ጥቂቶች በስሙ ነግደው ይሆናል እንጂ የትግራይ ህዝብ የተለየ ያገኘው ነገር የለም። ሚስተር ኤክስ አጠፋ ብለን የማያውቀውን መፈረጅና ማጥቃት ተገቢ አይደለም። የትግራይ ህዝብ መታገዝ መደገፍ የሚገባው ህዝብ እንጂ ተደምሮ የሚፈረጅ አይደለም። ደሃ ነው፤ ..ምንም የለውም..”

“ሕገ መንግስቱ የታሰረ ሰውን ግረፉ ጨለማ ቤት አስቀምጡ ይላል ወይ? ይህ የእኛ አሸባሪነት ተግባር ነው”

“ባድመ ጦርነት አቁሙ ሲባል እያለቀሱ ከተመለሱት አንዱ እኔ ነኝ…ስሜቱን አውቀዋለሁ…እናቴ ያሳደገችው የወንድሜን ልጅ ማሙሽን ባድሜ ላይ ነው ያጣሁት….ወንድሜን ገብሬበታለሁ…ብዙ ጓደኞቼን ቀብሬ አልፌያለሁ..ስሜቱን አውቀዋለሁ… ነገር ግን የአልጀርሱን ስምምነት ያጸደቃችሁት እናንተናችሁ…ቃለጉባኤውን ማየት ይቻላል..እኛ አዲስ ነገር አላመጣንም… የባድመ ጉዳይ አዲስ አይደለም .. ”

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ የሰጡት ማብራሪያ ሙሉ ቪዲዮና ዘገባ ይመልከቱ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማው በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዲሁም በወሰንና ድንበር ዙሪያ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ከሰጧቸው መልሶች መካከል፡
• አሁን ያለው የወሰን አስተዳደር ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ዳግም መለስ ብለን ከችግሩ የምንወጣበትን መንገድ መቀየስ ያሻል፡፡
• ክልልን ከክልል ብቻ ሳይሆን አገርን ከአገር የሚከልል ድንበር ከጎረቤቶቻቸን ጋር ሳይቀር ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር ያስፈልገናል፡፡
• ኢትዮጵያ ያለ ቪዛ እንግዶቿን ለመቀበል የሚያስችል አሰራር ለመተግባር እየተጠና ነው፡፡
• እንኳንስ በክልሎች መሃል ያለው ወሰንና አንድ የሆኑ ህዝቦችን ከፍሎ ያለው ድንበር እንኳን ሰው ሰራሽ በመሆኑ በጋራ መኖር የሚያስችል ሂደት መከተል አለብን ፡፡

የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሃት ማለት አይደለም ። በትግራይ ህዝብ ስም የተወሰኑ ሰወች ተጠቅመው ሊሆን ይችላል እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ጥቅም ያላገኘ ህዝብ ነው ።
የትግራይ ህዝብ መደገፍ፣ መታገዝ እንጂ ከህወሐት ጋር ተደምሮ በጥላቻ መታየት የለበትም።

• እንደ ቴሌ፡ አየር መንገድ ፣የኃይል አቅርቦት ዘርፉ እና አንዳንድ የመንግስት ተቋማት የተወሰነው ድርሻቸው የሚሸጠው እዳቸውን ጭምር መክፈል ስላቃታቸው ነው፡፡
• በውድድር ላይ የተመሰረተ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል፡፡
• ሽግግሩ ጥንቃቄ የሚፈልግ ስለሆነ እስከ ሁለት ዓመት ሊወስድ ይችላል፡፡
• የሀብት ብክነትን ያስቀራል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛው ልዩ ስብሰባ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት መንግስታቸው በዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረጉንና ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጎረቤትና የመከከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር በተደረገው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አመርቂ ድል ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊና ፖለቲካ ቀውሶች በመከሰታቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በ2008 በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን የኤልኒኖን ተፅዕኖ ተከትሎ የተፈጠረው የምርት መቀነስ በ2009 እና በ2010 ማገገም መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ወደ መስኖ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚው መስክ አገሪቱ የተበደረችውን ብድር የመክፈል አቅም ማጣቷንም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ተናግረዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ ብቻ 688.6 ሚሊዮን ዶላር እዳ ክፊያ መፈጸሙንና ኢትዮጵያ ከፍተኛ እዳ ጫና ካለባቸው አገራት ተርታ መሰለፏን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
መንግስት የሀሳብ ብዝሃነት እንዲጎለብት በርካታ እርምጃዎች እየወሰደ እንደሚገኝ የገለፁት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ይበልጥ እንዲሰፋ ያገበኛል የሚሉ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በርካታ እስረኞች ተፈተዋል፣ ውጪ የነበሩ ፖለቲካኞች ወደ አገር ውስጥ መግባት ጀምረዋል፣ መገናኛ ብዙኃን የህዝብ ድምጽ እንዲሆኑ በመደረጉ ሂደት ጥሩ ለውጥ መጥቷል፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጦማሪያን ሀሳባቸውን በነጻ እንዲገልጹ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡
በጥቅሉ የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያን ከዳር ለማድረስ የፍትሕ ማሻሻያ ምክር ቤት ተደራጅቶ ስራ መጀመሩንም ዶ/ር አብይ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መንግስት ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪ አድርጓል፡፡ በአገር ውስጥም ዜጎች በስጋት መተያየትንና መጠላላትን አስወግደው በጋራ መግባባት የተመሰረተ ውጤት እንዲያመጡ እየተሰረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመስራት መብት ከማስጠበቅ አንጻር የተሰሩ ስራዎች ውስንነት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለፓርላማው ካቀረቡት ሪፖርት ባሻገር ከምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡