የኢትዮጵያውያን ተጋሩ የውይይት መድረክ

June 15, 2018

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ክብር አሳልፎ የሰጠውን የአልጀርስ ስምምነትና የድምበር ኮሚሽኑን ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ እንደሚተገብረው አሳውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ከድል መንጋጋ ሽንፈትን መንጭቃ አወጣች እንደተባለው ከበርካታ መስዋዕትነት በኋላ ለምን ወደ ድርድር ተሂዶ መራራ ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት ማምጣት እንዳስፈለገ በውል ባይታወቅም፣ከዚያም በኋላ የአልጀርስ ስምምነት ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ፖለቲካዊ፣ታሪካዊና ህጋዊ ምክንያቶች እያሉ ለምን በአጣዳፊና ግብታዊ በሆነ መንገድ ውሳኔውን ተቀብለናል ማለት እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን ከጠርፍ እስከ ጠረፍ ወድ ሂወታቸውንና አካላቸውን ገብረው ያመጡትን ድል የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ግምት ውስጥ ባላስገባና እኔ አውቅልሀለሁ በሚል እብሪት የተወሰነውን ውሳኔ የአገራችንን ዘላቂ ሰላምና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ስለሆነ በጽኑ እንቃወማለን፡፡

ህወሀት ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን የኢሮብ በሔረሰብ ለማጥፋት በርካታ ሴራዎችን ሲሸርብና ሲተገብር መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡የኢሮብ ህዝብ ያንን ተቋቁሞ መዝለቅ ቢችልም ዛሬ ግን የድምበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ማለት በጭቆና ስር ያለውን ህዝብ ለሁለት በመክፈል ህልውናቸው እንዲዳከም ብሎም ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ የሚያድርግ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ስለሆነ ውሳኔውን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡

በስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ በቀጥታና በከፋ ሁኔታ ተጠቂ የሆነው በድምበር አካባቢ ያለው ህዝብ ማለትም የኢሮብን ጨምሮ የባድመ፣የግሎመከዳ (ዛላንበሳን አካባቢው) እና የዓፋር ህዝብ ድምጻችን ይሰማ እያለ ባለበት ሁኔታ ድምጹ ሳይሰማና እሱን ችላ ብሎ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ ሰላም ሳይሆን መቃቃርና ግጭት እንደሚያሰከትል መታወቅ አለበት፡፡በኢትጵያም በኤርትራም በኩል ያሉ የደምበር አካባቢ ህዝቦች አሁንም ዕድል ስጡንና ተወያይተን እንፍታው በሚሉበት ሰዓት ለህዝቦች ተገቢውን ዕድል ሳይሰጥ የሚደረግ የፖለቲከኞች ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

በአጠቃላይ የአልጀርስ ስምምነትና የደምበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንዳለ መቀበልና መተግበር ፍትሕን የማያመጣ፣ርትዕን ያለገናዘበ የህዝብና የሀገር ጥቅም የማያሰጠበቅ ብሎም ለሰላም ፋይዳ የሌለው ነው: ስለሆነም፤

ለኢትዮጵያ ህዝብ

በልጆችህ መስዋዐትነት የተገኘው ድል አሳልፎ የሚሰጥና ሉዓላዊነትህን የሚዳፈር ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት እየተሰናዳ ስለሆነ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ እንድትቃወመው ጥሪ እናደርጋለን፡፡አባቶቻችን ባደረጉት ታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት ታፍራና ተከበራ የቆየችን ሀገር በክህደትና በሸፍጥ በተመሰርተ የአልጀርስ ስምምነት ስትቆራረስ ማየት በታሪክም ተወቃሸ የሚያደርግ ስለሆነ በጽናት እንድተቃወመው ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ለትግራይ ህዝብ

የኢትየጵያ ሉአላዊ ግዛቶች ለኤርትራ አሳለፎ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ሰላማዊ ሰልፍና የተቃውሞ ድምጽ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው፡፡ ህወሀት በመለስ ዜናዊ መሪነት በክህደት የፈረሙትን

ስምምነትና የተቀበሉትን ውሳኔ መተግበር ማለት ለትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ያጠላ አደገኛ ጥላና ለቀጣይ የሀወሀት ጭቆናና ዐፈና አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ስለዚህ ጸረ-ህወሀት ተቃወሞው በድምበር ኮሚሸኑ ውሳኔ ላይ ብቻ ሳይገደብ በአጠቃላይ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ወደ ሚደረገው ትግል በማሰፋፋት ጫንቃህ ላይ እንደ መዠገር የተጣበቁትን የመለሰ ተከታዮችን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንድታስወግድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ለዶ/ር ዓብይ አህመድ

በእሰካሁኑ ሂደት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብር እየሰሩ ያሉትን ትልቅ ስራ በአክብሮት የምናየው ነው፡፡የአልጀርስ ስምምነትና የድምበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በተመለከተ ግን እርሶ የሚመሩት ፓርቲ ኢህአዴግ እንዳለ ለመተግበር የወሰነው ውሳኔ የኢትዮጵያን ክብርና የግዛት ሉዓላዊነት የማያስጠብቅ እንዲሁም የተመኙትን ሰላም የማያመጣ ነው፡፡ስለዚህ እርሶ የሚመሩት ድርጅት ውሳኔውን እንዲቀይር የተቻለዎትን በማደረግ ከታሪካዊ ስህተት እንዲድኑ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያ በልጆችዋ አንድነት ጸንታ ለዘላልም ትኑር !

15 June 2018