ሥዕል-አንድ፡ በኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ የተሰራ የአፍሪካ ካርታ
ከሶስት ወር በፊት አንድ ጥቁር አፍሪካን አሜሪካ ተማሪዬ ከዚህ በላይ የሚታየውን የአፍሪካ ካርታ ያለበትን ካኔቴራ ለብሶ በክፍል ውስጥ አየሁት። በምስሉ ግርጌ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ማንነትን ፍለጋ” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮበታል። በካርታው ላይ ያለው ባንዲራ እና ጽሑፍ ትኩረቴን ሳበውና ተማሪውን በካኔቴራው ላይ ስላለው ምስል አንዳንድ ጥያቄ ጠይቄው የሰጠኝ መልስ በጣም ስላስገረመኝ ለዛሬ ጽሑፌ መንደርደሪያ አደረግሁት። ስለምስሉ እና ጽሁፉ እንዲነግረኝ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ እንዲህ የሚል ነበር።
“እኛ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ጥቁር አፍሪካን አሜሪካን ወጣቶች ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ አለን። እንደማንኛውም ሰው መነሻዬ ከዚህ አገር ነው ብለን በእርግጠኝነት የምንጠራው አገር ፍለጋ ላይ ነን። በለበስኩት ካኔቴራ ላይ ካርታው የሚያሳየው አፍሪካ የጥቁር ሕዝቦች አገር መሆኗን ሲሆን ሰንደቅ-ዓላማው ደግሞ ነፃ ሕዝብን ይወክላል አለኝ”። አፍሪካን እንደ አንድ አገር ማየት የተለመደ የብዙ አሜሪካውያን የተሳሳተ ግንዛቤ ስለመሰለኝ አፍሪካ በውስጧ ብዙ አገሮችን የያዘች አህጉር እንደሆነች እንዲሁም እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ሰንደቅ-ዓላማ እንዳለው ለማስረዳት ሞከርኩ። የተማሪው ሐሳብ ግን ሌላ ስለነበር ማስረዳቱን ቀጠለ። “አየህ እኛ ጥቁር አፍሪካን አሜሪካን ሁሉንም የአፍሪካ አገሮችን እንደ አገራችን ነው የምንቆጥረው አለኝ”። እኔም በመቀጠል ሰንደቅ-ዓላማው እኮ የሚወክለው አንድን አገር ብቻ ነው ይህንንስ እንዴት ታየዋለህ ብዬ ጠየቅሁት። “ትክክል ነህ ሰንደቅ-ዓላማው አንድ አገር ብቻ ነው የሚወክለው ነገር ግን ይህ አንድ ሰንደቅ-ዓላማ አፍሪካን የመወከል የታሪክ እና የዘመን ብቃት አለው። አየህ አፍሪካውያን በባርነት ሰብአዊነታቸውን፣ በቅኝ ግዛት ደግሞ አገራቸውን ተቀምተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሰንደቅ-ዓላማ በዚያ በጨለማ ዘመን አፍሪካን ወክሎ የተውለበለበ ብቸኛ ሰንደቅ-ዓላማ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰንደቅ-ዓላማ አገራቸውን ከቀማኛ ለመከላከል መስዋዕትነትን ለከፈሉ ኩራት፤ አገራቸውን ለተቀሙ የዳግም ትንሳኤ ተስፋ፤ እንዲሁም በማንነት ፍለጋ ላይ ላሉ አፍሪካውያን የማንነት አሻራ ቤተመዘክር ነው” በማለት ፈጽሞ ያልጠበቅሁትን አስገራሚ መልስ ሰጠኝ።
የዚህ ጽሑፍ አላማ የተማሪዬን ሃሳብ ለመሞገት ሳይሆን የሰንደቅ-ዓላማ ጉዳይ የሰሞኑ የኢትዮጵያውያን መነጋገርያ ርዕስ ከመሆኑም በላይ የነገ የቤት ሥራ መስሎ ስለታየኝ የቤት ሥራውን ተባብረን ለመስራት ይረዳናል ብዬ ያሰብኩትን ሃሳብ ለማካፈል ይህንን መንደርደሪያ መረጥሁ። አሁን ያለንበት የለውጥ ሂደት ኢትዮጵያውያንን ከምንጊዜውም በላይ በአንድ ሃሳብና መንፈስ ያነሳሳ ቢሆንም ከላይ በአፍሪካ ካርታ ላይ የምናየው ሰንደቅ-ዓላማ ዶ/ር አብይ አህመድን ለመደገፍ በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመውለብለቡ የተደሰቱም የተከፉም ዜጎች እንዳሉ ግልፅ ነው። በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ እንደዚህ አይነት አለመግባባት በሌላም አገር የተለመደ ቢሆንም የኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርገው ችግሩን በውይይት እና በጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ ከመፍታት ይልቅ ወደ ጸብ እና ክርክር መሔዳችን ነው። በእኔ እይታ በዚህ ምልክት አልባ አረንጓዴ፤ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ ሶስት ዋና ዋና ቅሬታዎች ሲነሱ ይስተዋላሉ። የመጀመሪያው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ አይወክለኝም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ አማካኝነት ተጨቁኜአለሁ የሚል ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ከዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ጀርባ ጠርዝ የወጣ አስተሳሰብ አለ የሚል ነው። በእነዚህ አስተሳሰቦች ምክንያት በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ ስንጣላ እና ስናጣላ፤ ስናወግዝ እና ስንወገዝ፣ ስንከሰስ እና ስንከስ ይኸው እንደ ቀልድ ሃያ ሰባት ዓመት ሞላን።
አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ህዝቦች በጋራ ሊያግባባ የሚችል ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ እንደሚያስፈልጋት አሁን የምናያቸው ክስተቶች ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው። ስለሆነም የብሔራዊ ሰንደቅ-ዓላማን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በሚከተሉት ነጥቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የመጀመሪያ ስራችን መሆን አለብት።
ሀ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንድን ነው ˀ
ለ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማንን ይወክላልˀ
ሐ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን እንዴት ይወክላልˀ
መ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንን መወከል አይጠበቅበትምˀ ሠ. የኢትዮጲያ የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ምን ይመስላልˀ
ረ. በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ስጋቶች ምንድን ናቸው? ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን።
ሀ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንድን ነው ˀ
ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማለት የአንድ አገር ሕዝቦች በጋራ ሆነው በዘልማድ፤ በአዋጅ ወይም በህግ እውቅና በመስጠት አገርን እንዲወክል የመረጡት ምልክት ወይም አርማ ማለት ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ በተወሰነ መልክዐ-ምድር ውስጥ በድንበር ተከልላ የራሷ የሆነ መሬት፣ ነጻነት፣ የፖለቲካ መዋቅር እና ህዝብ ያላትን አገር የመሬት፣ የውሃ እና የአየር ክልል እንደ አገር እውቅና የሚሰጥ ምልክት ነው።
ለ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማንን ይወክላልˀ
ከላይ በሰንደቅ-ዓላማ ትርጉም ላይ እንደተመለከትንው የየትኛውም አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የሚወክለው አንድ ሉዓላዊ እና ነጻ አገርን ነው። ይህ ማለት ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ በኩል የአንድን ነጻ አገር ህልውና ሲያረጋግጥ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎችን እኩል የአገር ባለቤትነትን ያረጋግጣል። አንድ አገር ብዙ ሰንደቅ-ዓላማ ሊኖራት ይችላል። ነገር ግን አገርን ሊወክል የሚችለው ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ተብሎ የተሰየመው ብቻ ነው።
ሐ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን እንዴት ይወክላልˀ
አብዛኛውን ጊዜ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን የሚወክለው በያዘው ቀለማት፣ ቅርፅ፣ በላዩ ላይ በተቀመጡ ልዩ ልዩ ምልክቶች እንዲሁም ቀለማቱ እና ምልክቶቹ በተሰጣቸው ትርጉም አማካኝነት እንደሆነ ከብዙ አገሮች የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ መረዳት እንችላለን። እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር ቀለማቱ እና ምልክቶቹ ምን ማንጸባረቅ አለባቸው የሚለው ላይ ግንዛቤና አገራዊ መግባባት መፍጠር መቻል ነው። የብዙ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ቀለማትና ምልክቶች የአገርን የነጻነት ታሪክ፣ የአገርን ፍቅር፣ ለአገር የተከፈለን ወይም የሚከፈልን መስዋዕት፣ የአገርን የተፈጥሮ ፀጋ የሚያንፀባርቁ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አገሮች አገራቸውን በብሄራዊ ደርጃ በብቸኝነት የሚወክል ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ ወይም ሐይማኖታዊ ምልክቶችን ይጠቀማሉ። በየትኛውም መንገድ ቢሆን አላማው አንድ ነው፤ የአገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን የአገር ባለቤትነት የማረጋገጥ አላማ።
መ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንን መወከል አይጠበቅበትምˀ
የአንድ አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በየትኛውም ዓለም ወይም ሥፍራ ቢውለበለብ አላማው አንድ ሉዓላዊ አገርን መወከል ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ነጻ አገርን እና የዜጎችን እኩል የአገር ባለቤትነት ከመወከል ባሻገር ሌላ ተጨማሪ አገራዊ እሴቶችን እንዲወክል ማድረግ ቢቻልም እነዚህን እሴቶች በትክክል ለመወከል የአቅም ውስንነት አለበት። ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ፤ ብሔር፤ ባህል እና ሐይማኖት ባለቤት ለሆኑ አገሮች ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ብሔርን፤ ቋንቋን፤ ባህልን እና ሐይማኖትን መወከል አይጠበቅበትም። እነዚህ አገራዊ እሴቶች እና ማንነቶች እውቅና ማግኘት የለባቸውም ማለት ሳይሆን እነዚህን እሴቶችና ማንነቶች በተሻለ መልኩ ሊወከሉና እውቅና ሊያገኙ የሚችሉበት ሌላ መንገድ መኖሩን ለመጠቆም ነው። ከብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ አታካራዎች አንዱ መነሻ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማን ከአቅሙ በላይ ውክልና ስናሸክመው ነው። የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ጽንሰ-ሃሳብ ነጻ አገርን መወከል ስለሆነ አላማውም ጉልበቱም ይህንን የሚመጥን ነው። ከዚህ ያለፈ ውክልና ተሸከም ብንለው ሁላችንንም እኩል የማስተናገድ አቅም ያንሰዋል። ለዚህ ቀላሉ መፍትሄ ጭቅጭቅ ሳይሆን ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የተፈጠረለትን አላማ ማወቅ እና ለዚያ አላማ ብቻ መጠቀም ነው።
ሠ. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ምን ይመስላልˀ
የየትኛውም አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ ጀንበር የተፈጠረ ሳይሆን በረጅም ዓመታት የታሪክ፣ የባህል፣ የሐይማኖት እና የፖለቲካ ሒደት ውስጥ አልፎ እውቅና ያገኘ አርማ ነው። ሰንደቅ-ዓላማ አገርን ወክሎ መውለብለብ ከመጀመሩ በፊት በጦርነት ጊዜ ወገንን ከጠላት ለመለየት የሚውለበለብ ምልክት ነበር። ከጦርነትም በኋላ እንደ ድንበር ማረጋገጫ ሆኖ አገልግሎአል። አገሮች በሂደት የራሳቸውን ቅርፅ፣ ይዘት እና መጠን ሲይዙ በጦርነት ጊዜ ሲጠቀሙበት የነበረውን ምልክት እና ሌሎች ታያያዥ ታሪካዊ እውነታዎችን እንደ መነሻ በመውሰድ የራሳቸውን ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ፈጥረዋል።
ኢትዮጵያ አገራችን የረጅም አመት የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገራት አንዷ ነች። ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ምልክቶች ቢደረቡበትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንድቅ-ዓላማ መደበኛ ቀለማት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ናቸው። እነዚህ ቀለማት እንዴት ተመረጡ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያን የሰንደቅ-ዓላማን ታሪክ ማየት ግድ ይለናል። በአንድ ወቅት የአገሮችን ብሄራዊ ቀለም ለማወቅ ፈልጌ ወደ ኢንተርኔት መረጃ መረብ ጎራ አልኩኝ። ባገኘሁት የብዙ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም። በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቀለም ምንድነው ብዬ ስፈልግ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለጥያቄዬ መልስ ሊሆን የሚችል የመረጃ ምንጭ አገኘሁ። ኢትዮጵያን ብሄራዊ ቀለም ካላቸው አገሮች ስም ዝርዝር ውጭ ያደረጋትን መስፈርት ስመለከት በዝርዝሩ ላይ የተካተቱት አገሮች ብሄራዊ ቀለማቸውን በአዋጅ ለዓለም ያሳወቁ ሲሆኑ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱት ጥቂት አገሮች ግን የተወሰኑ ቀለማትን ለረጅም ዓመት ሲጠቀሙበት ስለቆዩ አዋጅ ሳያስፈልግ እንዲሁ የብሄራዊ ቀለም ባለቤትነት እውቅና ተሰጥቶአቸዋል የሚል መረጃ አገኘሁ።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን ለረጅም ዘመን ከመጠቀሟ የተነሳ እነዚህ ቀለማት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀለማት እንደሆኑ በዓለም ይታወቃል። ይህን ታሪክ እንዳነሳ ያስገደደኝ የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ብሄራዊ ቀለማት በአዋጅ የተገኙ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የረጅም ዓመት ቁርኝት ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያ በአብዛኛው እነዚህን ቀለማት መቼ መጠቀም እንደ ጀመረች በትክክል የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ጥንታዊ የስነ-ሥዕል እና ስነ-ፅሑፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምራ እነዚህን ቀለማት በብዛት እንደምትጠቀም ያሳያሉ። ለምሳሌ በዓለም በእድሜ ረጅሙ መፅሐፍ ቅዱስ እንደሆነ የሚነገርለት እና በተለምዶ የአባ ገሪማ መፅሐፍ ቅዱስ በመባል የሚታወቀው በአራተኛው እና በአምስተኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ ይገመታል። የዚህን መፅሐፍ ቅዱስ የሽፋን ገፅ ለማስጌጥ በጊዜው በሥራ ላይ የዋሉት ቀለማት በአብዛኛው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ናቸው። ይህም ከላይ የተጠቀሰውን ግምት ያጠናክራል።
ሥዕል-ሁለት፡ የአባ-ገሪማ መጽሐፍ ቅዱስ
ሥዕል ሶስት፡ በአስራ ስድስተኛው ክ/ዘመን ከተሰራ የኢትዮጵያ ካርታ የተወሰደ የካርታ መፍቻ ቁልፍ።
በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋሎች የጉዞ ማስታወሻ ላይ ተመስርቶ በአውሮፓውያን የተሰራ የኢትዮጵያ ካርታ እንደሚያሳየው ፖርቹጋሎች በጉዞአቸው ወቅት የህዝቡን የአለባበስ ባህል በማስታወሻቸው ላይ እንደመዘገቡ በዚህ የካርታ መፍቻ ላይ የምንመለከተው የልብስ ቀለማት ጉልህ ማስረጃ ነው። በምሥሉ ላይ የሚታዩት የልብሶቹ ቀለማት ኢትዮጵያውያን ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ያላቸውን ጥንታዊ ትሥሥር ያሳያል። በእርግጥ እንደ እነዚህ ያሉ ብዙ ማስረጃዎችን ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማቅረብ ቢቻልም የዚህ ፅሑፍ አላማ ይህ ስላልሆነ ለአሁኑ የኢትዮጵያን የባሕል አልባሳት ቀለማት መመልክት በራሱ በቂ ነው እያልኩኝ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስ።
ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ያላት የረጅም ዘመን ቁርኝት ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማውም የነዚህ ቀለማት ውጤት እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክቷል። የኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ከየት እንደ ሚጀምር ብዙ አፈ ታሪኮች ቢኖሩም በፅሑፍ የተደገፉ ማስረጃዎች ግን ጥቂቶች ናቸው። እነሱም ቢሆኑ ብዙ የመረጃ ክፍተት
እንዳላቸው ለአንባቢ መጠቆም እወዳለሁ። ለዚህ ፅሑፍ እንደ ዋና የመረጃ ምንጭ የተጠቀምኩት የቾናኪይ ስታኒስሎው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1963 የታተመ ጥናታዊ ፅሑፍን ነው። ይህንን ጥናታዊ ፅሑፍ የመረጥኩት ጥናቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በአፈ ታሪክ የተነገሩ መረጃዎችን ከአውሮፓውያን የጉዞ ማስታውሻ ፅሑፍ ጋር በማገናዘብ የቀረበ ስለሆነ ከሌሎች ምንጮች የተሻለ ታአማኝነት ይኖረዋል በሚል እሳቤ ነው። በዚህ ጥናት መሰረት “ዓላማ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ሰርፀ-ድንግል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ባራዳስ የተባለው ፖርቹጋላዊ በጉዞ ማስታወሻው ያስረዳል። ባራዶስ “አላማ” የሚለውን ቃል በፖርቹጋሊኛ/ጣሊያንኛ ባንዲዕራ/ባንዲራ ብሎ ተርጉሞታል። ዲልማ የተባለ ሌላ ተጓዥ ደግሞ “ሰንደቅ” የሚል ቃል በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በግዕዝ እና በአማርኛ በተጻፉ መዛግብት ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ጠቅሶ ነበር። የዲልማ የጉዞ ማስታወሻ እንደሚያትተው ሰንደቅ የሚለው ቃል አርማ ወይም ባነር ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው የሰንደቅ-ዓላማ ጽንሰ-ሃሳብ ከተጠቀሰው ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ እንደ ተጀመረ መገመት ይቻላል።
በአስራ ስምንተኛው ከፍለ ዘመን መጨረሻ እና በአስራ ዘጠነኛው ከፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሁለቱን ቃላት ማለትም “ሰንደቅን” እና “ዓላማን” በማገናኘት ሰንደቅ-ዓላማ የሚለውን ቃል በስፋት መጠቀም እንደ ተጀመረ የቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት ይጠቁማል። እስከ አስራ ስምንተኛው ከፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የነበረው የሰንደቅ-ዓላማ አጠቃቀም ወጥነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ምን አይነት ቀለማት በሥራ ላይ እንደዋሉ የሚገልጽ አሳማኝ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች ነው። የቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት እንደሚያሳየው አሁን ያለው የሰንደቅ-ዓላማ አይነት አርማ መታየት የጀመረው በአጼ ዮሃንስ እና አጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ይታመናል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1881 የአጼ ዮሃንስን ቤተ መንግስት የጎበኙ ስምዖን እና ራፋሬይ የተባሉ ሁለት ጎብኚዎች ባሰፈሩት ማስታወሻ መሰረት አጼ ዮሃንስ ቀይ እና ቢጫ ቀለም ያለው አርማ እንደ ነበራቸው ገልጸዋል። በቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት መሰረት ደግሞ አረንጓዴ ፣ቢጫ እና ቀይ ቀለም ያለው ባለ ሶስት ማዕዘን አርማ በአደባባይ የተውለበለበው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መስከረም 17-1895 ዓም አጼ ምኒሊክ የአድዋን ጦርነት ሲያውጁ ሲሆን ይኸው ሰንደቅ-ዓላማ በጦርነቱም ወቅት በሥራ ላይ ውሎአል። በ1897 አጼ ምኒሊክ እነዚህ ሶስት ቀለማት አንድ ላይ እንዲሰፉ በማዘዛቸው ሰንደቅ-ዓላማው የአሁኑን ቀለም እና ቅርፅ እንደያዘ ቾናኪይ ስታኒስሎው በጥናቱ ላይ ገልፆታል። ከዚህ ታሪክ እንደ ምንረዳው የኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ አመጣጥ መሰረቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ካለው ባህላዊ፣ ስነ-ጥበባዊ እና ስነ-ልቦናዊ ትሥሥር እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ቀለማቱ ነገስታት ወይም አጼዎች አመጡት ከማለት ይልቅ ቀለማቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህላዊ እና ስነ-ጥበባዊ ቅርስ ናቸው ብንል የበለጠ ያስማማናል።
ከአድዋ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ተደርጋ ስለ ምትታይ የሰንደቅ-ዓላማዋም ታሪክ ድምበር ዘልለ ሆነ። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በነጻነት ትግላቸው ወቅት የነጻነት ተስፋ እና በነጻነታቸው ማግስት ደግሞ የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማቸው መሰረት ሆኖ አገልግሏል። ይህ ታሪካዊ ትሥሥር ብዙ የአፍሪካ አገሮችን በኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ ላይ የባለቤትነት ስሜት አሳድሮባቸዋል። ስለዚህ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች የኢትዮጵያን ሰንደቅ-ዓላማ እንደ የአፍሪካ ቅርስ ጭምር ነው የሚያዩት። እንግዲህ በዚህ ድምበር ዘለል ታሪክ እና ባለቤት ባለው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ሰንደቅ-ዓላማ ላይ የየዘመኑ ገዢዎች ፍላጎትና አሻራ ሲደመርበት እና ከላዩ ላይ ሲቀነስ ዛሬ ላይ ደርሰናል። አሁንም ከመቀነስና ከመደመር አባዜ አልወጣንም።
ሥዕል-አራት፡ የመደመር እና የመቀነስ ሥሌት አዙሪት
