“ኢትዮጵያዊነትን እና ይቅር መባባልን ይዘው ብቅ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድና ባልደረቦቻቸው አጭር በሚባል የስልጣን ቆይታቸው ለወሰዶቸው በጎ እርምጃዎች እና ላሳዩን ኢትዮጵያዊ አለኝታነት አጋርነትን ማሳየት እና ከጎናቸው መቆም ጊዜው የሚጠይቀው አስፈላጊ ተግባር መሆኑን ስገልፅ በሚደረጉት የድጋፍ እንቅስቃሴዎች ላይ በሥራ አጋጣሚ በቦታው ባልገኝም በመንፈስ አብሬያችሁ መሆኔን ሳረጋግጥ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው።” ብሎናል ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ!
የዶክተር አብይን ንግግር ስንሰማ ሳይሆን ስናዳምጥ ቀድመው በአምሯችን የሚመጣው የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” እና “ሼ-መንደፈር” ናቸው። በጆሯችን የሚያቃጭለው ደግሞ ፍቅርን እና መቻቻልን የሚሰብከው “ፍቅር ያሸንፋል“ መፈክሩና “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት ነው።

ከቲም ለማ ቀድሞ የፍቅር እና የአብሮነትን እሴቶች፣ የመደመርን ጥቅም በዜማዎቹ ሁሉ መስበኩ የፈጠረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። ቴዲ በፌስቡክ ገጹ የለቀቀው የደስታ እና የአጋርነት መግለጫ የምኞቱን መሳካት አብሳሪ ይመስላል። ድል ለኢትዮጵያዊነት የሚል መፈክሩ የፌላ ኩቲን ‘ብላክ ፓወር’ ንቅናቄ ያስታውሰናል።
እነሆ ሰው ሰው የሚሸት ንግግር፣ ሃገራዊ ጠረን ያለው መሪ እየሰማን ነው። እንደ እህል ዘርን ሳይሆን ስብዕናን የሚያዜም፣ እንደ አፓርታይድ ክልልን ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚቃኝ መሪ! ሕልም ሊማስለን የሚችለው ይህ ክስተት በአንድ ሌሊት የመጣ እንዳልሆነ ሁሉም ይገነዘበዋል። ከቀን ጅቦች ጋር በነበረ ትንቅንቅ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። የ”ኢትዮጵያ” ስም ሲጠራ ብርክ እንደያዘው የሚሽመደመዱ፤ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እያልን በጣት ብቻ የምንቆጥራቸው የጥላቻና የበቀል ጉዶች ጋር የነበረ ትንቅንቅ! ዛሬ ይህ ትውልድን ደፍሮ ይናገርላቸዋል። በመደመር ሳይሆን በማከፋፈል – የደቡብ አፍሪካውን ባንቱስታ የተኩ ከፋፋዮች! በክፍፍላችን የበለጸጉ! በመተላለቃችን ሃብት ያካበቱ! በአጥንታችን ላይ ህንጻ የገነቡ ጅቦች!
ቴዲ “እረ አይነጋም ወይ ሌቱ …?” ሲል በአንድ ወቅት የተቃኘው ያለ ምክንያት አልነበረም። ተስፋ ግን አልቆረጠም። ገዢዎቻችን ኢትዮጵያዊነትን ቆፍረው በቀበሩበትና ኢትዮጵያዊነት ማንሳት እንደ ወንጀል በተቆጠረበት ሰዓት ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አርጎ መስበክ አደጋው ምን እንደነበር ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም። ከቀን ጅቦች ሊደርስበት የሚችለውን አደጋ ወስዶ ሲያደርገው የባለ ራዕያቸውን ህልም የተባለለት ቅዠት የደፈረ ድምጻዊ ተብሎ በጠላት መዝገብ ላይ የሰፈረ ድምጻዊ ነው።
ቴዲ በግፍ ታስሯል። ኮንሰርት እንዳያደርግ ታግዷል። ከሃገር እንዳይወጣ ተከልክሏል። የእቀባ ዘመቻ ሰለባ እስኪሆን በብዙ ተገፍቷል። በዚህ ሁሉ ተስፋ ቆርጦ ግን ዝም አላለም። በእሳት ላይ እየተራመደ ስለ ፍቅር እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀኑን አላቆመም። በአንድ ወቅት ጃማይካዊውን የጥበብ ሰው ጋሪሰን ሃውክን በመንተራስ አርቲስት ጂጂ ጋር ‘ጀግና አይፈራም … ተስፋ አይቆርጥም’! “ ሲል ብዙዎችን የሚያበረታታ እና የሚያነቃቃ ዜማ የተቃኘው በመከራም ተስፋው እንዳልጠፋ አሳይቶናል።
ከአዲስ አበባ ናይሮቢ-ኬንያ ይጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ከጀመረ በኋላ እንዲመለስ በመደረጉ ምክንያት አየር መንገዱ የሁለት መቶ ሺህ ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበት ተዘግቧል። ቴዲ አፍሮን ጭኖ ይጓዝ የነበረ ይህ አውሮፕላን ከመንገድ እንዲመለስ የተደረገው በአንድ የህወሃት ካድሬ ትዕዛዝ ነበር። ድምጻዊውን ለመበቀል ተሳፋሪዎች መጉላላት ነበረባቸው- የሃገር ሃብትም መውደም ነበረበት። ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን እንጠይቃለን። ማን ነው አሸባሪው? ስለ ፍቅር የተቃኘው ነው ወይንስ በዝርፍያ አምሮው የታወረው ካድሬ?
የቴዲ አፍሮ ጥፋቱ ምንድን ነው? ሲሉ መስፍን ወልደ-ማርያም ተይቀው ነበር። በወቅቱ ምላሽ ሲያጡ፤ “ቴዎድሮስን እንደሰው እንዳያዩት እዚያ ገና አልደረሱም። እንደ ኢትዮጲያዊ እንዳያዩት መናፍቃን ናቸው። እንደዘፋኝ እንዳያዩት ጆሮአቸው አይሰማም።” ነበር ያሉት።
አሁን ግን ለጥያቄያቸው መልስ ያገኙለት ይመስላል። “አሸባሪ ማለት ዜጋን ማጉላላት፣ ማሰቃየት፣ በጨለማ ቤት ማሰር፣ አካል ማጉደል ነዉ። ህንን ሲያደርግ የቆየው መንግስት ነዉ!” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ።
ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በአንድ ጽሁፋቸው፤ “ቴዲ – የፍቅር ነብዩን ተውት ስለ ፍቅር ደግሞ ደጋግሞ ይዘምር..” ብለው ነበር የዊልያም ሸክስፒርን “አስራሁለተኛው ሌሊት“ ተውኔት ጠቅሰው ላይ የኦርሲኖ መስፍን በአዳራሹ ተሰባስበው ለነበሩት ድምጻውያን የተናግረውን በመጥቀስ ፣ “ሙዚቃ የፍቅር ምግብ እስከሆነ ድረስ አሁንም ዘምሩ፣ በርካታ ሙዚቃዎችን ደግማችሁ ደጋግማችሁ ዘምሩልኝ…“
ፕሮፌሰር አል በእርግጠኝነት የተናገሩት አንድ ነገር ነበር “ቴዲ ከእርሱ ትውልድ የተስፋ፣ የእምነት፣ የብሩህ አመለካከት እና የጽናት ተምሳሌት ቀንዲል ነው።” በማለት!
“ኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲስ የሙዚቃ አልበምየህዝብን ቀልብ የተቆጣጠረ አቢይ ርእሰ-ጉዳይ መሆኑ ራሱ ለቴዲ አንድ ትልቅ ድል ነበር። ይህ አልበም በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ገኖ በመውጣት ቁንጮው ላይ አስቀምጦታል። በኢንዱስትሪም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም አልበም ሪኮርድ በአንደኝነት አድርጎታል። ግዜው መከፋፈልን ሳይሆን መደመርን የዋጀ ነበርና። ሼ-መንደፍርም ቢሆን ስለሃይማኖት መቻቻልና አንድነት የተቃኘ ነው። ቴዲ የደበዘዘውን ብሄራዊ ስሜት በጎላ ቀለም የጻፈ ጀግና ነው። ስለ ፍቅር እና ይቅር መባባል የተቃኘው ዜማ በሚልዮኖች ሰርጾ ትውልዱን አንጿል።
ዶክተር አብይ “ህገመንግሰቱ ጨለማ ቤት አስቀምጣችሁ ግረፉ፤ አሰቃዩ አይልም። አሸባሪዎቹ እኛ ነን። ይቅርታ ጠይቀናል። እኛን ማሰር የነበረት ህዝብም ይቅር ብሎናል። የቂም በቀል ፖለቲካ ይቁም ።” ሲሉ ሕዝብ በሙሉ ልብ የሚቀበለው ያለ ምክንያት አይደለም። የሚያሸንፈው ፍቅር እንጂ ጥላቻ እንዳልሆነ አስቀድሞ በውስጡ ስለሰረጸ ነው።
ፍቅር ያሸንፋል!
