ኢህአዴግ 100% የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ፓርላማ በአገሪቱ ወቅታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማብራሪያ መጥራቱ ተዘገበ::

ከአዲስ አበባ የመጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመጪው ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ተገኝተው ከሕዝብ ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ምክር ቤቱ ባደረገው ጥሪ መሰረት በነገው ዕለት ተገኝተው ገለጻ ያደርጋሉ::

ለመንግስት ቅርብ የሆኑ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የፓርላማ አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጧቸው የፈለጉበት ዋነኛ ጉዳይ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰብስቦ ባሳለፋቸው ሁለት መሠረታዊ ውሳኔዎች ላይ ነው::

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ መቀበሉና የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ አይዘነጋም ስል ሪፖርተር ዘግቧል::