አበው  በፍቅር ሲሉት ጠብ የሚሻ፣ሊያቅፉት ሲሉ የሚገፈትር፣ ሊስሙት ሲቀርቡት ፊት የሚያዞር ወዘተ ሲያግጥማቸው ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት ይላሉ፡፡ፍቅር ያልገዛውን ኃይል ይገዛዋል እንደ ማለት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን የመጡት የሚያዩትን የማያምኑ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት በህውኃት ታዝለው፣ በደህንነቱ ክፍል ለትኩሳት ማብረጃ ተዘጋጅተው ወዘተ ሳይሆን አንድም የለማ ቡድን መሬት ላይ የሰራው ድርጅታዊ ሥራ ሁለትም ህዝባዊው ማዕበል ለደደቢቶች የሚቋቋሙት ስላልሆነ ወደው ሳይሆን ተገደው አምነው ሳይሆን እጃቸውን ተጠምዝዘው ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ ሌላ ተጨማሪ መረጃና ማብራረያ ሳያስፈለግ ከዋዜማው እስከ ዛሬ በወያኔ  ሰፈር የሚደረገውን፣ የሚነገረውንና በየሰዎቹ ፊት ላይ የሚነበበውን ብቻ ማጤን በቂ ነው፡፡

እነኝህ ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መስራትም እንችላለን እያሉ ሲፎክሩና ሲያስፈራሩ የኖሩ፣ሀያ ሰባት አመት ቤተ መንግሥት ያቆያቸው ጠብ መንጃቸው አንደሆነ የሚያምኑና እነርሱ ከሚሉት ውጪ ሌላው የሚያስበውና የሚመኘው እውን ሊሆን ከቻለ በመቃብራቸው ላይ ብቻ እንደሆነ ሲነግሩን የባጁት ደደቢቶች ፉከራቸው ከሽፎ፣ ማስፈራሪያቸው ፈሪ አጥቶ ጠመንጃቸው አቅም አንሶት በእኛ ላይ አትጥልቅም ያሉዋት ጀንበር ማዘቅዘቅ ስትጀምር ምን እየሆኑ እንዳለ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡

ሌላውን በዜሮ ድምር ፖለቲካ የሚከሰው በሴራ ኮትኩቶ የተንኮል ውኃ እያጠጣ ያሳደጋቸውና በስራው በአጭር የተቀጨው መለስ እራሱ የዜሮ ድምር  ፖለቲካ አራማጅ ሆኖ ወይ ጠቅሎ መግዛት ካልሆነም ኢትዮጵያን ማጥፋት ብሎ ለዚሁ የቀመመውን መርዝ የሌጋሲው አራማጆች እየረጩ እዛና እዚህ የቀበረውን ፈንጅ እያፈነዱ እኛ ከሌለን እናንተ አትኖሩም ህልማቸውን እውን ለማድረግ መንደፋደፍ ጀምረዋል፡፡

እዚህ ላይ ከሁለት አቅጣጫ ሁለት ነገሮች በእጅጉ ያሳዝናሉ፡፡ የመጀመሪያው እነዚህ ደደቢቶች የሚፈጽሙት ነው፡፡ በሀገራችን ታሪክ ከሥልጣን ወርዶ በሀገር መኖር አልታየም አልተሰማም፡፡ የሚታወቀው ባህላችን አሸናፊው ወደ ቤተ መንግሥት ተሸናፊው ለሞት ፣ለእስራት፣ ለስደት፣ የሚዳረግበት ነው፡፡ደደቢቶች በአስራ ሰባት አመት የጫካ ኑሮአቸውም ሆነ በሀያ ሰባት አመት የምንይልክ ቤተ መንግሥት ቆይታቸው እኛ ከምናውቀው በላይ የሰፋና የከፋ ወንጀል መፈጸማቸውን ስለሚያውቁ ነው ይህን ባህል ታሪክ አድርገን ምንም ይሁን ምን በኃላፊነት ላይ የቆዩ ሰዎችን በክብር የመሸኘት አዲስ ባህል እንጀምር በሚል  የተዘረጋላቸውን የሰላም፣ የፍቅር የይቅርታ እጅ የሚያስነክሳቸው፡፡

የአብይ ለማ ቡድን በድርጅታዊ ሥራ በልጦ፣ በፖለቲካዊ ሀይል አንበርክኮ አይነኬ ያሉትን ሥልጣን ሲረከባቸው የትናንት ጥፋታቸውን ብቻ ሳይሆን የዛሬ እንቅፋት ፈጣሪነታቸውን እያወቀ ማሸነፍ በፍቅርና በይቅርታ ነው ብሎ ሞት ቢቀርላቸው መኖሪያቸው ቃሊቲ መሆን ይገባ የነበረ ሰዎችን ጭራሽ በክብርና በሞገስ ሲያሳርፋቸው ይህን የማይገባቸውን ነገር ግን እንደ እነርሱ ክፋትና ጥፋት ሳይሆን እንደ አብይ ለማ የፍቅር ሰውነትና እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽነት ያገኙትን እድል መጠቀም አለመቻላቸው ሰዎቹ የሚያስቡት ፈጣሪ በሰጣቸው ህሊና መሆኑን እስከመጠራጠር ያደርሳል፡፡

በሀያ ሰባት አመት ራሳቸውን በትትክክል ማወቅ አለመቻላቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብንም በመጠኑ እንኳን ቢሆን አለመረዳታቸው አስተሳሰባቸው ምን ያህል የተቀነበበ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ቀማሪና ቆማሪ የነበረው ክፉ ሰው ፈጣሪ በሥራው ተጠይፎት ከዚህ በላይ በህዝቤ ላይ ትቀልድ ዘንድ አልፈቅድልህም ብሎ እኛንም እሱንም በግዜ ገላግሎናል፡፡ የአሟሟቱን እንዴትነት ሆነ የሞተበትን ምክንያት በውል ባናውቅም፣ የተቀበረበት ሳጥን ተከፍቶ አይተነው ባንሰናበተውም፣ አስክሬኑ ከውስጥ መኖር አለመኖሩን ባናውቅም ሳጥኑን በማይገባው ቦታ ሥላሴ አሳርፈን በቀበሌና በየመስሪያ ቤታችን ተገደን ቤተ መንግሥት ተገኝተን አልቅሰንም ስቀንም ሸኝተነዋል፡፤

ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ የምናሸጋግራት እናንተ እንደምትፎክሩት እንደምትመኙት በመቃብራችሁ ላይ ሳይሆን በክብር አስቀምጠን እያሳየናችሁ ነው ተብለው የማይገባቸው ክብር የተሰጣቸው ደደቢቶች ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸው ንቀት በዚህ ሰአት እንኳን አልበርድ ብሎ የሚያሳዩት መንፈራገጥና የሚያሰሙት እሪታ እያንዳንዳቸው የመለስን እድል እንኳን እንዳያገኙ የሚያደርጋቸው ነው፡፡

ሁሉም ነገር ልክና ገደብ አለው፤ የለማ አብይ የለውጥ ሀይልም ትእግስቱ ሊያልቅ ይችላል፡፡በፍቅር የዘረጋው እጅ በጥላቻ ሲነከስ ወደ ቡጢ ሊዞር ይችላል፡፡በፍቅርና በይቅርታ ማሸነፍ የሚለው ቅዱስ መርህ አጥፊዎችን ለጥፋት የሚያበረታታ ሆኖ ከተገኘ ፍቅር ያልገዛውን ሀይል ይገዛዋል ወደሚል ሊቀየር የማይችልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ስለሆነም ደደቢቶች እንዲህ ካደደባቸው የደደቢት ልክፍታቸው በጾም በጸበልም ይሁን በዱአ አለያም እንደለመዱት ደቡብ አፍሪካም ሆነ ሩቅ ምስራቅ ሄደው ይፈወሱና በእነ አብይ ቸርነት የተሰጣቸውን የማይገባቸውን ገጸ በረከት  አርፈው በሰላም ሳያንኮሻኩሹ ቢጠቀሙበት፡ነው ለራሳቸውም ለልጆቻቸውም የሚበጀው፡፡

እነዚህ ደደቢቶች ከራሳቸው አልፎ የትግራይ ወንድም እህቶቻችንን ለዳግም ፈተና እየዳረጉዋቸው ነው፡፡ መግለጫቸው ዛሬም ህውኃት ማለት ትግሬ፣ ትግሬ ማለት ህውኃት በሚል ቅኝት የተጻፈና ተነስ ታጠቅ ተዘጋጅ የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡ የትግራይ ወገናችን ዛሬም እንደ ትናንቱ የደደቢቶች መነገጃ ለመሆን ወይንም ላለመሆን ውሳኔውን ማሳወቅ የሚኖርበት ይመስለኛል፡፡አዲስ አበባ ላይ አብረው የወሰኑትን መቀሌ ላይ ሄደው ማብጠልጠል ትግራይን በምሽግነት መጠቀም እንችላልን ብቻ ሳይሆን  ሀያ ሰባት አመት ምንይልክ ቤተ መንግሥት ተቀምጠው ዛሬም ከደደቢት አስተሳሰባቸው ስንዝር ያልተራመዱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡እናም  ወገኖቻችን እነርሱ እንደሚሉዋችሁ ወያኔ መሆናችሁን ወይንም እኛ ትግሬ ሁሉ ወያኔ አይደለም ስንለው የነበረውን ከሁለት አንዱን አረጋግጡልን፡፡ለደደቢቶች ጥፋት ወይንም ለተጀመረው ኢትዮጵያዊነት ሰልፋችሁ ከየት እንደሆነ በግልጽ ንገሩን፡፡

ሁለተኛው አሳዛኝም አሳፋሪም ነገር በኢትዮጵያ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን ነው የምንታገለው የሚሉ፣ ባይታገሉም የሚመኙ፣ እየተካሄደ ካለው የለውጥ ርምጃ አንጻር ሚዛን የማይደፋ አይደለም ውኃ የማይቋጥር ሰበብ እየደረደሩ፣ የለውጡን ባቡር ባያቆሙትም ፍጥነቱን ለመግታት፣ በተግባር ባይችሉም በፕሮፓጋንዳ የተሰለፉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት የተሰሩትና እየተሰሩ ያሉት የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋትና ወደ ዴሞክራሲ የሚያስኬደውን ጎዳና የመጥረግ ሥራዎች አያሳምኑኝም ቢባል እንኳን፣ እነዚህ ስራዎች የደደቢቶች የውስጥ እግር እሳት ሆነው ማየት ብቻ የለማ አብይን የለወጥ ርምጃ ለመደገፍ ከበቂ በላይ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻል በተለይም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እመኛለሁ ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡

እነርሱም እንደ ደደቢቶቹ እኛ የምንለው ካልሆነ፣ እኛ በመረጥነው መንገድ መጓዝ ካልተቻለ ሀገር ይታመስ ህዝብ ይተራመስ የሚል የዶሮዋ ብሂል እየተባለ የሚነገረውን ካልበላሁት ጭሬ ላፍሰው አቋም መከተል በእውነት ያስተዛዝብ ካልሆነ በቀር ይህ የለውጥ ጅማሮ የመጣው በፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ ሊያደናቅፉት አይቻላቸውም፡፡

ከእነዚህ በተለየ ሁኔታ የሚታዩት ደግሞ  በአንድ ጽሁፌ ዶ/ር አድማሱን ጠቅሼ ያነሳኋቸው ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩት ናቸው፡፡ እነዚህ ከተግባሩ የሌሉ ምላሳቸው ግን ጤፍ የሚቆላ ፣ ረጋ ብሎ የማያስተውለውን ጭልጥ አድርጎ ይዞ የመንጎድ አቅም ያላቸው ሲሆኑ ይሉኙታም ሀፍረትም የማያውቸው ናቸው፡፡ ስለሚያገኙት ጥቅም ሂሳብ እያሰሉ እንጂ ስለ ሀገርና ህዝብ እየተጨነቁ አይደለም የሚናገሩት፡፡ ይሉኝታ ቢሰነታቸው የትናንት ማንነታቸውን አያስታውሳቸውም፤ ሀፍረተ ቢሶች በመሆናቸው ደግሞ በማይታወቁበት ሀገር ብቻ ሳይሆን በምናውቃቸው ሰዎች መካከል ሆነው ቁርበት አንጥፉልኝ ይላሉ፡፡ በዙሪያቸው የተሰለፈውን ጀሌ ስድብና ዘለፋ በመፍራት የሌላው ዝም ማለት ደግሞ የልብ ልብ ሰጥቶቸዋል፡፡ ሳያውቃቸው የሚያጨብጭብላቸውና ነፋስ አይንካብን የሚላቸው መብዛቱ አጀግኖአቸው አበው ልቤ አደገና ያለ ቁመቴ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤቴ እንደሚሉት አድርጓቸዋል፡፡ እናም ጠዋት ማታ እየተነሱ ለውጡን ያብጠለጥላሉ የለውጡን መሪዎች ያጥላላሉ፡፡

ሰበባቸው ምንም ይሁን ምን የለውጥ ሂደቱን ባይደግፉ እንኳን ካልተገባ ውግዘትና አቃቂር ማውጣት ተቆጥበው ገንቢ ሂስ መካሪ አስተያየት ቢሰጡ ባልከፋ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉና ማንቋሸሽን ስራቸው ያደረጉ ወገኖች ለደደቢቶች ፍላጎት መሳካት እየሰሩ መሆኑን የሰሞኑን የወያኔ መግለጫ አንብበው መረዳትና ራሳቸውን ማስተካከል ካልቻሉ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳትበቃ ሆን ብለው የሚሰሩ ናቸው ለማት ያስደፍራል፡፡

ደደቢቶች የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት ከምድር ይሉት ሆነው ለተዘረጋላቸው የፍቅርና የይቅርታ እጅ ሰይፍ ሲስሉ፤ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው የምንታገለው የሚሉ ወገኖች  የለውጡን ባቡር ጉዙ ለመግታት ወደ ሀዲዱ የቃላት ናዳ ሲያወርዱ ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ተከፍሎበት የተገኘ የለውጥ ጅማሮ እንዳቀለበስ ከምንግዜውም በላይ ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

ሌባውን አጭበርባሪውን አደናቃፊውን አስመሳዩነን ወዘተ ሁሉንም በተግባራቸው መግለጽ ማጋለጥ አደጋ እንዳያደርሱ መጠበቅ እንጂ ጎመን በጤና እያሉ አለባብ በማረስ አረም ማፈስ መቆም አለበት፡፤ ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው በየእለቱ አዳዲስ ክንዋኔዎችን እያሳየ ልባችንን በተስፋ፣ ህሊናችንን በሀሴት እየሞላው ያለው የለውጥ ጅማሮ ለውጤት ሊበቃ የሚችለው፡፡

ከወያኔ በተቃራኒ ነን የሚሉ ግን በተግባር ከደደቢቶቹ ያልተናነሰ ጸረ ዴሞራሲ ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ወገኖችን በምክርም በጸሎትም እናግዛቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ከነገ ጸጸት ለማዳን፡፤