ አክበር» በማለት እጆቼን ወደላይ አነሳለሁ።አንገቴ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ለብሻለሁ። መስቀል የያዘው ክርስቲያን ወንድም መስቀሉን ወደ ላይ አርጎ ያሳያል። ጎበበዝ የፊል ጸሃፊ፣ ፕሮፓጋንዳን እንኳን ቢፈበርክ ይህንን መልእክት ለኢትዮጵያ ህዝብ አውጥቶ አይዘረግፈውም ነበር። እናም ኢቲቪን በጣም አመስግኜዋለሁ።
እኔን ካላሳዩ ደደቦች ናቸው ያልኩበት ምክንያት ምንድን ነው?
ህወሃት የሚባለው ቡድን በኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የምነት ተቋም ዉስጥ ጣልቃ ገብቶ አህባሽ የሚባል ጸጉረ-ልዉጥ አንጃ ከሊባኖስ ሲያመጣ ያገርን ሉዓላዊነት እንደደፈረ አደርጌ ነው የቆጠርኩት።ያገር ፍቅር ስሜቴን ለመግለጽ በሰላማዊ የትግል ጎዳና ላይ ተሰማራሁ። ይህንን የህወሃት ጥላቻ በፍቅር ማሸነፍ እንደሚቻል እምነት አደረብኝ። ህወሃት «አክራሪ፣አሸባሪ፣ጽነፈኛ» መጣ በማለት ኢትዮጵያዉያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞችን በማናቆር ለአለም የጸረ-ሽብር ዘመቻ (war on terrorism) ሽያጭ አቅርቦ የዉጭ ምንዛሪ ሊመነትፍበትና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ማሰቡ ግልጽ ነበር። ይህንን መርዛማ እሳቤ ማክሸፈ የሚቻለው በፍቅር መሆኑን ተረዳሁና አቅሜ በቻለው መጠን መስራቴን ቀጠልኩ።
ለምሳሌ፦ አላሁ አክበር የሚለው ቃል የጥፋት መነሻ ተደርጎ በተሳሳተ መልኩ ይጠቀስ ነበር።በየመድረኮቹ ላይ «ለዋልድባ ገዳም አላሁ አክበር» ማለትን ጀመርኩ።ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች «አላሁ አክበር፣ፈጣሪ ታላቅ ነው»በማለት ጥምረትን አሳዩ።
****
ሙስሊምና ክርስቲያን አክቲቪስቶች ባንድ ላይ
ቀሳውስትና ሼሆችን ባንድ ላይ እጅ ለጅ ተያይዘው ፎቶግራፍ እንዲነሱ አድርገን ተምሳሊታዊ የሆነ የፍቅር መልእክት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ አድርገናል። በሚዲያ፣በሶሻል ሚዲያ፣በፓልቶክና በየስብሰባው መድረክ ላይ በመገኘት ህወሃት ይዞት የመጣውን መርዛማ አላማ ለማርከስ የተቻለንን ሁሉ አድርገናል። በአሜሪካ ዉስጥ ያሉ መንግስታዊ ተቋማት ዘንድ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በጋራ በመሔድ የህወሃት መንግስት አሸባሪነትን እየፈበረከ ቀጣናዉን ለማናጋት እየሰራ መሆኑን አሳውቀናል።
አቡነ ፊሊጶስ መስቀላቸውን በጃቸው ይዘው ስለ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ለአሜሪካ መንግስት የሐይማኖት ጉዳዮች ተወካዮች ሲመሰክሩ «በኛ ሐይማኖት መንግስት ጣልቃ እንደገባው ሁሉ በነርሱም ገብቶ ነው የረበሻቸው» ሲሉ በምስክርነት ተመልክተናል።አቡነ መልከጸዲቅ ባህር ማዶ ያለችውን ቤተ-ክህነት በመወከል «የሙስሊሞች መብት መከበር አለበት፣በሙስሊማኑም ጉዳይ ቤተ-ክህነት ታስባለች» ማለታቸውን ያስተዋልን እድለኛ ትዉልዶች ነን። ፓስተር ዳንኤል መንግስት የጀመረው አካሔድ አስጊ ነው በማለት ከሼህ ኻሊድና ከቀሲስ አስተራዬ ጋር ሲመክሩ ተሳትፈናል።
በአምባገነናዊው ስርዓት ዉስጥ ሽንቁር በመፈጥር የመረጃ የመረጃ ፍሰትን ፈጥረናል።ህወሃት የሚቆጣጠራቸው መስሪያ ቤቶች ስልኮች፣ኮምፒዉተሮች፣የኢንተርኔት ስርጭት፣ዋይፋይ የለውጥ ትግልን እንዲያግዙ ባጋራ ተሰርቷል።ፖሊሶች፣የመንግስት ሰራተኞች፣ደህንንነቶችና ቅን ባለስልጣናት መረጃን በማቀበል በህወሃት ላይ አምጸዋል።ሌላዉ ቀርቶ ህወሃት ስማቸውንና ማንነታቸውን መግለጽ የማልፈልገው የህወሃት አገልጋይና ትልቅ ባለስልጣን ኢትዮጵያ ላሉ ጸሃፍት የሚደርስ ኮፒዉተር፣ለአክቲቪስቶችና ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚዉል ገንዘብ ይዘው እንዲገቡ ሳያውቁት ተመልምለው ግልጋሎት ሰጥተዋል።
ስለዚህ ይህንን ሽንቁር ለመድፈን ህወሃት እኔን የመሰሉትን ፊት ለፊት የሚታዩትን ሰዎች ለማስፈራራትና ለማሸማቀቅ በጂሃዳዊ ሐረካት ላይ ባያካትት ነበር የሚገርመው።
***
የኒዮርኩ ጉዞ
የአራት ሰዓትን የአዉቶብስ ጉዞ ጨርሼ ኒዮርክ ከተማ ደረስኩ።በባቡር ተጉዤ የምፈልገው ቦታ ደረስኩ።ጉዳይ ለመፈጸም የምሄድበት መስሪያ ቤት ስላልተከፈተ Dunkin’ Donuts ገባሁና ቡና በወተትና ሁለት french cruller ዶናት አዘዝኩ። ከደረት ኪሴ ላይ ብእሬን መዘዝኩ፣ ኪሴ ዉስጥ አጣጥፌ የያዝኩትን ወረቀት አወጣሁና መጻፌን ቀጠልኩ።ዶናት ቤቱ የባቡር ጣቢያ፣የአዉቶብስ መናኸሪያ አብረው ያሉበት ቦታ በመሆኑ ብዙ የሚረብሽ ድምጽ ነበር። መጻፌን ቀጠልኩ። ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ያኔ በህይወት ነበሩ «በሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴና በአይን ቀልድ እንደሌለ ልንነግሮት እንሻለን» አልኹኝና ወረቀቱ ላይ አሰፈርኩ። በማግስቱ ዲሲ ስመለስ ያንኑ ጽሁፍ አውጥቼ ሰልፍ ላይ አነበብኩ።በወቅቱ የሚያስቆጣ ገጠመኝ ስለገጠመኝ ንግግሬን በሐይልና በቁጣ ነው ያነበብኩት። ያ ንግግር ጀሓዳዊ ሐረካት ቀጣፊ ፊልም ላይ ገባ። ዛሬ ጀሃዳዊ ሐረካት «አፈር-ድሜ» በላና እስረኖች ተለቀቁ።
ከጀሃዳዊ ሐረካት ፊልም በሗላ
ጀሃዳዊ ሐረካትን ፊልም ካየሁ በሗላ በድንገት በእስክሪኑ ላይ ሌላ ምስል ብቅ አለ። ኡስታዝ አህመድ ሁለት እጆቹ ታስረው መርማሪው ይሳለቅበታል። መርማሪው ከህወሃት ወንጀለኞች አንዱ ለመሆኑ ካነጋገር ዘይቤው ያስታውቃል።ዉስጤ ተረበሸ።ታቃጠልኩ በተለይ የመርማሪው ስላቅ አንገበገበኝ። ኑረዲን የሚባል ወዳጅ ጋር ደወልኩና «የሆነ ቪዲዮ ከጀሃዳዊ ሐረካት በኋላ ኢቲቪ መስኮት ላይ ብቅ ብሎ ነበር አይተኸዋል? አልኩት… «ኢትዮ ቱዩብ ቀድቶታል» ሲል መለሰልኝ። ይህንን አሳፋሪና አስደንጋጭ መረጃ አርካይቭ ላይ አያስቀምጡትም የሚል ስጋት ነበረኝና መረጃዉ በመያዙ ህወሃት የሚደርስበትን ፖለቲካዊ ኪሳራ ገመትኩኝ። ያ የኡስታዝ አቡበክር ምስል ህወሃትን በማንኛውም መልኩ እንድታገለው ለራሴ ቃል እንድገባ አደረገኝ።(ይህንን ለወደፊቱ በሰፊው አብራራዋለሁ ኢንሻ-አላህ)
አሸባሪው ህወሃት
ከ40 አመታት በፊት በአማራ ጥላቻና በመገንጠል እሳቤ ደደቢት ጫካ ዉስጥ የተመሰረተው ህወሃት የቀጣናው ጠንቅ ሆኖ ቆይይቷል።በማርኪሲዝም ሌኒኒዝም እሳቤ የትግል «ሀሁ» የጀመረው ህወሃት የአቋም አኮሮባት እየሰራ እስከዛሬ ደርሷል።ህወሃት በተለያዩ የጥናትና የጸረ-ሽበር ተቋማት አሸባሪ ብሄርተኛ በሚል መጠሪያ ሰፍሯል(https://www.trackingterro rism.org/group/tigray-peoples- liberation-front-tplf)።ሌላው ቀርቶ የህወሃት ቁንጮ የነበሩት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ሰብብ የሆኑትን የሶቭየት ህብረቱን ጆሴፍ እስታሊን እንደ አርዓያ የሚከተሉ በመሆናቸው «ምእራቡ አለም ለምን ይረዳቸዋል»ሲል ቢቢሲ ሞግቷል https://www.bbc.com/news/ world-africa-19332646ህወሃት ማለት በአለማችን ላይ የከሸፉ ርዮተ-አለማት ጭነት የተራገፈበት የሽብር ቡድን ነው።
ባንዳንድ መድረኮችና ጽሁፎች ላይ ህወሃትን በጀርመኑ ናዚ መስያለሁ።ናዚዎች በአይሁዳና በሌሎች አናሳ ቁጥር ባላቸውያገሪቱ ሰዎች ጥላቻ ነበር የተመሰረቱት። ህወሃትም «አማራ ህብረተሰባዊ ሰላምን አታገኝም» ብሎ በአማራ ጥላቻ ትግልን ጀምሯል የሚለው የአቶ ገ/መድህን አራያ ጽሁፍ ህሊናዬ ዉስጥ ተቀርጿል።ናዚዎች Auschwitz የመሳሰሉ ሰውን ማስወገጃ ካምፕን ገንብተዋል። ህወሃትም «ባዶ ሽድሽተ» የመሰሉ ሰውን ማስወገጃ ዋሻዎችን መስርተዋል።ናዚዎች የመሬት ይዞታን ካጎራባች አገራት በመንጠቅ መስፋፋትን ያደርጉ ነበር።ህወሃት የአፋርንና የአማራን መሬት ሰርቀው «የኔ ነው» በሚሉት ድርቅና እየዳከሩ ቤን ሻንጉል ጉምዝን ይዘው ጋምቤላ ለመዝለቅ መቃዥታቸውን ልብ ይሏል።ግን ያ እርኩስ የናዚ እሳቤያቸው ዛሬ ከሽፏል።
ህወሃቶች ያገር ሐብትን፣የመከላከያ ሰራዊትን፣የደህንነት ተቋምን፣ሚዲያንንና ባጠቃላይ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ገፈው እነርሱ የባሪያ አሳዳሪ ኢትዮጵያዉያን ባሪያ ሆነው የሚኖርበት ዘመን አብቅቷል።‹ከወደቁ በሗላ መንፈራገጥ መላላጥ› እንደሚባለው እነዚህ ወንጀለኞች ሲንፈራገጡ በዘር፣በሐይማኖት፣በክልል፣በዞንና በወረዳ ችግሮች እንዳያጫርሱን ጥንቃቄ ያሻል።
በርግጥም ጂሃዳዊ ሐረካት ህወሃታዊ ሐረካት ነበር በማለት ዛሬ በልበ ሙሉነት መናገር ችላለሁ። ልክ በፊልሙ ላይ መልክቴን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዳስተላለፉልኝ ዛሬም«እነሆ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድነት ድምጻችንን እናሰማለን አላሁ አክበር!»ልባዊ ደስታ ይሰማኛል።ሳዲቅ አህመድ ነኝ።ልብ ያል ያለው ልብ ይበል።
