*መሳጭ የሐዋሳ ትዝብት (በታሪኩ ወዳጆ)
፨ ናፍቄ ከምጎበኛት ሐዋሳ በምጥና በጭንቀት ወጣሁ፡፡
፨ ለሁለት ተከፍለው ድምጻቸወን ለዶ.ር. አብይና ለሽፈራው ሽጉጤ የሰጡ ኹለቱ ወገኖች ነገር
፨የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ፣ የለውጥ ኃይሉን የሚደግፉ ሆነው ሳለ ስለቀውሱ የሚሰጡት መግለጫ ግን የተቃራኒው ነወ፡፡
፨ፖሊሶች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ደርሰው እንኳን ችግሩን ተቆጣጥረው ማረጋጋት ሲጀምሩ ባስቸኳይ ውጡ የሚል መመሪያ እየደረሳቸው ሲበሳጩ አይቻለው፡፡
፨አብዛኛዎቹ አፈናቃዮችና ተፈናቃዮች በአንድ ቤተ እምነት አብረው የሚያመልኩ፣ጎን ለጎን ሆነውአብረው የዘመሩ ናቸወ፡
፨የሐሰት ወሬ ከሚነዙት መካከል የክልሉ ልዩ ኃይሎች ጭምር ይገኙበታል፡፡

የተፈጠረው ግርግር ቀለል ያለ ነው በሚል እምነት ረቡዕ ማታ (ሰኔ 6 ቀን 2010) ሐዋሳ ከተማ ለስራ ገባሁ፡፡ ስደርስ ከተማዋ ጭር ብላለች፡፡ እየገረመን ሻንጣችንን ሴንትራል ሆቴል አስቀምጠን እራት ፍለጋ ወጣን፡፡ ያ ሁሉ የሐዋሳ ምግብ ቤት ዝግ ነው፡፡ ከኛና ፓትሮል ከሚያደርጉ መኪኖች በቀር መንገድ ላይ ሌላ አይታይም፡፡ ወደ ሆቴላችን ተመልሰን እዚያው የተገኘውን ተቃምሰን አደርን፡፡ ሐዋሳ ሴንትራል ሆቴል አካባቢ በሐዋሳ ከተማ የተሰማሩ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የአጋዚ ወታደሮች፣ የተሰማሩበት ስፍራ ነው፡፡

ሐሙስ ጠዋት ቀጠሮ ወደያዝኩበት መስሪያ ቤት አምርቼ ሰርቼ፣ ምሳ ሰዓት ላይ አንዳንድ ግጭቶች ስለተስተዋሉ፣ ማየት የምፈልገውን ዶክመንት ይዤ ወደ ሆቴል አመራሁ፡፡ ስለራሴ ሆነ ስለከተማዋ ደህንነት መረጃ ለመቃረም እየሞከርኩ እኒህን ሁኔታዎች በአይኔ ተመለከትኩ፣ በጆሮዬም ሰማሁ፡፡

1. ደህዴን ተከፍሏል፡፡ የለውጥ ኃይሉን የሚደግፉና የሚቃወሙ የደህዴን አባላት በሁለት ጎራ ተከፍለው እየተፋለሙ ነው፡፡ ይህ ልዩነት ዶ.ር. አብይ ወደ ስልጣን ሊመጣ ሰሞን የጀመረ ለመሆኑ ማሳያው፣ በምርጫው ወቅት ለሁለት ተከፍለው ድምጻቸወን ለዶ.ር. አብይ የሰጡና ለሽፈራው ሽጉጤ ድምጽ የሰጡ ሁትለ ወንገ መሆናቸው ነው፡፡ አሁን በደቡብ ክልል የተፈጠረው የደህዴን ለሁለት መከፈል የፈጠረው ቀውስ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የቲም አብይን ለውጥ የማይፈልጉ ኃይሎች የተቀናበረ አርቴፍሻል ብጥብጥ ፈጠሩ፡፡ በሐገሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀው ቀውስ በዶ.ር. አብይ አህመድ አመራር መፍትሔ አንዳላመጣ በማሳየት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዳግም እንዲታወጅ በማድረግ በዶ.ር. አብይን መሳቂያ ለማድረግ በተሰማራ ኃይል የተቀናበረ ብጥብጥ ነው፡፡ በደህዴን አመራር ውስጥ የኃይል ሚዛኑ የለውጥ ደጋፊውና የዶ.ር. አብይ ደጋፊ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዶ.ር አብይ የትም አይደርስም፣ ለውጥም አያመጣም በሚል፣ ለውጡን ማስቆም የሚሹ፣ ቡድኖች ያጋለደ ነው። ለዚህም ማሳያው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ፣ የለውጥ ኃይሉን የሚደግፉ ሆነው ሳለ ስለቀውሱ የሚሰጡት መግለጫ ግን የተቃራኒውን ወገን ውሳኔ መልእክት የሚያስተላልፉ መሆኑ ነው፡፡ አቶ ደሴ ዳልኬ በባህርያቸው ትሁትና ነገርን ፊት ፊት ከመፋለም ይልቅ የሚሸሹ እንደሆኑ ተነገሮኛል፡፡ ስለሆነም ክልሉን እንደ ቲም ለማ ከለውጥ ኃይሉ ጋር መሳ ለመሳ ገጥሞ ከመምራት ይልቅ በተቃራኒው ጎራ የመጠምዘዝ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለለውጥ ሲሉ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ቢደነቅም፣ ከደህዴንም መውጣታቸው የለውጥ ፈላጊውን የደህዴን መዋቅር የኃይል ሚዛን አዛብቶታል፡፡ ባይለቁ ኖሮ በደቡብ የምናየው ቀውስ በርሳቸው ተጽዕኖ ምክንያት ላይፈጠር ይችል ነበር፤ ወይም ቀውሱ በዚህ መጠን አይሆንም ነበር፡፡

2. የጸጥታ ኃይሉ እንዲወዛገብና መከላከል ላይ እንዳያተኩር ተሰርቷል፡፡ በሐዋሳ 4 የተለያዩ አካላት የሚያዟቸው የጸጥታ ኃይሎች ተሰማርተዋል፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የከተማው ፖሊስ፣ የአጋዚ ወታደርና፣ ፌደራል ፖሊስ ናቸው፡፡ እኒህ አራቱ የጸጥታ አካላት በተለያየ መዋቅር የተለያየ መመሪያ የሚቀበሉ ናቸው፡፡ ለጊዜው የተቀናጀ አመራረ ለመስጠት የሚያስችል ጥረት ቢደረግም ውጤታማ አልነበረም፡፡ እስከዛሬ የፀጥታ አሰራር ባልተለመደ መልኩ፣ የከተማው ፖሊስ አልፎ አልፎ ከመታየታቸው እና በፒክ አፕ መኪና ከተማዋን ከሚቃኙ የጸጥታ አካላት በቀር፤ አብዛኛዎቹ የጸጥታ አካላት ሐዋሳ ሴንትራል ሆቴል አካባቢ ሰፍረው፣ ችግር ከተፈጠረ በኋላ፣ ችግር ወደተፈጠረበት ስፍራ እየሔዱ እየበተኑ ይመለሳሉ፡፡ በለተያዩ ፒክአፕ መኪኖች ከተማዋን ፓትሮል ያደርጋሉ እንጂ ከዚህ ቀደም በተለመደው የጸጥታ አጠባበቅ ዓይነት ሁለት ሁለት ሆነው በሁሉም የከተማዋ መንደሮች አልተሰማሩም፡፡ እንደዛ ተሰማርተው ቢሆን በየአካባቢያቸው በግሩፕ የተሰባሰቡትን ወጣቶችን በመበተን ሊፈጠር የሚችልን ስጋት በእንጭጩ ያስቆሙት ነበር፡፡ የተደረገው ግን ዘረፋ ከተካሄደ፣ ቤት ከተቃጠለ፣ ሰው ከተጉዳ በኋላ ደርሰው፣ አካባቢውን ቃኝተው፣ ለደቂቃዎች ወጣቶችን እንዲበተኑ አድርገው ወደ ቤዛቸው ይመለሳሉ፡፡ ይህ የጸጥታ ኃይሉ ስምሪት አደጋን ለመከላከል የሚያስችል መልኩ
እንዳይሰራ ቀድሞ የተቀናበረ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ዶ.ር. አብይ የጸጥታ ኃይሉ፣ ከልክ ያለፈ ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ እንዳይወስዱ ማዘዛቸው፣ በቀን ጅቦቹ ዘንድ ከዚህ ቀደም ያልተለመደ አመራር እየሰጡ የጸጥታ ኃይሉ እንዳይቀናጅና የተወዛገበ ስምሪት እንዲኖረው ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡

3. የሐሰት ወሬ የብጥብጡ ማስጀመሪያ ክብሪት ነበር፡፡ የብጥብጡ ጀማሪዎች ጥቂት ተልኮው የተሰጣቸው ግለሰቦች ለመሆናቸው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የቀን ጅቦቹ ህዝብ ከህዝ ጋር እንዴት እንደሚጋጭ የሚያውቁና በዚህ የተካኑ ስለሆኑ፣ ትልቁ የግርግር ማስነሻ መሳሪያቸው የሐሰት ወሬ ማስወራት ነበር፡፡ ሐሙስ ጠዋት፣ አንዲት የሲዳማ ሴት ወላይታዎች ጡትዋን ቆርጠው ገደሏት፣ አንድ የሲዳማ ወጣት በወላይታ ታረደ፣ አንዲት ወላይታ ሴት የሲዳማን ባህላዊ ልብስ አህያዋን አልብሳ ወጣች፣ ወዘተ… የሚል ወሬ ከእንቅልፉ ለሚነቃው ለሐዋሳ ሕዝብ አናፈሱ፡፡ በተመሳሳይ ወላይታዎችም ጋር የነርሱ ወገን ላይ በሲዳማዎች አሰቃቂ ግድያ እንደተፈጸመ ተደርጎ ወሬ እንዲናፈስ ተደረገ፡፡ በሁለቱም ወገን ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን በማቧደን መንገድ በመዝጋት በየሰፈራቸው የሚያልፈውን ሰው ብሔርህ ምንድነው በማለት፣ ማጥቃት ተጀመረ፡፡ ተልኮው የተሰጣቸው ጥቂት ግለሰቦች የዋሀኑንና ለብሔሩ ተቆርቋሪ የሆነን ወጣት በመሳሪያነት በመጠቀምና ብሔርተኞችን በማደራጀት፣ ብጥብጡ በተሳለጠ ሁኔታ እንዲቀጥል አደረጉ፡፡ ልብ በሉ፣ ይህ በቀን ጅቦቹ አማካኝነት ለሰፊው ግጭት ክብሪት እንደመለኮስ የተጠቀሙት ዘዴ ነው፡፡ ወዲያው ቀጣይ እርምጃቸው የተመረጡ ግለሰበቦች ቤት በብሔር ተለይቶ እንዲቃጠል ተደረገ፡፡ ቤት ማቃጠል የተጀመረው የታዋቂና በህብረተሰቡ በጣም የተከበሩና ግለሰቦችን ቤት ኢላማ በማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ አብዛኛወን ሰው ፈንቅሎ እንዲወጣና እርምጃ እንዲወስድ ይጠቅማቸዋልና ነው፡፡ ከዚያ በሔርን መሰረት አድርጎ ወርቅ ቤቶችና ሱቆች እየተለዩ ተዘረፉ፡፡ በነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የጸጥታ ኃይሎች ዝርፊያውና ጉዳቱ ከተፈጸመ በኋላ እየተደወለላቸው ቦታው ይደርሱ ነበር እንጂ፣ በጥቃቱ ስፍራ ቀድመው እንዲገኙ አልተደረገም፡፡ በእለቱ ወደ ከተማው ፖሊስ የሚያስኬደኝ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚያም የከተማው ፖሊሶች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ደርሰው እንኳን ችግሩን ተቆጣጥረው ማረጋጋት ሲጀምሩ ባስቸኳይ ውጡ የሚል መመሪያ እየደረሳቸው ሲበሳጩ አይቻለው፡፡ የሚገርመው የሐሰት ወሬ ከሚነዙት መካከል የክልሉ ልዩ ኃይሎች ጭምር ይገኙበታል፡፡ አንዱን ቀረብ ብለን ስናወራ በወላይታ ሶዶ ተመሳሳይ ብጥብጥ ተካሔዷል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ዘጠኝ የሲዳማ ልጆች ተገድለዋል አለን፡፡ ልዩ ኃይል ወታደር፡፡ ስልኬን አነሳውና በወላይታ ሶዶ የማውቀው ፖሊስ ጋር ደወልኩ፡፡ በርግጥ በወላይታ ሶዶ መጠነ ሰፊ ዝርፊያና በመንግስትም ሆነ በግለሰብ ንብረቶች ተቃጥለዋል፡፡ የሞት አደጋ ያጋጠማቸው አራት ሰዎች ናቸው፡፡ አራቱም ወላይታዎች ናቸው አለኝ፡፡ ታዲያ ለዚህ ሁሉ ቀውስ የሆነው ይህ የውሸት ዜና በማንና ለምን ተፈበረከ?

4. አፈናቃዮች፡- አርብ ከሰዓት በኋላ ሲዳማዎች ወደ ሚበዙበት ሰፈር ያሉ ወላይታዎች ቤት እየተቃጠለና፣ በር እየተንኳኳ፣ ባስቸኳይ ከሐገራችን ውጡ የሚል መመሪያ ለብዙ ምስኪን ወላይታዎች ተሰጣቸው፡፡ ወላይታዎችም በሚበዙባቸው ቦታዎችም እንዲሁ የተወሰኑ ሲዳማዎችን ሲዳማዎች እንዲወጡ ተደረገ፡፡ በክልሉ ልዩ ኃይል ታጅበው፣ በፌስታል ልብሳቸውን ይዘው፣ በጀርባቸው ልጆቻቸውን አዝለው፣ ከሚኖሩበት ከፍለ ከተማ ወደ ሐዋሳ መስቀል አደባባይ ከ5ሺ የሚበልጡ ወላይታዎች ተሰደዱ፡፡ ሲዳማዎች ደግሞ በክልሉ ባህል አዳራሽ እንዲጠለሉ ተደረገ፡፡ 90 ፐርሰንት የሚሆኑት ስደተኞች ወላይታዎች ናቸው፡፡ አኒህ ስደተኞች በተቀናበረ መልኩ ከየቤታቸው የሚያስወጡ እና እንደከብት አየነዱ አሸባሪን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ይመስል አጅበው ወደ ሐዋሳ መስቀል አደባበይ የወሰዷቸውና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸውን አይቻለው፡፡ ከክልሉ ልዩ ኃይል ያመለጡ ተፈናቃዮች ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተሸሸጉ፡፡ አንዳንዶች መሔጃ አጥተው፣ ህጻናትን ታቅፈው ጎዳና ላይ ግራ ተጋብተው የቆሙ እናቶችን ሴቶችን ታዝያለው፡፡ አርብ ማታ የዛው ከተማ ስደተኛ፣ እናቶችና ጡት የሚጠቡ ህጻናት ጨምሮ 5ሺ የሚያህሉ ወላይታዎች በብርድና በዝናብ ሐዋሳ አደባባይ ውስጥ ተቆፎባቸውና ዙሪያቸውን መሳሪያ በደቀኑና፣ አሸባሪን ለማጥቃት የተሰማሩ በሚመስሉ የክልሉ ወታደሮች ተከበው ሜዳ ላይ ተበትነው እንዲያድሩ ተደረገ፡፡ ሲዳማዎችም በክልሉ ባህል አዳራሽ እንዲሁ፡፡ በነጋታው ጠዋት ቀይ መስቀል፣ ባንዲራውን እያውለበለበ እርዳታ ለመስጠት መሯሯጥ ጀመረ፡፡ የክልል ልዩ ኃይል የሚባለው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዚህ ቀውስ መሪ ተዋናይ ነበር፡፡ የቀን ጅቦቹ መዋቅር ይህንን ኃይል ለብጥብጡ በሚመች መልኩ ለማደራጀቱ ይህ ተግባር ምስክር ነው፡፡

5. አስተዳደራዊው መዋቅርና ችግሮቹ፡- ሐዋሳ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መዲና ናት፡፡ የደቡብ ክልል መዲና ትሁን እንጂ የሁሉም ብሔር የከተሙባት ሁሉም ብሔሮች ያደመቋት ናት፡፡ ሐዋሳ ያለ ሌላው ብሔር ምንም ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተለየ ሐዋሳ የሁሉም ብሔረሰቦች ድምቀት ናት፡፡ ሁሉም ብሔረሰቦች የሐዋሳ ፈርጦች ናቸው፡፡ ስለሆነም የክልሉ አስተዳደር ይህን ህብረ ብሔራዊ ማንነት ማስተዳደር የሚችል ውድ መሆን አለበት፡፡ በኔ ግምት 70 ከመቶ ከተማዋ ነዋሪዎች ሲዳማዎች ከሲዳማ ውጪ የሆኑ የሌላ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ ታዲያ በክልሉም ሆነ በከተማው አስተዳደር ከ90 በመቶ በላይ ሲዳማ ብቻ እንዲሆን ተደርጎ እንዴት ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ ይቻላል? ይህ ኢ-ፍትሐዊነት ለሰሞኑ መበጣበጥ የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል፡፡ ስለዚህም ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ አስተዳደሩ የነዋሪዎቿና ክልሉ ትክክለኛ ወክልና ያለው መዋቅር ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም በአዲሱ የክልሉ መዋርቅ ክለሳ የሚቃኝ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

6. የክልል ይገናኛል ጥያቄ፡- ክልል እንሁን አንሁን የሚለው ጥያቄ የፖለቲከኞች ቁማር እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ አይመስለኝም፡፡ ሐዋሳ ክልል ብትሆን የሚጎዳው ሲዳማው ነው፡፡ በዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሌሎች የደdቡብ ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከ56ቱ የክልሉ ብሔረሰቦች ሲዳማ ክልል ቢሆን 55ቱን በሔረቦች የሚወክል አዲስ ክልል በወላይታ ወይም በአርባምንጭ ከተማ ሌላ ክልል ሊቋቋም ይችላል፡፡ ይህ ማለት 70 ከመቶ የሚሆነው የሌላው ክልል በጀትና የሰው ኃይል እንዲሁም ሌሎች ወደ አዲሱ ክልል ይዛወራል ማለት ነው፡፡ ይህን የነገሩኝ የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑ ሲዳማዎች ናቸው፡፡ ሐዋሳን ሰረቋት፣ ፌደራል ከተማ ልትሆን ነው፣ ክልል ካልሆነች የሚሉ ጥያቄዎች ለአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚጠቅሙ ሳይሆኑ የፖለቲካ ትርፍ የሚገኝባቸው ቁማሮች ናቸው ተብያለው፡፡ ከዚህ የተለየ አመለካከት ያለው ሊኖር ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ በዶ.ር. አብይ የመደመር ስሌት፣ ክልል እንሁን ሚለው ጥያቄ ለጅቦቹ የማበጣበጫ አጀንዳ ጠቀማቸው እንጂ ለሐዋሳና ነዋሪዎቿ የሚያስቸኘው ትርፍ እምብዛም ሆኖ ነው የታየኝ፡፡

ስለጉዳዩ ከአንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ሳወራ፣ አብዛኛዎቹ አፈናቃዮችና ተፈናቃዮች በአንድ ቤተ እምነት አብረው የሚያመልኩ፣ ጎን ለጎን ሆነውአብረው የዘመሩ፣ በክፉም ሆነ በበጎ ብዙ ብዙ አብረው ያሳለፉ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ ያ ሁሉ አሴት ጠፍቶ እንዲህ አይነት ምስቅልቅ ማየት እጅግ ያማል፡፡ ስለሐዋሳና ስለ ህዝቦቿ የምንቆረቆር ማናችንም የቀን ጅቦቹን ቀመር ተረድተን ከዶ.ር. አብይ ጋር በጽናት በመቆም፣ የማረጋጋት ስራ ላይ እንሰማራ፡፤ ለዚህም የኦሮሚያ ክልል እና ቲም ለማ በብዙ ርቀት የሔዱ በመሆኑ ከኦሮሚያ ትምህርት ወስደን ኢትዮጵያ ያለኛ አመራር ሶሪያ ትሆናለች ብለው የሚያምኒኑና የዶ.ር. አብይ አመራር ከሽፎ ማየት የሚናፍቁትን የቀን ጅቦች አናሳፍራቸው፡፡ ሲዳማው ለወላይታው፣ ወላይታው ለሲዳማው ዘብ በመቆም የአንድነት አንድ መሆናችንን እናስመስክር፡፡ ይቅር ተባብለን አጅ ለእጅ ተያይዘን ዶ.ር. አብይ ሐዋሳን ለመጎብኘት ሲመጡ በእርቅ መንፈስ እንቀበላቸውና ጠላቶቻቸውን እናሳፍር፡፡
*ይህ ጽሑፍ የአይን ምስክርነት፣ ትዝብትና ለመፍትሔ አካላት በ 10/10/10 ዓ.ም. ተጻፈ፡፡
ታሪኩ ወዳጆ
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!