ሥዕል-አንድ፡ በኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ የተሰራ የአፍሪካ ካርታ

ከሶስት ወር በፊት አንድ ጥቁር አፍሪካን አሜሪካ ተማሪዬ ከዚህ በላይ የሚታየውን የአፍሪካ ካርታ ያለበትን ካኔቴራ ለብሶ በክፍል ውስጥ አየሁት። በምስሉ ግርጌ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ማንነትን ፍለጋ” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮበታል። በካርታው ላይ ያለው ባንዲራ እና ጽሑፍ ትኩረቴን ሳበውና ተማሪውን በካኔቴራው ላይ ስላለው ምስል አንዳንድ ጥያቄ ጠይቄው የሰጠኝ መልስ በጣም ስላስገረመኝ ለዛሬ ጽሑፌ መንደርደሪያ አደረግሁት። ስለምስሉ እና ጽሁፉ እንዲነግረኝ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ እንዲህ የሚል ነበር።

“እኛ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ጥቁር አፍሪካን አሜሪካን ወጣቶች ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ አለን። እንደማንኛውም ሰው መነሻዬ ከዚህ አገር ነው ብለን በእርግጠኝነት የምንጠራው አገር ፍለጋ ላይ ነን። በለበስኩት ካኔቴራ ላይ ካርታው የሚያሳየው አፍሪካ የጥቁር ሕዝቦች አገር መሆኗን ሲሆን ሰንደቅ-ዓላማው ደግሞ ነፃ ሕዝብን ይወክላል አለኝ”። አፍሪካን እንደ አንድ አገር ማየት የተለመደ የብዙ አሜሪካውያን የተሳሳተ ግንዛቤ ስለመሰለኝ አፍሪካ በውስጧ ብዙ አገሮችን የያዘች አህጉር እንደሆነች እንዲሁም እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ሰንደቅ-ዓላማ እንዳለው ለማስረዳት ሞከርኩ። የተማሪው ሐሳብ ግን ሌላ ስለነበር ማስረዳቱን ቀጠለ። “አየህ እኛ ጥቁር አፍሪካን አሜሪካን ሁሉንም የአፍሪካ አገሮችን እንደ አገራችን ነው የምንቆጥረው አለኝ”። እኔም በመቀጠል ሰንደቅ-ዓላማው እኮ የሚወክለው አንድን አገር ብቻ ነው ይህንንስ እንዴት ታየዋለህ ብዬ ጠየቅሁት። “ትክክል ነህ ሰንደቅ-ዓላማው አንድ አገር ብቻ ነው የሚወክለው ነገር ግን ይህ አንድ ሰንደቅ-ዓላማ አፍሪካን የመወከል የታሪክ እና የዘመን ብቃት አለው። አየህ አፍሪካውያን በባርነት ሰብአዊነታቸውን፣ በቅኝ ግዛት ደግሞ አገራቸውን ተቀምተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሰንደቅ-ዓላማ በዚያ በጨለማ ዘመን አፍሪካን ወክሎ የተውለበለበ ብቸኛ ሰንደቅ-ዓላማ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰንደቅ-ዓላማ አገራቸውን ከቀማኛ ለመከላከል መስዋዕትነትን ለከፈሉ ኩራት፤ አገራቸውን ለተቀሙ የዳግም ትንሳኤ ተስፋ፤ እንዲሁም በማንነት ፍለጋ ላይ ላሉ አፍሪካውያን የማንነት አሻራ ቤተመዘክር ነው” በማለት ፈጽሞ ያልጠበቅሁትን አስገራሚ መልስ ሰጠኝ።

የዚህ ጽሑፍ አላማ የተማሪዬን ሃሳብ ለመሞገት ሳይሆን የሰንደቅ-ዓላማ ጉዳይ የሰሞኑ የኢትዮጵያውያን መነጋገርያ ርዕስ ከመሆኑም በላይ የነገ የቤት ሥራ መስሎ ስለታየኝ የቤት ሥራውን ተባብረን ለመስራት ይረዳናል ብዬ ያሰብኩትን ሃሳብ ለማካፈል ይህንን መንደርደሪያ መረጥሁ። አሁን ያለንበት የለውጥ ሂደት ኢትዮጵያውያንን ከምንጊዜውም በላይ በአንድ ሃሳብና መንፈስ ያነሳሳ ቢሆንም ከላይ በአፍሪካ ካርታ ላይ የምናየው ሰንደቅ-ዓላማ ዶ/ር አብይ አህመድን ለመደገፍ በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመውለብለቡ የተደሰቱም የተከፉም ዜጎች እንዳሉ ግልፅ ነው። በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ እንደዚህ አይነት አለመግባባት በሌላም አገር የተለመደ ቢሆንም የኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርገው ችግሩን በውይይት እና በጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ ከመፍታት ይልቅ ወደ ጸብ እና ክርክር መሔዳችን ነው። በእኔ እይታ በዚህ ምልክት አልባ አረንጓዴ፤ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ ሶስት ዋና ዋና ቅሬታዎች ሲነሱ ይስተዋላሉ። የመጀመሪያው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ አይወክለኝም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ አማካኝነት ተጨቁኜአለሁ የሚል ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ከዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ጀርባ ጠርዝ የወጣ አስተሳሰብ አለ የሚል ነው። በእነዚህ አስተሳሰቦች ምክንያት በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ ስንጣላ እና ስናጣላ፤ ስናወግዝ እና ስንወገዝ፣ ስንከሰስ እና ስንከስ ይኸው እንደ ቀልድ ሃያ ሰባት ዓመት ሞላን።

አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ህዝቦች በጋራ ሊያግባባ የሚችል ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ እንደሚያስፈልጋት አሁን የምናያቸው ክስተቶች ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው። ስለሆነም የብሔራዊ ሰንደቅ-ዓላማን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በሚከተሉት ነጥቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የመጀመሪያ ስራችን መሆን አለብት።
ሀ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንድን ነው ˀ
ለ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማንን ይወክላልˀ
ሐ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን እንዴት ይወክላልˀ
መ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንን መወከል አይጠበቅበትምˀ
ሠ. የኢትዮጲያ የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ምን ይመስላልˀ
ረ. በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ስጋቶች ምንድን ናቸው?
ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን።
ሀ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንድን ነው ˀ
ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማለት የአንድ አገር ሕዝቦች በጋራ ሆነው በዘልማድ፤ በአዋጅ ወይም በህግ እውቅና በመስጠት አገርን እንዲወክል የመረጡት ምልክት ወይም አርማ ማለት ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ በተወሰነ መልክዐ-ምድር ውስጥ በድንበር ተከልላ የራሷ የሆነ መሬት፣ ነጻነት፣ የፖለቲካ መዋቅር እና ህዝብ ያላትን አገር የመሬት፣ የውሃ እና የአየር ክልል እንደ አገር እውቅና የሚሰጥ ምልክት ነው።

ለ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ማንን ይወክላልˀ
ከላይ በሰንደቅ-ዓላማ ትርጉም ላይ እንደተመለከትንው የየትኛውም አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የሚወክለው አንድ ሉዓላዊ እና ነጻ አገርን ነው። ይህ ማለት ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ በኩል የአንድን ነጻ አገር ህልውና ሲያረጋግጥ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎችን እኩል የአገር ባለቤትነትን ያረጋግጣል። አንድ አገር ብዙ ሰንደቅ-ዓላማ ሊኖራት ይችላል። ነገር ግን አገርን ሊወክል የሚችለው ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ተብሎ የተሰየመው ብቻ ነው።
ሐ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን እንዴት ይወክላልˀ
አብዛኛውን ጊዜ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አገርን የሚወክለው በያዘው ቀለማት፣ ቅርፅ፣ በላዩ ላይ በተቀመጡ ልዩ ልዩ ምልክቶች እንዲሁም ቀለማቱ እና ምልክቶቹ በተሰጣቸው ትርጉም አማካኝነት እንደሆነ ከብዙ አገሮች የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ መረዳት እንችላለን። እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር ቀለማቱ እና ምልክቶቹ ምን ማንጸባረቅ አለባቸው የሚለው ላይ ግንዛቤና አገራዊ መግባባት መፍጠር መቻል ነው። የብዙ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ቀለማትና ምልክቶች የአገርን የነጻነት ታሪክ፣ የአገርን ፍቅር፣ ለአገር የተከፈለን ወይም የሚከፈልን መስዋዕት፣ የአገርን የተፈጥሮ ፀጋ የሚያንፀባርቁ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አገሮች አገራቸውን በብሄራዊ ደርጃ በብቸኝነት የሚወክል ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ ወይም ሐይማኖታዊ ምልክቶችን ይጠቀማሉ። በየትኛውም መንገድ ቢሆን አላማው አንድ ነው፤ የአገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን የአገር ባለቤትነት የማረጋገጥ አላማ።
መ. ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ምንን መወከል አይጠበቅበትምˀ
የአንድ አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በየትኛውም ዓለም ወይም ሥፍራ ቢውለበለብ አላማው አንድ ሉዓላዊ አገርን መወከል ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ነጻ አገርን እና የዜጎችን እኩል የአገር ባለቤትነት ከመወከል ባሻገር ሌላ ተጨማሪ አገራዊ እሴቶችን እንዲወክል ማድረግ ቢቻልም እነዚህን እሴቶች በትክክል ለመወከል የአቅም ውስንነት አለበት። ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ፤ ብሔር፤ ባህል እና ሐይማኖት ባለቤት ለሆኑ አገሮች ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ብሔርን፤ ቋንቋን፤ ባህልን እና ሐይማኖትን መወከል አይጠበቅበትም። እነዚህ አገራዊ እሴቶች እና ማንነቶች እውቅና ማግኘት የለባቸውም ማለት ሳይሆን እነዚህን እሴቶችና ማንነቶች በተሻለ መልኩ ሊወከሉና እውቅና ሊያገኙ የሚችሉበት ሌላ መንገድ መኖሩን ለመጠቆም ነው። ከብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ አታካራዎች አንዱ መነሻ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማን ከአቅሙ በላይ ውክልና ስናሸክመው ነው። የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ጽንሰ-ሃሳብ ነጻ አገርን መወከል ስለሆነ አላማውም ጉልበቱም ይህንን የሚመጥን ነው። ከዚህ ያለፈ ውክልና ተሸከም ብንለው ሁላችንንም እኩል የማስተናገድ አቅም ያንሰዋል። ለዚህ ቀላሉ መፍትሄ ጭቅጭቅ ሳይሆን ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የተፈጠረለትን አላማ ማወቅ እና ለዚያ አላማ ብቻ መጠቀም ነው።

ሠ. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ምን ይመስላልˀ
የየትኛውም አገር ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ በአንድ ጀንበር የተፈጠረ ሳይሆን በረጅም ዓመታት የታሪክ፣ የባህል፣ የሐይማኖት እና የፖለቲካ ሒደት ውስጥ አልፎ እውቅና ያገኘ አርማ ነው። ሰንደቅ-ዓላማ አገርን ወክሎ መውለብለብ ከመጀመሩ በፊት በጦርነት ጊዜ ወገንን ከጠላት ለመለየት የሚውለበለብ ምልክት ነበር። ከጦርነትም በኋላ እንደ ድንበር ማረጋገጫ ሆኖ አገልግሎአል። አገሮች በሂደት የራሳቸውን ቅርፅ፣ ይዘት እና መጠን ሲይዙ በጦርነት ጊዜ ሲጠቀሙበት የነበረውን ምልክት እና ሌሎች ታያያዥ ታሪካዊ እውነታዎችን እንደ መነሻ በመውሰድ የራሳቸውን ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ፈጥረዋል።
ኢትዮጵያ አገራችን የረጅም አመት የሰንደቅ-ዓላማ ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገራት አንዷ ነች። ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ምልክቶች ቢደረቡበትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንድቅ-ዓላማ መደበኛ ቀለማት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ናቸው። እነዚህ ቀለማት እንዴት ተመረጡ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያን የሰንደቅ-ዓላማን ታሪክ ማየት ግድ ይለናል። በአንድ ወቅት የአገሮችን ብሄራዊ ቀለም ለማወቅ ፈልጌ ወደ ኢንተርኔት መረጃ መረብ ጎራ አልኩኝ። ባገኘሁት የብዙ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም። በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቀለም ምንድነው ብዬ ስፈልግ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለጥያቄዬ መልስ ሊሆን የሚችል የመረጃ ምንጭ አገኘሁ። ኢትዮጵያን ብሄራዊ ቀለም ካላቸው አገሮች ስም ዝርዝር ውጭ ያደረጋትን መስፈርት ስመለከት በዝርዝሩ ላይ የተካተቱት አገሮች ብሄራዊ ቀለማቸውን በአዋጅ ለዓለም ያሳወቁ ሲሆኑ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱት ጥቂት አገሮች ግን የተወሰኑ ቀለማትን ለረጅም ዓመት ሲጠቀሙበት ስለቆዩ አዋጅ ሳያስፈልግ እንዲሁ የብሄራዊ ቀለም ባለቤትነት እውቅና ተሰጥቶአቸዋል የሚል መረጃ አገኘሁ።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን ለረጅም ዘመን ከመጠቀሟ የተነሳ እነዚህ ቀለማት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀለማት እንደሆኑ በዓለም ይታወቃል። ይህን ታሪክ እንዳነሳ ያስገደደኝ የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ብሄራዊ ቀለማት በአዋጅ የተገኙ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የረጅም ዓመት ቁርኝት ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያ በአብዛኛው እነዚህን ቀለማት መቼ መጠቀም እንደ ጀመረች በትክክል የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ጥንታዊ የስነ-ሥዕል እና ስነ-ፅሑፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምራ እነዚህን ቀለማት በብዛት እንደምትጠቀም ያሳያሉ። ለምሳሌ በዓለም በእድሜ ረጅሙ መፅሐፍ ቅዱስ እንደሆነ የሚነገርለት እና በተለምዶ የአባ ገሪማ መፅሐፍ ቅዱስ በመባል የሚታወቀው በአራተኛው እና በአምስተኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ ይገመታል። የዚህን መፅሐፍ ቅዱስ የሽፋን ገፅ ለማስጌጥ በጊዜው በሥራ ላይ የዋሉት ቀለማት በአብዛኛው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ናቸው። ይህም ከላይ የተጠቀሰውን ግምት ያጠናክራል።

ሥዕል ሶስት፡ በአስራ ስድስተኛው ክ/ዘመን ከተሰራ የኢትዮጵያ ካርታ የተወሰደ የካርታ መፍቻ ቁልፍ።


ሥዕል-ሁለት፡ የአባ-ገሪማ መጽሐፍ ቅዱስ

በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋሎች የጉዞ ማስታወሻ ላይ ተመስርቶ በአውሮፓውያን የተሰራ የኢትዮጵያ ካርታ እንደሚያሳየው ፖርቹጋሎች በጉዞአቸው ወቅት የህዝቡን የአለባበስ ባህል በማስታወሻቸው ላይ እንደመዘገቡ በዚህ የካርታ መፍቻ ላይ የምንመለከተው የልብስ ቀለማት ጉልህ ማስረጃ ነው። በምሥሉ ላይ የሚታዩት የልብሶቹ ቀለማት ኢትዮጵያውያን ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ያላቸውን ጥንታዊ ትሥሥር ያሳያል። በእርግጥ እንደ እነዚህ ያሉ ብዙ ማስረጃዎችን ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማቅረብ ቢቻልም የዚህ ፅሑፍ አላማ ይህ ስላልሆነ ለአሁኑ የኢትዮጵያን የባሕል አልባሳት ቀለማት መመልክት በራሱ በቂ ነው እያልኩኝ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስ።

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ያላት የረጅም ዘመን ቁርኝት ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማውም የነዚህ ቀለማት ውጤት እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክቷል። የኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ከየት እንደ ሚጀምር ብዙ አፈ ታሪኮች ቢኖሩም በፅሑፍ የተደገፉ ማስረጃዎች ግን ጥቂቶች ናቸው። እነሱም ቢሆኑ ብዙ የመረጃ ክፍተት እንዳላቸው ለአንባቢ መጠቆም እወዳለሁ። ለዚህ ፅሑፍ እንደ ዋና የመረጃ ምንጭ የተጠቀምኩት የቾናኪይ ስታኒስሎው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1963 የታተመ ጥናታዊ ፅሑፍን ነው። ይህንን ጥናታዊ ፅሑፍ የመረጥኩት ጥናቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በአፈ ታሪክ የተነገሩ መረጃዎችን ከአውሮፓውያን የጉዞ ማስታውሻ ፅሑፍ ጋር በማገናዘብ የቀረበ ስለሆነ ከሌሎች ምንጮች የተሻለ ታአማኝነት ይኖረዋል በሚል እሳቤ ነው። በዚህ ጥናት መሰረት “ዓላማ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ሰርፀ-ድንግል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ባራዳስ የተባለው ፖርቹጋላዊ በጉዞ ማስታወሻው ያስረዳል። ባራዶስ “አላማ” የሚለውን ቃል በፖርቹጋሊኛ/ጣሊያንኛ ባንዲዕራ/ባንዲራ ብሎ ተርጉሞታል። ዲልማ የተባለ ሌላ ተጓዥ ደግሞ “ሰንደቅ” የሚል ቃል በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በግዕዝ እና በአማርኛ በተጻፉ መዛግብት ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ጠቅሶ ነበር። የዲልማ የጉዞ ማስታወሻ እንደሚያትተው ሰንደቅ የሚለው ቃል አርማ ወይም ባነር ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው የሰንደቅ-ዓላማ ጽንሰ-ሃሳብ ከተጠቀሰው ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ እንደ ተጀመረ መገመት ይቻላል።

በአስራ ስምንተኛው ከፍለ ዘመን መጨረሻ እና በአስራ ዘጠነኛው ከፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሁለቱን ቃላት ማለትም “ሰንደቅን” እና “ዓላማን” በማገናኘት ሰንደቅ-ዓላማ የሚለውን ቃል በስፋት መጠቀም እንደ ተጀመረ የቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት ይጠቁማል። እስከ አስራ ስምንተኛው ከፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የነበረው የሰንደቅ-ዓላማ አጠቃቀም ወጥነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ምን አይነት ቀለማት በሥራ ላይ እንደዋሉ የሚገልጽ አሳማኝ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች ነው። የቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት እንደሚያሳየው አሁን ያለው የሰንደቅ-ዓላማ አይነት አርማ መታየት የጀመረው በአጼ ዮሃንስ እና አጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ይታመናል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1881 የአጼ ዮሃንስን ቤተ መንግስት የጎበኙ ስምዖን እና ራፋሬይ የተባሉ ሁለት ጎብኚዎች ባሰፈሩት ማስታወሻ መሰረት አጼ ዮሃንስ ቀይ እና ቢጫ ቀለም ያለው አርማ እንደ ነበራቸው ገልጸዋል። በቾናኪይ ስታኒስሎው ጥናት መሰረት ደግሞ አረንጓዴ ፣ቢጫ እና ቀይ ቀለም ያለው ባለ ሶስት ማዕዘን አርማ በአደባባይ የተውለበለበው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መስከረም 17-1895 ዓም አጼ ምኒሊክ የአድዋን ጦርነት ሲያውጁ ሲሆን ይኸው ሰንደቅ-ዓላማ በጦርነቱም ወቅት በሥራ ላይ ውሎአል። በ1897 አጼ ምኒሊክ እነዚህ ሶስት ቀለማት አንድ ላይ እንዲሰፉ በማዘዛቸው ሰንደቅ-ዓላማው የአሁኑን ቀለም እና ቅርፅ እንደያዘ ቾናኪይ ስታኒስሎው በጥናቱ ላይ ገልፆታል። ከዚህ ታሪክ እንደ ምንረዳው የኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ አመጣጥ መሰረቱ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ጋር ካለው ባህላዊ፣ ስነ-ጥበባዊ እና ስነ-ልቦናዊ ትሥሥር እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ቀለማቱ ነገስታት ወይም አጼዎች አመጡት ከማለት ይልቅ ቀለማቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህላዊ እና ስነ-ጥበባዊ ቅርስ ናቸው ብንል የበለጠ ያስማማናል።

ከአድዋ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ተደርጋ ስለ ምትታይ የሰንደቅ-ዓላማዋም ታሪክ ድምበር ዘልለ ሆነ። ስለሆነም የኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች በነጻነት ትግላቸው ወቅት የነጻነት ተስፋ እና በነጻነታቸው ማግስት ደግሞ የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማቸው መሰረት ሆኖ አገልግሏል። ይህ ታሪካዊ ትሥሥር ብዙ የአፍሪካ አገሮችን በኢትዮጵያ ሰንደቅ-ዓላማ ላይ የባለቤትነት ስሜት አሳድሮባቸዋል። ስለዚህ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች የኢትዮጵያን ሰንደቅ-ዓላማ እንደ የአፍሪካ ቅርስ ጭምር ነው የሚያዩት። እንግዲህ በዚህ ድምበር ዘለል ታሪክ እና ባለቤት ባለው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለም ሰንደቅ-ዓላማ ላይ የየዘመኑ ገዢዎች ፍላጎትና አሻራ ሲደመርበት እና ከላዩ ላይ ሲቀነስ ዛሬ ላይ ደርሰናል። አሁንም ከመቀነስና ከመደመር አባዜ አልወጣንም።

ሥዕል-አራት፡ የመደመር እና የመቀነስ ሥሌት አዙሪት

ረ. በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ስጋቶች
ከላይ በሥዕል-አራት ላይ እንደ ምንመለከተው የኢትዮጵያ ገዢዎች ከአጼዎች እስክ ኢሕአዲግ ድረስ በአገዛዝ ዘመናቸው የተለያዩ ሰንደቅ-ዓላማዎችን ተጠቅመዋል። ይሁን እንጅ ሁሉም በሽግግር ወቅት የተጠቀሙት ሰንደቅ-ዓላማ ምልክት አልባውን ነው። ምንም እንኳን ይህንን ምልክት የሌለበት ሰንደቅ-ዓላማ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ማውለብለብ በህግ የሚያስጠይቅ ቢሆንም ሰንደቅ-ዓላማው ከብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ የወጣ አይመስልም። ስለሆነም ሰንደቅ-ዓላማው በመንግስትም በሕዝብም ዘንድ አወዛጋቢነቱ በአሁኑ ወቅት በአደባባይ ጎልቶ እየታየ ስለመጣ ውዝግቡ ትንሽ ቆይቶ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳያስገባን እፈራለሁ። በጽሑፌ መጀመሪያ ላይ እንደ ጠቀስኩት በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ስጋቶች በዋናነት ሶስት ናቸው።
 የውክልና ጥያቄ
 ከሰንደቅ-ዓላማው ጀርባ ያለ ጫፍ የረገጠ አስተሳስብ
 በሰንደቅ-ዓላማው ጥላ ስር የተፈጸሙ ግፎች እና በደሎች ናቸው
የውክልና ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች ሰንደቅ-ዓላማው አጼዎችን እንጅ እኔን አይወክልም የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ያቀርባሉ። በእርግጥ አጼዎቹ የራሳቸው ሰደቅ-ዓላማ ቢኖራቸውም ምልክት አልባው ሰንደቅ-ዓላማም የዚሁ አካል ተደርጎ ስለተቆጠረ የውክልና ጥያቄ አስነስቶበታል። በመሰረቱ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የሚወክለው አንድ ሉዓላዊ አገርን ሲሆን ለዜጎቿ ደግሞ የአገር ባለቤትነት ማረጋገጫ ነው። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ሥርዓትን አይወክልም። የሁሉንም ሕዝብ እምነት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ርዕዮተ-ዓለም እና አስተሳሰብ በእኩል የመወከል ተፈጥሮአዊም ሆነ ሕጋዊ አቅም የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የአንድን ዜጋ የአገር ባለቤትነት የማረጋገጥ አለማቀፋዊ አቅም አለው። ይህ ማለት ደግሞ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን (አይወክለኝም የሚሉትንም)ጨምሮ የአንድ ሉዓላዊ አገር ባለቤትነትን ሲያረጋግጥ የኖረ ሲሆን ወደፊትም ማረጋገጡን ይቀጥላል። የውክልና ጥያቄውን በዚህ አውድ ካየንው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ እኩል የአገር ባለቤትነት ውክልና አለው ማለት ነው። እዚህ ላይ ግን ማረጋገጥ እና ማስከበር ሁለት ያተለያዩ ነገሮች ናቸው። ብሔራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የማረጋገጥ እንጂ የማስከበር ጉልበት የለውም። የተረጋገጠም መብት ካልተከበረ እንደሌለ ይቆጠራል። ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ያረጋገጠልንን የባለቤትነት መብት የምናስከብረው እኛና የወከለን መንግስት ነው። ችግሩ የውክልና ሳይሆን ውክልናው የሰጠውን መብት ማስከበር አለመቻል ነው። ይኼን ችግር ያመጣው ደግሞ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ሳይሆን ያለፍንባቸው ሥርዓቶች እና መሪዎች ናችው። ስለዚህ መፍትሔው ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማን መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር መቀያየር ሳይሆን ስርዓቱን ማስተካከል ነው።

እንደ አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ አይነቶች ጥላ ስር በገዢዎቹ መከራ እና ስቃይ ደርሶበታል። በአሁኑ ግዜ የክልሎችንም ባንዲራ ጭምሮ ያለውም ቢሆን ከየትኛውም ዘመን እጅግ ከከፋ መከራና ስደት ዜጎችን መታደግ አልቻለም። ይኼ በግልፅ የሚያሳያው ችግሩ ሰንደቅ-ዓላማው እንዳልሆነ ነው። እዚህ ላይ አንድ ሁላችንንም የሚያስማማን ቁምነገር የችግሩ ተጠያቂ ሰንደቅ-ዓላማው ሳይሆን ሥርዓቱ እና የሥርዓቱ ቁልፍ መሪዎች ናቸው። ታዲያ ለምን የችግሩ ምንጭ ያልሆነ ነገር ላይ ጊዜ እናጠፋለን? ካለብን ተደራራቢ አገራዊ ችግር አንጻር የሰንደቅ-ዓላማን ችግር አግዝፈን ካየነው ሌሎች ግዙፍ ችግሮቻችንን ለመፍታት አቅም ያጥረናል። በሰከነ መንፈስ ከተወያየን ግን በቀላሉ ልንፈታው የምንችለው ጉዳይ ነው።

ድሮ ልጅ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር እንደ ቀልድ ስቀን ያለፍነው ክስተት ምን ያህል ትልቅ ቁም ነገር ያለው ታሪክ እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው። ተወልጄ ያደግሁት በመሃል ኢትዮጵያ ነው። ባደግሁበት ሰፈር ታዳጊ ወጣቶች በቡድን ተከፋፍለው የሚጫወቱት “ፈለሎ” (አሁን ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም)የሚባል ጨዋታ አለ። ይህ ጨዋታ ጭቃ እያድቦለቦሉ በመወርወር የተቃራኒን ቡድን ማሳደድ ነው። ታዲያ ከእለታት ባንዱ ቀን ይህ በጭቃ የመማታት ጨዋታ ወደ እውነተኛ ፀብ ይቀየር እና ጭቃው ቀርቶ ድንጋይ መወራወር እና ሰውን መጉዳት ተጀመረ። በዚህ መሃል ጨዋታውን ከዳር ቆሞ ሲመለከት የነበረ በእድሜው ጠና ያለ ሰው ሁኔታው ስላላማረው ጣልቃ መግባት ፈለገ። ይህ ሰው ምን አደረገ መሰላችሁ፤ በጭንቅላቱ ላይ ያደረገውን ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ የተሰራ የሹራብ ኮፍያ እንጨት ላይ ሰክቶ ከፍ አድርጎ በመያዝ “ አደራ ባንዲራ!!! በባንዲራ አምላክ!!!” እያለ መጮኽ ጀመረ። በሚገርም ሁኔታ ወዲያውኑ ፀቡ ቆሞ ወደ እርቅ ተገባ። በዚያን ዘመን ባንዲራ ሲያስታርቅ እንጂ ሲያጣላ አይቼ አላውቅም ነበር። በአካባቢዬ ሰዎች “አደራ ባንዲራ” ብለው ጮኸው በደልን ሲያስቆሙ አይቻለሁ። ሰዎች “አደራ ባንዲራ” ብለው ጮኸው ሕገ-ወጥነትን ሲያስቆሙ አይቻለሁ። ሰዎች “አደራ ባንዲራ” ብለው ተማፅነው ሰዎችን ሲያስታርቁ አይቻለሁ። ይህንን ትልቅ ማሕበራዊ እሴት ከጣልን እነሆ ሩብ ክፍለ ዘመን አስቆጠርን።

ከሰንደቅ-ዓላማው ጀርባ ያለ ጫፍ የረገጠ አስተሳሰብ አለ የሚባለው ሁለተኛው በሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሳ ስጋት ነው። ይህም ”አንድ አገር አንድ ባንዲራ” የሚል አስተሳሰብ ነው። እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት በዓለም ላይ የየትኛውም አገር የሚወከለው በአንድ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ብቻ ነው። አንድ ዜጋም ሊኖረው የሚችለው አንድ የትውልድ አገር ብቻ ነው። ከላይ የተነሳውን ሃሳብ በዚህ አውድ ካየነው ለእኔ ሃሳቡ እውነት እንጅ ጫፍ የረገጠ አስተሳሰብ አይደለም። ይህን ሃሳብ ጫፍ የወጣ አስተሳሰብ የሚያስብለው አንድ ሰው ከብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ውጭ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሌላ ሰንደቅ-ዓላማ ማየት አልፈልግም ብሎ ሲያስብ እና በአንድነት ስም ብዙሃንነትን ለመጨፍለቅ ሲሞክር ነው። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ አይኖረውም ፤የሚወገዝም አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያ በህዝብ ይሁንታ ባገኘ አንድ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ሥር የተለያዩ ሰንደቅ-ዓላማ ሊኖራት ይችላል። ጫፍ የወጣን አስተሳስብ ማስቀረት የምንችለው ግን ሰንደቅ-ዓላማን በሕግ በመኮነን ሳይሆን በመነጋገር እና በሰንደቅ-ዓላማ ውስጥ የተደበቀውን ሃሳብ በመታገል መሆን አለበት። ምንም እንኳን ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ለብሔራዊ መግባባት እንደ አንድ ግባት ቢያገለግልም በምንም መስፈርት ብቸኛ የአንድነት ዋስትና ተደርጎ መወሰድ የለብትም።

ሌላው ቅሬታ ደግሞ በሰንደቅ-ዓላማው ጥላ ስር የተፈጸሙ ግፎች እና በደሎችን የሚመለከት ሲሆን ይህን ሃሳብ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚጋራው የአገራችን ትልቁ ችግር እንደሆነ እሙን ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ የመደበኛ ቀለማት ትርጉም ይህንን ይመስላል። አረንጓዴው ልምላሜን እና የተፈጥሮን ፀጋን፣ ቢጫው ነጻነትን፣ ፍትህን እና እኩልነትን፣ ቀዩ ደግሞ የአገር ፍቅርን፣ ጀግንነትን እና ለአገር የሚከፈል መስዋዕትነትን ያሳያል። እንደ አለመታደል ሆኖ የአገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ጥላስር ሆነው፤
 ነጻነት ሲገባቸው በአገራቸው በባርንት ቀንበር ስር ማቀዋል
 እኩል የመሬት ባለቤትነት ሲገባቸው መሬት አልባ ሆነው አስከፊ የጭሰኝነት ኑሮ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል
 በአገራቸው ፍትህ ሲገባቸው ያላግባብ ታስረዋል፣ተገርፈዋል፣ተሰቃይተዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ተገድለዋል
 ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት እያላቸው በገዢዎቻቸው በግፍ ተወስዶባቸዋል

 ሕጻናት በሰላም ወጥተው መግባት ሲገባቸው ባልሰሩት ሀጢያት በአደባባይ እንደ አውሬ አዳኝ በአልሞ ተኳሽ ተገድለዋል
 በአገር የምትመሰለው እናት ክብር እና እንክብካቤ ሲገባት በጨካኝ እና አረመኔዎች የልጇ እሬሳ ላይ እንድትቀመጥ ተገዳለች
 ኢትዮጵያ የዜጎቿ መኖሪያ መሆን ስትችል ገዢዎቿ የዜጎቿ እስር ቤት አድርገዋታል
 ኢትዮጵያ ለሁሉም እናት መሆን ስትችል ለአብዛኛው ክፉ የእንጀራ እናት ተደርጋለች
 ኢትዮጵያ ለጥቂቶች የምትታለብ ላም ለብዙዎች ደግሞ ሲዖል ሆናለች
እንግዲህ እነዚህ የውድቀት ታሪኮች ከብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማችን ጀርባ ከተደበቀው ገመናችን ከብዙ ጥቂቱ ነው በእርግጥም ያሳፍራል፤ ተጠያቂዎቹ በጊዜው የነበሩ ሥርዓቶች እና ገዢዎቹ ቢሆኑም ባንዲራውንም ተወቃሽ አድርጎታል። መፍትሔው ግን ሌላ እንጂ ሰንደቅ-ዓላማን መቀያያር አይደለም። ምክንያቱም ይኽው ሰንደቅ-ዓላማ እንደመታደል ሆኖ የምንኮራበትም ታሪክ አለው፤
 “ጥቁሮች ጌታ እንጂ አገር አያስፈልጋቸውም” ብሎ አገርን ለመቀማት የመጣውን ነጭ ወራሪ፤ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ቅስሙን ሰብረው ለዓለም ጥቁር ሕዝብ ድልና ኩራትን ያበሰሩት በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 የአፍሪካን የነጻነት ተስፋ የወለደው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 የአፍሪካን የነጻነት ትግል ችቦ የለኮሰው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 ፓን አፍሪካኒዝም የተወለደው በዚህ ሰንደቅ-ዓላማ ስር ነው
 ኢትዮጵያን የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል አድርጎ የሚወክለው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 ኢትዮጵያ ከአራት በላይ የተቃጣባትን የውጭ ወራሪ መክታ ስታሸንፍ ድሉን ያበሰረው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የአለም ጥቁሮችን ትኩረት የተቸረው ይህ ሰንደቅ-ዓላማ ነው
 አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሕዝቦች ወክለው የሚሮጡለት አገር እንኳን በሌላቸው ዘመን ጀግናው አበበ ቢቂላ አፍሪካን ዳግመኛ በሮም አደባባይ ሲያኮራ በአገሩ እንዳይውለበለብ በተገዳደረችው ጣልያን አደባባይ ላይ ተውለብልቦ ኢትዮጵያውያንን ያስፈነደቀው ይኸው ታሪከኛ ሰንደቅ-ዓላማ ነው።
 አፍሪካ በአለም ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ጥማቷን የሚያረካላት ሴት ልጅ አጥታ እንደ የወላድ መካን ስትቆጠር፤ ጀግናዋ ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና አደባባይ ላይ ለአፍሪካ በሴቶች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ይዛ ድንገት ብቅ ብላ አፍሪካን ስታኮራ ይህ ሰንደቅ-ዓላማ አሁንም አፍሪካን ወክሎ በመውለብለብ የአሁጉሩ የኩራት ምልክት ሆነ።
ይህ ከላይ የጠቀስኩት ከሰንደቅ-ዓላማ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ድንበር ዘለል አኩሪ ታሪካችንን ነው። በአጠቃላይ በሰንደቅ-ዓላማችን ጀርባ የምንኮራበትም የምናፍርበትም ታሪክ አለ። ይሁን እንጂ የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ጉዳይ ዛሬም እያወዛገበን ይገኛል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንደተገለጸው አብዛኛዎቹ የሚያወዛግቡን ጉዳዮች እኛ በግድ ከሰንደቅ-ዓላማ ጋር አያያዝናቸው እንጂ የማይገናኙ እና በሌላ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ናችው። በእኔ እምነት የብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማን ውዝግብ በዘላቂነት ለመፍታት አሁን ያለው የለውጥ ሂደት ጥሩ አጋጣሚን እና ሶስት ምርጫዎችን ከፊታችን አስቀምጦልናል። እነሱም፤
 አሁን ባለው ላይ ተስማምቶ መቀጠል
 ወደ ምልክት አልባው አረንጓዴ፤ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ-ዓላማ መመለስ
 ሌላ አዲስ አማራጭ መፈለግ

የትኛውንም መንገድ ለመምረጥ መብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እኔም እንደ አንድ ዜጋ የራሴን ምርጫ ላስቀምጥና ምክንያቴን ላስረዳ። የእኔ ሃሳብ ወደ ምልክት አልባው አረንጓዴ፤ ቢጫ እና ቀይ ብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ብንመለስ ያዋጣናል የሚል ነው ። ምክንያቴ ደግሞ ይኸው፤
 ይህ ባንዲራ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የሕዝብ ይሁንታ የማግኘ እድሉ ሰፊ ነው ብዬ ስለማምን
 በዚህ ባንዲራ ዙሪያ ያሉ ብዥታዎችን ተነጋግሮ በቀላሉ ማጥራት ይቻላል ብዬ ስለማምን
 የባንዲራው ቀለም መሰረቱ አጼዎች የፈጠሩት ሳይሆን የኢትዮጵያ የባህል እና የስነ-ጥበብ ውጤት ስለሆነ የአገር ቅርስ ነው ብዬ ስለማምን
 አድዋ ላይ በዚህ ባንዲራ ጥላ ሥር ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር እና ብሔረሰቦች የሕይወት እና የአካል መስዕዋትነትን ስለከፈሉ ይህ ባንዲራ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን በታሪክ እና በስነ-ልቦና ያስተሳስራል ብዬ ስለማምን
 ይህ ባንዲራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ለከፈለው እና ለሚከፍለው መሥዕዋትነት የቃል-ኪዳን ማሰሪያ ስለሆነ
 የቀለማቱ ትርጉም ግልጽ እና ኢትዮጵያን እንደ ሉዓላዊ አገር ይገልጻታል ብዬ ስለማምን
 ባንዲራው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ጭምር በታሪክ እና በስነ-ልቦና የመወከል አቅም ስላለው
 ባንዲራው በጥቁሮች ዘንድ እንደ ቅርስ ጭምር ስለሚታይ ኢትዮጵያ ይህንን ቅርስ በአደራ የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለባት።
 ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ባንዲራ ይልቅ ይህ ባንዲራ አፍሪካን በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የተሻለ አቅም ስላለው።
 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ ቆመው አገራቸው ለአፍሪካ የሚበቃ መሪም ባንዲራም እንዳላት በኩራት ለመናገር
አጋጣሚውን ስልሚፈጥር ጭምር ነው።
በአገራችን ኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በብሄራዊ ሰንደቅ-ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ጥንቃቄን የሚሹ እና ትኩረት ተሰጥቶባቸው ከሕዝብ ጋር በመወያየት መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። የዚህ ጽሑፍ አላማም ለውይይት ሊረዱ የሚችሉ ሃሳቦችን ለመጠቆም ነው። ጽሑፉ የግሌ ሀሳብ እንጂ ማንንም ወክዬ እየተናገርሁ እንዳልሆነ በመግለጽ ሕዝብ መክሮ ላጸደቀው ሃሳብ ተገዢ መሆኔንም በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቅስ አላልፍም።

አመሰግናለሁ!

እግዚአብሔር ከዘመነ አብሮ መደመር ወደ ዘመነ አብሮ ማደግ በሰላም ያሸጋግረን!!!

ይርጋዓለም (ዶ/ር)
ሐምሌ 2010
Yirgalemm2001@yahoo.com