
ከሶማሊያ፥ ከጅቡቲ፥ ከኤርትራ ጋር መዋሃድ፥ ሌሎች አፍሪካውያን ያለ ቪዛ እንዲገቡ መፍቀድ፥ የአፍሪካን ሕብረት ወደ ውህደት/ጥምረት መውሰድ/ማሸጋገር፥ የመንግሥትና የሕዝብ የሆኑ ንብረቶችን የግል ለማድረግ መወሰን፥ … ወዘተ እነዚህ ሁሉ ትላልቅ ውሳኔዎች ናቸው። ትላልቅ አገራዊ (እና አህጉራዊ) አንድምታም ያላቸው ጉዳዮች ናቸው።
ትላልቅ እንደመሆናቸውም መጠን፥ በእነሱ ለይ የሚደረግ ውሳኔና ለአተገባበሩ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ አካሄዶች በሙሉ በአንድ (ለዚያውም ምንም ዴሞክራሲያዊ credential እና mandate በሌለው፥ የጭንቅ ጊዜ [የሽግግር እንኳን ያልሆነ]) ጠቅላይ ሚኒስትር ግለሰባዊ (personal) ዲፕሎማሲ የሚደረግ አይደለም።
ከጉዳዮቹ ግዝፈት የተነሳ፥ ለጉዳዮቹ ግዝፈትና ትልቅነት የሚመጥን ግዙፍና ትልቅ መንግሥታዊ (ተቋማዊ)፥ ሕገ-መንግሥታዊ፥ ሕጋዊ፥ ዲሞክራሲያዊና ሕዝባዊ አካሄድ፥ ምክክርና የአወሳሰን ሂደት ያስፈልጋቸዋል።
እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች መያዝ፥ መታየትና መወሰን ያለባቸው፣ በመንግስት (ያውም በምርጫ የተረጋገጠ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ ማንዴት ባለው መንግሥት)፥ በዓለምአቀፍ ሕግና ሥርዓት መሠረት፥ ከዛም በግልፅ በሕዝበ-ውሳኔ በተገለፀ የሕዝቦች ፈቃድና ይሁኝታ ብቻ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዛሬው ውይይትና ውሳኔ (እንዲሁም ቀደም ያሉት ግዙፍ አገራዊ ጉዳዮች) እንደምኞት መግለጫ (declaration of good intentions) መልካም የግላዊ ዲፕሎማሲ (personal diplomacy) ሥራ ሊታዩ የተገባ ነው/ናቸው። ከዚህ በላይ ተደርገው ሊወሰዱ አይገባቸውም፤ ሊወሰዱም አይችሉም።
ለምን?
1. ይሄ መንግሥት፣ የቀውስ ጊዜ መንግሥት (Crisis-Time Government) ነው። የሽግግር ጊዜ መንግሥትነት ክብር እንኳን የለውም። ወደ ሽግግር መንግሥትነት ለመራመድ የተደረገ የተግባርም ሆነ የፈቃደኝነት ምልክት እንኳን አላሰየም። የቀውስ ጊዜ መንግሥት ቀርቶ በህግ እውቅና ያለው ባለአደራ መንግሥት (care taker government) እንኳን አንዲትም አዲስ የፖሊሲና የሕግ ውሳኔ ወስኖ ለማሳለፍ እንዳይችል ፅኑ ሕገ-መንግሥታዊ ገደብ ተጥሎበታል።
እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻውን በግሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥት እራሱ እንዲህ ባሉ ግዙፍ ጉዳዮች ለይ ለመወሰን ቅንጣት ታህል የህግ ሥልጣን የለውም።
ከ1991 እስከ 1993 የኤርትራን ጉዳይ በሬፈረንደም ለመፍታት የሚደረገው የተቻኮለ እርምጃ እንዲዘገይ ይጠየቅ የነበረውም የመለስና የኢሳያስ ጊዜያዊ መንግሥታት እንዲህ ያለን ግዙፍ ውሳኔ ለመወሰን ሕጋዊ ስልጣንም ዴሞክራሲያዊ ማንዴትም አልነበራቸውምና ነው። ይሄው በግለሰቦችና (በፓርቲዎቻቸው) በጎ ፍቃድ ብቻ የተወሰደ ውሳኔ ይኸው እስከዛሬ ድረስ እያመረቀዘ ለሕመም እየዳረገን አለ።
ይሄ መንግሥት፣ እንደቀውስ ጊዜ መንግሥትነቱ፣ ሥራው መሆን ያለበት፣
ሀ. ሰላምና መረጋጋት መፍጠር፤
ለ. አላግባብ የፖለቲካዊ ኃይል ተግባር ተጠቂ የሆኑ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፤
ሐ. የታፈኑ ፓርቲዎችን ፥ የታገዱ የግልና ሲቪክ ድርጅቶችን፥ የታገዱ የመገናኛ ብዙኅን ተቋማትን ከአፈናና ከእግድ ነፃ ማድረግ፤
መ. አፋኝ ህጎችን፥ አሠራሮችንና ተቋማትን መሻርና እንደአስፈላጊነቱ ማፍረስ፤
ሠ. ለመሥረታዊና አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ መስጠት፤
ረ. ወንጀለኞችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ፤
ሰ. የዕለት ተዕለት ማህበራዊና አስተዳደራዊ ግልጋሎቶችን መስጠት፤
ሸ. ሁሉን-አቀፍ፥ አካታችና አሳታፊ ውይይትና ምክክር ከፓርቲዎች ጋር ማድረግ፤
ቀ. ስለሽግግር ጊዜ ፍትህ [ማለትም፦ ስለ ምህረት፥ ይቅርታና ፍርድ ወዘተ] ምክክርና ድርድር መጀመር፤ ወዘተ ብቻ ነው።
ከዚህ ያለፈ እርምጃ መውሰድ ከሕጋዊ አቅም በላይ መንጠራራት ፖለቲካዊ ድፍረት (political overreaching) ነው።
2. ይሄ መንግሥት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቀባይነት የሌለው (ወይም ገና ያላገኘ)፥ ያልተመረጠ መንግሥት ነው።
3. ዴሞክራሲያዊ ማንዴት ያለው እንኳን ቢሆን፣ ተግባሩ እና ውሳኔው ተቋማዊ እንጂ ግላዊ መሆን አይችልም።
መንግሥቱ ደግሞ በሚንስትሮች ምክር ቤትና በፓርላማው እንደጉዳዩ ሁኔታም በሕዝበ-ውሳኔ ጉዳዩን ያስፈፅማል እንጂ በአንድ ግለሰብ ግላዊ ውሳኔ ምንም ማድረግ አይችልም፤ አይገባውም።
4. ይሄ መንግሥት፣ ውሳኔና ተግባሩም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረትና ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ካልተቀበለ ለሕግ የበላይነት የማይገዛ ተራ የመንደር አምባገነን ከመሆን አያልፍም።
ሁሉን እየያቀረቡና እየቀረቡ መወያየት፥ መመካከርና መግባባት ጥሩ ነው፤ የሕዝቡን ችግር በትክክል ለመረዳት ይረዳልና።
ነገር ግን ውይይትና ምክክር እንደወትሮው ኢሕአዴጋዊ አሰራር ሕዝብን “አሳምኖ” ለመመለስና የዜጎችንና የሕዝቦችን መብቶች ለመገደብ ወይም ለመጨፍለቅ የሚደረግ ከሆነ፥ ተራ የሽፍታ ሕገ-ወጥነት ነው፤ ፀረ-ሕዝብነት ነው።
5. ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች አገር ናት። እኒህ ብሔሮች የእኩል መስራችነትና(co-founding) የእኩል ባለቤትነት (co-ownership) እኩል የሆነ (co-eval) ሉዓላዊነት (sovereignty) ሥልጣን አላቸው።
በሕገ-መንግሥቱ፥ at least textually, የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው፥ የጋራ አገራቸውን ጉዳይ በጋራ መወሰን በሚያስችል መርህ ለይ ተመስርተው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው።
አገሪቱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሉዓላዊ ሥልጣንን እንደመብት ብቻ ሳይሆን እንደመመስረቻ/መደራጃ መርህ (organizing principle) የተቀበለች በመሆኗ ክፍት ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ (open constitutional frame) ያላት መሆኗን በአትኩሮት ማስተዋል ያስፈልጋል።
ይህም በመሆኑ ያልተመቸው ሊሄድ፥ በዲሞክራሲያችን የማለለ
ደግሞ ሊዋሃደን የሚችልበትን ዕድል ይሰጣል። የመለየትም (secession) ሆነ የመጣመር (reunion እንደ ኤርትራና ጅቡቲ፥ ወይም እንደ ሌሎቹ እንደ አዲስ ለመቆራኘት) ውሳኔ የሚፈፀመው በሕዝበ-ውሳኔ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር መዋሃድ፥ መጣመር (“መደመር”) ወዘተ እንድትችል የሚወስኑት ሕዝቦቿ እንደ ብሔሮች በሚወስኑት ሕዝበ-ውሳኔ እንጂ በአንድ ግለሰብ ወይም በመንግሥት አይደለም።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ፥ ተደብቆ የከራረመ የጠቅላይ-ተስፋፊነት ሕልምን (hidden imperial ambitions) ለማርካት፤ ወይም የሕዝቦችን እውነተኛ ወንድማማችነትና ተጨባጭ የሆነ አጋርነትን ለማረጋገጥ ሳይሆን፥ የወደብና የገበያ ፍላጒትን ለማርካት እና የጠቅላይነት መጎምዠት (imperial desire) የፈጠረው መሻት ብቻ ከሆነ ይኼን የሚፈቅድ ሕገ-መንግሥታዊ ሥነምግባርና መርህ፣ እንደ ሕዝብና እንደ አገር፣ እንደሌለን ሊሰመርበት ይገባል።
በመሆኑም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ያለ ዴሞክራሲያዊ ማንዴት፥ ያለ ሕዝብ ፈቃድ፥ ያለተቋማዊ አግባብ፥ ያለተጠያቂነትና የህግ የበላይነት መርህ፥ ያለሕገ-መንግሥታዊ መሠረትና ማዕቀፍ በግላዊ ዲፕሎማሲ፥ በግላዊ በጎ ፍቃድና፥ ይህንኑ በሚገልፁ መልካም ንግግሮች ኃይል ብቻ (እንደፈላጭ-ቆራጭ ንጉሥ) በግዙፍ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ መወሰን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል።
PS. I had vowed not to say a word about the PM and OPDO anymore. But I couldn’t help this one, Prime Minister. Sorry, you keep getting it wrong!
