“ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” ይባላል፡፡ ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ በኔ ዕድሜ ይህ አባባል እውን ሲሆን ማየት አልቻልኩም፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ተስፋ ያለኝ ይመስለኛል፡፡ ዕድሜ ለዕንባ አባሹ አንድዬ!
ወያኔ ከየሥርቻው ለቃቅሞ አራት ኪሎ ፓርላማ ያስገባቸውን ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩር ብዬ ያየኋቸው ገና ትናንት ነበር – ሰኔ 11 ቀን 2010ዓ.ም፡፡ ቁም ነገር አገኛለሁ ብዬ ኢቲቪን መቼም ቢሆን አልመለከትም፡፡ ውሸትና ግነት በልቦለድ ዓለም እንጂ በእውነተኛው ሕይወት እንዲህ እንደኢቲቪ በዝቶ ሲገኝ ያስጠላልና በኢቲቪ ቱሪናፋ አንጎሌን ማዞር አልፈልግም ብዬ ትቸው ነበር፡፡ ትናንት ግን አንድ ጓደኛየ ስልክ ደውሎ የዶ/ር አቢይን የፓርላማ ንግግር እንዳዳምጥ ጎተጎተኝ፡፡ እያየሁት የነበረውን የእንግሊዝንና የቱኒዝያን የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ትቼ ወዲያው ወደ ኢቲቪ ዞርሁ፡፡ የሚገርመው ነገር ቲቪውን ስከፍት እየተነገረ የነበረው ጓደኛየ የነገረኝ የአንዲት ወያኔ የፓርላማ አባል ጥያቄና የጠ/ሚኒስትሩ መልስ ነበር፡፡ ከዚያን በፊት የነበረው አምልጦኛል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረውን ግን ተከታትየዋለሁ፡፡ በጣም አስደሳች ነበር፡፡ በማግሥቱም ደገምኩት፡፡
የፓርላማ አባላቱን ለቅጽበት ቃኘኋቸው፡፡ እኛን የሚወክሉ እንደመሆናቸው በነሱ ውስጥ እኛን አየሁ፡፡ እስከዚህን ድረስ መጎሰቆላችንን አላውቅም ነበር፡፡ በአእምሮየ የመጣልኝ ነገር ቢኖር ውድቀታችን ሊሸፈን ወይ ሊስተባብል የማይችል ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ነው፡፡
የፓርላማ አባላቱ ወያኔ ኢትዮጵያን የመዝረፍና የማፈራረስ ሤራውን ለማሳካት እንዲያመቸው ብሎ ከትምህርትም ከዕውቀትም ከግንዛቤም ከምንም ከምንም የፀዱ ማይማንን መርጦ የጎለታቸው ናቸው፡፡ ዋነኛ ሥራቸውም እንደሚታወቀው ማጨብጨብ ነው፡፡ ነቃ ያሉት ደግሞ ከነገሩ ጦም እደሩ ብለው በጦፈ የጭብጭባ ወቅት ሳይቀር ዕንቅላፋቸውን የሚደቁ ናቸው፡፡ የአውሮፓንና የአሜሪካንን ፓርላማ የሚያውቅ ሰው በነዚህ የፓርላማ ተብዬ አባላት ምን ያህል እንደሚያፍር ግልጽ ነው፡፡ እኔ እጅግ አፍራለሁ፤ በወያኔ መናቄም እየታየኝ እነሱን ባሰብኩ ቁጥር እጨነቃለሁ፡፡
ከሰው መርጦ ለሹመት ዛሬ የለም፡፡ ከንንጨት መርጦ ለታቦትም ዛሬ የለም፡፡ ፖለቲካውም ሃይማኖቱም በማይረቡ ወሮበላ ሰዎች ተጠልፎ እንዳይሆን ሆኗል፡፡ ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራልና የመንደር አውደልዳይ የፓርላማ አባል ይሆናል፡፡ ባዶ ጭንቅላት የያዘች የሠፈር ተርቲበኛ የፓርላማ አባል ትሆናለች፡፡ ወይራና ዝግባ ተንቀው እምባጮና ብሣና ታቦት ሆነዋል፡፡ ምሥጢረ መለኮት በአልባሌ ሰዎች ይዋረዳል፡፡ በዘሟቾችና ንስሃን በማያውቁ ኃጢኣተኞች ሥጋ ወደሙ ይፈተታል፡፡ ዘመነ ግርምቢጥ፡፡ በዚህ መሀል ሀገርና ሕዝብ ለባዕድ አምልኮና ለአጋንንታዊ ኃይል ይጋለጣል፡፡ ሀገራችንን ዲያብሎስ የሚጋልባትና ሠራዊተ አጋንንት የሚጨፍርባት እንግዲህ በዚህ ሂደት ነው፡፡ ከጠፋንበት ሊታደገን ፈጣሪ ፊቱን ካልመለሰልን አካሄዳችን እጅግ አደገኛ ነው፡፡ አሁን የፈጣሪ ፊት ወደኛ የዞረ ይመስለኛል፡፡
የፓርላማ አባላትን በ“ሦስተኛው ዐይኔ”ና በ“ስድስተኛው” የስሜት ሕዋሤ አነበብኳቸው፡፡ ለነገሩ ማንም ቢያነባቸው እንደኔው ይረዳቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ሌሎችም ቢመለከቷቸው ማንነታውን በቀላሉ ይረዷቸዋል – ከአዳራሹ የሚያንስ ዋጋ እንዳላቸውም ማንም ይገነዘባል፡፡ ግዑዝና ግዑዝን ማመሳሰል ደግሞ ስህተት አይደለም፡፡ መብላትና መጠጣት ብቻውን ሰው አያደርግምና፡፡
የሰውነት አቋማቸው ራሱ ስለማንነታቸው ብዙ ያሳብቃል፡፡ አለባበሳቸውና ትክለ ሰውታቸው ብዙ ይናገራል፡፡ ከአእምሯቸው በላይ በሀነባቸው አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አነጋገርና ገለፃ ሳቢ ጦጣ ሆነው ሲቁለጨለጩ ማየት አንጀትን ይበላል፡፡ የአቢይን ንግግር ስለመረዳታቸው እርግጠኛ መሆንም አይቻልም፡፡ መቁለጭለጭ ብቻ፡፡ የለመዱት ተጽፎ የተሰጣቸውን ማነብነብ በመሆኑ ይህ አዲሱ የአቢይ አካሄድ ሊገባቸው የቻለ አይመስልም፡፡ በወረቀት ተጽፎ የሚሰጣቸውን ጥያቄ መጠየቅ የለመዱት “የፓርላማ አባላት” አሁን የፈለጉትን መጠየቅ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ግራ ገባቸው፡፡ እናም ማይክራፎን ተቀብለው “በወረቀት የጻፍኩትን ነው የምጠይቀው” ማለት ጀመሩ – ያሳፍራል፡፡ ጥያቄ እንዲሁ ይጠየቃል እንጂ እንዴት ከአዳራሽ ውጭ ተጽፎ ይመጣል? ተጽፎ ይምጣ – ግዴለም፡፡ ሲጠይቁ መንተባተብን ምን አመጣው? የገዛ ጽሑፍን ማንበብ አለመቻልን የመሰለ የድንቁርና መገለጫ ደግሞ የለም፡፡ እነዚህ ናቸው ወካዮቻችን፡፡ እነዚህ ናቸው ህግ አውጭዎቻችን፤ እነዚህ ናቸው “በሕዝብ የተመረጡ” መሪዎቻችን፡፡ ወያኔ የተባለ ጉድ የሠራልን ሥራ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የሚያሳዝነኝ አቢይ ነው፡፡ ከነዚህን መሰል ጦጣና ዝንጀሮዎች ጋር ምን ተመካክሮ እንዴት ሥራ ላይ ሊያውል እንደሚችል አስቡት፡፡ ለቤተ ሙከራ ሠርቶ ማሳያ የተሰባሰቡ ፈቃደኛ ሰዎች ይመስላሉ እንጂ በጭራሽ የፓርላማ አባላት አይመስሉም፡፡ ቢኖሩ ባይኖሩ የማያጎድሉ ወያኔ የጠፈጠፋቸው Guinean pigs ናቸው ቢባል አሳምሮ ያስኬዳል፡፡ በአገላለጼ ክረት አዝናለሁ፡፡ ከተጎዳ ሥነ ልቦና የሚወጣ ቃል እንደሚያም ግልጽ ነውና ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ …
ዶ/ር አቢይን እግዚአብሔር በጭንቅ ቀናችን የሰጠን የክፉ ቀን ልጃችን ነው፡፡ ይህን የክፉ ቀን ልጃችንን አለመደገፍ ማለት ነባሩን የሕወሓት ዘረኛ አገዛዝ የሙጥኝ ብሎ ወያኔን “አትሂድብኝ” እንደማለት ነው፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይህን ሰው ወፌ ቆመች ለማለት አለመፈለግ ልዩ ተልእኮ ያነገበ የሀገር ፀርነት ነው፡፡
የዛሬው ፓርላማችን ወደፊት ጥርሳችንን ተነቅሰን እንስቅበት ዘንድ በሁሉም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተቀርጾ የሚቀመጥ የጅላንፎዎች ስብስብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቀጣዩ ፓርላማ ግን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው ዓይነት በተማሩና በበቁ ሰዎች – በሁሉም ረገድ ከተራው መንጋ በተሻለ ሁኔታ በተመረጡና በተከበሩ ዜጎች የተሞላ እንደሚሆን ተስፋዬ ብርቱ ነው፡፡
ስለአቢይ እግዚአብሔር በአብዩ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ኢትዮጵያ እንደገና ትልቅ ስትሆን ይታየኛል፡፡ የሚዲያ አካላት አፍራሽ ነገሮችን ከማቅረብ ቢጠነቀቁ፣ ጸሐፊዎችም ገምቢና አስታራቂ በሆኑ ነገሮች ላይ ቢያተኩሩ፣ ተስፋ በመቁረጥ ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤቶችም ከየተደበቁበት ጉድጓድ እየወጡ የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉ፣ በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ ተጋሩ ወደኅናቸው ተመልሰው መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ እውነት ጋር ቢስማሙ … ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይን በሚገባ ማገዝ ይቻላል፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋልና ከእንግዲህ “ምን አገባኝ”ን መተው አለብን፡፡
