የ”መንግስት” ጦር ጭካኔ እና “ኦራል አራግፈው የመለሱት” አርበኞች
(ጌታቸው ሺፈራው)
ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖም አርማጭሆ ውስጥ ስለሚፈፀመም ጭካኔ ስታወራው የሚያምንህ የተወሰነ ነው። አንድም ጉዳዩን በቅርብ ርቀት የሚያውቅ ወይንም በተደጋጋሚ ጉዳዩን የሰማ ብቻ ሊሆን ይችላል። ከሚፈፀመው በደልና ጭካኔ አንፃር ቀሪው ላያምን ይችላል። ለምሳሌ የመንግስት ጦር የገደለውን አስከሬን 50 እና 60 ኪሎ ሜትር በመኪና መሬት ለመሬት ይጎትታል ቢባል ማን ያምናል? በጠጠር መንገድ ከ5 ሰዓት በላይ ጦርነት ገጥሞት የገደለውን ባላንጣ አስከሬን ይጎትታል ቢባል ምኑ ይታመናል? ከሚያውቀውና በተደጋጋሚ መረጃውን ከሰማው ውጭ!
ጦርነት ገጥሞ የተገደለንና ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ መኪና ላይ የተጠለፈ ገመድ አስሮ መሬት ለመሬት ላይ የተጎተተን ሰው አስከሬን ቤተሰብ ፊት አስቀምጦ “ትልና አሞራ ይበላዋል እንጅ አይቀበርም!” የሚል ጭካኔ ይፈፅማል ብሎ ማን ይገምታል?
አርማጭሆ ላይ ግን ባለፉት 27 አመታት ይህ ጭካኔ ተፈፅሟል። እየተፈፀመ ነው። ሽንኩ ከፌ እና ዳኛቸው በላይ መንግስት ነኝ የሚለው ጦርና ካድሬ በህዝብ ላይ የሚፈፀመውን በደል አይተው ውሏቸውን ዱር አደረጉ። ትህነግ/ህወሓት ወልቃይትና አርማጭሆ ላይ የሚፈፅመውን በደል አይተው የወጡት እነ ሽንኩ በተደጋጋሚ የመንግሰት ጦርና ካድሬዎች ላይ እርምጃ ወስደዋል። በመንግስት ጦር የተፈሩ፣ በሕዝብ ደግሞ የተከበሩ አርበኞች ነበሩ። አሁንም እረኛውም አርበኛውም የእነሱን ስም ያነሳል! በዘፈን፣ እንጉርጉሮና ለቅሶው!
ግንቦት 19/2004 ዓም ፉጭና የሚባል ቦታ ላይ ከልዩ ሀይል፣ መከላከያና ፀረ ሽምቅ ጋር በተደረገ ጦርነት አርበኞቹ አልቀናቸውም። ከባድ መሳርያ ታጥቆ በመጣው ጦር ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሱት አርበኞች ይገደላሉ። የገደላቸው የመንግስት ጦር ግን ሁለቱን በመግደል ብቻ አልረካም።
በህይወት እያሉ የሚያርዱትን፣ እንደ አካባቢው አጠራር “ኦራል አራግፈው የሚመልሱትን” አርበኞች አስከሬን ላይ ከወታደር የማይጠበቅ አስነዋሪና ዘግናኝ ድርጊት ፈፅመው አርበኞቹ በሕይወት እያሉ የፈፀሙባቸውን ለመበቀል ጥረዋል። ሹርባቸውን ከግንድ ጋር በማሰር በመኪና እየጎተተ ከፉጭና እስከ ሳንጃ መሬት ላይ ጎትተዋቸዋል። መንገዱ ወጣ ገባ ነው። በመኪና ከ5 ሰዓት በላይ ያስኬዳል። ይህ የመንግስት ጦር ሁለቱን አርበኞች ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ወደ ሳንጃ ከተማ ከወሰዱ በኋላ ቤተሰብ እንዳይቀብራቸው ከለከሉ። የሚያለቅሱትን እናቶችና ህፃናት ሳይቀር ደበደቡ። “ትልና አሞራ ይበላቸዋል እንጅ አይቀበሩም” ብለው አዋጁ። ደግነቱ እነ ጎቤ መልኬ ነበሩ። አስከሬናቸው አንድ ቀን ፀሀይ ላይ እንደተሰጣ አርበኛ ጎቤ መልኬ ከመንግስት ጦር ጋር ተጋፍጦ አስቀብሯቸዋል።
የሽንኩ ወንድም ማሩ ከፌ እንዲሁም የዳኛቸው በላይ ወንድም ለውጤ በላይ በወንድሞቻቸው ላይ የተፈፀመውን አይተዋልና እነሱም መሳርያ ወልውለው ውሏቸውን ዱር አደረጉ። ከ2000 ዓም ጀምሮ በአርበኝነት ከነበሩት ጋር አብረው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሀገር ውስጥ በ”መንግስት” ጦር ጋር ትልቅ ጉዳት እንደሚያደርሱ ያወቀው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ወደ ኤርትራ እንዲሻገሩ ጠየቃቸው። ከ20 በላይ ምልምል 9 ታጣቂ ሆነው ጥር 2005 ዓም ወደ ኤርትራ ሲሻገሩ የመንግስት ጦር ተከዜ ላይ ገጠማቸው። 4 ክላሽ፣ አንድ ስናይፐር ማርከው ወደ ኤርትራ ሲሻገሩ አንድ ሰው ብቻ ቁስል ሆነባቸው።
አርበኞች ግንባር ለተወሰኑ ወራት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጣና ከሰጣቸው በኋላ ግንቦት 2005 ዓም 9ኙ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ግንቦት 24 እና 25 ከመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይልና የአካባቢው ሚሊሻ ጋር በተደረገ ጦርነት 14 መከላከያ ገድለዋል፣ 10 መከላኩ አቁድለዋል፣ 4ሚሊሻ ገድለወሰል፣ 3 አካል አጉድዋል ብሎ መንግስት ክስ አቅርቦባቸዋል። በእውነታው ግን “መንግስት” ጦር ላይ የደረሰው ጉዳት ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። በዚህ ጦርነት መሬት ለመሬት የተጎተቱት ሽንኩ እና ዳኛቸው ወንድሞችም ተሳትፋዋል።
ከአርበኞቹ ወገን ገብረማርያም ገ/ስላሴ (ትውልዱ ወልቃይት)፣ አሸናፊ ጥግነህ ( አርማጭሆ)፣ ማሩ ከፌ ( የሽንኩ ወንድም ከአርማጭሆ)፣ ቸርነት ሙላው (ከአርማጭሆ)፣ ተገን ግደይ ፣(ከአርማጭሆ) ከባድ መሳርያ በታጠቀው የመንግስት ጦር ተገደሉ። ይህ አረመኔነትን መገለጫው ያደረገው የ”መንግስት” ጦር አስከሬናቸውን ሁመራ ከተማ ላይ ወስዶ አሰጣው። አርበኞቹ የወልቃይትን ጥያቄም ጭምር ይዘው የተነሱ እንደመሆናቸው የሁመራን ሕዝብ ለማስፈራራት ነው። ሆኖም ሕዝቡ በ”መንግስት” ጦር ላይ ጩኸት አሰማ። ሕዝብ “ከእናንተ የተሻሉ መሆናቸውን አሳይተዋል። ስንትና ስንት ጨርሰውባችኋል። ታውቋቸዋላችሁ። አሁን አስከሬናቸውን ፀሀይ ላይ የምታሰጡትም ለዛ ነው። ከእነ ነፍሳቸውማ ምን እንደሚያደርጓችሁ ታውቋቸዋላችሁ” ያለው አረመኔው ጦር አስከሬናቸውን በመኪና ጭኖ ወዳልታወቀ ቦታ ወሰደ። ከወር በኋላ አስከሬናቸው በርሃ ላይ ተገኘ። ለወር ያህል ሜዳ ላይ ተጥሎ ነበር። የሕዝብ መነጋገሪያ ሲሆን አረመኔው ጦር በመኪና አፈር ጭኖ በመውሰድ አስከሬኖቹ ላይ አፈር ቆልሎ ተመለሰ።
በሌላ በኩል ሶስቱ ማለትም ያዘዘው አለሙ (ደረቱ ላይ)፣ ባበይ ማሞ (ታፋውን) እንዲሁም ዳኛቸው በላይነህ እጁ ላይ ቆስለው ሲያዙ፣ ለውጤ በላይ (የዳኛቸው በላይ ወንድም) ሳይቆስል ተማረከ።
የተማረኩት በሀከር የሚባል ቦታ መከላከያ ካምፕ ለ6 ቀን እንዲሁም መቀሌ 12 ቀን እየተደበደቡ ካቆዩዋቸው በኋላ ወደ ማዕከላዊ አመጧቸው። ያዘዘው አለሙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሰኔ 2005 ዓም ከሌሎቹ ነጥለው ወሰዱት። ሶስቱን ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ ያዘዘው አለሙ ተነጥሎ ቀረ። በአሁኑ ወቅት መቀሌ እንዳለ ይወራል። ምን አልባትም የተለየ ጭካኔ ፈፀረመውነት ሕዝብ እንዳያይ ደብቀውት ይሆናል። በሕይወት ስለመኖሩም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ትግራይ ክልል ተወስደው በማንነታች በርካታ ግፍ እንደተፈፀመባቸው የሚገልፁት ባበይ ማሞ፣ ዳኛቸው በላይነህ እና ለውጤ በላይ ማዕከላዊ 2 ወር ተሰቃይተዋል። መንግስት ካመነው በላይ ቁጥር ጠርተው “ተዋግተናል፣ ገድለናል፣ አቁስለናል” ብለው ቢያምኑም ድብደባው አልቀረላቸውም።
ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ከተቀየሩ በኋላም ለውጤ በላይ 20 አመት፣ ባበይ ማሞ እና ዳኛቸው በላይነህ 19 አመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ቆይተዋል። ባባይ ማሞ ቁስሉ ከአመት በላይ እየደማ ምንም አይነት ህክምና አልተደረገለትም። “ከአንድ አመት በላይ ቁስሉን በሶፍት ስጠርግለት ከመግሉ ጋር የተሰባበረ አጥንት ይወጣ ነበር። በዚህ ወቅት ግን ምንም አይነት ህክምና አልተደረገለትም። ሕክምና ስንጠይቅም የነበረው ስድብና ዘለፋ የከፋ ነበር” ሲል ጓደኛው አጫውቶኛል።
እነ ሽንኩ፣ እነ ማሩ እና ሌሎችም በአርማጭሆ ሕዝብ ዘንድ ይዘመርላቸዋል። አሁንም ድረስ አደብ ባልገዛው “መንግስት ነኝ” የሚል አካል የሚበደለው የአርማጭሆና የወልቃይት ገበሬ በደሉ ሲበዛበት ፈለጋቸውን ይዞ “ኧረ ጥራኝ ዱሩ” ብሎ የአርበኝነት ህይወቱን ይመራል። በሰርግ በለቅሶው ያስታውሳቸዋል። በእስር ቤት ወጣቶች የእነ ሽንኩን ብቻ ሳይሆን ከእነሱ በኋላ የታገሉትን የእነ ለውጤን ታሪክ አውርተው አይጠግቡም። “ኦራል አራግፈው ይመልሳሉ” ብለው ይደመሙባቸዋል።
ለውጤ በላይ፣ እነ ባበይ ማሞ እና ዳኛቸው በላይነህ ሰኔ 8/2010 ዓም ከቃሊቲ ተፈትተዋል። አሁንም ከወታደራዊ ካምፕ ነጥለው ስለወሰዱት የክፉ ቀን ጓደኛቸው ያዘዘው አለሙ ያስባሉ። በወሬ ብቻ መቀሌ አለ መባሉን ሰምተው በሕይወት ስለመኖሩ ተስፋ ያደርጋሉ። ከጎናቸው ስለወደቁት፣ ከዛ በፊትና በኋላም ተገድለው መሬት ለመሬት ስለሚጎተቱት የአርማጭሆና የወልቃይት ወጣቶች ሲያስቡ ይተክዛሉ።
የእነ ለውጤ ወንድሞች ገና 20 አመት ሳይሞላቸው ነው የህዝብን መበደል አይተው ጫካ የገቡት። እነ ለውጤ ጫካ የገቡት በ20ዎቹ አጋማሽ እድሜ ላይ ነው። ዳኛቸውን “ለምንድን ነው ወደአርበኝነት የገባችሁት?” ብየ ጠይቄው ነበር። መልሱ “እናቶቻችንና ሕፃናት ሳይቀሩ ሽፍታ አስጠግታችኋል እየተባሉ የሚደርስባቸው በደል የሚያስቀምጥ አልነበረም። ሕዝብ እየተሸማቀቀ ነው የሚኖረው። የወልቃይት ጉዳይ ያኔም ነበር። ሰው ገድለው በመኪና ሲጎትቱም ዝም ብዬ ማየት አልፈለኩም” የሚል ነበር! እነዚህ የሕዝብን ስቃይና ሰቆቃ ለመታደግ አርበኝነቱን የተቀላቀሉ ጀግኖች ላለፉት አምስት አመታት ከአርማጭሆ እረኞች፣ አርበኞችና የስቃይ ሰለባ የሆነ ሕዝብ በእንጉርጉሮና በቀረርቶ ከሚያወድሳቸው ውጭ ያስያወሳቸው ሌላ አልነበረም። በተለይ ከታሰሩበት አላማ አንፃር ያገባኛል የሚል አካል ዞር ብሎ አያያቸውም። መቀሌ እንደታሰረ የሚነገርለትን ያዘዘው አለሙም እስካሁን ማንም በሕይወት መኖሩን አላረጋገጠም!
(ፎቶው ላይ በቅደም ተከተል ለውጤ በላይ፣ ዳኛቸው በላይነህ እና ባበይ ማሞ ናቸው።)

