ሰኔ 25 2010

Ethiopians react after an explosion during a rally in support of the new Prime Minister Abiy Ahmed in Addis Ababa, Ethiopia June 23, 2018. REUTERS/Stringer

አብዛኛውን ጊዜ ለአንዳንድ አጋጣሚዎች የሚሆኑ ጣል የሚባሉ የጀርመንኛ አነጋገሮች አሉ። አንድ ሰው ጨዋታ እየተጫወተ ወይም እየቀለደ ባለበት ሰዓት ደስ የሚለውን ሁኔታ ለመረበሽ ሲል አንዱ በመነሳት ሳይታሰብ የማይሆን ነገር ሲናገርና ተሰብሳቢውን ሲያሳዝን እንደዚህ ዓይነቱን ሰው ጨዋታ አበላሽ፣ (Killjoy) በጀርመንኛው አነጋገር ደግሞ ሽፒል ፈርደርበር(Spielverderber)ብለው ይጠሩታል።  ቅዳሜ 16፣ 2010 በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ወንጀል ከዚህ በላይ የሆነ፣ ከ90% በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ፣ ያስለቀሰ፣ ያበሳጨና አንጀት ያሳረረ የአረመኔዎች ድርጊት ነው። የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱና፣ ከ165 ሰዎች በላይ በሚቆጠሩ ላይ የተለያየ መጠን ያለው አደጋ መድረሱ ሁላችንንም የሚመለከትና ሀዘን ውስጥ የከተተን ነው። ለፍቅር፣ ለዕርቅና እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ አገራችንን እንገንባ ብሎ በወጣቱ አነሳሽነት እንደዚህ ዐይነት የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠራ ለዚህ ትብብር ከማሳየት ይልቅ፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚጠሉ ኃይሎች እንደዚህ ዐይነቱን እርኩስ ተግባር አስበው ወንድማችንን ዶ/ር አቢይንና የተቀሩትን ባለስልጣናት ለመግደል መነሳት ከሰው በታች የሚያስቆጥራቸው ነው። ዓላማቸውና ድርጊታቸው የሚያረጋግጠው የቱን ያህል ጭንቅላታቸው ያልዳበረ መሆኑን ነው። በዶ/ር አቢይ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ በእሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያንም ላይ ነው። አደጋው ያነጣጠረው፣ ለዲሞክራሲ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ድህነትና ረሃብን አጥፈተው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ትልቅ አገር ለመገንባት በሚመኙትና ደፋ ቀና በሚሉት ኢትዮጵያውያኖችም ላይ ነው። ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ ቢሳካ ኖሮ የኢትዮጵያን ህዝብ ተሰፋ አጨልሞ ለዝንተ-ዓለሙ በሀዘንና በድህነት፣ እንዲሁም በተመጽዋችነት እንዲኖር ለማድረግ ነው። ድርጊቱ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የስልጣኔውን በር ለመዝጋት የታሰበ ነው።

ማን ፈጸመው ማን ድርጊቱ እጅግ አረመኔያውነት የተሞላብትና ከማሰብ ኃይል ጉድለት የመነጨ ነው። ድርጊቱን ያቀነባበሩት ጭንቅላታቸው በሁሉም አቅጣጫ  ማሰብ እንዲችል ሆኖ ባለመታነፁ ይህንን ዐይነቱን እጅግ አሳዛኝ ድርጊት እንዲፈጽሙ ተገደዋል። ወንጀል አቀነባባሪዎች ያሰቡት ዓላማ ሙሉ በሙሉ ቢሳካ ኖሮ ድርጊታቸው ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ አደጋና አገርን ማተረማመስ ለአንድ ደቂቃ ያህልም እንኳ ለማገናዘብ በፍጹም የቻሉ አይደሉም። ለመሆኑ ድርጊቱ ቢሳካ ኖሮ፣ ማለትም ዶ/ር አቢይ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስ ኖሮ የድርጊቱ አቀነባባሪዎች እንደገና ተመልሰው ስልጣን ላይ በመቆናጠጥ በዚያው በአረጀውና በአፈጀው የአገዛዝ ስልታቸው ሊቀጥሉ ይችላሉ ወይ? ህዝቡስ ዝም ብሎ ያያቸዋል ወይ? ለዝንተ-ዓለም በህዝብ ትክሻ ላይ እየጋለቡ ለመኖር የሚችሉ መስሏቸዋል ወይ? በአጭሩ ምን አስበው ነው ይህንን ዐይነቱን የጥፋት ማዕበል ለማቀነባበር ያቀዱት? ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ባለፉት ሁለት ወራት የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደከታተልነው ከሆነ አንዳንዶቹ ከስልጣን ከመወገዳቸው በስተቀር አሁንም ቢሆን ስትራቴጂክ የሚባሉ የአገዛዝ መዋቅሮችን የሚቆጣጠሩ ናቸው። በተጨማሪም ባለፉት 27 ዓመታት እየዘረፉ ያካበቱት ሀብት አልተነካባቸውም። ዶ/ር አቢይ የነገሩን ውስብስብነትና አደገኛነት በመገንዘብ ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ከማካሄድና፣ ስለፍቅርና ተቻችሎ ስለመኖር ከመስበክ ወይም ከማስተማር በስተቀር እነሱን ጦር የሚያስመዝዝ አነጋገር ከአንደበታቸው በፍጹም አልወጣም። እንደወንድማማችና እንደአንድ አገር ዜጋ ሆነን ለጋራ ዓላማ እነነሳ፣ ዘላቂነትና ተከታታይነት ያለውን የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገት ለመጎናጸፍ የምትችል ኢትዮጵያን እንገንባ ከማለት በስተቀር ያስተላለፉት፣ እነሱን የሚያስኮርፍ ተንኮል የተሞላበት ድርጊት አልወሰዱም። አዎ የህወሃት አዛውንቶች የጎደላቸው ነገር ቢኖር እንደ አለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ እንደፈለጉ ለማሽከርከር የማይችሉበትና ሀብት እየዘረፉ የውጭ አገር ከበርቴዎችን የሚያደልቡበት ጊዜ ቀስ በቀስ እያከተመ መምጣቱ  ነው። ይህ ሁኔታ እጅግ እንዳበሳጫቸው የወያኔ አዛውንቶች ከሚያስተላልፉት የዛቻ መልዕክት ሰምተናል፤ እየሰማንም ነው። ይሁንና ግን እነዚህ አዛውንቶች ያልገባቸው ነገር ቢኖር በእንደዚህ ዐይነቱ በአረጀና በአፈጀ የአፈና አገዛዛቸው ወደፊት ለመቀጠል እንደማይችሉ ነው። ያልገባቸው ነገር አንድ ህዝብ እድሜውን በሙሉ በጭቆና ሰንሰለት ተተብትቦ ለመኖር እንደማይችልና ነፃነትንም እንደሚፈልግ ነው። አሁንም ያልገባቸው ነገር ቢኖር በአንድ አገር ውስጥ ሰላምና ብልጽግና ሊሰፍኑ ወይም ሊታዩ የሚችሉት ሰፊው ህዝብ የተሟላ ነፃነትንና ዲሞክራሲን የተቀዳጀ እንደሆን ብቻ ነው። ነፃነትና ዲሞክራሲ፣ እንዲሁም በሁሉም መልክ የሚገለጽ ፍትሃዊ አገዛዝ ከሰው ጭንቅላት ጋር አብረው የተፈጠሩ መሆናቸው ነው። እነዚህ ውስጣዊ ባህርዮችና ፍላጎቶች ታፍነው የሚቀሩ እስከሆነ ድረስ ደግሞ አንድ ህዝብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለንታዊነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ዕድገትን ማምጣት እይችልም።  በቂም በቀልና በጥላቻ የተወጠሩት የወያኔ አዛውንቶች እነዚህንና ለአንድ ህብረተሰብ የተሟላና ጤናማ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ሃሳቦች በፍጹም አልገባቸውም። የሚመስለው በማዕከለኛው ዘመን የሚኖሩ እንጂ በ21ኛው በሃይቴክ ክፍለ-ዘመን የሚኖሩ አይመስሉም። በጣም የሚያሳዝንና ወደ ኋላ የቀረ አስተሳሰብ !

የድርጊቱን አፈፃፀም እንደተከታተልነው የተቀነባበረው በፖሊስ ኮሚሽነሩ በትግሬው በግርማዬ ካሳና በሌሎችም ተባባሪዎች ነው። ኮሚሽነር ግርማዬ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣብያ ላይ ቀርቦ ስለድርጊቱ አካሄድ ረጋ ብሎ ሲገልጽ እጅግ በቀዘቀዘ የደም መንፈስ ነበር። እሱም እንደሌለበት እድርጎ የድርጊቱን አፈጻጸም ሲገልጽ እንደዚህ ዐይነት ደርበብ ያለ ሰው እንደዚህ ዐይነቱን ዘግናኝ ድርጊት ይፈጽማል ብሎ የገመተ ሰው በፍጹም አልነበረም። የኋላ ኋላ ዕውነቱ እየወጣ ሲሄድ ኮሚሽነር ግርማዬ ካሳ የቱን ያህል ጨቃኝ ሰውና፣ በእጁም ላይ ስንትና ስንት ደም እንደፈሰሰና፣ ቁጥራቸው የማይታወቁ ወጣቶች በእሱና በግብረአበሮቹ እጅ እንደተሰቃዩና አካለ ስንኩላን ለመሆን እንደበቁ ተገንዘበናል። በዚህ ዐይነት ድርጊቱም ከወያኔ ባለስልጣናት በሹመት ላይ ሹመት እየተጨመረለት ከፍተኛ ማዕረግን ለመቀዳጀት እንደበቃ ለመረዳት ችለናል። የመጨረሻ መጨረሻ ላይ ግን በዚህ ዐይነት እርኩስ ተግባሩ ሊቀጥል እንደማይችል በአንዳንድ ቆራጥና አገር ወዳድ የፖሊስ መኮንኖች ሊጋለጥ በቅቷል። ማንኛውም ሰው እድሜውን በሙሉ ሰውን እያታለለና እያሰቀየ ወይም እየገደለ ሊኖር እንደማይችል በኮሚሺነር ግርማዬ ላይ የደረሰው መጋለጥ ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክ ውስጥም በዚህ መልክ በሰው ልጅ ላይ ጉዳትና ስቃይ የሚያደርሱ ግለሶቦችም ሆነ ድርጅቶች የመጨረሻ መጨረሻ በሰፈሩት ቁና ልክ መሰፈራቸው እንደማይቀር ነው። ያለፈው አልፏል ከእንግዲህ ወዲያስ ? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በአገራችን ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ዐይነት በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ ተደጋጋሚ አደጋ ሲደርስ ወይም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ ሲጨክንና ሲያጠፋው የኮሚሽነር ግርማዬ ካሳና የግብረ አበሮቹ ድርጊት የመጀመሪያው አይደለም። እንደዚህ ዐይነት እርኩስ ድርጊት የወያኔዎችም ብቻ አይደለም። በታሪካችን ውስጥ እንደ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ለገሰው አስፋው፣ የጎንደሩ መላኩ ተፈራ፣ በማርክሲዝም ስም ይምሉ ይገዘቱ የነበሩ ጥቂት የዚህና የዚያ ድርጅቶች መሪዎችና፣ እነ ተምራት ላይኔ የመሳሰሉት በሙሉ… ወዘተ. በጭፍን ጥላቻና በዝቅተኛ ስሜት በመነሳሳት ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ኢትዮጵያውያንን ገድለዋል፤ አስገድለዋልም። እኛ ኢትዮጵያውያን ቆንጆ አገር ለመገንባት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመፍጠርና፣ ለሌሎች ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራዎች ያልተፈጠርን ይመስል ሰውን ማሰቃየት፣ ተንኮል መሸረብ፣ ለውጭ ኃይሎች መሰለልና አገርን ማከረባበት እንደባህላችን አድርገን መቁጥር ከጀመርን ዘመናት አልፈዋል። አብዛኛውን ጊዜ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለአገር መውደድ እያወራን፣ በተግባር የምንፈጽመው ግን የተቃራኒውን ነው። በጣም በሚያሳዝን መልክ በአገር ላይ የሰለለ፣ አገሩ ላይ ጦርነት ያወጀና ወንድሙን የገደለ ወይም ያስገደለ የሚከበርበት አገር ቢኖር እንደ አገራችን ያለ ሌላ አገር ያለ አይመስለኝም። ስንትና ስንት ሰው የጨፈጨፈ፣ በአገር ላይ በመሰለል ወያኔን የመሰለ አረመኔያዊ ኃይል ሰተት ብሎ እንዲገባ ያደረገ በየቴሌቪዥኑና በራዲዮ ጣቢያዎች ላይ ተጋብዞ የቃለ-ጥያቄ ምልልስ ሲሰጥ ስሰማ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ግድፈት እንዳለብን ለመገንዘብ ችያለሁ። በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ የሚታወሱት ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም ደራሲዎችና አገር ገንቢዎች እንጂ  ወንጀል የፈጸሙ አይደሉም። ሰለ ፖለቲካ፣ ስለፍልስፍና፣ ስለኢኮኖሚና ስለአገር ግንባታ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የሚጋበዙ ወንጀለኞች ሳይሆኑ፣ ከወንጀል ንጹህ የሆኑና በነገሮችም በቂ ግንዛቤ ያላቸው ናቸው። ሂትለራዊ አቋምን የሚያንጸባርቁ ወይም ሰፊን ህዝብ በመጨረስ የሚታወቁ እንደምሁር አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በአውሮፓ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ወይም በራዲዮ ሲጠየቁ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ወደኛ አገር ስንመጣ ግን፣ በተለይም በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ደግሞ የሚዲያ አስተናጋጆች ማንን እንደሚጠይቁ ግራ የተጋቡ ይመስለኛል። ያም ተባለ ይህ፣ የወያኔ አገዛዝ ፍጻሜውን አገኘም አላገኘም እኛ ራሳችን አስተሳሰባችንን ካልቀየርን በስተቀር፣ ወይንም ጭንቅላታችንን በትክክለኛው ዕውቀት በማነጽ እንደሰው ማሰብ እስካልቻልን ድረስ እንደወያኔና እንደኮሚሽነር ግርማዬ ካሳ ዐይነት የመሳሰሉት እየተፈለፈሉ በእርኩስ መንፈስ በመመራት ሊያሰቃዩንና አገራችንን ለመበታተን ይችላሉ። ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ የቀጨጨ አስተሳሰብ ለመላቀቅና የስልጣኔ ባለቤት ለመሆን ከፈለግን ራሳቸንን ለማነጽ ከአዲስ ዕውቀት ጋር መተዋወቅ አለብን። ከፍተኛ የሆነ የጭንቅላት ስራ መስራት አለብን።

ከዚህ ስንነሳ በዶ/ር አቢይ አህመድ ላይ የታቀደው የመግደል ዓላማ በኮሚሽነር ግርማዬ ካሳና በወያኔ መሬዎች ብቻ የተቀነባበረ ነው ብዬ አላምንም። አልዋጥልንም፣ ማየትም አንችልም፥ አንቀበልምም ካላልን በስተቀር ላለፉት 27 ዓመታት ከወያኔ ጀርባ ሆነው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያተረማምሱትና የጭቆናውና የስቃዩ ተባባሪ ወይም አቀነባባሪዎች  የጀርመን የስለላ ድርጅት፣ ሲአይ ኤ(C.I.A)፣ የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድና የእንግሊዙ የስለላ ድርጅት ኤም አይ ሲክስ ናቸው። ወያኔና ግብረአበሮቹ በነዚህ ሰይጣናዊ ድርጅቶችና የሰላም ጠንቅ ኃይሎች እየተረዱና እየተመከሩ ነው በህዝባችን ላይ ጦርነት እንዲያውጁ ለማድረግ የበቁት። የከፋፍለህ ግዛ የክልል ፖለቲካና፣ ህዝባችንን ወደድህነት የገፈተረውና ከተማዎችን የቆሻሻ መጣያ ያደረገው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክ ፖሊሲ የዓለም ኮሚኒቲው በሚባለው የተቀነባበረ ነው። ባጨሩ በአገራችን ውስጥ ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ መስፈኑ፣ የዲሞክራሲና የነፃነት እጦት፣ የብዝበዛውና የአገራችን የጥሬ ሀብት መዘረፍና ወደውጭ መውጣት፣ ከውጭ ኃይሎች በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባትና ከማዘዝ ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን የሚክድ ወይም የማይቀበል ካለ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው ማለት ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ለውጭ ኃይሎች የዶ/ር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ በውጭው ዓለም ተቀባይነትን ያስገኘ ቢመስልም፣ በሌላ ወገን ግን የውጭ ኃይሎች እነሱ በፈለጉት መንገድ ኢትዮጵያ ለመበታተን አለመቻሏ፣ ወይንም ህዝባችን በዶ/ር አቢይ ጀርባ ሆኖ ድጋፍ መስጠቱና በአንድነት መነሳቱ ያላስደሰታቸው ኃይሎች እጅግ ብዙ ናቸው። ይጎዝላቢያ እንደተበታተነ፣ ሊቢያና ኢራክ እንደወደሙ፣ ሶሪያም እንደፈራረሰ አሜሪካና ሌላው የተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት አገር የኢትዮጵያን መበታተን ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት መቆሙ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ማውለብለቡ፣ በአንድ ቋንቋ መናገሩና ነፃነት እያለ መዘመሩ፣ የተለያዩ ባህሎች ማሸብረቃቸውና ለአዲስ ኢትዮጵያ መነሳት… ወዘተ. … ወዘተ.  እነዚህ ሁሉ ስለጠንኩኝ የሚለውን የምዕራቡን የካፒታሊስት ዓለም ያስፈራዋል። እሱ የሚፈልገው የደከመችና ጦርነትን የምታስተናግድና የሚካሄድባትን ኢትዮጵያን እንጂ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ነፃነት፣ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰፈነባትን፣ ከዚህም በላይ ውብ በሆኑ ከተማዎችና መንደሮች ያሸበረቀች ኢትዮጵያን አይደለም። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ታላቅነትና ጥንካሬ፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ በልጽጎ መገኘት የምዕራቡ አጀንዳ አይደለም። ስለሆነም ወደዚያ የሚያመራውን መንገድ መቃወምና ማሰናከል፣ እንዲሁም ፍቅርና ሰላም ብለው የሚነሱ መሪዎችን ማስወገድ ሰለጠንኩኝ የሚለው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም የፖለቲካ ስሌትና ስትራቴጂ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብና ዶ/ር አቢይም የምዕራቡን ዓለም ድጋፍ አግኝተዋል እያሉ ማስወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ እርኩስ ፖለቲካ እንደሚቀነባበርና እንደሚካሄድ ካለማወቅ የተነሳ የሚናፈስ አዘናጊ አባባል ነው። ስለሆነም  በቅዳሜው ዕለት በዶ/ር አቢይ ላይ የተቀነባበረውና በብዙ ሚሊዮን ህዝብ ላይ ያነጣጠረው የፍርሃት ድርጊት ዋናው ዓላማ በዚህ መልክ ሁኔታው ሊቀጥል እንደማይችል ለማሳሰብ ነው። በዚህ መልክ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደትርምስ ውስጥ ሲገባና ሲደናገር ዕርዳታ እሰጣለሁ ብሎ በመግባት ለሱ የሚመች ቡችላ ኃይሎችን ስልጣን ላይ ለማውጣት የታቀደ ነው። ከዚህም ባሻገር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የነበረው የተከማቸ ወርቅ በእንግሊዝና በካናዳ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች(Multinational Companies) ተሟጦ ስላለቀ ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚገኘውን የወርቅ ክምችት ለመዝረፍ የሚያመቻቸውና ለነሱ የሚስማማ እጅግ ደካማ አገዛዝ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለማስፈንም ነው። ስለሆነም ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና ግብረአበሮቻቸው የወያኔ አገዛዝ ዘመን እንዳከተመለትና ከእንግዲህ ወዲያ የእነሱን እርኩስ ተግባር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይችል ከተገነዘቡ ዘመኑ አልፏል። የሚያወጡትና የሚያወርዱት ለነሱ የሚመች፣ ተለማማጭ የሆነና የኢትዮጵያን የጥሬ ሀብት የሚያዘርፍና ህዝባችንን ለዝንተ-ዓለም ደሃ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ ኃይል ነው።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የፖለቲካ አመለካከታችንና አተናተናችንን ሰፋ ባለና በተወሳሰበ መልክ ማየት አለብን ማለት ነው። ቀድሞም ሆነ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምንና ነፃነትን፣ እንዲሁም እኩልነትን የሚያሰፍን ፖለቲካ ተካሂዶ አያውቅም። ወደፊትም ሊካሄድ አይችልም። ኢምፔሪያሊስቶችና ቡችሎቻቸው እስካሉ ድረስ የዓለም ህዝብ እጣ ፍርሃት፣ ድህነትና መሰደድ ነው። ከዚህ ዐይነቱ አደጋ ለመዳን የምንችለው፣ እንደራሽያኖችና እንደቻይናዎች ስናስብ ነው። ተንኮልንና መጠራጠርን አስወግደን ለአንድ ዓላማ በአንድነት የቆምን እንደሆን ብቻ ነው። ለመደምርና ለአንድ ዓላማ ለመቆም የግዴታ በትክክለኛ ዕውቀት መታነጽ አለብን። በግልጽና በድፍረት መወያየት አለብን። የኢትዮጵያን ህዝብ ጠላት ማወቅና መጠቆም አለብን።

ሰልሆነም ወደፊት እንደዚህ ዐይነቱ አደጋ በድጋሚ እንዳይከሰት፣ 1ኛ) በአገራችን ውስጥ የውጭ ኃይሎችን እንቅስቃሴ መከታተል ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ምድር የአሻጥር ፖለቲካ የሚካሄደው ሼራተንና በአንዳንድ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ስለሆነ በእነዚህ ሆቴሎች ውስጥ ከፈረንጆች ጋር ተቀምጦ የሚዶልት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግበት ያፈልጋል። በዚህ መልክ የተለያዩ የምዕራቡ የስለላ መዋቅሮችን መከታተልና መበታተን ያስፈልጋል። 2ኛ) የአሜሪካን ኤምባሲ፣ የእንግሊዝና የእስራኤል ኤምባሲዎች ሰላዮች የሚኮተኮቱበት ነው። በመሆኑም በየኤምባሲዎች የሚገቡትንና የሚወጡትን ኢትዮጵያውያንን መከታተል እጅግ አስፈላጊ ነው። 3ኛ) በዕርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ በመንግስት የሚደገፉና ከመንግስት ድጋፍ የማያገኙ የተራድዖ ድርጅቶች የሚባሉት ዋናው ስራቸው አንድን ብሄረሰብ ከሌላው ብሄረሰብ ጋር በማጋጨት አጠቃላይ የወንድማማች የርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ ማድረግ ነው። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት በሃማኖት ሰበካ ስም በአገራችን በልዩ ልዩ ግዛቶች፣ በተለይም በደቡቡ ክፍል ሚሺነሪዎች በመሰማራት የደቡቡ ህዝብ በአማራው ብሄረሰብ ላይ እንዲነሳ የውስጥ ለውስጥ ቅስቀሳና የጥላቻ መንፈስ መዝራት ዋና ዓላማው ማቆሚያ የሌለው የርስ በስር ጦርነት እንዲቀጣጠል ለማድረግ ነው። ከዚህም ባሻገር እነዚህ ድርጅቶች ቆሻሻ ባህልን በማስፋፋትና በድረግ ስርጭት በመሰማራት በአገራችን ላይ የኦምፕየም ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ዘመናት አልፈዋል። ስለሆነም ሁሉም የተራድዖ ድርጅቶች የሚባሉትና፣ በሰበካ ስም የተሰማሩት ሚሺነሪዎችና የቱርክን የበላይነት ለማስፈን የተሰማሩ በማህበራዊ ዕርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችና ድርጅቶች ቀስ በቀስ ኢትዮጵያን ለቀው የሚወጡበት ሁኔታ መዘጋጀት አለበት። ከውጭ በሚመጣ ዕርዳታ አገራችን የበለጸገች ሳትሆን የባሰ ድሃና ጥገኛ እየሆነች ነው የመጣችው። ባጭሩ ዶ/ር አቢይና አገዛዛቸው ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ማየት ያለባቸው እንጂ በየዋህነት መነፅር መመልከት የለባቸውም። እኛም በበኩላችን ሁኔታውን በጥብቅ በመከታተል ወደፊት እንደዚህ ዐይነቱ በዶ/ር አቢይ ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሙከራ እንዳይደገም ሌት ተቀን በትጋት መስራትና ኢንፎርሜሽኖችን መለዋወጥና ማጋለጥ አለብን። መልካም ግንዛቤ !!

fekadubekele@gmx.de